ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, August 4, 2012

¨ሰማሽ አንቺ እማማ ኢትዮዽያ ቃል የ እምነት ዕዳ ነው እንጂ የ አባት የ እናት እኮ አይደለም¨

  • የ ህገ መንግስቱ ችግር ¨ ኢትዮዽያ የምትባለው ሃገር የማን ናት? ህገ መንግስቱ የ ሃገር ባለቤትነትን ለማን ስጥቷል? የሚሉትን ጥያቄዎች በ አግባቡ አለመመለሱ ነው።
  •  ¨ኢትዮዽያ የምትባል ሃገር ኢህአዲግ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ብቻ የምትኖር ከሌለ ግን (ክልሎች ሁሉንም ማረግ ስለሚችሉ) ማእከላዊ መንግስት ብዙም የማያስፈልጋት ነች።¨ ለማለት ነው የፈለጉት:: የ አቦይ ስብሃት የ ገለጻ አንደምታ ለ እኔ እስከገባኝ ድረስ ።
  • ኤርትራ በብዙ የ ፖለቲካ ተንታኞች አይን ( በ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይንም) የምትታየው ¨እያነባ እስክስ¨ የሚል መንግስት ያላት ምስኪን ሃገር ተደርጋ ነው።
  • የ አሜሪካ ብቻ ሳይሆን የ ፖለቲካው አለም መርህ ¨ የዘላለም ጥቅም እንጂ የዘላለም ወዳጅ የለውም¨ በሚል መርህ ላይ ይመሰረታል።
ልጅ ሆኜ በ ኢትዮዽያ ቴሌቭዥን ቅዳሜ ማታ በቀጣዩ ቀን በ አዲስ አበባ ቲያትር ቤቶች  ስለሚታየው ቴያትር ማስታወቂያ ማየት የተለመደ ነበር።ጥቁር እና ነጭ ቲቪያችን (ከለር ቲቪ በሃገራችን የተጀመረው ከ ''ኢሰፓ'' ምስረታ ጋር በ1977 ዓም መሆኑን ልብ በሉልኝ)   የምወድላት ማስታወቂያ ነበራት።''ቴዎድሮስ'' ለሚለው ቲያትር ፍቃዱ ተክለማርያም እንዲህ ሲል ልቤን ይነካዋል።¨ሰማሽ አንቺ እማማ ኢትዮዽያ ቃል የ እምነት ዕዳ ነው እንጂ የ አባት የ እናት እኮ አይደለም¨ ( አፄ ቲዎድሮስ)። ፍቃዱ ህይወት የዘራበት ይህ ታሪካዊ ተውኔት ብዙ ቁም ነገሮችን ይዟል። በዘመነ መሳፍንት ሃገራችን  ማዕከላዊ መንግስት ያልነበራት፣ መሳፍንቱ ሁሉ በያለበት አዛዥ ናዛዥ የነበረበት፣ ትንሽ ጊዜ ቢያገኝ ኖሮ ዘመነ መሳፍንት በትክክል ሃገራችን ስም ታሪኳ ጠፍቶ ትናንሽ መንግስታት የመፈጠር እድላቸው በ ሂደት የሚያሰጋበት ነበር። ይህ ደግሞ በጊዜው ከሚያንዣብበው የ አውሮፓውያን የ ቅኝ ግዛት ጥማት አንጻር እና ከ በርሊኑ ስምምነት በኋላ አስጊነቱ አሌ የማይባል ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ግን ከ ቋራ ገስግሰው የ ጎንደርን፣የወሎን፣የጎጃምን፣የትግራይን እና የ ሸዋን የ አካባቢ ንጉሶች ሁሉ ድል አድርገው አንዲት ኢትዮዽያን መልሰው አቆሙ።
ኢትዮዽያ የምትባለው ሃገር የማን ናት?
በ 1997 ዓም የ ቅንጅት እንቅስቃሴ ኢዴፓን ወክሎ የተሰለፈው በኋላም በ ቅንጅት መፍረክረክ ድንጋይ ወርውረሃል የተባለው ልደቱ አያሌው ከ ሰሞኑ ለ ቪኦኤ በከፍተኛ ትምህርት ላይ ከሚገኝበት ለንደን እንደ ፓርቲው አባልነት ሳይሆን በግሉ በሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ህመም ዙርያ እና የ ህገመንግስቱ ጉዳይ አንድ አበክሮ ያነሳው እና የሳበኝ ጉዳይ ነበር::እንደ ልደቱ አገላለጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማን ይተካል ከሚለው ጥያቄ በላይ የ ህገ መንግስቱ ችግር ¨  ኢትዮዽያ የምትባለው ሃገር የማን ናት? ህገ መንግስቱ የ ሃገር ባለቤትነትን ለማን ስጥቷል? የሚሉትን ጥያቄዎች በ አግባቡ አለመመለሱ ነው።ምክንያቱም ህገ መንግስቱ ከ ሰማንያ አምስት አመተ ምህረት በፊት ኢትዮዽያ የምትባለው ሃገር እንደነበረችም እውቅና አይሰጥም ።አዲስ ኢትዮዽያ ብሔሮች በውክልና ተሰብስበው የፈጠሯት መሆኑን መግለጹ በ ህገ መንግስቱ ላይ የሚነሳ መሰረታዊ ችግር ነው።'' ይላል። ይህ ትክክለኛ ምልከታ ይመስለኛል። ከ አቦይ ስብሃት ሌላው የ ሰሞኑ የ ቪኦኤ ገለጻ ጋር ያመሳክሩት።

''ክልሎች እራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ነው ምን ይመጣል?''  አቦይ ስብሃት
አቦይ ስብሃት የ መለስ ዜናዊ በአለመኖር በ ኢትዮዽያ ፖለቲካዊ አንደምታ ላይ ማብራርያ እንዲሰጡ ሲጠየቁ በ አስርቀን ይመለሳሉ ከማለታቸው በፊት ¨ክልሎች የራሳቸው በጀት እና የ አስተዳደር መዋቅር አላቸው ምንም ችግር የለም¨የሚል አንደምታ ያለው መልስ ሰጥተዋል።በ ሌላ አነጋገር ''ሃገር የየራሱ መንግስት ስላለው የ ፌድራል መንግስት ሚና ብዙም አይደለም'' ማለት ነው።ይገርማል! ¨እኔ እስካለሁ ድረስ ጎጆ ውጡ አንልም። እኔ ከሌለሁ ግን ጎጆ ውጡ¨ ይሉሃል ይህ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታመሙ ጊዜ ክልሎች እራሳቸውን የቻሉ መንግስት ይሆናሉ። ባልታመሙ ጊዜ (ኢህአዲግ መንግስቱን በያዘበት ዘመን) ክልሎች በ ክልል ምክር ቤት በኩል ጉዳያቸውን ለ ፌድራል መንግስት ማቅረብ ይገባቸዋል። ¨ኢትዮዽያ የምትባል ሃገር ኢህአዲግ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ብቻ የምትኖር ከሌለ ግን (ክልሎች ሁሉንም ማረግ ስለሚችሉ) ማእከላዊ መንግስት ብዙም የማያስፈልጋት ነች።¨  ለማለት ነው የፈለጉት:: የ አቦይ ስብሃት የ ገለጻ አንደምታ ለ እኔ እስከገባኝ ድረስ ።
ይህ አጉል የ ፖለቲካ ቁማር ብቻ ሳይሆን በሃገር እና በ ህዝብ ላይ የሚሰራ ትልቅ ደባ ነው። በሰሞኑ ከ አቶ መለስ መሰወር ጋር በተያያዘ የ ኢትዮዽያ ፖለቲካ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ለመድረስ እያኮበኮበ ነው። አቅጣጫው እና ቅርጹ ግን ገና ያልለየለት ግን በ አደገኛ ሃይሎች ዙርያ የተከበበ ይመስላል።ለመሆኑ አደገኛ ሃይሎች አሰላለፍ ምን ይመስላል?

¨እያነቡ እስክስታ¨ ኤርትራ
ኤርትራ በብዙ የ ፖለቲካ ተንታኞች አይን ( በ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይንም) የምትታየው ¨እያነባ እስክስ¨ የሚል  መንግስት ያላት ምስኪን ሃገር ተደርጋ ነው። ከጥቂት አመታት በፊት በ ሃገር ቤት በምትታተመው ¨አዲስ ነገር¨ጋዜጣ ደግሞ ¨ካለ አቅሟ የምትንጠራራ ሃገር፣ማውጣት ከሚገባት በላይ ድምጽ የምታወጣ ሃገር¨ ትባላለች።በከፍተኛ የ ወጣቶች የ ሲኦል ምድር መሆንዋ የተነገረላት ሃገርን የመሰረቱት አቶ ኢሳያስ  ከእዚህ በፊት በተከተሉት የ ውጭ ፖሊሲ ክስረት ማካካሻ አድርገው ማቅረብ የሚፈልጉት እና ¨የ እኔ ስራ በስተመጨረሻ እንዲህ ነው¨ለማለት በሰሞኑ በ ሃገራችን ከ አቶ መለስ መሰወር ጋር በትያያዘ በሚነሱ ትኩሳቶች በ ቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸውን በማስገባት ቀን ከ ሌሊት ያለሙትን የ አካባቢ ሃያልነት ለማግኘት ከሚያደርጉት መዋተት ይነሳል።

 ሰሞኑን የ ሱዳኑን እና የ ግብጽን አምባሳደሮች አስጠርተው ¨የኢትዮዽያ ተቃዋሚዎች ደካማ ናቸው።በ አካባቢው ለሚነሱ ችግሮች ኤርትራ የራስዋን ሚና ትጫወታለች¨ አዘል ንግግር ማረጋቸው  የ ህዋሃትን የ ጦር ሹማምንት አበሳጭቷል። በ እዚህ በ ቀውጢ ሰዓት እንዲህ አይነት አናዳጅ ንግግር መናገር እንደ አንድ የ ምእራብ ዲፕሎማት አነጋገር ቁጡነት የሚቀናው አንዱ የጦር ሹም ሁኔታው አናዶት በ እራሱ አንዳች እርምጃ በኤርትራ ላይ እንዳይወስድ ያሰጋል። ተው የሚል ጠቅላይ የጦር አዛዥ ( አቶ መለስ) በሌሉበት ማለት ነው። ይህ ብቻ አይደለም ከሱዳን ተነስቶ የ ኤርትራን መሬት የሚያገናኝ የ አስፋልት መንገድ በገንዘቧ የገነባችው እና በ ብዙ የ ግጭት ጉዳዮች የምትታየው ኳታርን ጨምሮ የ ኢራን እና የ ሱዳኑ አልበሺር  ከ ኤርትራ ጋር የሚያደርጉት ሹክሹክታ ሁሉ የ ኢትዮዽያን የወደፊቱን የ ሃይል ሚዛን በሚፈለገው መንገድ ለመጠምዘዝ መሆኑን አሜሪካ ያልሰማች የሚመስለው ካለእንዲሰማ አይገደድም::

 የ አቶ ኢሳያስ ሁለቱ ከባድ ፈተናዎች
አቶ ኢሳያስ የገቡበት የ አጣብቂኝ ወጥመድ ውሉ የጠፋ ነው። የመጀመርያው  አጣብቂኝ የተነሳው ከ ኤርትራ ተወላጆች ሲሆን ይህም የ ኢሳያስ ገተር እና ደረቅ ያለ የውጭ ፖሊሲ ይዞ ይነሳል። ኤርትራ ከ አሜሪካ ጋር እንዲህ ''የ አይጥና የ ድመት'' ግንኙነት እንዲሆን ያረጉት የ ኢሳያስ ያልሰለጠነ እና መካሪ ያጣ የውጭ ፖሊሲ ለመሆኑ የ ፕሬዝዳንቱ ብቸኛ ቃለ መጠይቅ አድራጊ የ ቪኦኤ አማርኛው ክፍል ጋዜጠኛ አዳነች ፍስሃዪ ከብዙ የኢሳያስ ተቺዎች በቀረበላት ማሳሰቢያ አንድ ሰሞን የ  አቶ ኢሳያስን የውጭ ፖሊሲ በተለይ ከ አሜሪካ ጋር የነበረውን ለማቅረብ ሙከራ አድርጋ ነበር። በ እዚህ ፕሮግራም በተለይ የ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስርያ ቤት ለ አዳነች ከ ኤርትራ ኤምባሲ ጋር የተቀጣጠሩትን ቀጠሮ ሁሉ እያሳየ ሲያስረዳ እነ አቶ የማነ (የ አቶ ኢሳያስ አማካሪ) ግን በ ብዙ መንገድ ሲከላከሉ ሲታዩ አቶ ኢሳያስ ትልቅ የውጭ ፖሊሲ የ ግትርነት ችግር ውስጥ መሆናቸውን ለወዳጆቻቸው ሁሉ የ አደባባይ ሚስጥር ሆነ።በተለይ የከሰረው ፖሊሲ  አቶ ኢሳያስ ¨አልሸባብ¨ የተባለውን አሸባሪ ቡድን በመደገፍ ቆመዋል ሲባሉ ፖሊሲው ገደል መግባቱ ብቻ ሳይሆን የ ኢጋድ አባል ሃገራትን ጨምሮ የ አፍሪካ ሃገራትን ብሎም ምእራባውያንን ጥርስ አስነከሰች::

ሁለተኛው የ አቶ ኢሳያስ አጣብቂኝ ኤርትራ የምትባል ሃገር ከተመሰረተች በኋላ የ ማንነት ጥያቄን ለመመለስ መቸገር ነው
ይህ የማንነት ጥያቄ ከ ዘጠኝ አመት በፊት በ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በ ኢትዮዽያ አለም አቀፍ የጥናት ጉባዔ ላይ በሰፊው ተወስቷል። ህንድ ከ ፓኪስታን ብትለይ የ ባህል፣የሃይማኖት እና የቋንቋ ልዩነት ኖሮ ነው። የ ኤርትራ ግን በሁሉም ነገር ከ ኢትዮዽያ ጋር አንድ መሆን አይደለም ወደ ማንነት ጥያቄ ሲመጣ ዞሮ አክሱም ታሪክ ላይ መውደቁ የ አስመራ ዩንቨርስቲ የ ታሪክ ምሁራንን ብቻ ሳይሆን ተማሪዎችን ምን ብሎ የራስዋ ታሪክ ያላት ሃገር ማስተማር ብሎም ማንነትን ማስረጽ እንደሚቻል አዳጋች መሆኑ ያፈጠጠ ሃቅ ነው።
ለ እዚህ እንደማስረጃ ብዙዎች የሚያሳዩት በ ሁለቱ ሃገሮች ድንበር መሃል ሰፍሮ የነበረው የ ተባበሩት መንግስታት ሰራዊት ለቆ ሲወጣ ህዝቡ ገብያ ውሎ፣በማህበራዊ ኑሮው ተረዳድቶ ወዘተ መኖሩ እና ምንም በ ህዝቡ መሃል ችግር አለመኖሩ የ ማንነት ጥያቄ በላብራቶሪ አያሰድጉት ነገር ቸግሯቸዋል -አቶ ኢሳያስ ። አሁን ያለው እድል አንድ ነው በ ሰሞኑ የ አቶ መለስ መሰወር(መሞት፣ ወይም የሃኪም እረፍት ) ተጠቅሞ አንድ ነገር ማድረግ።አዎ! አንድ ነገር ብቻ ማደረግ። ቢቻል የ ተቃዋሚ ሃይል ብዙም ሳይበዛ ቢደገፍ ግን በኋላ የ እሳቸውን እርዳታ የሚጠይቅ ቢሆን ይፈልጋሉ።። ይህ ከላይ የተወሱትን ሁለት አጣብቂኞች ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻግራል ብለው ያምናሉ አቶ ኢሳያስ። ህዝቡ አላልኩም።

¨የዘላለም ጥቅም እንጂ የ ዘላለም ወዳጅ የለም¨
ልዕለ ሃያልዋ አሜሪካ የ ሰሞኑን የ አቶ መለስ መሰወር እንዳልሰማች መስላ ግን ሙሉ ጊዜዋን የምታጠፋበት ጉዳይ ሆኗል። አሜሪካ ብቻ አይደለችም የተቀሩት ልዕለ ሃያላን ሃገሮችም ሆኑ የ አረብ ሃገራት ኢትዮጵያን የ አካባቢው ( የ አፍሪካ ቀንድ)  ልዕለ ሃያል ብቻ ሳይሆን ቁልፍ ስትራተጂክ ሃገር መሆንዋን ያምናሉ።በ አባይ ወንዝ ከ ሰማንያ ፐርሰንት በላይ መመንጫ ሃገር መሆንዋ ብቻ አይደለም በ አካባቢው በ ህዝብ ብዛት ዙርያ ገባውን በ እጥፍ መብለጧ እና የ አፍሪካ ህብረት መቀመጫ ብሎም ተጽኖ ፈጣሪ ከመሆንዋ አንጻር ሁሉ ይመነጫል። በሌላ በኩል ከ ሰሞኑ የ ግብጽ የ ፖለቲካ ሃይል አሰላለፍ አንጻር ጽንፈኛ የ አክራሪ እስልምና ሃይሎች (የ እስላም ወንድማማቾች ህብረት በ ግብጽ በምርጫ ማሸነፉን ልብ ይሏል):: ከ ሰሜን ሱዳን ጀመሮ ከ ሱማልያው አልሸባብ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሁሉ መፍትሄ ተደርጋ የምትታየው ሃገራችን ነች።
የ እንደዚህ አይነቱ የመፈለግ ደረጃ ለ አንዲት ሃገር እድገት ወሳኝ መሆኑን የ ልማት ባለሙያዎች ይመክራሉ። ለእዚህም አብነት የሚሆኑት ደቡብ ኮርያ እና ጀርመን ናቸው። ከ ሁለተኛው አለም ጦርነት ፍጻሜ ቀጥሎ በተከሰተው የ ምዕራቡ እና የ ምስራቁ ፍጥጫ ደቡብ ኮርያ በ ከፍተኛ የ ገንዘብ እና የ ሰው ሃይል ልማት ፣ጀርመን ደግሞ ¨ማርሻል ሎው¨በተሰኘው የ አሜሪካ የ ልማት መርሃ ግብር ተነስተው ዛሬ ቢጠሯቸው የማይሰሙ ቱጃሮች ሆነዋል።ይህ ማለት ግን እርዳታ ብቸኛ የ ልማት መንገድ ነው ለማለት ሳይሆን ሲፈለጉ እንዲህ ተለምኖ መደጎም አለ ማለት ነው።
በሌላ አንጻር ግን የ አሜሪካ ብቻ ሳይሆን የ
ፖለቲካው አለም መርህ  ¨ የዘላለም ጥቅም እንጂ የዘላለም ወዳጅ የለውም¨ በሚል መርህ ላይ ይመሰረታል።የዛሬው የ አሜሪካ ወዳጅ ነገ እራሱን ተፈላጊ ካላድረገ የማይገለበጥበት ምክንያት የለም። ለዚህም ነው አሜሪካ ከ ሁለት ወር በፊት በ ሰሜን አፍሪካ ለተነሱት አጥባቂ የ እስልምና ፓርቲዎች የምክክር ስብሰባ ብላ ያወያየችው። ለእዚህም ነው የ ሶርያ ተቃዋሚዎች ባሻር አል አሳድ እስከተቃወሙ ድረስ ሩስያና ቻይና የ ባሻር ተቃዋሚዎች ከ ¨አልቃይዳ¨ጋር ግንኙነት አላቸው እያሉ ቢናገሩም አሜሪካ መጀመርያ ባሻር አል አሳድ ይውረዱ የምትለው። ይህ ተለዋዋጭ አለም ነው የበለጠ የ ዲፕሎማሲውን አለም ውስብስብ የሚያደርገው።
የኢትዮዽያ ፖለቲካ በ ሰሞኑ ከራሞት ምን ይሆን ይሆን?
ኢትዮዽያ ውስጥ የሚኖረው የ ፖለቲካ አሰላለፍ ቅርጽና ይዘቱ በ ጊዜው ጊዜ የሚታይ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሱት ውጭያዊ ሁኔታዎች የ እራሳቸው አንደምታ እና ተካታይ ሁነቶችን ይዘው እንደሚመጡ ማሰብ ተገቢ ነው።በዋናነት የታጠቀው የ ጦር ሰራዊት በ አዛዥነት ያሉት መኮንኖች በ አብዛኛው ከትግራይ ቢሆኑም ለለውጥ የሚያስገድዱ ወሳኝ ሁኔታዎች ግን ከ ጠረንዼዛ ላይ የተዘረጋ አጀንዳ ነው። አንደኛው የ አቶ ኢሳያስ ከ ሱዳን እና ከ ግብጽ ጋር ያደረጉት ምክክር እራሳቸውን በ አውራነት ለማውጣት በመጀመርያ ትግራይን መሸምቀቅ እንደሚሆን ስለሚገመት ¨ሳይቀድሙ መቅደም ¨ በሚል ¨አጭር ግን የማያዳግም ¨የሚሉት እርምጃ በ አቶ ኢሳያስ ላይ መውሰድ አማራጭ  ተብሎ ይወሰድ ይሆናል። ይህም ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ማውረድ የሚል የሰሞኑን በ አቶ መለስ ሳቢያ የደረሰ ንዴት ለማብረድ ያግዛል ተብሎ ሊታሰብ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል።ይህ በህዋሃት ውስጥ አከራካሪ እንደሚሆን ግን ቢይንስ ለ አቅጣጫ ማስቀየርያ እንደሚረዳ ሊታመንበት ይችላል።
ሁለተኛው ኩነት በ አቶ መለስ ዘመን የተከፉት የ ቀድሞ ታጋዮች እንደነ ስዪ አብርሃ እና ገብሩ አስራት የመሰሉትን ስሜት ተጋርቶ የተወጠረውን የ ፖለቲካ አየር ማቀዝቀዝ ነው። ለእዚህ ግን እንደ እነ በረከት ያሉ ¨ልብ አላላች ሁ ይሆናል እንጂ አለመናገር የድርጅታችን ባህል ነው የሚሉ¨የ አራዳ ልጆች ¨ሸዋጆች¨የሚሏቸውን ከ አካባቢው ማራቅ ይጠይቃል። ለእዚህ ደግሞ ብዙ የሚመዘዙ ክሮች ስለሚኖሩ ወታደራዊ መፈንቅል ቢጢ ሽው ማለት አለባት። አለበልዝያ ማን ይሰማል ብላችሁ ነው።
ሶስተኛው ከቁጥጥር ውጭ የሚሆነው እና ማዕበላዊው እና በወቅቱ አነጋገር ¨አሸባሪው¨ ድንገተኛ የ ህዝብ መነሳሳት ነው። ይህ የስርዓት መጥፋትን ብቻ ሳይሆን በቶሎ ስርዓት በሚያስይዝ ሃይል ካልተተካ የ አቦይ ስርዓት ¨ክልሎች እኮ ድሮም እራሳቸውን ነው የሚያስተዳድሩት እና ማእከላዊ መንግስት አያስፈልግም¨ ይምትለው ቀልድ ደግማ ልትተረክ ትችላለች። ያን ጊዜ ግን የ ፍቃዱ ተክለማርያም የመድረክ ትወና ታስፈልጋለች።¨ሰማሽ እማማ ኢትዮዽያ ቃል የ እምነት እዳ ነው እንጅ የ አባት የ እናት እኮ አይደለም¨ የምትለዋ!

4 comments:

Anonymous said...

This is informative.

Anonymous said...

Ewnetun tenagro kemeshebet mader. Tusen Takk.

Anonymous said...

EYITAW TIRU NEW. KIDMYA HAGER YAMESEW YE WEQTU CHIGIR WEYANE NEW.

Anonymous said...

You will have to explain.

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...