ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, December 20, 2012

በ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ የቀጠለው እገታ


· ዛሬ ምዕመኑም ሆነ አባቶች ቅድምያ ዕርቅ መፈፀም አለበት ብለው ደፋ ቀና ሲሉ መንግስት የተወሰኑ አባቶች ጋር ሆኖ ድብቅ ሕግ አርቃቂ፣ፓትርያሪክ መራጭ እና አስመራጭ የሆነበት ሂደት መንግስት ሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱ ጠላቶች ጋር ለመሰለፉ አመላካች ምልክት ነው፣

· ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ እረፍት ወዲህ ደግሞ ኢህአዲግ ሁለት አይነት ፖሊሲ እየተከተለ ነው፣

· ኢህአዲግ ቤተክርስትያንን እንደ አንድ ስጋት እንዳያይ ያልተፃፈ፣ያልተነገረ ምክር የለም፣

· '' ሕዝባዊ ትግል'' ወደ ስልጣን ወጥቻለሁ ያለ መንግስት ህዝብን ማስተዳደር ካልቻለ ስልጣኑን ባፋጣኝ እንዲለቅ መጠየቅ አለበት፣

· ኢህአዲግ ሃያ አንድ አመት ካልተማረ መቼ ነው የሚማረው ? የትናንት ዝምታ ዛሬ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ተገብቶ ፓትሪያርክ ልሰይም ካለ ነገ ፓትርያሪክ አያስፈልግም ለማለት እንዲሚዳዳው አይጠረጠርም።

ከተማ በሚኖሩ ምዕመናን ዘንድ እረፍት ቀናትን እያስታከኩ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙትን ጥንታውያን ገዳማት መሳለም እና መጎብኘት የተለመደ ነው በሄዳችሁበት ቦታ ደግሞ ስለ ቤተክርስቲያን፣ስለ ሃገሩ፣ስለወንዙም ማውራት ይኖራል።በብዙ ቦታዎች (ገዳማቱ በሚገኙበት አካባቢ የሚኖረውም ሕዝብ) በተለይ አዲስ አበባ ነው የመጣነው ካላችሁ አዲስ አበባ ሁሉም ጋር የምትደርሱ የሚመስላቸውን ሰዎች ማግኘት እንግዳ አይደለም። ለምሳሌ እናንተ ወደ ክፍለሀገር ወጣ ብላችሁ '' አዲስ አበባ ነው የመጣሁት'' ካላችሁ ''አዲስ አበባ አንድ ወንድም ነበረኝ ታውቀዋለህ?'' የሚል ጥያቄ ቢገጥማችሁ ''አዲስ አበባ እኮ ሰፊ ነው ሁሉም ሰው እርስ በእርሱ አይተዋወቅም'' እንደምትሉት ማለት ነው።የ እኔ እውነተኛ ገጠመኝ ግን ሁል ጊዜ ሲታወሰኝ ይኖራል። በገተመኙ ውስጥ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ ሞራላውም ሆነ ሃይማኖታዊ ስርዓት እየተጣሰ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ምዕመኑ በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ነገር እጅግ ቅጥ እያጣበት ያለ መሆኑን ለመረዳት አላዳገተኝም።

ገጠመኝ - አክሱም ፅዮን ሶስት ቀናት ቆይታ

አዲስ አበባ ንጋቱ 11 ሰዓት ላይ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን በር ላይ የሚጠብቀኝን አውቶቡስ ላይ ሻንጣየን ጀርባ መጫኛ በኩል ከትቼ ጉዞ ቀጠልኩ።መንገዳኛው ከተለያየ ቦታ ቢመጣም ቀጠሮው ወደ አክሱም ፅዮን ማርያም ነውና በመንገድ ላይ የነበረው የምሳ ዕረፍትም ሆነ አዳር ቀደም ብሎ በተነገራቸው እና እንግዶች መምጣትን ይጠባበቁ በነበሩ አብያተ ክርስትያናት ነበር። መቀሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አዳር ካደረግን በኃላ ቀጥለን አክሱም ፅዮን የገባነው ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ነበር።በ ጊዜው ብዙ መንገዶች አዲስ አበባ ውጭ የነበሩት ግንባታ ላይ ስለነበሩ መንገድ እያሳበሩ መሄድ ጎርባጣውን ቦታ ቀስ ብሎ ማለፉ ሁሉ መግባት ከሚገባን ሰዓት መዘግየታችንን አስታውሳለሁ።

ርዕሰ አድባራት አክሱም ፅዮን ስንደርስ ግቢው መግቢያ በር ተዘግቶ አካባቢው ፀጥታ አውቶቡስ ተሳፍሮ የመጣው ምዕመን አካባቢውን እንዳይረብሽ ሹክሹክታ ብቻ እያወራ ቤተክርስቲያኑ መግቢያ በር ላይ ፈሰሰ።ይህ ጉዞ ንግሥ በዓል የሌለበት (አዘቦት) ቀን ነበር እና በሩ ዝግ ሊሆን እንደሚችል አውቶቡስ ላይም እየተውያየን ነበር።ግምታችን አልቀረም ተዘግቷል። ሁሉም በትካዜ እንደቆመ ቤተክርስትያኑ ጥበቃዎች ደረሱ እና ከየት እንደመጣን ጠየቁን።ከ አዲስ አበባ መምጣታችንን እና ቤተክርስቲያን ያፃፍነውን ደብዳቤ አሳየናቸው። መጀመርያ ግቢውን በር ለመክፈት አንገራግረው ነበር በኃላ ግን ''አሁን ንቡረ ዕድ ሳይፈቅዱ ማደርያ ክፍል ማሳደር አንችልም የግቢውን በር እንክፈትላችሁ እና እዚሁ ሳሩ ላይ ታድሩ እንደሆነ? ---'' አሉን። ተሳፋሪው ተደሰተ ''ከደጇ አድርሶን ደጇ ለማደር አብቅቶን'' እያልን መሬት የማረፍያ ቦታ ለማግኘት ጠጠሩን፣ስንጥሩን ማነሳሳት ጀመርን። ብርዱ እንቅልፍ በፊት እንጂ እንቅልፍ በኃላ ሁሉም የት እንደወደቀ ሳያውቅ ቤተክርስቲያን ደውል ሲደወል እና ኪዳን የሚመጡት ምእመናን ኮቴ ስንሰማ አክሱም ፅዮን መሆናችንን አውቅን።
የ ሙሴ ፅላት የሚገኝበት ( አክሱም ፅዮን)
 

በሚቀጥለው ቀን ንቡረ ዕድ( አክሱም ፅዮን እና አዲስ አለም ማርያም ቤተክርስትያን አለቃ የሚሰጥ ማዕረግ ስም ነው) እንግዳ ማረፍያ ቦታ አዘጋጅተውልን በቆየንባቸው ቀናት ሁሉ እየለቱ ይጎበኙን ያስተምሩን እንደነበር አስታውሳለሁ። እዚህ ፅሁፍ ገጠመኝነት ላነሳ የፈለኩት ግን ቆይታችን ላይ ስለነበረች አንዲት ምሽት ነው።በ ማረፍያ ቦታችን የምግብ ሰዓት ላይ ለመንገደኛው የሚጠጣ ውሃ ለማምጣት ከተመደቡት ውስጥ እኔ ነበርኩ እና ውሃውን አክሱም ፅዮን አምስት ደቂቃ እርቀት የሚገኝ ሬስቱራንት ለማምጣት ሄድኩ። በወቅቱ ቤተክርስቲያኑ የሚደርሰው ውሃ ያልነበረ መሆኑን ( ቴክኒክ ምክንያት) ይህ ሬስቱራንት ግን ባለውለታ የነበረ መሆኑን አባቶች ደጋግመው በማመስገን ሲገልጡ ሰምቻለሁ።ይችን ምሽት ታድያ ሬስቱራንቱ ጋር ውሃ ስናመላልስ የተዋወቅነው ጎልማሳ ወደ ደብረ ዳሞ በሚቀጥለው ቀን ስለምንሄድ ደህና ሰንብት ዛሬ የመጨረሻ ምሽታችን ነው ለማለት ሰላምታ ማቅረብ ስጀምር ቁጭ እንድል ጠየቀኝ። የመጨረሻውን ባለዲ ውሃ ስላደረስኩ ለመቀመጥ አላንገራገርኩም።

''ሰሞኑን ሁሉ ስራችሁን ስመለከት ነበር። በጣም ነው የገረመኝ'' አለኝ።

''እኛ እንበል እንጂ ሶስት ቀን ሙሉ ስናስቸግር ሰነበትን '' አልኩት ዝም አለኝ። ቆየ እና በረጅሙ ተነፈሰ እና ትኩር ብሎ አየኝ።

ቀጠለ እና ''ትግርኛ ትችላለህ?'' አለኝ።

''አልችልም'' አልኩት። ወደ ኃላው ደገፍ አለ። ለምን እፎይታ እንደተሰማው ግራ ተጋባሁ። ቀጠለና :-

'' አየህ ትውልዴም ሆነ እድገቴ እዚሁ አክሱም ነው። ወላጅ እናቴ ወልዳ ታሳድገኝ እንጂ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ብቻ ሳይሆን ለነገ እኔነቴ እግዚአብሔር ወሳኝ እንደሆነ አውቃለሁ። አሁን ልነግርህ የፈለኩት ቤተክርስቲያን ላይ ስለደረሰው አደጋ ነው። አክሱም ፅዮን እንደ እናንተ እንግዳ መጥቶ ሲሄድ ችግር ውስጥ ያለ የማይመስለው ብዙ ሰው ነው። ብዙ ፈተና ላይ ነው ያለነው። አንድ ወቅት እንዲያውም ማንም ጳጳስ እንዳይመጣ ብለን ማስጠንቀቅያ ሰጥተን ነበር።ፓትርያርኩም እንዳይመጡ የሀገር ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ንቡረ ዕዱን ጠየቀዋል። አሁን በቅርብ ስንት አማላጅ ልከው በመንግስት አስገድደውን ነው ለንግስ ዘንድሮ ስንት ፖሊስ አጀብ የመጡት።'' አለኝ።

ብዙ ማውራት አልፈለኩም። የሆነ ሃሳብ እኔ ፈልጎ መሰለኝ እና '' ፈተና ነው ቤተክርስቲያን በፈተና ነው የኖረችው'' አልኩት።

''እኛ እኮ ኢትዮጵያ ነን።በጣልያን ጊዜ ማን ባንዳ እንደነበር ዛሬም ኢትይጵያን እና ቤተክርስቲያኗን ሊያፈርሱ የተነሱት እነማን እንደሆኑ እናውቃለን። አየህ'' አለና የቀዳት ስፕራይት ግማሽ አደረሳት እና ቀጠለ-

'' አየህ ባለፈው ሰሞን አንድ ፈረንጅ አክሱም ፅዮን ታቦት ማየት አለብኝ ብሎ ቱሪስት ሆኖ መጣና አንድ ቀን ድንገት አክሱም ፅዮን ታቦት ወዳለችበት ቅጥር ዘሎ ገብቶ ተያዘ።ካህናቱም ሕዝብ የወከላቸው ሀገር ሽማግሌዎችም ፈረንጅ ፖሊስ አስረክበው ተገቢው ፍርድ እንዲሰጥ ጉዳዩን ለመከታከል ወሰኑ። ግን ፈረንጁ ምን እንደተደረገ ታውቃለህ?'' አለና ጠጋ አለኝ። ዙርያውን መልከት አለና '' ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ እና መንግስት ሽንጣቸውን ገትረው ተከራከሩለት ሶስት ቀን ብቻ ታስሮ ወደ አዲስ አባበ ተላከ እና ወደ ሃገሩ እንዲገባ ተደረገ።በኃላ የሀገር ሽማግሌዎች ማስጠንቀቅያ ሁሉ ተሰጣቸው።'' አለ እና ንዴቱን እንዳላይበት ፊቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ ደጋግሞ ያዞር ጀመር።

'' እና ነገሩ እንዲሁ ተዳፍኖ ቀረ?'' አልኩት።

'' ህዝቡ ተወያየ እና አሁን በኃላ መንግሥትንም ቤተክህነትንም አናምንም አክሱም ፅዮን ያለነው እኛ ብቻ ነን። ስለዚህ በድብቅ ህዝቡ በተራ ጠባቂ እያስቀመጠ አንዳች ፀጉረ ለውጥ ሰው ድብቅ ክትትል እንዲደረግበት አቅም በላይ ለሆነ ነገር ሁሉ ደውል እንዲደወል ወሰነ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን አሁንም ትልቁ ፈተና ያለብን መንግስት ነው። እኔ ይህን የምነግርህ የምተነፍስበት ስላጣሁ ነው።ሰሞኑን የናንተን ሥራ ስለወደድኩት እና ቤተክርስቲያን ልጆች መሆናችሁን ስላመንኩበት ነው።'' አለኝ። ''ገረመኝ።በተለይ እዚህ ፅሁፍ ላይ ያልገለፅኩት ጣልያን ወረራ ጀምሮ የነበረውን የባንዳነት እንቅስቃሴ አክሱምን ልጆች ኢትዮጵያ ያደረጉትን ተጋድሎ ዘመኑን ባንዳነት እና አክሱም ልጆች እግር እሳት ስለሆነባቸው ነገር በሰፊው ያጫወተኝ ሁሉ ዛሬም አእምሮዬ ላይ ይመላለሳል።

'' የሚገርም ታሪክ ነው'' አልኩት በዝምታ ሁለታችንም ስናስብ ቆየን በኃላ። ሰዓቴን ተመለከትኩ ለካ እኩለ ሌሊት ሊሆን አምስት ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውታል። ለመሄድ ተነሳሁ ከመስማት በቀር ጉዳዩን ስላላረጋገጥኩ ምንም ማከል አልቻልኩም።

እሱም ተነሳ እና እንዲህ አለኝ።

'' እናንተ ብዙዎቻችሁ ወጣቶች ናችሁ። ብዙ ለሀገራችሁ መስራት ይጠበቅባችኃል። ዛሬ ቤተክርስትያናችን በመንግስት እና ጥቅመኛ አገልጋዮች ታግታለች። እመነኝ ታግታለች። እግዚአብሔር ያድናታል ግን ለመታዘብ ዝም እንደምንል እና እንደማንል ሊታዘብ ጥቂት ጊዜ ዝም ብሎ ያየናል።ስለ እውነት ከተነሳን እግዚአብሔርም ይነሳል። እለት ኑሮ ብለን ሐሰተኞች ጋር ከቆምን መጀመርያ እኛ ላይ ፈርዶ ሌላ እውነተኛ ሰው ያስነሳል። ለማንኛውም ሰላም ግቡ።'' አለኝ። ትከሻውን ከትከሻዬ አስነክቶ ተሰናበተኝ። አንድ ጥያቄ ሳልጠይቀው መሄድ እንደሌለብኝ ተረዳሁ እና ጠየኩት ''ግን የመንግስት ፍላጎት ምን ይመስልሃል?'' አልኩት። መለሰልኝ '' የተለያየ ነው። አንዱ ቤተክርስቲያን ድሮ ስርዓት ናፋቂ የተሰበሰበባት ነች ብሎ መንግስት ስለሚያስብ መቆጣጠር እና መምራት አለብኝ ብሎ ሃያ አመት በፊት ያስብ ነበር። ሌላው ኦዲተር የማያየው ሲሰረቅ የማይታይባት ጥገት ላም ሆናለች እና ቤተርክርስቲያን ገንዘቧን እየዘረፉ ብዙዎች 'ሚሊየነር' ሆነዋል እዚህ ላይ ብዙ ባለስልጣናት ይታማሉ።ሌላው ግን ሚስጥርም የመንግስት የበጀት ማሟያ ሆናለች።'' አለኝና ድጋሚ ተሰናበተኝ

ወደማደርያችን ስመለስ ባብዛኛው ተኝተው እራት ያስተናገዱት ልጆች ብቻ እኔ ማምሸት ደንግጠዋል።ይቅርታ ጠይቄ ተኛሁ።ሆዴን ቢርበውም መብላት አልቻልኩም።''ቤተክርስቲያን ታግታለች'' የሚለው ንግግር ጆሮዬ ላይ ደወልብኝ።

ቤተክርስቲያን ላይ የቀጠለው እገታ

ባለፉት 21 አመታት ውስጥ ቤተክርስቲያንን ኢህአዲግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቤተክርስቲያን ላይ የልዩነት ማስፋት ስራውን በብዙ መንገድ ሲሰራ ከርሟል። ሌላው ቀርቶ አጥብያ የተነሱትን ገንዘብ ብክነት ጋር የነበሩ ችግሮችን ለምሳሌ ልደታ ቤተክርስቲያን ገንዘብ ዝርፍያ ጋር ተነስቶ ለነበረው ችግር እንደመንግስት ጉዳዩን ከመመርመር ይልቅ ፈድራል ፖሊስ ልኮ ማሰር እና ወጣቶችን አፍሶ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ አሸዋ ላይ እንብርክክ እያስዳሄ ቁም ስቅል ማሳየትን መርጦ ነበር።በቤተክርስቲያን ላይ የነበረውን አይን ያወጣ ዘረፋ ሁሉ እንዳላየ ሲያልፍ። በል ሲለው ደግሞ ልዩነቶች በተነሱ ቁጥር እርሱን አጀንዳ ለማቅረብ ሲታትር ተስተውሏል።

ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ እረፍት ወዲህ ደግሞ ኢህአዲግ ሁለት አይነት ፖሊሲ እየተከተለ ነው። የመጀመርያው ምዕመኑ አባቶችን እንዲያናንቅ ቀጥሎም በሚከፈተው መንገድ ሁሉ ቤተርክስትያኒቱን ሙሉ በሙሉ ለመንግስት ''ሲጠሯት አቤት ስትላክ ወዴት'' እንድትል ብሎም ሙሉ በሙሉ ትዕዛዝ ተቀባዩ እንድትሆን እየጣረ ነው። እዚህ ወር ውስጥ በተደረገው ውጭ የሚኖሩ እና በሃገርበት ባሉ አባቶች መካከል በዳላስ በተደረገው ውይይት ላይ እንደ መንግስት ኦፊሴል ''ችግሩ እንዲፈታ የመንግስት ምኞት ነው'' የሚል አረፍተ ነገር ለመናገር የኮራው መንግስት ፕሬዝዳንት ግርማ ለፃፉት'' አቡነ መርቆርዮስ ወደመንበራቸው ይመለሱ'' ለሚለው ደብዳቤ እጅግ እንዳስቆጣው ቀጥለው መቶ አለቃ ግርማ በሰጡት የተርበተበተ ንግግር እና ቃል በቃል ቪኦኤ በሰጡት ቃል ''አባቶች ተቸግረዋል ችግር ላይ ናቸው'' ማለታቸው ያመላክታል።

ይህ ሁሉ ታልፎ አባቶች ከዳላስ ውይይት ቀጥለው ሎሳንጀለስ ላይ ለመነጋገር በቀጠሮ ተለያይተው ካበቁ ከቀናት በኃላ ያውም ውይይት ወደ አሜሪካ የሄዱት አባቶች ገና ወደ ሀገርቤት ሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ሪፖርት ሳያደርጉ መንግስት በለመደው አካሂያድ ስድስተኛ ፓትርያሪክ እንዲመረጥ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲመሰረት አዘዘ።

አቡነ ጳውሎስ ምርጫ የከፋ አመራረጥ ሂደት

ቤተክርስቲያን ካለ ፓትርያሪክ መኖር አለባት የሚል ክርክር በማንም ወገን አልተነሳም።ሁለት ነገሮች ግን ግንዛቤ መግባት አለባቸው። እነርሱም እርቅ ሂደቱ በትክክል መከናወን እና አቡነ መርቆርዮስን ፕትርክና ለማዕረጉ ማብቃት ብሎም ሁለት ሲኖዶስ ታሪክን ምዕራፍ ምንም አይነት ዋጋ ቢያስከፍል መዝጋት የሚሉት ናቸው። 1984 ዓም በነበረው አቡነ ጳውሎስ ፕትርክና ምርጫ ሂደት ቢያንስ ነገሮች በስውር የተሄዱ መሆናቸው ተዘግይቶ ቢታወቅም ምርጫው ላይ የሁሉም ሃገረ ስብከት አባቶች ጥሪ ተደርጎ አሁን በውጭ ያሉ አንዳንድ አባቶችም በተገኙበት የተከወነ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ዛሬ ምዕመኑም ሆነ አባቶች ቅድምያ ዕርቅ መፈፀም አለበት ብለው ደፋ ቀና ሲሉ መንግስት የተወሰኑ አባቶች ጋር ሆኖ ድብቅ ሕግ አርቃቂ፣ፓትርያሪክ መራጭ እና አስመራጭ የሆነበት ሂደት መንግስት ሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያኒቱ ጠላቶች ጋር ለመሰለፉ አመላካች ምልክት ነው።

መፍትሄው ምንድነው ?

ኢህአዲግ ቤተክርስትያንን እንደ አንድ ስጋት እንዳያይ ያልተፃፈ፣ያልተነገረ ምክር የለም።እለት እለት ያልገባው እየመሰለ ይብሱን ሲያደማት ግን ተስተውሏል።ዋልድባ ገዳም ድረስ ሄዶ ገዳሙን አርሷል፣የ አትክልት ቦታቸውን ነቅሏል፣መቅብራትን ፈንቅሏል፣የገዳሙን አባቶች በተገኙበት እንዲያዙ (ከሰሞኑ) ማዘዣ ቆርጧል። ከአሁን በኃላ የሚኖሩት መፍትሄዎች እነኝህ ይመስሉኛል።

1/ ምዕመኑ ወደ ቤተክርስቲያን የሚሰጠውን ገንዘብ ለሚቀጥሉት አምስት ወራት      እንዲያቆም ማድረግ

ምዕመናን የሚሰጡትን ገንዘብ ላላተወሰነ ጊዜ ሳይሆን ለተቆረጠ ለምሳሌ ለሚመጡት አምስት ወራት ማቆም አለባቸው። ይህን ሲያደርጉም ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ። ቅድመ ሁኔታዎቹም

-መንግስት  ቤተርክስቲያን ላይ እጁን እንዲያነሳ፣

- ፓትርያሪክ ምርጫ በፊት ዕርቅ ሂደቱ እልባት እንዲያገኝ፣

- ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚደረገው ሙስና ቆሞ የቤተክርስቲያኒቱ ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ አካል ስር ምርመራ ተደርጎ የገንዘብ ገቢ እና ወጪ ሂደቱ ለምዕመናን ግልፅ በሆነ መንገድ እንዲቀርብ እና

-በሙስና ተግባር ንክክነት ያላቸው ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲደረግ ወዘተ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል።

2/ መንግስት ስልጣን ይልቀቅ

ከላይ የተጠቀሰው ፈጣን መፍትሄ ከጅምሩ እንቅፋት ሊገጥመው እንደሚችል ይገመታል።በመሆኑም '' ሕዝባዊ ትግል'' ወደ ስልጣን ወጥቻለሁ ያለ መንግስት ህዝብን ማስተዳደር ካልቻለ ስልጣኑን ባፋጣኝ እንዲለቅ መጠየቅ አለበት። ህዝብን ማስተዳደር ከባድነቱ አንድ ነገር ነው። ማስተዳደር አለመቻል ደግሞ ሌላ ነገር ነው።እናም ኬንያ ፕሬዝዳንት ኪባኪ ዛሬ ፓርላማቸው በመጪው የስልጣን ውድድር እንደማይቀርቡ በማስታወቅ ስልጣን እንደሚለቁ እንደገለፁ ሁሉ ኢህአዲግም ሀገርንም ቤተክርስቲያንንም ወደ ባሰ ገደል ሳይከት ስልጣኑን መልቀቅ ይገባዋል። አንዳንዶች ነገሮችን በማሽሞንሞን የሚሻሻል የዋሃን ሊኖሩ ይችላሉ። ሃያ አንድ አመት አንድ ሰው ተወልዶ ሀገር ለመምራት የሚደርስበት እድሜ ነው።ኢህአዲግ ሃያ አንድ አመት ካልተማረ መቼ ነው የሚማረው ? የትናንት ዝምታ ዛሬ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ተገብቶ ፓትሪያርክ ልሰይም ካለ ነገ ፓትርያሪክ አያስፈልግም ለማለት እንዲሚ ዳዳው አይጠረጠርም። አክሱሙ ወንድሜ እንዳለው '' ቤተክርስቲያን ታግታለች'' ልጆቿ ሁሉ ሊጮሁላት እግዚአብሔርን ይዘው ስለ እውነት ሊቆሙ የሚገባበት ጊዜ ነው።

አበቃሁ
ጌታችው
ኦስሎ
 

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...