ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, August 17, 2012

መልካም እሴቶቿ የተጎሳቆሉባት ሃገር!

  • ህብረተሰብ በተለያዩ ማህበረሰባዊ ተቋማት ውስጥ ይገኝ እንጂ የጋራ በሆኑት መልካም እሴቶቹ ላይ ግን ብዙ ባይቀልዱበት ይመርጣል።
  •  የመንግስት እና የ ሃይማኖት ተቋሞቻችን በ መልካም እሴት ጥበቃ አንጻር ስንመዝናቸው ከ አመት አመት አይደለም ከ ቀን ቀን በሚበር ፍጥነት እየወረዱ ነው።
  • እያንዳንዱ የመልካም እሴት መሸርሸር ዜና ከ ጠላ እና ጠጅ ቤቶች እስከ ሸራተን ሆቴል ውስጥ እስከሚገኘው ¨ኦፊስ ባር¨ድረስ በ ህዝቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በ ውጭ ሃገር ዲፕሎማቶች ዘንድ ሁሉ ይፈተሻል::
  • ህዝብ መልካም እሴቶቼን መልሱ ብሎም በግድ ይጠይቃል። አሁንም በእዚህ አያቆምም መልካም እሴቶችን ያጎሳቆሉቱኑ ተቋማት አፍርሶ በተሻለ ለመቀየር ይወስናል።
  • በ ሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በ ሚልዮን የ ሚቆጠር ገንዘብ የሰረቀ፤ሲበጠብጥ ሲያበጣብጥ የነበረን፤ አልተሳካም እንጂ ያለውን ጦር ሁሉ የወረወረን የሚሸልም ህብረተሰብ አለን እንዴ?
ማንኛውም ነገር መለኪያ ተቀምጦለታል።ያልተለካ ነገር መጠኑ እንዴት ይታወቃል? በጎ ስራም ሆነ ክፉ ስራ መለኪያ አለው።በስራው ቁጥር አልያም በ ጥራቱ ይለካል።ቅዱስ መጽሃፍ የ አንድ በጎ ስራ ወይንም ተግባር መለኪያው ''የ ስራ ፍሬ'' እንደሆነ ያስተምረናል።¨ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ¨ የሚለው ቃል የ ተግባር ፍሬ የ አንድ ሰው የ ስራ   መለኪያ ነው ማለት ነው።ቅዱስ መጽሃፍም የእምነት ሰውን  ካልሆነው ሰው የሚለይበት መለኪያ እያደናገረ እንዳይኖር ¨በ ፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ¨ ብሎ ፍሬ የበጎ ስራ መለኪያ መሆኑን አስቀምጦልናል።
አሁን ያለንበት ወቅት የ አዲሱ ትውልድ ከ ቀደመው ትውልድ መረከብ የጀመረበት፤ ያለፈው ትውልድ በ ዘመን እርጅናም ሆነ በ ስራ መልቀቅ ለ አዲሱ ትውልድ ቀስ በቀስ እየለቀቀ የመጣበት፤ ይህ ሂደት በ ጥሩ መሰረት ላይ ከተመሰረተ ሃገራችን የማደግ እድሏ ከፍ የሚልበት ሁኔታ መፍጠሩ የማይቀር ነው።
¨ከ ትናንት ብንዘገይ ከ ነገ እንቀድማለን¨
ትናንትን እያነሳ የሚቆዝም ህብረተሰብ የ ዛሬን ከ እጁ እንደሚጥል ሳይታለም የተፈታ ነው። እዚህ ላይ ግን ካለፉት ስ ህተቶች ተምሮ ለወደፊቱ በጎ መሰረት መጣል የሚቻለው ህብረተሰቡን  ¨የመሸለም እና የመውቀስ¨ ልምድ ያለው በማድረግ   ብቻ ይመስለኛል።
 ቀደም ባሉት መንግስታቶችም ሆነ ዛሬ እንደ ክፉ አባዜ ያልለቀቀን እና ከስር እየወጣ ያለው ታዳጊ ወጣትንም እያስተማርነው ያለነው።በጎ የሰራ ሲሸለም፤ ክፉ የሰራ ሲቀጣ አይደለም። ይህ ደግሞ ዛሬ አለንበት ከምንለው ችግር በባሰ የተደራረበ ችግር ይዞ የሚመጣ አደገኛ መርዝ ነው።
ማህበረሰባዊ ሽልማት ምንድን ነው?
ህብረተሰብ ካለፈበት ፖለቲካዊም ሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ሂደት ዋጋ የሚሰጣቸው እሴቶች ተጠብቀው ሲያገኝ ያንን መልካሙ እሴት እንዲጠበቅ የረዳውን ወይንም መልካሙን እሴት በተግባር ያሳየውን ሁሉ ይሸልማል።ሽልማቱ በቁሳዊ ነገር አይላካ ይሆናል። በ ሞራላዊ እሴት ግን ያንበሸብሻል። የ ህብረተሰባችን መልካም እሴቶች:-
አለመዋሸት፣
አለመስረቅ፣
አለመክዳት፣
እልከኝነትን ማራቅ፣
ይቅር ባይነት፣
መተዛዘን፣
ጸረ ዘረኝነት፣
ታማኝነት፣
ወ ዘ ተ
በ ህብረተሰባችን ዘንድ ዋጋ የሚያስጡ መልካም እሴቶች ናቸው። ህብረተሰባችን ተቋማትን የሚለካበት መስፈርት በ እነኝህ መልካም እሴቶች አንጻር መሆኑ እሙን ነው። ለ ሃገር እድገት ደግሞ እነኝህ መልካም እሴቶች እጅግ አስፈላጊ ግብአቶች ናቸው። የ እነርሱ መሸርሸር የ እድገት ቁልቁልዮሽ ጉዞ ጅማሮ ብሎም  እንደ ህዝብ እና ሃገር የመቀጠል አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከ ፊት ለፊት የመደቀን አደጋቸውም የ እዚህኑ ያህል ያጎሉታል።
ህዝብ ይመዝናል
ህዝብ የማይጨበጥ እረቂቅ ነገር አይደለም። በመንገድ ላይ ስንሄድ፤ ከ ቤት ስንገባ፤ በ ማህበራዊ ድህረ ገጾች ሁሉ የምናገኘው ምናባዊ ያልሆኑ የሚናገሩ፣የሚዳሰሱ እና የሚያዳምጡ ሰዎች ስብስብ ነው-ህዝብ።ይህ ህዝብ በ ስብስብ መልኩ ተቋማዊ መልክ ሲላበስ ህብረተሰብ ይባላል። ህብረተሰብ በተለያዩ ማህበረሰባዊ ተቋማት ውስጥ ይገኝ እንጂ የጋራ በሆኑት መልካም እሴቶቹ ላይ ግን ብዙ ባይቀልዱበት ይመርጣል። እሴቶቹን ለጠበቁለት የሚሸልመውን ያህል። ላጎሳቆሉበት ደግሞ ጥሩ አድርጎ መቅጣት ያውቅበታል።
ዲሞክራሲ ለ ህብረተሰብ የሚሰጠው እድል ይህንን ነው። በ መናገር መብትህ ታግዘህ መልካም እሴቶች ህን ያጎሳቆለብህን ውቀሰው ይላል- ዲሞክራሲ። ለ እዚህም ነጻ የ ሚድያ እድል ይሸልማል -ዲሞክራሲ።በ የትኛውም ተቋም ስር ተሸሽጎ መልካም እሴቶችህን የሚነካብህን በ ነጻ ምርጫ ምታው ይላል። አሁንም -ዲሞክራሲ።እድገትም እና ልማትም ከ እዚህ ይነሳል።
እኛን ያቆሰለን
ወደ ሃገራችን ስንመለስ መንግስት እና የ ሃይማኖት ተቋሞቻችን በ መልካም እሴት ጥበቃ አንጻር ስንመዝናቸው ከ አመት አመት አይደለም ከ ቀን ቀን በሚበር ፍጥነት እየወረዱ ነው። ይህ ነው የነገን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የ አሁኑም ትውልድ የመኖር ህልውናውን በ ከፍተኛ አደጋ ላይ የመጣል እድል ያለው። በማስረጃ ላብራራ።
ኢትዮዽያ ለ መንግስት ስሪት አዲስ አይደለችም። በ ሺህ ለሚቆጠሩ አመታት መዋቅር ያላቸው፤ህግ እና ስርዓት የተበጀለቸው(በ ወቅቱ ይመጥናል በተባለ ደረጃ)፤ ተጠያቂነታቸው ለ ሰውም ለ እግዚያብሄርም ያደረጉ መንግስታትን በየ ዘመኑ አሳልፋለች። በ እነኚህ መንግስታት አሰራር ስርዓት ውስጥ ግን ሚስጥራዊው ዋስትና የ ህብረተሰቡን ብቻ ሳይሆን ¨ሰው¨ ተብሎ የተፈጠረ ፍጥረት ዋጋ የሚሰጣቸውን እሴቶች በ ወቅቱ ህብረተሰቡ በደረሰበት የ እድገት ደረጃን እና ስነ ልቦናዊ ንቃት በመጠነ መልክ አክብረው እና አስከብረው በመኖራቸው ነው።
መልካም እሴቶች በ አጼ ሃይለ ስላሴ እና በ ደርግ ዘመን
ባለፉት ሃምሳ አመታት ውስጥ የነበሩንን ሶስት መንግስታት ታሪኮች (የ አሁኑ ኢህአዲግን ጨምሮ) መሰረታዊ የመቀየር ባህሪያቸው የሚመነጨው ከ ህብረተሰቡ መልካም እሴት ጋር መታረቅ ሲያቅታቸው ነው። የ አጼ ሃይለ ስላሴ መንግስት አብዮቱ ከመፈንዳቱ ቀደም ብሎ ህብረተሰቡ ያነሳቸው የነበሩ ቀላል የሚመስሉ ግን ግዙፍ የሆነ የ መልካም እሴትን የማስከበር ጥያቄ እንደዋዛ ታይተው እናያቸዋለን። የወሎ ረሃብ ጉዳይ የተያዘበት አያያዝ፤ የንጉሱ የ ሰማንያኛ የልደት በዓል የተቀናጣ መሆን፤ የ ፊውዳል ባለ መሬት በጭሰኛ ገበሬው ላይ የሚያደርሰው ግፍ እና የመሳሰሉት ህዝቡ ¨በጎ እና መልካም እሴቶቼ¨ ከሚላቸው ጋር እየተጣረሱ ¨ፍት ህን፣እውነትን እና ርህራሄ¨ የተሰኙትን እሴቶች ማንም እንደማያስከብራቸውም ሆነ እንደማያከብራቸው ያረጋገጠው ህዝብ ሊያስከብራቸውም ሆነ የሚያስከብር ሊሾምላቸው እራሱ ተነሳ።አብዮቱ ፈነዳ።

ይህንኑ ጉዳይ በ ደርግ ስርዓት በ ባሰ እና በገዘፈ መንገድ እናገኘዋለን።ደርግ በመጀመርያ የ መልካም እሴት ጥሰት የጀመረው ጊዜያዊ መንግስት ነኝ ብሎ ከመጣ በኋላ በመጀመርያ ኢሰፓአኮ (የ ኢትዮዽያ ሰራተኞች አደራጅ ኮሚሽን) በመቀጠል ኢሰፓ (የ ኢትዮዽያ ሰራተኞች ፓርቲ) መች በእዚህ አበቃና ኢህድሪ (የ ኢትዮዽያ ህዝባዊ ዲሞክራሳዊ ሪፓብሊክ) ብሎ ¨አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው¨ እንዲሉ መለዮውን አውልቆ ሲቪል ሆንኩ አለ።¨እውን ደርግ አለን¨  ተብለናልና። ይህ የመስረታዊ መልካም እሴት ጥሰት ብቻ ሳይሆን በ ህብረተሰባችን ዘንድ ወንጀልነቱ ታምኖ ቅጣቱን ለመስጠት ቀን ሲታሰብለት ኢህአዲግ የሚባል ድርጅት ሲገኝ ገበሬው በተለይ ያ የተነካበትን መልካም እሴት ለማስመለስ መንገድ እየመራም፣እየተራዳም አዲስ አበባ ድረስ ይዞት ገባ።

ኢህአዲግ በ ገጠር ትግሉ ወቅት የህዝቡን ልብ ያገኘው በሌላ በምንም ሳይሆን ¨መልካም እሴትን የሚጠብቅ ነው¨ ተብሎ በ ገበሬው ዘንድ ስለታመነ ነበር። ኢህአዲግም የዛሬን አያድርገው እና ¨''ብልጠት'' ነበረበት። ሰራዊቱ በ ገጠር ያለች ቤተ ክርስቲያን ካገኘ ለጥ ብሎ በመሳለም (ደርግ በ አይሮፕላን ሲመታ በ ኢላማ ስ ህተትም ይሁን በምን  ባይታወቅም) ፤ ከ ገበሬው ቤት ተጠግቶ ¨እማዪ ይችን ልጋግር ነበር ብረት ምጣድዎን ልዋስ ዱቄት አለኝ አላስቸግርም¨ ብሎ ሰራዊቱ ሲናገር የ ገጠር እናቶቻችን ¨መሳርያ ይዞ ሞሰቡን ልገልብጥ ማለት ሲችል ¨ እያሉ እንጀራቸውንም እየጨመሩ ሰጡ።

 መልካም እሴት መጠበቅ ለትልቅ ድል ለማብቃቱ ማስረጃ ነው። ተመሳሳይ በ ኤርትራም የሆነው ይህ ነው። ከ ከተማ ታፍሶ የሚሄደው እና በ ግድ የተመለመለው ሰራዊት ሴቶችን በመድፈር ሲታማ የ ሻብያ ተዋጊዎች ግን መልካም እሴት አቃብያን ሆነው ብቅ አሉ። ¨ይህ የሆነብህ የ ደርግ ጸረ ዲሞክራሲ አሰራር ነው¨ ተብሎ ሳይሆን ለ ህዝቡ የተነገረው ¨አንተ ኢትዮዽያዊ ስላልሆንክ ነው መልካም እሴት ህን ሊያጠፉብህ መጡ¨ እየተባለ ተወሸከተለት። መልካም እሴቱን ያከበሩለት ቀዳማዊ አጼ ሃይለ ስላሴማ ከ አስመራ ወደ ምጽዋ ሲሄዱ (በ ምጽዋ የ ቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያን እና መስጊድ እንዲሰራ በ አንድ ቀን የመሰረት ድንጋይ ለመጣል ሲሄዱ) በ ፍርሃት ሳይሆን በ ፍቅር ህዝቡ ልብሱን እያወለቀ መሬት እያነጠፈ መቀበሉን በወቅቱ የ እንግሊዝ እና የ አለም የ ዜና መገናኛዎች የዘገቡት ጉዳይ ነበር።የ መልካም እሴት የመጠበቅ የ ህዝብ ክፍያ።
መልካም እሴታችን  በዘመነ ኢህአዲግ
ከላይ ለማብራራት እንደተሞከረው። ህዝብ መልካም እሴቶች ከ መንግስትም ሆነ የ ሃይማኖት ተቋማቱ እየተሸረሸሩ ሲሄዱ በ አንክሮ ይከታተላል። እያንዳንዱ የመልካም እሴት መሸርሸር ዜና ከ ጠላ እና ጠጅ ቤቶች እስከ ሸራተን ሆቴል ውስጥ እስከሚገኘው ¨ኦፊስ ባር¨ድረስ  በ ህዝቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በ ውጭ ሃገር ዲፕሎማቶች ዘንድ ሁሉ ይፈተሻል፣ይተረካል ብሎም ይተቻል። በ እዚህ ብቻ ግን አያቆምም ህዝብ መልካም እሴቶቼን መልሱ ብሎም በግድ ይጠይቃል። አሁንም በእዚህ አያቆምም መልካም እሴቶችን ያጎሳቆሉቱኑ ተቋማት አፍርሶ በተሻለ ለመቀየር ይወስናል።ይህን የሚያደርገው እሴቶቹን ያጎሳቆሉት እራሳቸውን የማረቅያ በቂ ጊዜ ከሰጠ በኋላ አንድም ከ ተሳሳቱበት መንገድ መመለስ ሲያቅታቸው አልያም በ እራሳቸው ጊዜ መፈራረስ ሲጀምሩ ነው።
 መልካም እሴቶች ከ መንግስት
የመልካም እሴታችን ሽርሸራ ኢህአዲግ የጀመረው ከ አመሰራረቱ ባህሪ ላይ ነው። ¨ህወሃት¨ የተባለው ድርጅት ሰሜን ወሎ ላይ ¨ኢህዲን¨  ሰላሌ ላይ ከ ደረግ የተማረኩ ወታደሮችን አሰባስቦ ¨ኦህዴድ¨ ሀዋሳ ሲደርስ ደግሞ ¨ደቡብ ህዝቦች¨ የ እንቶን ግንባር ወዘተ እያለ ቀጠለ  ።  ምርጫ ዘጠና ሰባት፤ ቀጠለ 99%  የ ፓርላማ ምርጫ አሸነፍኩ አለ:: ከሁሉ የባሰ የሚያሳዝን የ መልካም እሴታችንን እንጦሮጦስ ያወረደው እና አለምን ¨አጀብ¨ያሰኘው የ ሰሞኑን የ አቶ መለስን መሰወር አስመልክቶ ከ መንግስት የሚሰጡት መግለጫዎች ናቸው።ግልጽነት፣ተጠያቂነት፣እንደ መንግስት ማሰብ ሁሉ ገደል የገቡበት።ህብረተሰቡ ያፈረበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የት እንዳሉ ለማወቅ መብት እንደሌለው የተረዳበት ሆኖ አርፎታል።በሚሰጡት መግለጫዎች ህዝቡ እምነት ከማጣቱም በላይ ተስፋ አስቆራጭ ሆነውበታል።
 መልካም እሴቶች ከሃይማኖት ተቋም

መልካም እሴቶች በ ጎላ መልኩ ይገለጽባቸዋል በተባሉት የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ ሙስና የሰፈነባቸው፣እውነት ታጥባ እራቁት የቆመችበት አስከፊ ጊዜ ላይ ነው ያለነው። አሰቃቂው ጉዳይ ግን በ ሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በ ሚልዮን የ ሚቆጠር ገንዘብ የሰረቀ፤ሲበጠብጥ ሲያበጣብጥ የነበረን፤ አልተሳካም እንጂ ያለውን ጦር ሁሉ የወረወረን የሚሸልም ህብረተሰብ አለን እንዴ? እዚህ ደረጃ ከደረስን መጪው ትውልድ ምን ሊማር ነው? የሰረቀ ሲቀጣ፤ የዋሸ ሲከሰስ፤ እውነት የተናገረ ሲሸለም ካላየ ታዳጊው ትውልድ 'እገሌስ ይህን ሁሉ ወንጀል ሲሰራ ከርሞ ይህን ያህል ሙገሳ እና ክብር ካገኘ' ብሎ እዲያስብ እያደረግን መሆኑንስ ልብ ብለነዋል?
ለመልካም እሴት ክብር የሚሸልም፤ ለ እኩይ ስራ አድራጊ የሚቀጣ ህብረተሰብ እናፍራ። ይህ ደግሞ ከምንም አይነሳም ክፉ አድራጊውን እስከ ዘላለም በመውቀስ እና በጎ አድራጊውን በመሸለም ይጀመራል።
አበቃሁ
ጌታቸው በቀለ

2 comments:

ተክሉ said...

መልካም ነው ጌታቸው
ለመሸለምም ሆነ ለመቅጣት የዘገየን ሆነናል ዝም ብሎ የማለፍ አባዜ ይህ ደግሞ ጨቋኝ መንግስታት ያሳደሩት ተጽኖ ነው በተለይ ደርግና ያሁኑ ግን አሁን ጎህ እየቀደደ ይመስላል

Anonymous said...

Good values of socity are a key issue for sustainabe development.