ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, January 6, 2015

በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መባ ካቀረቡት ነገስታት ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያዊ ንጉስ ባዜን ለመሆኑ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ (ከዲ/ን ኢንጅነር አባይነህ ካሴ ገፅ ላይ የተወሰደ)



ያገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በፊቱ ይሰግዳሉ
"ያገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ ወጸላእቱሂ ሐመደ ይቀምሑ ነገሥተ ተርሴስ ወደሰያት አመኃ ያበውኡ ነገሥተ ሳባ ወአረብ ጋዳ ያመጽኡ ወይሰግዱ ሎቱ ኲሎሙ ነገሥተ ምድር ወይትቀነዩ ሎቱ ኲሎሙ አሕዛብ "
"በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ። የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ። ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል። አሕዛብም ሁሉ ይገዙለታል።" መዝ ፸፩፥፱-፲፩።
ቅዱስ ዳዊት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ፱፻ /ዘጠኝ መቶ/ ዓመት በፊት ከተናገራቸው ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ከተመለከቱ ትንቢቶች መካከል አንዱ እና ተጠቃሹ ይህ ከፍ ብለን በርእስ ደረጃ ያነሣነው ሲሆን እጅግ የሚያስደምም መልእክት ያለው ነውና በጥንቃቄ ልንመረምረው ይገባል፡፡
ከሁሉ አስቀድመን ቅዱስ ዳዊት ስለ ኢትዮጵያ ሲናገር ይኽ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ ከዚህ ቃል አስቀድሞ "ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር- ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች" ሲል መናገሩን ያስታውሷል፡፡ መዝ ፷፯፥፴፩። 
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እጆቿን ሲል እጅ ኃይል ነው፡፡ ወድቀው ይነሧል በእጅ፣ አጥተው ይከብሯል በልጅ እንዲሉ በእጅ የራቀውን ያቀርቡበታል፣ የቀረበውን ያርቁበታል፡፡ በእጅ ቢይዙ ያጠብቁበታል፣ ቢሰነዝሩ ያደቅቁበታል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ እጅ ሲል ኃይል፣ ጉልበት፣ መመኪያ ለማለት ሲሆን እርሱም እግዚአብሔር መሆኑን ያጠይቃል፡፡ ትመካበታለች እና ጠላት ሲመጣባት እርሱን ይዛ እርሱን ተማምና ተዋግታለች፡፡ ድል አቀዳጅቷትም ለዓለሙ የነፃነት ፋና ወጊ ሆና ስታበራ ትኖራለች፡፡ ስለሆነም በእግዚአብሔር ዘንድ ልዩ ስፍራ ያላት ቅድስት ሀገር ናት ለማለት ሁለት ጊዜ ማሰብ አያስፈልግም፡፡
ከፍ ብሎ በተነሣው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት ኢትዮጵያ በፊቱ ይሰግዳሉ የሚል ትንቢት አለ፡፡ ይኽ ትንቢት ደግሞ ከወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ጋር ተያይዞ የተነገረ ነውና ልብ ብሎ ለተመለከተው ስለ ዳግማዊዉ ልደት የተነገረ መሆኑነ መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ሲወለድ ይኽ ቃለ ትንቢት ተፈጽሟልና፡፡ 

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ ጌታችን በተወለደ ጊዜ ከተፈጸሙት ድርጊቶች መካከል ሰብአ ሰገል ለሕፃኑ ስግደት አምኃ ማቅረባቸውን ነግሮናል፡፡ እንዲህ ሲል "እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር ዐዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።" ማቴ ፪፥፱-፲፩።
ሕፃኑን ዐዩት፣ ሰገዱለት፣ እጅ መንሻ አቀረቡለት የሚሉት ተከታታይነት ያላቸው ቃላት እጅግ ትኩረት የሚስቡ ናቸው፡፡ ሰብአ ሰገል ሕፃኑን ዐዩት ሲል በሥጋ ምርያም በክበበ ትስብእት በግርማ መለኮት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም ዐዩት ብሎ አልቆመም፡፡ አስከትሎ ሰገዱለት አለ አንጂ፡፡ ግርማ መለኮቱን ቢያዩ የእነርሱን ማዕረግ ትተው ዘውዳቸውን አውልቀው ለጌቶች ጌታ ለነገሥታት ንጉሥ ጎንበስ ቀና ብለው ሰግደውለታል፡፡ ሕፃን ነው ብለው አልተጓደዱም ወይ አላመነቱም፡፡ ቀጥለውም ለእርሱ መንግሥት ገባሪዎች መሆናቸውን ሲያጠይቁ እጅ መንሻን ሰጥተውታል፡፡  
በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት የተነገረው ትንቢት እንደሚገልጠው እጅ መንሻ የሚያቀርቡ ሰዎች ማንነት ነገሥታት መሆናቸው እርግጥ ነው፡፡ በከብቶች ግርግም በእመቤታችን እቅፍ በግእዘ ሕፃናት ሲነጋገር አግኝተውት ለጌታችን እጅ መንሻ ያቀረቡትን ቅዱስ ማቴዎስ ሰብአ ሰገል ይላቸዋል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ነገሥታት ሲላቸው ቅዱስ ማቴዎስ ሰብአ ሰገል በማለት ጠርቷቸዋል፡፡ ሁለቱንም ግን አምኃና ሰጊድ ማቅረባቸው አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በፊቱ ይሰግዳሉ እንዳለው ቅዱስ ማቴዎስ ደግሞ ወድቀውም ሰገዱለት ብሏልና፡፡  
ቅዱስ ዳዊት እነዚህን ቅዱሳን ከኢትዮጵያ ጋር ማዛመዱ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሲጀምር "ኢትዮጵያ በፊትህ ይሰግዳሉ" ብሎ ሲሆን ሲፈጽምም "የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ" ብሎ ነው፡፡ በዚህ ቃለ ትንቢት ውስጥ ጉልህ ድርሻ የተሰጣት ኢትዮጵያ ለመሆኗ አንድ ጊዜ ኢትዮጵያ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሳባ በሚሉ የሀገሪቱ ተለዋዋጭ መጠሪያ ስሞች ደጋግሞ መጥራቱ ራሱ ምስክር ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከሰብአ ሰገል መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በኩራት መናገር ይቻላል፡፡ 

ሰብአ ሰገል፣ የጥበብ ሰዎች እየተባሉ ከሚነገሩት ሦስት ነገሥታት አንዱ ኢትዮጵያዊው ባዜን በተነገረለት ትንቢት በተቆጠረለት ሱባኤ መሠረት ገስግሶ ተጉዞ ቤተልሔም ከከብቶች ግርግም ደርሶ ሰግዶ አምኃውን አቅርቦ ተባርኮ ተመልሷል፡፡ ስለልደተ ክርስቶስ ለመናገር በሀገር ደረጃ ሊቀድመን የሚችል ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ነቢዩ እና ወንጌላዊው ተባብረው መስክረውልናልና፡፡ ስለሆነም የጌታችን ልደት ለኢትዮጵያ የተለየ ትርጉም አለው፡፡ ለማን መስገድ እንዳለብን የምናውቅ ሕዝቦች ነን፡፡ ጌታችንንም እመቤታችንንም ያወቅናቸው እዚያው ቤተልሔም ተገኝተን ግርማውን ዐይተን፣ ቅዱሳን መላእክት ከእረኞች ጋር ሲዘምሩለት ሰምተን፣ አድግና ላሕም ትንፈሻቸውን ሲገብሩለት ተመልክተን፣ የሌሊቱን ግርማ በመሎኮታዊ ሥልጣኑ በብርሃን ጸዳል ሲሞላው ዐይተን እንጂ በስሚ ስሚ ያወቅነው አይደለንምና ፍቅሩን ከልቡናችን ያወጣብን ዘንድ የሚችል አይኖርም፡፡ እኛው ሽተነው እኛው ፈልገነው ሄደናልና፡፡ 

እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!!!

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...