ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, August 24, 2012

አልቦ ብሔርነት የ ኢትዮዽያ ህዝብ'' ሶፍት ዌር ''

  •   የ አምባገነኖች መሸሸጊያ ጉረኖ ዘረኝነት እና የዘር መርዝ መንዛት ነው፤
  •  የ አቶ መለስን ስ ህተት የ አቶ መለስ ካድሪዎች'' እሱ ብሎ ነበር አልሰማ አሉት'' በሚሉ ወሬዎች ህዝቡን ሰለባ አድርገውታል፤
  • በ ሳምንቱ ለ አቶ መለስ እረፍት የ ኢህ አዲግ ፎረም አባለትን ጨምሮ (ለኑሮ የገቡቱ) እና ታዳጊው ወጣት ሁሉ የ ኢህ አዲግን ፖሊሲ ደጋፊ ሆኖ የወጣ አይደለም። ከ እዚህ ይልቅ ሁኔታው ያመላከተው ሁለት ነገሮች ናቸው፤
  • ከ ነሃሴ 27 የ ቀብር ስነ ስርዓት ቀጥሎ ትልቁ የ ህዝቡ ስራ በ ብሔር የተደራጀውን ኢህአዲግን በ አልቦ ብሔር መሰረት ባለው ኢትዮዽያዊ መንግስት በ ማንኛውም መንገድ መመስረት ቅድምያ የሚሰጠው የ አዲሱ አመት ስራ መሆኑን አልቦ ብሔር ሶፍት ዌሩ ይነግረዋል::
የ አራዳ ልጅ  ብሔር? ሲባል ምን እንደሚል ታውቃላችሁ? ''አልቦ ብሔር  '' ነው። አልቦ ብሔር ማለት  ብሔር የሌለኝ ግን ኢትዮዽያዊ ነኝ ሲላችሁ ነው።በ 1960 ዎቹ መጨረሻ ላይ የተነሳው እና በ ¨ት ሃ ቶች¨ ታሽቶ በ 1987 ዓም ¨እስከ መገንጠል¨ የሚል ቃል አክሎ፤ በ ህገ መንግስቱ ላይ ጨምሮ ፤አስጨብጭቦ፣ ሰው በቋንቋ መከፋፈልን (¨ከ¨ ሲላላ) እና መከፋፈልን (¨ከ¨ ሲጠብቅ) በሃገሪቱ ላይ የነገሰው አስተሳሰብ በትክክል ግብአተ መሬቱ ሊከናወን ሰዓታትን መቁጠር ግድ ይለዋል። ይህ የሚሆነው በ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው።
የ ዘር ፖለቲካ ለ አለማችን አዲስ ክስተት አይደለም።የ አምባገነኖች መሸሸጊያ ጉረኖ ዘረኝነት እና የዘር መርዝ መንዛት ነው። ሂትለር የጦርነት ጥማቱን ለማርካት የ ጀርመንን ህዝብ የተለየ ህዝብ አድርጎ ማቅረብ ነበረበት። ¨እናንተ የ ጀርመን ህዝቦች የ 'አርያን'ዘሮች ¨ እያለ ይሸነግል ነበር።ሰዎች በባህሪያችን ብልህ የመሆናችንን ያህል  የመሆኑን  ጅልነትም አያጣንም።ሰው እኮ በዛፍ የማመን፣ አምላክ ነው የማለት አስቂኝ ሞራል ያለው ፍጡር ነው።¨አንተ ዘርህ የ እገሌ ነው፤ታላቅ ነህ፤ ያንተ ዘር እገሌ ድሮ እንዲህ ያደረገ፤ እገሌ የተባለው መሪህ ካንተ መንደር የተወለድ¨ ሲባል ልቡ ደንገጥ የሚል ይጠፋል ብለን አናስብ። 
 የ ሁለተኛው አለም ጦርነት እልቂት  አቶ ሂትለር ''ጀርመን ሆይ! ¨አንተ እኮ የ አርያን ዘር ነህ¨ ብሎ ነው ለ አለም የ ጥፋት እሳቱን የለኮሰው። ሞሶሎኒም ለ ኢጣልያ ህዝብ ኢትዮዽያን መውረር እንዳለበት ለማሳመን ¨የ ታላቋ ሮማ ህዝብ ሆይ!¨ የምትለዋን የ ዘረኝነት ቃል መጠቀም በቂው ነበር። አምባገነኖች የ ዘር ፖለቲካቸው ሲናድ ይደነግጣሉ፣ይርዳሉ።ስለ እዚህ ዘረኝነትን ይንከባከቡታል::
ኢትዮዽያ በ እዚህ ሳምንት ያየነው እውነታ ምንድን ነው?
ማክሰኞ ነሃሴ 15/2004 ዓም ማለዳ ላይ አቶ በረከት የ አቶ መለስን ማረፍ ለ ኢትዮዽያ ቴሌቭዥን እንዲናገር ፈቀዱለት። ቀደም ብሎ ዜናውን ከ ኢሳት የሰማ ቀድሞ ተለማምዶ ነበር እና ምንም አልመሰለውም። ብዙው ህዝብ ግን ለመረጃ እሩቅ ስለሆነ ቢያንስ አዲስ ነገር ሲሰማ ስሜታዊነት ውስጥ መግባት ሰዋዊ ባህሪው ነው። እና ሁለት አይነት ስሜት ተሰማው።
 የመጀመርያው በ አይነ ህሊናው ተቃዋሚ መሪ፤ አማተረ የለም።የሚሰማ ተስፋ የለም። ኢትዮዽያ ያለ ምንም የቀረች መሰልው እና ቀድሞ አቶ መለስን በሚገባ ቦታ ሰጥቶ የማይውቅ ሁሉ በነገሩ ክስተት ለሃገሩ አለቀሰ።
ሁለተኛው ስሜት'' የ ሆድ ብሶት'' የሚባል ስም ያለው ስሜት ተጋሪ ነው። ሃገራችን ወዴት እየሄደች እንደሆነ ህዝቡ በምናቡ ይገነዘባል። የ ዘር ፖለቲካ እና ቋንቋን መሰረት ያደረገ አከላለል ውድቀት መሆኑን ይረዳል። ይህ አደጋ ትንሽ ምክንያት ቢያገኝ ሃገሪቱን ወደ ገደል ይዞ ይሄዳል ብሎ ስላሰበ 'ሳግ' ያዘው፤ ስለ እራሱ አለቀሰ። እውነታው ይህ ነው።ከ እዚህ ውጭ ለ ፖለቲካ ትርፍ ኢህአዲግ የሚላቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደሉም።

የ ኢትዮዽያ ህዝብ ''ሶፍት ዌር¨'' አልተቀየረም
በ ሰሞኑ የ አቶ መለስ እረፍት የ ኢህ አዲግ ትርፍ የመሰላቸው የዋሆች ለመኖራቸው የ ኢትዮዽያ ቲቪን የሰሞኑን ፕሮግራም ያየ ይረዳል።የ ኢትዮዽያ ህዝብ ሶፍት ዌር አልተቀየረም። ሶፍት ዌሩ ኢትዮዽያዊነት  ነው።ሶፍት ዌሩ አልቦ ብሔርነት ነው። ይህን አስተሳሰብ የሚቀይር ምድራዊ ሃይል የለም።ወደፊትም አይገኝም።በ ሳምንቱ ለ አቶ መለስ እረፍት የ ኢህ አዲግ ፎረም አባለትን ጨምሮ (ለኑሮ የገቡቱ) እና ታዳጊው ወጣት ሁሉ የ ኢህ አዲግን ፖሊሲ ደጋፊ ሆኖ የወጣ አይደለም። ከ እዚህ ይልቅ ሁኔታው ያመላከተው ሁለት ነገሮች ናቸው።
የመጀመርያው አቶ መለስን ከ ኢህ አዲግ ለይቶ ነው የወጣው። እንዴት? ልትሉ ትችላላችሁ።አቶ መለስን ''ኢህ አዲግ እራሱ ሲያቆስላቸው ነው የኖረው'' የሚሉ ብዙ የ ቡና ላይ ወሬዎች አሉ። የ አቶ መለስን ስ ህተት የ አቶ መለስ ካድሪዎች'' እሱ ብሎ ነበር አልሰማ አሉት'' በሚሉ ወሬዎች ህዝቡን ሰለባ አድርገውታል። ስለ እዚህ ከህዝቡ አቶ መለስን ከ ኢህ አዲግ ለይቶ ሳጥን ውስጥ ያስገባ አለ። ይህ ለ አቶ በረከት አልገባቸውም።  ኢህ አዲግን አልደግፍም ግን በ አቶ መለስ እረፍት አዘንኩ።ሃዘኑ ግን አንድም በሁኔታው ድንገት መስማቱ(የመረጃ ማነሱን ልብ እንበል) ሃገሪቱ ምን ልት ሆን ነው የሚል ስጋት ያዘው።
ሁለተኛው ምክንያት ህዝቡ የ አልቦ ብሔር ስሜቱን በ ወንዝ እና በ መንደር ለሚያስቡ የ ኢህ አዲግ አባላት በሙሉ የሚያስተምርበት ትክክለኛ ወቅት መሆኑን ተረዳ። የ አራዳ ልጅ ሰው አክባሪ፣ ሰው አፍቃሪ ብቻ አይደለም አልቦ ብሔር መሆኑን አስመሰከረ።¨እንኳን ከ ወርቅ ህዝብ ተፈጠርኩ¨ላሉት አቶ መለስ ከ አድዋ መጣ ከ ጉለሌ  አልቦ ብሔሩ ኢትዮዽያዊ አክብሮ አስከሬን ተቀበለ።በ ነሃሴ 27 ይቀብራል።

ኢህአዲግ ከ አቶ መለስ ውጭ?
በ አቶ መለስ እረፍት የሆነው እንዲህ ነው። አቶ በረከት እና ኢህ አዲግ  በ ቲቪ ሲናገሩ ያየነው  ሁሉንም ስራ  የሰሩት አቶ መለስ ናቸው። የመንገድ መብራቱ ደሞ በ ኢህ አዲግ አደለም በ አቶ መለስ ፖሊሲ እና ስትራተጂ ነው። ሁሉም ነገር ለካ የተሰራው፣ አመራሩ ሁሉ በ አቶ መለስ ነበር። አያጣላም:: ምግብ እንድንበላ ያረጉን፤ ውሃ እንድንጠጣ ያደረጉን አቶ መለስ ናቸው። ቆዩ አያጣላን:: ለጊዜውም ቢሆን። ባጠቃላይ ኢህአዲግ በ እራሱ ምንም አይደለም አቶ መለስ ግን ሁሉም ነገር ነበሩ። ነው የተነገረው። ጥሩ።
አቶ ስየ አብርሃ ከ አቶ መለስ ጋር አብረው በረሃ የወረዱ በ ኢህ አዲግም እስከ መከላከይ ሚኒስትርነት የደረሱ አሁን የ አቶ መለስ ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆኑ (አልቦ ብሔር  ኢትዮዽያዊነታቸውን አስቀድመው) ካለ አቶ መለስ ኢህ አዲግ ምንም ማለት አይደለም ብለው ለ አውራምባ መልቲ ሚድያ በ እዚህ ሳምንት አረጋግጠዋል። ¨
¨ አቶ መለስ ለ ህወሃት ብቻ ሳይሆን ለተቀሩት የ ኢህ አዲግ ፓርቲዎች ቀለበቱ ነበር። ካለ መለስ ኢህ አዲግ ችግር የለበትም የሚሉ ትክክል አደለም።¨ ብለዋል። ይህም ያስማማል። ኢቲቪም ህዝቡ አለ ብሎ አሳይቶናል። ለካ እነ አቶ በረከት ምንም አይሰሩም ነበር ማለት ነው? አቶ መለስ ብቻቸውን ነበር ይህን ሁሉ ስራ ሲሰሩ የከረሙት?
ስለ እዚህ ነሃሴ 27  የ ኢህ አዲግ የ ቀብር ቀን ነው ማለት ነው?
አቶ መለስ ሁሉም ነገር ከሆኑ ከ አሁን በኋላ አቶ በረከት 'ኢህ አዲግ ፖሊሲው እና ፕሮግራሙ ነው የሰራው' የሚል አረፍተነገር ለመናገር ሞራላዊ ብቃት ሊኖራቸው አይችልም።ህዝቡም (ለ አቶ መለስ ያዘነው፤ ያላዘናም አለና) በ ኢህ አዲግ ፕሮግራም የመመራት ሞራላዊ ግዴታ የለበትም። ''ለ አቶ መለስ አዘንኩ ግን አቶ መለስን የሚተካ ተቋማዊ አሰራርም ሆነ አመራር የማግኘት መብት  አለኝ'' ሊል ነው ማለት ነው  ። ባይሆን ለ አቶ መለስም ሆነ ለ ቀዳማዊ አጼ ሃይለስላሴም ሃውልት መስራት መብቱ ነው።ስለ እዚህ ከ ነሃሴ 27 የ ቀብር ስነ ስርዓት ቀጥሎ ትልቁ የ ህዝቡ ስራ በ ብሔር የተደራጀውን ኢህአዲግን በ አልቦ ብሔር መሰረት ባለው ኢትዮዽያዊ መንግስት በ ማንኛውም መንገድ መመስረት ቅድምያ የሚሰጠው የ አዲሱ አመት ስራ መሆኑን አልቦ ብሔር ሶፍት ዌሩ ይነግረዋል።
አበቃሁ።

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...