ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, March 24, 2015

በኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብፅ መሃከል የተደረገው ስምምነት የሚጨበጨበለት አይደለም።ለግብፅ ሶስት ጥቅሞችን ሰጥቷል (የጉዳያችን ልዩ ዘገባ)



ኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብፅ ትናንት መጋቢት 14/2007 ዓም ካርቱም ላይ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም እና በተለይ ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ  አጠቃቀም ዙርያ አንድ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የአባይ ጉዳይ ከአፍሪካ ቀንድ አልፎ በግብፅ ሳብያ እስከ መካከለኛው ምስራቅ ድረስ የፀጥታ ችግር የመሆን ዕድል ይኖረዋል የሚል ስጋት በብዙ ሀገሮች ውስጥ ስለነበር ማንኛውም ስምምነት ደመቅ ተደርጎ ቢነገርለት ሊገርመን አይገባም።ለእዚህም ነው ትናንት ሰኞ ስምምነቱ ካርቱም ላይ እንደተፈረመ ቢቢሲ፣ኤኤፍፒ እና  በሰበር ዜናነት ደግሞ 'ኢየሩሳሌም ፖስት' የዘገቡት።እዚህ ላይ በዓለም አቀፍ የውሃ አጠቃቀም ሕግ እና በአባይ ጉዳይ በቂ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ስምምነቱ ከኢትዮጵያ አንፃር ያለውን አዎንታዊ አልያም አሉታዊ ተፅኖ በሚገባ ተንትነው እንደሚያቀርቡልን ተስፋ እያደረኩ አሁን ግን ከስምምነቱ አንፃር ግልፅ የሆኑ አሉታዊ ጉዳዮችን፣ማን ምን ተጠቀመ የሚለውን እና ለምን ስምምነቱ አሁን ተፈለገ?በሚሉት ዙርያ ማውሳት እፈልጋለሁ።

1/ ስምምነቱ ''የአባይ ወንዝ አጠቃቀም ኢንሼቲቭ'' ፈራሚ ሀገሮችን ዲፕሎማሳዊ ድጋፍ  የማግኘት ጉዳይ  

ኢትዮጵያ የአባይን ግድብ ስትጀምር ከፍተኛ ተግዳሮት የገጠማት ከግብፅ እንደነበር እና የሱዳን ሚና ቢከፋ የተፅኖ ፈጣሪነት እና የግብፅ መረማመጃ እንዳትሆን የሚል ስጋት እንደነበር ይታወቃል።በእዚህን ወቅት ኢትዮጵያ ቀደም ብሎ በቅኝ ግዛት ዘመን ሱዳን እና ግብፅ ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ የተፈራረሙትን ስምምነት ባለመቀበል ሌላ የትብብር ግንባር ከፍታ ነበር።በእዚህም መሰረት ''የአባይ ወንዝ አጠቃቀም ኢንሸቲቭ'' (The Nile Basin Initiative) የተሰኘ ትብብር በአባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ አጠቃቀምን የሚያሰፍን የተባለ ስምምነት በተለይ የታችኞቹን የአባይ ተፋሰስ ምንጭ ሀገሮችን ያካተተ ስምምነት ተደርገ።ትብብሩ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 22/1999 ዓም በኢትዮጵያ፣ደቡብ ሱዳን፣ዑጋንዳ፣ብሩንዲ፣ሩዋንዳ፣ኬንያ፣ግብፅ፣ሰሜን ሱዳን፣ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ እና ታንዛንያ ሲመሰረት የትብብሩን ዋና አካል የሆነውን እና የቅኝ ግዛት ውሎችን የማይቀበውለውን ''ውሃውን በእኩልነት እና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መጠቀም'' በሚል መርህ ላይ የተመሰረተውን ስምምነት ግብፅ እና ሱዳን ሲቃወሙት የተቀሩት አብዛኛዎቹ ሃገራት ፊርማቸውን አስቀምጠዋል።

የአባይ ወንዝ ከ80% በላይ የሚሆነው መነሻ ምንጩ ከኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች መሆኑ ይታወቃል።ያም ሆኖ ግን በጥቂቱ ቀሪውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ የሚባሉ እንደ ነጭ ዓባይ መነሻ ዑጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን የወንዙ አጠቃቀም ፍትሃዊ መሆን አለበት ብለው ከኢትዮጵያ ጋር አብረው ለመቆም ብዙም ያላመነቱ የቁርጥ ቀን ሀገሮች  ናቸው።ሃገራቱ ይህ ነው የሚባል ተፅኖ በውሃው ላይ ባይኖራቸውም የፖለቲካ ተሰሚነትን ስለሚያስገኝ እና አካባቢያዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ተፅኖ ለማሳደግ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ በፍጥነት ጎራቸውን ከግብፅ እና ሱዳን አርቀው ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሰለፉ አደረጋቸው።

እነኝህ ሃገራት ግብፅ እና ሱዳንን በመውቀስ እና ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሳዊ ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ናቸው።ትናንት ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር ስትፈራረም የእነኝህን ሀገራት በቀጥታ የስምምነቱ አካል ማድረግ ባይቻልም የምምክር ሥራ ግን ይጠበቅ ነበር።እስካሁን ባሉ ዘገባዎች ግን እነኝህ ሃገራት ከኢትዮጵያ ጋር በአንድነት የመቆማቸውን ያህል ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ በአንድ አይነት መልክ ማስተናገድ  አለመቻሏ ውሎ አድሮ ተፅኖ ይኖረዋል።ምክንያቱም በአባይ ጉዳይ ላይ የግብፅ እና የሱዳን አጀንዳም ሆነ ስልት የታወቀ እና እንዲህ በአጭር ጊዜ ይቀየራል ተብሎ ስለማይታሰብ ለዘለቄታው ጥቅም ሶስቱ ሃገራት በተናጥል ስምምነት ሲያደርጉ አንድ አይነት ቅሬታን አይፈጥርም ብሎ ማሰብ አይቻልም።ግብፅ እና ሱዳንም ኢትዮጵያ ''ከኢንሼቲቭ'' ፈራሚ ሃገራት ጋር የሚፈጥረው አንድ አይነት የመገለል ቅሬታ እንደሚኖር አይጠፋቸው።ይልቁንም ይፈልጉታል።

2/ ስምምነቱ ለግብፅ ሶስት ጥቅም ሰጥቷል 

የትናንቱ ድልድል በዋናነት የሰጠው ጥቅም ምንድነው? ብለን ብንመለከት ለኢትዮጵያም ለግብፅም የሚሰጠው የእራሱ ጥቅም ይኖረዋል።ሆኖም ግን አሰጣጡ ፍትሃዊ አይደለም። ለኢትዮጵያ ያስገኘው ነገር አንድ ብቻ ነው። ይሄውም ግብፅ ቢያንስ ግድቡን አላውቅም ኢትዮጵያ መስራት አትችልም የሚል ድፍን ያለ ቅዋሜን ትታ ለግድቡ እውቅና መስጠት እና በዲፕሎማሲያዊ አነጋገር ቢሆንም ለሶስቱ ሀገሮች ይጠቅማል የሚሉ ንግግሮችን በአደባባይ እንድትል ማድረጉ ነው።ይህ ብቻ አይደለም ግብፅ እና ሱዳን በአባይ ላይ ከፍተኛ የመስኖ ልማት እያደረጉ ኢትዮጵያ ግን በምግብ እጥረት እየተሰቃየች የግድቡን ውሃ በከፊልም ቢሆን ለመስኖ እንዳታውለው ስምምነቱ ያስገድዳል።ለመብራት ማመንጫነት ብቻ የሚል አንደምታ አለው።ሱዳን እና ግብፅ በአባይ ወንዝ ተጠቅመው ከምግብ ፍጆታነት ባለፈ ከፍተኛ የጥጥ ምርት እንደሚያመርቱ ይታወቃል።

አሁን ያለው አዲስ ነገር ግብፅ የስልት ለውጥ ማድረግ መቻሏ ነው።ይሄውም ቀደም ብሎ የቅኝ ግዛት ውልን ብቻ ነው የምቀበለው የሚለውን ያፈጀ አነጋገር የትም እንደማያደርስ እና ይልቁንም ሱዳን ከጎኗ አለመቆሟ ግብፅ ተለሳልሳ እንድትታይ አጽጌድዷታል።በመሆኑም አንድ ስምምነት በማድረግ በስምምነቱ ዙርያ ካርድ እየመዘዙ መጫወት የሚለው የግብፅ አዲሱ ስልት ነው።

ግብፅ ከእዚህ ስምምነት ሶስት አይነት ጥቅም አግኝታለች

የመጀመርያው የግድቡን ማናቸውንም እንቅስቃሴ በይገባኛል እና ከባለቤትነት ባልተናነሰ መልኩ ኢትዮጵያን አሳሪ ስምምነት ለመፈራረም ችላለች።የስምምነቱን አንቀፆች ብንመለከት በአንዲት ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ሀገር ውስጥ በተገነባ ግድብ ላይ የግድቡን ሥራ ከኤሌክትሪክ ማመንጫነት ባለፈ ለምንም ነገር ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም በተዘዋዋሪም ቢሆን ያስገድዳል።ይህ ማለት ውሃው በግድቡ ውስጥ ገብቶ የመብራት ማመንጫ ተርባይነሩን ከመታ በኃላ መለቀቅ እንዳለበት ያረጋግጣል።ይህም በስምምነቱ አንቀጽ ሁለት ላይ ''የግድቡ ተግባር'' ተብሎ ተቀምጧል።

ሁለተኛው የግብፅ ጥቅም ስምምነቱ አጠቃላይ ድፍን ቃላትን እንደመጠቀሙ ለወደፊት ፀብ መጫርያነት ለግብፅ በቀላሉ ልትጠቀምበት እና ፍትሃዊ ጦርነት እንዳደረገች ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳመን ይረዳታል።በስምምነቱ ላይ የተጠቀሱት ቃላት ለምሳሌ አንቀፅ ሶስት ላይ Principle of not causing significant damage:''በወንዙ አጠቃቀም ላይ አይነተኛ አደጋ አለመሆን'' በሚለው ስር ''አደጋ'' የሚለው ቃል ምን ማለት ወይንም የትኛው አደጋ እንደሆነ አያብራራም።ለግብፅ አደጋ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ ለመስኖ ስትጠቀም ይሆናል።ለኢትዮጵያ አደጋ የምትለው ግብፅ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እርዳታ ማድረግ መቻሏ ሊሆን ይችላል።በአንቀፅ 4 ላይም ''ፍትሃዊ አጠቃቀም'' ሲል ኢትዮጵያ ለመስኖ ከአባይ ውሃ ብትጠቀም ፍትሃዊ አጠቅቀም የሚለውን አንቀፅ 4 አፈረሰች ሊባል ነው? የሚል ተገቢ ጥያቄ ያስነሳል።በመሆኑም የስምምነቱ አንቀፆች ግልፅ ባለ መልኩ አለመቀመጥ ግብፅ በማንኛውም ጊዜ በፈለገችው መንገድ ተርጉማ የምትመዘው ካርድ ሆኖ ያገለግላታል።

ሶስተኛው  የግብፅ ጥቅም የትናንቱ ስምምነት እንደ አዲስ ምዕራፍ ከፋች መሆኑን እና ያለፈውን የግብፅ እና የሱዳንን የቅኝ ግዛት ውል አያጣጥልም።ከእዚህ በፊት ባለፉት ሁለት መንግሥታትም ጭምር ኢትዮጵያን እና ግብፅን ካላስማሟቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ እና ዋናው የቅኝ ግዛት ውልን ኢትዮጵያ እንደማትቀበል መግለጧ ነበር። በእዚህ ስምምነት ላይም ይህ ውል የቅኝ ግዛት ውሉን የሚተካ ወይንም የሚወቅስ አንዳችም አንቀፅ የለውም።ይህ ግብፅ ወደፊት በፈለገች ጊዜ የምትጠቅሰው  ውል እንደሚሆን  አመላካች ነው።

ማጠቃለያ 

ባጠቃላይ የትናንቱ ስምምነት ለኢትዮጵያ ይዞ የመጣው አንድ እና አንድ ነገር ሲሆን ለግብፅ ግን ሶስት ድርብ ጥቅም ነው።ከእዚህ ሁሉ በላይ ግን ይህ ስምምነት በተለይ በግብፅ በኩል ከልብ የመነጨ ፍላጎት ነው ወይንስ ለጊዜያዊ ስልት ብቻ ያደረገችው ነው? ኢትዮጵያስ እውን ግድቡ በበቂ የገንዘብ፣የቁሳቁስ እና ጥራት ደረጃ እየሰራች ነው? 80 ቢልዮን ዶላር ይፈጃል የተባለው ግድብ እስካሁን ከ8 ቢልዮን ያልበለጠ መገኘቱን ስናይ እውን ለግብፅ ግድቡ ስጋት ነው? ግብፅስ ምን ያህል የግንባታው ሂደት መሳካት ላይ እምነት አድሮባታል? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል።ቁልፉ ጥያቄ ግን ለምን አሁን መፈራረሙ አስፈለገ? የሚለው ነው። መልሱ ብዙም ከባድ አይደለም ኢትዮጵያ ኢህአዲግ/ወያኔ  በእዚህ ዓመት ከኤርትራ በረሃዎች የሚነሱ አንዳንዶቹ እንደሚገልፁት ''እንደ ተርብ የሚናደፉ'' የተቃዋሚ ታጣቂ ኃይሎች ወደ ሰሜናዊ ጎንደር አርማጮ እና ትግራይ እየተመሙ መሆኑ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው ሁኔታ አስጊ መሆኑ በቶሎ በአግባቡ ያልተጠና ስምምነት እንድትፈርም እንዳደረገ ይጠረጠራል።

በግብፅ በኩል ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ የተነሳው ፅንፈኛ 'አይ ኤስ ኤስ' በሀገር ውስጥ ካለው ''እስላማዊ ወንድማማቾች ህብረት'' ጋር እዳይገጥም ስጋት አላት።በእዚህ ላይ የደቀቀው ምጣኔ ሃብቷ ቢያንስ በመጪዎቹ ሶስት እና አራት ዓመታት ማንሰራራት አለበት።ሱዳንም ተመሳሳይ ችግር ከደቡብ ሱዳን ጋር አለባት።ስለዚህ በር ላይ ያለውን የአባይ ጉዳይን ለጊዜው የሚያቆዩበት መላ ሶስቱም ሀገሮች ሲፈልጉ ነበር እና የእዚህ አይነቱን ''መሃል ሰፋሪ'' አይነት ስምምነት ተፈራረሙ።ባጭሩ ስምምነቱ ብዙም የሚባልለት ወይንም የሚጨበጨብለት አይደለም።ግዜያዊ ዕረፍትን ለማግኘት ብቻ የታለመ ነው።በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ቀድሞ አልቀበለውም ያለችው ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን የግድቡን አካባቢያዊ ተፅኖ (EIS -Environmental Impact Assessment) የጥናት ውጤት ገና ብዙ ሊያስብል ይችላል።የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች በግድቡ ተፅኖ ላይ የሚሰሩትን ጥናት ኢትዮጵያ ለእረጅም ጊዜ ይህ የሉአላዊነት ጉዳይ ብለው ስትቃወም ነበር።በቅርቡ ነገሩ ተገልብጦ ተቀበለች።ይህስ የሉዓላዊነት ጉዳይ አይደለም? ግን እንደ ገዢዎቻችን እይታ ሉዓላዊነት ከስልጣን አይበልጥም።

ኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብፅ ኢትዮጵያ በምትገነባው የአባይ ግድብ ጉዳይ የተስማሙበትን ሰነድ ይዘት ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
መጋቢት 15/2007 ዓም (ማርች 24/2015)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።