ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, March 16, 2015

''ኢህአዲግ/ወያኔ'' ሁን እንጂ አስተዳዳሪነቱም፣ቅስናውም፣ድቁናውም፣ችግር የለውም እየተዘገነ ይሰጥሃል! ይህ አውሮፓ ሀገር ቤት ባለው ሲኖዶስ እመራለሁ በሚሉ አባት የሚሰራ ስርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ ተግባር ነው (አትናትዮስ ከአውሮፓ)
ጉዳያችን ጡመራ አልፎ አልፎ ከአንባብዎቿ የሚደርሷትን ፅሁፎች ታስተናግዳለች።ለዛሬ ''አትናትዮስ ከአውሮፓ'' በሚል የደረሰንን ፅሁፍ ከእዚህ በታች እንዳለ አስፍረነዋል።
===========================
በአውሮፓ ዘረኝነት፣የገንዘብ ጥቅም እና ምንፍቅና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለመበጥበጥ በመሳርያነት እያገለግሉ ነው በድርጊቱ  ላይ በሀገር ቤት ሲኖዶስ ስር ያሉ በጵጵስና ማዕረግ ያሉ አባትም ተዘፍቀውበታል።
==============================
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ሐዋርያዊት፣እናትነቷ የሁሉም ፣እና መሰረቷ በክርስቶስ ደም የተመሰረተች ነች።ቤተ ክርስቲያን ዘር፣ጎሳ፣ቀለም እና የትውልድ ስፍራ የማትለይ አመሰራረቷም ንፅህናን ገንዘብ ባደረጉ፣በሃይማኖታቸው፣በምግባራቸው እና በአብነታቸው አንቱ በተባሉ አባቶች እና ምእመናን እንጂ የእነርሱን የትውልድ ስፍራ እና ቋንቋ የሚያሞካሹ አባቶች እና ምዕመናን  እንደፈለጉ እንደ ሱቅ በደረቴ የሚመሰርቷት አይደለችም።

1/ ዘረኝነት

በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአንፃራዊ መልኩ የተሻለ ሰላማዊ አካባቢያዊ ሁኔታ የነበረ መሆኑ ይታወቃል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለመመስረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይነት ሳይሆን ፍፁም ዘረኝነት በሆነ መልክ የአድዋ ትግርኛ መናገር እንደ መስፈርት እየተደረገ መምጣቱ የብዙ ምዕመናን ሃዘን ሆኖ ሰንብቷል።የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ገደማ ነው አንድ አገልጋይ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ናይሮቢ ወደሚገኘው የመድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ያመራል።እዝያ እንደደረሰ ግን የተመለከተው እና የተናገረው አሁን ድረስ አይረሳኝም።የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የትናገሩትን አሁን ድረስ እየነዘረው ያወሳዋል።አስተዳዳሪው አዲስ አበባም የአንድ ደብር አለቃ ሆነው ደብሩን በጎጥ በተንሸዋረረ እይታቸው እንዴት አምሰውት እንደ ነበር ስለማውቅ የናይሮቢ ንግግራቸውን ስሰማ ለእኔ ብዙም አልደነቀኝ።እንደ ወዳጄ አነጋገር እኝሁ አለቃ ናይሮቢ ላይም ከቅዳሴ በኃላ የተናገሩት ቃል በቃል እንዲህ የሚል ነበር  ''እኔ በትግሬነቴ እኮራለሁ ከእዚህ አስተዳዳርነቴ የሚያነሳኝ የለም'' ነበር ያሉት።ይህ ንግግር ሲነገር ምዕመኑ በድንጋጤ መላቀስ ጀመረ።በክርስትና ሕይወት ቋንቋ መሰረት ሆኖ አያውቅምና ኢትዮጵያውያን ተሰብስበው ተላቀሱ።

ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድም፣ለአሕዛብም፣ለሮማውያንም ለአፍሪካውያንም ለሁሉም የሰው ዘር መሞቱን የሚያውቁ ምእመናን ብቻ አይደሉም አገልጋይ ካህናት እና መዘምራን በሙሉ ''አባት'' ከተባሉ መነኩሴ ይህ ሲነገር አንቀጠቀጣቸው።ወድያው ምእመናን ፊርማ አሰባስበው የአዲስ አበባውን ቤተ ክህነት ሞገቱት።ለነገሩ ዋናው በዘረኝነት የታሸ የሰው ኃይል እንደተሞላ በተግባር ያረጋገጠው ቤተ ክህነት አለቃውን ከቦታቸው ለማንሳት ብዙ ማንገራገሩ የብዙ ምዕመናንን ድካም አስከትሏል።የሚያሳዝነው ነገር ተመሳሳይ የናይሮቢው የዘረኝነት ንግግር አውሮፓ ላይ መሰማቱ ነው።ማንም ሰው አንድ አይነት የፖለቲካ አመለካከት ሊኖረው አይችልም።ይህ አይጠበቅም።የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት መኖር ደግሞ በእራሱ ተፈጥሮአዊ ነው።ነገር ግን ይህንን አጀንዳ በቤተክርስቲያን ስም ለማራመድ መጣር ይልቁንም ደካማ ጎሳዊ አስተሳሰብን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማስረፅ መድከም ከእግዚአብሔር ብቻ አይደለም በምድራዊ ሕግም ትልቅ ወንጀል ነው።

በተመሳሳይ መንገድ የኢህአዲግ/ህወሓት መመርያ እናስፈፅማለን የሚሉ እና ''በአድዋነታችን እንመካለን'' የሚሉ ግለሰቦች በአውሮፓ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን በሃይማኖት ስም በተጀቦነ የዘረኝነት መርዝ ለመበጥበት መንቀሳቀስ ጀምረዋል። የሚገርመው ጉዳይ ደግሞ ለእንደዚህ አይነቱ እኩይ የዲያብሎስ ሥራ በተባባሪነት እየተንቀሳቀሱ ያሉት በዘርኝነት መርዝ የተወጉ የኢህአዲግ/ወያኔ መዋቅርን መጠቀምያ በማድረግ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በሕዝብ እና በሃይማኖት ላይ እየተፈፀመ ያለ ወንጀል ነው።ይህ የሃይማኖት ጉዳይ ነው! በሃይማኖት ምስክርነትን መስጠት እና ማን ምን እንዳደረገ፣ማን ማንን እንደበደለ  ማውራት፣መመስከር ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው።

ምንፍቅና እና የገንዘብ ጥቅም 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በእዚህን ያህል ደረጃ በመላው ዓለም ተሰራጭታ ግን ደግሞ ጠባቂ እና ተከላካይ ያጣችበት ወቅት ያለ አይመስለኝም። አሁን ያለው አዲስ እና አስደሳች ነገር የመረጃ ፍሰት በእያንዳንዱ ግማሽ ደቂቃ መሆኑ እና በርካታ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያናቸውን ነቅተው እና ተግተው የሚጠብቁ መሆናቸው ብሎም በጥርጥር መንፈስ የቤተ ክርስቲያናን አንድነት እና መሰረተ እምነት ለመናድ የሚንቀሳቀሱቱ ገና ከጅምራቸው ተግባራቸው እየመከነባቸው መምጣቱ እና መላወሻ የማጣታቸው እውነታ ነው።

በጥርጥር መንፈስ የምንፍቅና ተግባራቸውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማስፈፀም የሚሞክሩቱ ለሁለት የተከፈለውን የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አስተዳደር መሃል ገብተው የእራሳቸውን ''የካርታ''ጫወታ የሚጫወቱ ናቸው።የእነኚህኞቹ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች መለያ ባህርያት አሏቸው።እነኝህ መለያዎቻቸው  -

1/ በሁለቱ የሲኖዶስ አስተዳደሮች መካከል ልዩነትን ማስፋት

ግለሰቦቹ  ሲፈልጉ በውጭው ሲኖዶስ ስር ካሉት ጳጳሳት ዘንድ ተጠግተው  የሰበካ አስተዳደሮችን መቆጣጠር እና አገልግሎቱን ማበላሸት።በተመሳሳይ መልኩ በሀገር ቤት ስር ባሉ አባቶች የሚመራ አጥብያ ቤተ ክርስቲያን  ልንመሰርት ነው በማለት ተጠግቶ የቀረ ምንፍቅናቸውን ማራገፍ እና ለመሰሎቻቸው መንገድ መጥረግ፣

2/ ማህተም ለግል ጥቅም 

አሁንም በሁለቱም አባቶች ተጠግተው የቤተ ክርስቲያንን ንብረት፣ገንዘብ እና ማህተም ለግል ጥቅማቸው በማዋል በሀገር ቤት በእራሳቸው እና በዘመዶቻቸው ስም ሀብት ማካበት፣

3/ የመንፈሳዊ አገልግሎቶችን ማበላሸት  

የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ፈፅሞ እንዲበላሽ በያዙት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በመጠቀም ለምሳሌ የሰንበት ትምህርት ቤት እንዳይመሰረት፣ ሕፃናት ኦርቶዶክሳዊ እና ኢትዮጵያ ሆነው እንዳያድጉ አገልግሎቱን ለመጀመር የሚጠይቁ ምዕመናንን እና አገልጋይ ወጣቶችን የሐሰት ስም እየለጠፉ ማራቅ እና ምእመኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይመጣ ለማድረግ አገልግሎቱን በተንዛዛ ሰዓት በማርዘም ማስመረር (ለምሳሌ የታቦተ ሕግ መውጫ ቀናትን እየጠበቁ አላስፈላጊ መርሃግብር እየጨመሩ ምዕመኑ እንዲማረር ማድረግ)፣

4/ ሊቃውንትን መግፋት  

የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በአግባቡ የተማሩ ቤተ ክርስቲያን በተማሩት የአብነት ትምህርት የምታከብራቸው ለምሳሌ በመሪ ጌታነት፣በብሉይ እና አዲስ ኪዳን መፅሐፍት መምህርነት ደረጃ ያሉትን ሊቃውንት ባላቸው የሰበካ ጉባኤ ስልጣን እንዲገፉ በማድረግ እና አላስፈላጊ የቅጣት እርምጃ በመውሰድ ማስመረር፣ስማቸውን ለማጥፋት በመሞከር እና ምንም አይነት የመድረክ አገልግሎት እንዳያገኙ በሀገር ቤትም ሆነ በሀገር ቤት ስር ያሉትን አባቶች በመነዝነዝ መስራት፣በመጨረሻም አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን በማይመጥኑ ካህናት እንዲያዝ በማድረግ፣

5/ ለቤተ ክርስቲያን ፈፅሞ የማይመጥኑ ካህናት እንዲሾሙ ማስደረግ

ለቤተ ክርስቲያን ፈፅሞ የማይመጥኑ ካህናት እንዲሾሙ ማስደረግ ማለት ለምሳሌ ለተዋህዶ ልጆች የመጨረሻ አሳፋሪ የሆነ ''አቡነ ዘበሰማያት'' በቅጡ የማይሉ፣''ውዳሴ ማርያም'' ፈፅሞ የማይደግሙ የቅስና ማዕረግ ተሹመው ክቡሩን የጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ መስቀል እንደ ''ክልል ባንዲራ'' እያውለበለቡ የሚሄዱ ከትህትና ይልቅ በዘመናችንም ያላየነውን ''እዩኝ እዩኝ'' የሚያበዙ አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ ''ቀሳውስት''ተብለው የሚጠሩ መኖራቸውን መንገሩ በቂ ነው።

ይህ ብቻ እንዳይመስላችሁ አንድ ቀን እንደ ዲያቆን ሆኖ ''ተንስኡ ለፀሎት'' ብሎ የማያውቅ ለጥቂት አመታት በድቁና የተሾመ በእዚሁ ደረጃ እንዳለ ''ቀሲስ'' ተብሎ ሲሾም ያየነው  አሁንም እዚሁ አውሮፓ ላይ ነው።ይህንን ያደረጉት ''በሀገር ቤት በሚመራው ሲኖዶስ ስር ነኝ'' የሚሉ ሊቀ ጳጳስ መሆናቸውን መጥቀሱ ሌላው አሳዛኝ ተግባር ነው።

6/  የገንዘብ ዝርፍያ በየዘርፉ

የገንዘብ ዝርፍያ በየዘርፉ ይከናወናል።ሰበካ መመረጥ ''መኪና እንደ ሸሚዝ መለዋወጥ ነው እንዴ?'' እስኪባል ድረስ በሰበካ ጉባኤነት ጭረውም ሆነ አጭበርብረው በተሰየሙበት የአገልግሎት መንበር ስም ሆነው የአውሮፓ ምርጥ መኪና እየያዙ መሸክርከር የተለመደ ነው።በአንድ ቤት ሁለት መኪና መያዝ ምንም ላይሆን ይችላል።ሶስት ሲሆን ያውም የህዝብ ትራንስፖርት እንደልብ በሚመላለስበት እንደ ስካንዲንቭያን ሀገሮች ላይ ሲመልከቱ ''ነዳጅ ሳሎን ላይ ፈልቆላቸው ይሆን?'' ብለው ሶፋዎ ስር ያላዩት የነዳጅ መቅጃ ለመኖሩ ለማወቅ በገዛ ቤትዎ መፈለግ ሊጀምሩ ይችላሉ።

ይህ አውሮፓ ነዋ! የሚደንቀው እና ሕዝብ አያውቅብንም ብለው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ንብረት ልክ እንደ ሀገር ቤቶቹ ተምነሻናሾች ናቸው  በንብረቷ የሚጫወቱቱ። በሰበካ ጉባኤ አባልነት የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት ሽባ አድርገው አንድ ትውልድ ሃይማኖቱን እንዳይማር ገድለው እፍረት አይሰማቸውም። ሌላው የተካኑበት ሰይጣናዊ ተግባር ሰነድ በመደለዝ እና በመሰረዝ ብሎም በቤተ ክርስቲያን ደብዳቤ በህገወጥ የሰው ዝውውር (ዘመዶቻቸውን በአግልግሎት ስም ወደ አውሮፓ ሃገራት በማስገባት) ላይ መሳተፍ ነው።በእዚህ ተግባር ላይ መሰማራታቸው ተጋልጦ በምዕመናን ''እሪታ!'' የተጋለጡ እና ያልተጋለጡ ግን ቀናት የሚቆጥሩ ካህናት ተብዬዎች ተሞልታለች አሁንም ይህችው አውሮፓ! ይህ አውሮፓ ነዋ! ለነገሩ ተመሳሳይ ተግባር ስሩ ሀገር ቤት እንዳለ አለመዘንጋቴን ያዙልኝ።

መፍትሄው  

አሁን በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚደረገውን የዘረኝነት፣የምንፍቅና፣እና የገንዘብ ዝርፍያ ቤተ ክርስቲያን እንደሚገጥማት ሐዋርያው እንዲህ በማለት በቅዱስ መፅሐፍ ውስጥ አሳስቦናል
  
''በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ። ስለዚህ ሦስት ዓመት ሌሊትና ቀን በእንባ እያንዳንዳችሁን ከመገሠጽ እንዳላቋረጥሁ እያሰባችሁ ትጉ። 
አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ። ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም፤እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ። እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ። '' የሐዋርያት ሥራ ምዕ 20፣28፣35

ከላይ የተጠቀሱት በተለይ በእዚሁ በአካባቢያችን በአውሮፓ በቤተክርስቲያን ላይ የሚፈፀሙ ዘርን፣ምንፍቅናን እና ጥቅምን ያማከለ ቤተ ክርስቲያንን እና ምዕመናንንን የማወክ ተግባር ለቤተ ክርስቲያን ልጆች አዲስ ክስተት አይደለም።ይልቁንስ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 24፣ቁጥር 15 ላይ 
''እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል''  እንዳለ የዘረኘነት ርኩሰት በተቀደሰች ቤተ ክርስቲያን ላይ ቆሞ ስናይ እናስተውላለን።ምንፍቅና በተቀደሰች ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲቆም እናስተውላለን፣ምዝበራ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲቆም እናስተውላለን።በእዚህ ዙርያ የሚሰበሰቡ ግሪሳ መሰል አሞራዎችንም እናያቸዋለን።

እርግጥ ነው።በአንዳቸው ላይ ግፍ እንዳልተሠራ፣በግፍ እንዳልተገፉ ምስክር ነን።በሰላም እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ገብተው ሲወጡ ነበር።ይህ ማንም በማንነቱ (ቤተ ክርስቲያንን የሚያደማ ሥራ መስራቱ እየታወቀም) አለመገፋቱ የህሊና ደስታ ነው።ቤተ ክርስቲያን ስገፏት አትጋፋም ይልቁንም ለልጆቿ አብዝታ ትፀልያለች እንጂ።ይህ በትክክል ለመሆኑ ለምስክርነት በመቆማችን አምላካችንን እናመሰግነዋለን።ዛሬ ግን ከልኩ አለፈ።ቤተ ክርስቲያንን እንደ ቅርጫ እንከፍላታለን የሚል እሾህ ምንፍቅናቸውን ሊያራግፉ ሲሞክሩ የሚታገስ ህሊና የለም።

እውነት ነው ለዘመናት ምንፍቅናቸውንም፣የከረፋ ዘረኝነታቸውንም ሆነ መኪና እና ቤት ሲቀያይሩ ተሸክመናቸው ኖረናል። ውስጣችን በቤተ ክርስቲያን ላይ ለሰሩት ግፍ አምላክ ይቅር እንዲላቸው እየለመንን ከርመናል።ከእዚህ በላይ ግን ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ  ምእመናንን እንዲያምሱ ሊፈቀድላቸው አይገባም።የሚገርመው በአውሮፓ ከመሰረትነው 18 ዓመቱ ነው በሚሉት አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እነሱ ከሰበካ ጉባኤ እስከሚወርዱበት በእነኝህ ሁሉ 18 አመታት ውስጥ አንድም ቀን የሰንበት ትምህርት ቤት እንዳይመሰረት ሲከላከሉ የነበሩ መሆኑን ሁሉ የተሸከሙ ምእመናን  ያሉባቸው አብያተ ክርስቲያናትን መስማት የምንፍቅናውን ተግባር በገሃድ የሚያመላክት ነው።ይህ  ለሰሚ ሊገርመው ይችላል።ምንፍቅና ምሱን ዘረኝነትን ሲያገኝ ከእዚህም በላይ ማድረጉ እውነት ነው አሁንም አውሮፓ ባለችው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን።


ለመሆኑ በአውሮፓ ላለው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፈተና ምእመኑ ምን አይነት የመፍትሄ እርምጃ ሊወስድ ይገባል? 

1ኛ/ ምዕመናን በቅድምያ መረዳት ያለባቸው በአባቶች መካከል ''የውስጥ እና የውጭ'' የሚለውን ስያሜ ምእመናን ያመጡት ጉዳይ አይደለም።የችግሩን መንስኤ እናውቀዋለን።በሀገራችን የሰፈነው ፍፁም አምባገናዊ ስርዓት ነው።ከሁለት አመታት በፊት በዳላስ፣አሜሪካ ለእርቅ የደረሱትን ብፁዓን አባቶች እንዴት እንደተጨናገፈ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።የቀድሞው ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ሳይቀሩ የፃፉትን አስታራቂ የዋስትና ደብዳቤ በዜና ማሰራጫዎች ከተሰራጨ በኃላ ፕሬዝዳንቱ እንዴት እንዲቀለብሱ እንደታዘዙም መረጃው በግልፅ ተቀምጧል።
ለዘለቂታዊ መፍትሄ የምእመናን ሚና በረጅም ጊዜ ተሳትፎ ውስጥ መኖሩ ባይካድም በዋናነት የአባቶች ኃላፊነት ቀዳሚ በመሆኑ በዚያ ጉዳይ ከመጠመድ አሁን ምዕመናን ማድረግ ያለባቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ከዘረኝነት፣ከፖለቲካ መድረክነት፣ከምንፍቅና እና ከገንዘብ ቀበኞች መጠበቅ ነው።

2ኛ/ ከወትሮው በተለየ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እና ከቅዳሴ፣ከትምህርት እና ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች መሳተፍ፣

3ኛ/ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በፍፁም ቅንነት፣መንፈሳዊነት እና ትጋት መሳተፍ፣

4ኛ/ ቤተ ክርስቲያን በማናቸውም አባቶች ስም አዲስ ተከፈተ ብሎ የመናፍቃን የእሳት እራት ከመሆን በፊት መመርመር።ይሄውም አመሰራረቱን፣ሂደቱን፣የቤተክርስቲያኑ መመስረት አላማን፣በአገልግሎት የሚታዩት ግለሰቦች ሃይማኖታዊ ንፅህናን፣ያለፈ ታሪካቸውን እና ድርጊታቸውን ሁሉ መመርመር እራስን ከበለጠ አደጋ ይጠብቃል።ከእዚህ በተለየ ''መንፈሳዊ ሰው ይመረምራል እንጂ በማንም አይመረመርምና'' ማስተዋል ተገቢ ነው።

4ኛ/ ቤተ ክርስቲያን በተለይ በባህር ማዶ የሕይወት እስትንፋሳችን መሆኗን መረዳት።ምክንያት ከሰማያዊ ሕይወት ጋር የምታገናኘን ብቸኛ ስፍራ፣የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫ፣የእርስ በርስ መተሳሰብያችን እና ለምንኖርበት ሀገር ህዝቦች አብነት የምንሆንባት ሁሉ ነች። በመሆኑም በገንዘባችን፣በጉልበታችን እና በእውቀታችን ለቤተ ክርስቲያን መስራት የሚገባንን ሳንውል ሳናድር መነሳት ከሁሉም ምዕመናን ይጠበቃል።

ለመደምደም 
ዕብራውያን 3፣16-18 
''ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን።''


አትናትዮስ 
ከምድረ አውሮፓ 

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...