ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, January 13, 2015

በኢትዮጵያ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ቢከሰት ጉዳቱ ምንድነው? (የጉዳያችን ጡመራ ወቅታዊ ምልከታ)


ኢትዮጵያ ከንጉሳዊ መንግስት ወደ ወታደራዊ ደርግ ከወታደራዊ ደርግ ወደ ኢህአዲግ/ወያኔ የጎሳ ፖለቲካ ከተሻገረች አራት አስር አመታት አለፉ።ከአራት አስር አመታት በፊት በየካቲት፣1966 ዓም የተነሳው የለውጥ ነፋስ ኢትዮጵያ ልጆቿን ሲያሰድድ እና ሕዝቡን ሲያስነባ ዘመናትን አሳልፏል።

ዛሬ በመላው አለም ከሁለት ሚልዮን ያላነሱ ኢትዮጵያውያን ከቀያቸው ተሰደው በማያውቁት ቦታ በስደት ይኖራሉ።ሕዝብ የገቢው መጠን ከእለት ወደ እለት እያሽቆለቆለበት መቆምያ ጠፍቶበታል።የወር ደሞዝተኛው ህይወቱን ለማቆየት ያህል ደሞዙን ይቀበላል እንጂ ተስፋ መቁረጥ አንገላቶታል።ነጋዴው ከባለስልጣናት ጋር አብሮ ካልሰራ ወይንም የስርዓቱ አካል መሆን ካልቻለ የትም እንደማይደርስ አውቆታል።ተማሪው ከትምህርት ስርዓቱ ጋር ያለው ችግር እንዳለ ሆኖ ተምሮ ወዴት እንደሚሄድ፣ምን እንደሚሰራ እና ቤተሰቡን መደገፍ እንደማይችል ተስፋ በቆረጠ ስሜት ውስጥ ነው። መምህራን አንድ ለ አምስት በተጠረነፉበት አገዛዝ ስር ሆነው ነፃ የማሰብ እና የመደራጀት መብታቸው ተገቶ በከፍተኛ ምሬት ውስጥ ገብተዋል።ዩንቨርስቲዎች በቁጥር ይጨምሩ እንጂ በ 1960ዎቹ ወቅት ከነበረው ሃሳብን የመግለፅ፣የመሰብሰብ መብቶች ሁሉ የወረደ ደረጃ ላይ ይጋኛሉ።

ከከተሞች እርቆ የሚኖረው ሕዝብ በጎሳ ፖለቲካ የመኖር ዋስትናው ጠፍቷል።አፋር፣ጉጂ ዞን፣ሁመራ፣ሞያሌ፣ኡጋዴን፣ቡራዩ (አዲስ አበባ ዙርያ)፣ድሬዳዋ፣ሐረር-አረማያ(ዩንቨርስቲ)፣አዲግራት እና ሌሎች ቦታዎችም ከስርዓቱ አሰራር እና ፖሊሲ ሳብያ ግጭቶች ተስፋፍተዋል።

በሌላ በኩል በስርዓቱ ውስጥ ያሉት አካላቱ እራሳቸው  በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ መሆናቸው ያስታውቃል።የአመራሩ ደካማ አቅም ከጎሳ ፖለቲካ እና አደረጃጀት ጋር ተዳምሮ መድረሻን የማያውቅ የዕለት ኑሮውን ብቻ የሚያስብ ተንቀሳቃሽ ማሽን እየመሰለ ነው የስርዓቱ አካል።

የውጭ ንግዱ መሰረት ያደረገው የቡና ገበያ መቀነሱን እራሱ መንግስት ያመነው ጉዳይ ነው።የውጭ ምንዛሪ መጠን ተመናምኗል። ሙስና ከመንሰራፋቱ የተነሳ ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል።የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ውስብስብ ዲፕሎማሲን እያስከተለ ነው።የግድቡ ግንባታ ከሕዝቡ ያሟጠጠውን ሀብት ያክል እየተሰራ ነው ወይ? ሲባል አለመሆኑን መመልከት ይቻላል።ኢቴቪም የግድቡን ጉዳይ ከወሬ አርስትነት አውጥቶታል።

ፎቶ-ሱማልያ አሚሶን የተቀላቀለ የኢትዮጵያ ወታደር (KEYDMEDIA)

ባጭሩ አሁን ያለንበትን ጊዜ ለመናገር ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ያልታወቀ በብዙ ችግሮች ውስጥ ተወጥራ ሳለ መንግስቷ ግን በዝምታ የሚመለከታት ሀገር ሆናለች።ምላሽ እና ብዙ አፋጣኝ ውሳኔ የሚጠብቁ ጉዳዮች ጠረንጴዛ ላይ ተቀምጠዋል።የኤርትራ ፖለቲካ ጉዳይ ገና አልተፈታም።ኢትዮጵያ የባሕር በር መብቷን አቶ መለስ ''አያስፈልጋችሁም'' በማለታቸውም ጭምር አለም አቀፍ ተፅኖ የመፍጠር አቅማችን ተድበስብሶ ቆይቷል። መቼም ቢሆን ግን ጉዳዩን ማድበስበስ አይቻልም።በአለም ላይ 90 ሚልዮን ሕዝብ ሆነን የባሕር በራችን በሰበብ አስባቡ የተዘጋብን ብቸኛ ሀገር ነን።ቀይባህር ላይ የሚደረገው ማናቸውም ኮሽታ ለፀጥታም ሆነ ለሰላም በቅርብ የሚያገባን እና የሚመለከተን ሕዝብ ነን።

የለውጥ ምልክት ብቻ ሳይሆን ስሜቱ እየጋለ ነው

የለውጥ ምልክት ብቻ ሳይሆን ስሜቱ እየጋለ ነው።ለውጡ ግን በታምር ሊሆን አይችልም።የሃሳቦች መስፋት እራሳቸው ከየትም ቦታ እና በማንኛውም ጊዜ ለውጥ የመከሰቱን ሁኔታ በእራሳቸው አመላካቾች ናቸው።ሕዝብ ለውጥ ለማምጣትእና በአንድነት ውሳኔ ላይ እንዳይደርስ ከአንድ ለአምስት መጠርነፍ ጀምሮ እስከ ኑሮ ማክበድ አለፍ ሲል ደግሞ በጎሳ መከፋፈል እየተሰራባቸው ያሉ የስርዓቱ የወቅቱ ስራዎች ናቸው።ሁሉም ግን ውሎ አድሮ የድንጋይ ላይ ቅቤ ሆነው መቅለጣቸው አይቀርም።

የሥርዓት መበስበስ መዘዙ ቀላል አይደለም።ሀገር ይዞ መጥፋት ብቻ ሳይሆን ለተከታታይ ትውልድ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል። ጥያቄው የርዕዮተ አለም ብቻ አይደለም።የጎሳ ፖለቲካ ከግለሰብ መብት መከበር መሰረት ካደረገው ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ጋር ብቻም አይደለም።ኢትዮጵያን ከውስጥም ሆነ  ከውጭም ከከበባት የህልውና አደጋ ጋር ሁሉ የሚደረግ ትንቅንቅ ነው።መጪውን የለውጥ ሁኔታ ወዳልተፈለገ እና ፈፅሞ ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ለመውሰድ የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ ፅንፈኛ ብሔርተኞች የተቻላቸውን እያደረጉ ነው።ለእዚህም እንዲረዳቸው ከወዲሁ ህዝብን በዘር የማናከስ ሙከራ ከኢህአዲግ/ወያኔ ባልተናነሰ መልክ ተያይዘውታል።ለእነኝህ የለየላቸው ጠላቶች የበለጠ አመቺ የሚሆነው የኢህአዲግ/ወያኔ የጎሳ ፖለቲካ በቦታው እንዲቆይ ሲደረግ ነው።የእርሱ መነሳት የእነርሱን የአውሬ በሕሪ ፍንትው ብሎ እንዲታይ ያደርጋል።

ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ምንም ያክል ቢገዝፉ ግን የኢህአዲግ/ወያኔ ፖሊስ እና አመራርን የሚሸከም ህዝብም ሆነ ሀገር የለም።እኔ ባላወራውም በተፈጥሮ ሂደት ኢህአዲግ/ወያኔ በራሱ መቀጠል የማይችልበት የመጨረሻዋ ምዕራፍ ላይ ይደርሳል።ቀጥሎ ማን ሀገር ሊያረጋጋ ይችላል? 

ቀጥሎ ማን ሀገር ሊያረጋጋ ይችላል? 

አፍርሶ የመስራት አባዜ የሆነ ቦታ እንዲቆም ከፈለግን መጪውንም አፍርሶ ከመስራት በተሰራው ላይ መስተካከል የሚችለውን በማስተካከል የተበላሸውን ማረም ተገቢ ነው።አሁን ያለው የኢህአዲግ ሰራዊት ከየትም የመጣ አይደለም።ከኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።ምንም ያክል የበላይ መኮንኖች ተዋፅኦ ከተወሰነ አካባቢ መሆኑ ቢታወቅም ከስር ያለው ሰራዊት ተዋፅኦ የተሻለ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።ኢህአዲግ/ወያኔ የደርግ ሰራዊትን በመበተን የሰራው ስህተት መልሶ እራሱን እንደጎዳው እና መልሶ ልመና መግባቱን የምናስታውሰው ጉዳይ ነው።በመሆኑም ሰራዊቱ ባጠቃላይ ባይሆንም ለሀገር የሚቆም እና የለውጥ ሐዋርያ የማይሆንበት ምክንያት የለም።

ስርዓቱ እራሱ በውስጡ በሶስት ቅራኔዎች ተወጥሯል።የእዚህ አይነት መወጠር ደግሞ መውጫ የሚፈልግ ሰራዊት እንዲነሳ ይጋብዛል።የስርዓቱ ሶስቱ የተወጠረባቸው ጉዳዮች -

1ኛ/ ልክ በሌለው ሙስና በተዘፈቁ እና ሙስናው ውስጥ በሌሉ መካከል፣
2ኛ/ የኤርትራ ተወላጆች በስልጣን እርከን ላይ መኖር ባስከፋቸው እና ባላስከፋቸው መካከል እና 
3ኛ/ የኢህአዲግ/ወያኔ የጎሳ ፖለቲካ መቀየር አለበት በሚሉ እና እንዳለ እንቀጥል በሚሉ መካከል ናቸው።

እነኝህ ቅራኔዎች በተለይ በትግራይ የአረና ትግራይ ጨምሮ የአዲግራት፣አክሱም ተውላጅ የሆኑ የሰራዊቱ አባላት ዙርያም ከፍተኛ ጉርምርምታ ፈጥሯል።''ከ ኤርትራ ጋር ለመነጋገር አስመራ ድረስ ለመሄድ ዝግጁ ነኝ'' ካሉት ከ አቶ ኃይለማርያም ጀምሮ ኢትዮጵያ በእዚህ ደረጃ ስትዋረድ ዝም ባሉ አካላት ላይ ሁሉ ጥርስ ያልነከሱ የሰራዊቱ አባላት የሉም ማለት አይቻልም። 

አንድ ምሽት ወይንም ንጋት ላይ በኢትዮጵያ ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግስት ቢደረግ ምን ይመጣል? 

ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግስት በኢትዮጵያ ቢደረግ ኢህአዲግ/ወያኔ ያለፈ የጎሳ ፖለቲካውን መልሶ ሊዘፍንበት አይችልም።አሁን ያለንበት አለም አቀፍ ሁኔታ ደርግ ከነበረበት ሁኔታ ይለያል።ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ጥያቄ ኢትዮጵያን ከእነ ክብሯ እና አንድነቷ ማስቀጠል ነው።አሁን በኢህአዲግ/ወያኔ የተያዘው መንገድ ሊያስከትል ከሚችለው ጥፋት አንፃር የመፈንቅለ መንግስት የሚያመጣውን  መነቃቃት፣የተሰደደው ሁሉ ምህረት ተደርጎለት ወደሀገር የመግባት ዕድል መፍጠር፣የነፃ ሚድያ መፈጠር፣የሙያ ማኅበራት እና የፖለቲካ ድርጅቶች በሕዝብ በግልፅ ተተችተው ነጥረው የሚወጡበት ዕድል ከመፍጠር  አንፃር ኢትዮጵያን ጉዳት ላይ የሚጥላት አይመስለኝም።

በሌላ በኩል መፈንቅለ መንግስት የበለጠ አፋኝ እና አምባ ገነን መንግስት ቢያስከትልስ? የሚል ስጋት እንደማይጠፋ አምናለሁ።አሁን ባለው የአለም ተጨባጭ ሁኔታ ይህ ሊሆን አይችልም።የአለም ተጨባጭ ሁኔታ ብቻ አይደለም ኢትዮጵያውያን የደረስንበት የአለፈው እና የመጪው ተሞክሮ በእራሱ ቀላል አይደለም።አሁን ያለው ችግር ያለንን አቅምም እንዳናዳብር በጎሳ ፖለቲካ የሚጮህ መንግስት መኖሩ እና ሁሉ ነገር ባለበት መርገጥ መሆኑ ነው።እናም ለውጥ ከወታደር ቤትም ቢመጣ አስፈሪ አይደለም።ይልቁን በመግባባት ትክክለኛ የሽግግር ወቅት ለማድረግ የሚጠይቀው የአንድ ወይንም ሁለት አመታት ጊዜ ሊሆን ይችላል።መግነጢሳዊ የሆነ የሕዝብ ንቅናቄ ተፈጥሮ ለውጥ ቢመጣ ዞሮ ዞሮ ኃላፊነቱ ወደ ጦር ሰራዊቱ መዞሩ አይቀርም።ያን ጊዜ እንድያውም ከፍ ያለ ንቀት እና ጥላቻ በሰራዊቱ ላይ ይፈጠር እና አለመደመጥ ሊፈጠር ይችላል።ሰራዊቱ ቀድሞ አንድ እርምጃ ከሄደ ግን የውጭም ሆኑ የውስጥ የጥፋት ኃይሎችን ከሕዝቡ ጋር አደብ የማስገዛቱ እንዲሁም አዳዲስ የእድገት ሃሳቦች እንዲመነጩ ሕዝብ ወደ እርቅ እና ሰላም የሚሄድበት መንገድ ሊፈጠር ይችላል።

ጉዳያችን ጡመራ 
ማሳሰቢያ - ይህ ፅሁፍ ጥር 28/2006 ዓም በእዚሁ በጉዳያችን ብሎግ ላይ ወጥቶ ነበር።አሁን ካለንበት ወቅት ጋርም ስለተስማማ እንደገና ጥር 5/2007 ዓም ወጥቷል።

No comments: