ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ያለ የሌለ ኃይሉን አሰባስቦ የመጣው ጣልያን በዳግማዊ አፄ ምንሊክ መሪነት፣ በእቴጌ ጣይቱ ሃሳብ አፍላቂነት እና የጦር አዝማችነት ከመላዋ ኢትዮጵያ በዘመቱ ኢትዮጵያውያን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ሊባረር እና ኢትዮጵያም ነፃነቷን ጠብቃ ለመኖር ችላለች።
ይህ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኩራት እንደሆነ እስከዛሬ ደርሷል።የአድዋ ድል ታላቅነትን በአግባቡ ለመረዳት ጦርነቱ ከተደረገበት ወቅት በፊት የነበረውን የዓለም የፖለቲካ ሂደት በአግባቡ መረዳትን ይፈልጋል።ይህ ወቅት አውሮፓውያን ''የበርሊኑ ጉባኤ'' (በርሊን ኮንፍረንስ) በተሰኘ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካን እንደ አዲስ በአውሮፓ የወቅቱ ጉልበተኛ መንግሥታት አማካይነት ቅኝ ተገዥ እንድትሆን የተፈረደባት ወቅት ነበር።ይህ ፍርደ ገምድል የሆነውን የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ጥማት ግን ኢትዮጵያ ላይ በአድዋ ድል ሙሉ በሙሉ ከሸፈ።
ይህ ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ የሆነ የድል በዓል ላይ የሚዘባበቱ 'የጤፍ እንጀራ ደንበኞች' አልጠፉም።የጤፍ እንጀራ ደንበኞች ማለቴ ከኢትዮጵያ ተፈጥረው በኢትዮጵያ ስም ከበረው እና የእራሷኑ እንጀራ በልተው መልሰው ''እንጀራዬን የበላ ተረከዙን አነሳብኝ'' እርሷኑ የሚሰድቡ ጉዶችን በጉያዋ ኢትዮጵያ መያዟን ለማመላከት ነው።
የአድዋን ድል የማያውቁ የአድዋ ልጆች የአድዋ ድልን ለማኮሰስ ላይ የሚዘምቱባቸው ሁለት እኩይ ባዕድ-አደር መንገዶች አሏቸው።እነርሱም ዳግማዊ አፄ ምንሊክን እና እራሱ በዓሉ ላይ ጥላ ያጠላል ያሉትን የወሬ ዘመቻ መክፈት እና የአድዋን ድል በራሱ የጎጥ ታፔላ ለመለጠፍ መሯሯጥ ናቸው።በእዚህ እኩይ ባዕድ አደር ተግባራት ላይ የተሰማሩ የታሪክ እና የእውነት ደመኞች ደግሞ በሁለት ክፍል ተከፍለው እናገኛቸዋለን።የመጀመርያዎቹ በኦሮሞ የጎሳ ጥያቄ ዙርያ ጥያቄውን አስቂኝ (እኔ አስቂኝ ነው የምለው) ወደ ሆነው 'የቅኝ ግዛት ጥያቄ' የሚያስፈነጥሩትቱ ሲሆኑ።ሁለተኛዎቹ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የህወሓት ጎሳን መሰረት ያደረገው ስርዓት አቀንቃኞች ናቸው።
የመጀመርያዎቹን ክፍሎች ስንመለከት የኦሮሞ ጎሳ የመብት ጥያቄ እንደማንኛውም የኢትዮጵያውያን የመብት ጥያቄ በተጨባጭ ያለ መሆኑን ባምንም ''የቅኝ ግዛት ጥያቄ'' የሚለው በጎሳው ስም እና ፅንፍን በያዘ የእስልማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታትሩት ግን ሌላ መዘዝ እንዳያመጡ እና ቆመናል የሚሉትን እንደ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ ውብ የሆነ አገላለፅ ''የኢትዮጵያ ግንድ'' የሆነውን የኦሮሞ ብሄረሰብን ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ጋር ለማጋጨት የሚሞክሩት ሙከራ ብዙ ዋጋ እንዳያስከፍላቸው ስጋት አለኝ።
ሁለተኛው እና በእዚህ ፅሁፍ ላይ ላተኩርበት የተነሳሁት ባዕድ-አደር ፖሊሲ የሚገለፀው አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሓት አቀንቃኞች በአድዋ በዓል ዙርያ የሚያንፀባርቁት ታሪክን የተፃረረ አካሄድ ነው።የስርዓቱ ደጋፊዎች በአድዋ በዓል ላይ የሚያሳዩት የተንሸዋረረ አተያየት ፍፁም የወረደ የጎሳ ዘረኝነት የሚንፀባረቅበት ነው።ይህም ሁኔታ በሶስት መንገዶች ይገለፃል።
የመጀመርያው በዓሉን የማደብዘዝ ሥራ የሚገልጠው በህወሓት ቀጥታ ትእዛዝ ስር በሚተዳደረው የሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ነው።የኢትዮጵያ ቴሌቭዝንም ሆነ ራድዮ በዋዜማው ምንም አይነት የአድዋ በዓልን የሚያስታውስ መርሃ ግብር የለውም።ለምሳሌ በዘንድሮው የ2007 ዓም የመገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ቴሌቭዥን ጨምሮ ማለት ነው ምንም አይነት መርሃ ግብር አልተላለፈም።ይህ ሁኔታ በሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ አማካይነት የተዘጋጁ መርሃ ግብሮችን አይመለከትም።
ሁለተኛው በዓሉን የማደብዘዝ ሥራ የሚሰራው በማህበራዊ መገናኛ አውታሮች ለምሳሌ በ''ፌስ ቡክ'' አማካይነት ስለ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ፣እቴጌ ጣይቱ ወዘተ የፈጠራ ወሬዎችን በመለጠፍ ነው።ለምሳሌ የስርዓቱ የማህበራዊ ሚድያ አፈቀላጤ መሆኑ የሚነገርለት እና ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት እንዳለው እራሱም ደጋግሞ የሚነግረን ዳንኤል ብርሃነ የዘንድሮውን የአድዋ በዓል አስመልክቶ ሲሳለቅ ''አፄ ምንሊክ በአድዋ ጦርነት ወቅት የነበሩበትን ትክክለኛ ቦታ ማግኘት አልቻልኩም '' በማለት ነበር።
ሶስተኛው የአድዋን ድል የማያውቁ የአድዋ ልጆች በዓሉን የማደብዘዝ ሥራ የሚሰሩት በዋናው የበዓሉ ቀን የሚደረገውን የበዓል አከባበር 'ተራ' መልክ በመስጠት ነው።ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ እንደሚያስታውሰው የአድዋ በዓል በአዲስ አበባ አከባበሩ (የአበባ ጉንጉን በፓርላማ አፈጉባኤ አባ ዱላ ከማስቀምጥ አላለፈም) በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የምሽቱ የዜና እወጃ ወቅት የተሸፈነው ሁለት ደቂቃ ባልሞላ እንድያውም አንዱ አንድ ደቂቃ ብቻ በወሰደ የዜና አቀራረብ ሰዓት ነበር።
ልብ በሉ! ያ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ኩራት የሆነ ታላቅ ታሪካዊ ድል በደቂቃ የዜና ዘገባ ሲታለፍ ከባእዳን ጋር ሳይሆን በእርስ በርስ ጦርነት ለሞቱት የህወሓት ሰማዕታት ግን በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ብር ወጥቶ ''አስረሽ ምችው'' ተይዟል።ይህ ፅሁፍ በተፃፈበት የአድዋ በዓል ዋዜማ ዕለትም በአዲስ አበባ ሚሊንየም አዳራሽ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ የተከሰከሰበት የህወሓት 40ኛ ዓመት እየተከበረ ነው።ይህንን ሁሉ ድርጊቶች እያየን አድዋ ላይ የሞቱትን ኢትዮጵያውያን እናስባለን።ከጫፍ ሀገር ኢትዮጵያ እስከ አድዋ ድረስ ተጉዘው የሞቱልንን፣ዛሬ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ያበቁንን ሰማዕታት በከፍተኛ ክብር እንዘክራለን፣አርማቸውን እናነሳለን።የአድዋን ድል የማያውቁ የአድዋ ልጆች ልብ ግዙ! እንላለን።ባዕድ-አደር ጫወታቹን እንድታቆሙሉንም ትጠየቃላችሁ።
ጉዳያችን የካቲት 23/2007 ዓም (ማርች 2/2015)
No comments:
Post a Comment