ከ ፅሁፉ በታች የምታዩት ዛፍ ቀድሞ የነበሩት ጓደኞቹ- (ዛፎች) የት ሄዱ? አልኩ እና ምናልባት ዛፍነታቸውን እረስተው ሌላ መሆን ፈልገው ትተውት ሄደው ይሆን? ብዬ አሰብኩ። እናም የ ዛፉ ታሪክ እንዲህ መሆን አለበት አልኩኝ። ከ እዚህ በፊት ዛፍ ሆነው ለ መርከብነት፣ለ ታቦትነት ወዘተ ስለተመረጡ ዛፎች ታሪክ አውቅ ነበር።እኔ ግን ዛሬ ታሪኩን መቀየር አማረኝ። ዛፉ ከሚቆረጥ ዛፍ እንደሆነ ቢፀናስ? ብዬ አሰብኩ እና እንዲህ ጫጫርኩት።
ይህ ዛፍ ድሮ ብዙ ዛፎች አብረውት ነበሩ። ሌሎቹ ዛፎች ዛፍ መሆናቸውን ትተው ወንበር፣በር፣ወዘተ መሆን አማራቸው።እናም ዛፍ የመሆን ክብራቸውን ለወጡት።
በመጨረሻ እንዲህ ሆነ
''ዛፍ ሆነን ከሜዳ ላይ ከሚበርደን ከ ቤት ገብተን ወንበር ሆነን ሰዎች ከ ክብር አዋርደው ቢቀመጡብን፣በር ሆነን እንደፈለጉ ቢወዘውዙን ይሻላል'' ብለው አምላክ የሰጣቸውን የ ዛፍነት ክብር ተዉት።
ይህ ዛፍ ግን ብቻውን ቆሞ ሁሉም ሲሄዱ ታዘባቸው።
በመጨረሻ እንዲህ ሆነ
በመጨረሻ ግን በ ሃገሩ የተገኘ ብቸኛ ዛፍ ነው እና የሃገሩ ሰዎች ተሰብስበው ቤተክርስቲያን ሊሰሩ ሲያስቡ እስከመጨረሻ ወደ ጸናው ዛፍ መጡ። አከበሩትም ቤተክርስቲያን ከ ጎኑ ሰሩ።ዛፉም በ ቤተክርስቲያኑ ቅፅር ግቢ ውስጥ ተከለለ። ቀጥሎም አንድ ቀን የኔታ ወደ ዛፉ መጡ። ብቻውን የቆመባቸውን እነኛን ክፉ ዘመናት አስበው ተከዙ። ተክዘውም አልቀሩም።የሚያስተርምሯቸውን ተማሪዎች ከ ዛፉ ስር ለማድረግ ወሰኑ። ከዛፉ የተሻለ ስለ ፅናት የሚያስተምር ምሳሌ እንደማይገኝ አውቁ። አስበውም አልቀሩ የኔታ ወንበራቸውን ከ ዛፉ ስር ዘረጉ። እነሆ ዛፉ በእራሱ አርጅቶ ካልወደቀ በቀር እንደማይቆረጥ ቁርጥ ሆነ። የ ሌሊት ማህሌት፣ የ ማለዳ ቅዳሴ፣ የቀን ቅፀላ ምግቡ ሆነ። ''እስከመጨረሻ የሚፀና እርሱ ይድናል'' የሚለውን ቃል አሰበ። ቀድሞ ወንበር እና በር ለመሆን ዛፍነታቸውን የከዱ የድሮ ጓደኞቹ ቀኑበት። አሁን እነርሱ ወንበርነታቸው አብቅቶ ከደጅ ተጥለው ለ ማገዶነት የሚመጣውን አመት በዓል ይጠባበቃሉ። እስከመጨረሻ የፀናውን ዛፍ ያድርገን።ዛፍ መሆን ወንበር ከመሆን ይሻለናል።
እነሆ የ ዛፉ ታሪክ ተፈፀመ።
ጌታቸው
ኦስሎ
2 comments:
This is superb. I prefer to be the tree, hence my name_ Teklu.
This is superb. I prefer to be the tree, hence my name_ Teklu.
Post a Comment