ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, March 25, 2012

ከ ታላቁ የ ዋልድባ ገዳም ጋር የ መንግስት ንትርክ ትርፍና ኪሳራው ሲሰላ


ብዙ ነገሮች መርፈዳቸው ያስታውቃል። ዛሬ ስለ ሃይማኖት፣መንግስት፣ልማት፣ወዘተ አዲስ ማብራርያ መስጠት  በራሱ እንዲህ ብየ ነበር ለማለት  ያህል የተሰነዘረ የ ቃላት ስብስብ ብቻ እየመሰሉኝ ከመጡ ከረምረም ብሏል ።
ዛሬ ላይ ሆነን የነገን ተስፋ ስናማትር  እንደትውልድ እና ሀገር የማያስቀጥሉን ጋረጣዎች ከፊታችን ተቀምጠው በትክክል አፍጠው እየመጡ ነው።አላየንም ብሎ  ችግሩን ላለመተው ሰው መሆን ብቻውን አስገዳጅ  መመዘኛ ይመስለኛል።ድሮ ድሮ ቤተመንግሱ ሕዝብ ምን እያለ እንደሆነ ለማወቅም ሆነ የተከፋበትን ጉዳይ ለመረዳት ነገሥታቱ ''እረኛ ምን አለ?'' ብለው ጉድለታቸውን ይለኩበት ነበር አሉ ። ዛሬ ደግሞ ምናልባት ''ፌስ ቡክ ምን አለ? ኢንተርኔት ምን አለ?'' ሳይሆን አይቀርም።የሚያሳዝነው  ግን መፍትሄ ለመስጠት ሳይሆን ማን ከነማን ጋር ቆመ? ለማለት መሆኑ ነው። 
ሰሞኑን በ ሀገራችን በቤተ እምነቱና ቤተ መንግስቱ በሁለት ጎራ ሆነው ቤተ መንግስቱን እየሞገቱት ነው።አንድም የ እስልምና እምነት ተከታዮች ወንድሞቻችን  ''መጅልሱ'' ይውረድ ብለው ባቀረቡት ጥያቄ፣ ሌላም የ ኢትዮጵያ ቤተክርስትያን መነኮሳት አባቶች ና ምእመናን  ''የ  ዋልድባ ገዳም ይዞታ  ይከበር'' ብለው። ለሁለቱም ቤተመንግስቱ መልሶችን ሰጥቷል ። መልሶቹ ግን አስገራሚ፣አስደናቂ እና አሳዛኝም  ናቸው። የሚመሩትን ሀገር ባህል ና አምነት በአግባቡ አለመረዳት ለካ ምን ያህል ትልቅ በሽታ ነው ጎበዝ!።የ ችግሩ ዋነኛ መነሻ ይሄው  አትዮጵያን ለማወቅ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መፈጠር አልያም ህብረተሰቡ ውስጥ እይተከባበሩ ማደግን የግድ ይላልና።

በ ሁለተኛው ዓለም  ጦርነት መዳረሻ በ 1928 ዓም ኢትዮጵያ በ ኢጣልያ ተወራ በነበረችበት ወቅት  የ ኢትዮጵያ መወረር ካንገበገባቸው ብርቅዬ የ ባህር ማዶ ሰዎች መሃከል አንግሊዝያዊትዋ ወ/ሮ ሲልቭያ ፓንክረስ ይጠቀሳሉ። አኚህ የ ኢትዮጵያ ታሪክ ምሁሩ የ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስ እናት ከ ነፃነት በሁዋላ ኢትዮጵያ መኖራቸው ና ቀብራቸውም አዲስ አበባ በሚገኘው በ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ መሆኑ ይታወቃል። አሁን ግን ልነግራችሁ የፈለኩት ስለ ወ/ሮ ሲልቭያ ፓንክረስ የ ልጅ ልጅ አሉላ ፓንርክረስ ነው። አሉላ በ ኢትዮጵያ ታሪክ የተሳበ ወጣት ብቻ ሳይሆን የ ማህበረሰቡ የ አኗኗር ዘይቤ በራሱ የሚማርከው ወጣት  ነው።ባልሳሳት ከ ስድስት ዓመት በፊት ይመስለኛል ከ አዲስ አበባ ከ 5oo ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ የገጠር አንዲት ከተማ ከመስርያቤቴ ባልደረቦች ጋር ባንድነት  ገዳም ለመሳለም በሄድኩበት ጊዜ  አዳፋ ጋቢ ለብሶ በከተማዋ መንገድ ላይ ሲሄድ አየሁት።እኔ ና ጉአደኞቼ በሚቀጥለው ቀን ለሚኖረን ጉዞ ለመዘጋጀት በ ጊዜ እራት በልተን ለመተኛት እራት የሚገኝበትን  ቤት እያሰስን ነበር። ከ አዚህ በፊት በቴሌቭዥን የማውቀው አሉላ ለምን እዚህ  መጣ ? ደግሞስ ለምን የ አደፈ ጋቢ አርጎ ይሄዳል? እኔና ጉአደኛዬ ግራ ተጋባን።በሁአላ ግን ተጠግተን ሰላምታ ተለዋውጠን  እራት አብረን እንድንበላ ጠየቅነው አላቅማማም እሺታውን ገለፀልን። በ እራት ሰዓታችን በተቀላጠፈ አማርኛው ሁሉን ተረከልን። ባጭሩ እርሱ የ ''ሶሻል ዎርክ''ትምርቱን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እያጠና መሆኑን፣ አሁን እዛች ከተማ ውስጥ ከመጣ አራት ወራት ማስቆጠሩን፣ለጥናቱ እንድረዳው ትንሽ  ቤት ተከራይቶ መንደር ውስጥ እንደሚኖር እና ይህም ለ ጥናቱ አስተዋፆው  እንደሆነ  ተረከልን። በነገራችን ላይ አሉላ ጥናቱን ሲሰራ ከ ህዝቡ ጋር አብሮ እየኖረ፣ጠላ ቤት አብሮ እየሄደ፣ጠጅ ቤት አብሮ እየጠጣ መሆኑን ሲነግረን። ህዝብን ማወቅ ሁሉን ነገሩን መሆን እንደሚገባ ትልቅ ተሞክሮ የሚያዝበት መሆኑን  ያስተምረናል። ለ እዚህ ነው ኢትዮጵያን ለማወቅ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መፈጠር አልያም ህብረተሰቡ ውስጥ እይተከባበሩ ማደግን የግድ የሚለው።
ሃይማኖት ና መንግስት እስከ ደርጉ ዘመን
በ ኢትዮጵያ ታሪክ ቤተመንግስት ከ ቤተ ክህነት ጋር ባብዛኛው እየተባበሩ አልያም ቤተ ክህነቱ ቤተመንግስቱን እየመከረ ቤተመንግስቱም እየተመከረ ኖረዋል።ይህ ሁኔታ በ 1966 ቱ አብዮት ድረስ ቀጥሎ ታይቷል። የ አብዮቱ መምጣት ቤተ ክርስትያን የነበራትን የመሬት ምሪት (ምንም  የቤተ ክርስትያን ይዞታዋን  በቀጥታ አላዘዘችበትም የሚሉ ቢኖሩም) መወሰዱ በ ምመናን አስተዋፅኦ ና በ አዲሱ የ ቤተክርስትያን መዋቅር '' የ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ'' በሚል እራሷን ለመቻል ጥረት አደረገች።በዚህ ብቻ ለምግፋት አለመቻሏን ያየ ደርግም በ አካፋ ንብረቷን ወስዶ በ ማንክያ  በ ዓመት የ ሁለት ሚልዮን ብር ድጎማ ለ ቤተክርስትያን ይሰጥ እንደነበር በ ወቅቱ ጉዳዩን የሚያውቁ የሚናገሩት ነው። በ ዘመነ ደርግ ቤተክርስትያን እምነቷን ለማስፋፋት ከ ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ ና ፍልስፍና አንፃር ፊት ለፊት የተጋፈጠችበት፣ቅዱስ ፓትርያርኩ  ሰማአትነት የተቀበሉባት፣ብዙዎች አንደ ሊቀ ትጉሃን  ቀሲስ ጌጡ (አሁን በ ስዊድን ስቶኮልም የሚገኙት) በ ባሌ ጎባ ከተማ እግዝያብሔር አለ ብለው ለ ሃይማኖታቸው በ አደባባይ ተናግረው ለ እስር የተዳረጉበት፣ለ ደርግ ቅርበት ያላቸው የ ሶሻሊስት ርአዮት አቀንቃኝ የነበሩት ልጆቻቸውን ክርስትና ለማስነሳት ፈርተው በ ድብቅ የምፈፅሙበት ቤተክርስትያን ና ምመኖችዋ አሳዛኝ ወቅት ላይ የነበሩበት ጊዜ ነበር።
ይህ በ እንዲህ እያለ ግን ደርግ የ ሃይማኖትን በ ህብረተስቡ ውስጥ ያለውን ሚና አልረሳውም። እንደ ወቅቱ አገላለፅ ህብረተሰቡ በ ኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ '' 'እስኪነቃ' ድረስ ሃይማኖትን አለማራቅ'' የሚል ''ራሽያው'' አስተሳሰብ ነበረው። ለ ዚህም ይመስላል የ እስልምና አና የ ክርስትና ሃይማኖቶች መሪዎች በ ወቅቱ ''ብሔራዊ ሸንጎ'' ተብሎ በሚጠራው የመንግስት  ምክርቤት ስብሰባ እንዲገኙ የሚያደርገው።በነገራችን ላይ የ ወቅቱ ምክርቤት የ ይስሙላ ምርጫ ''ኢሰፓ'' (የ ኢትዮጵያ ሰራተኞች  ፓርቲ ) ያሸነፈው ወንበር ና ባለፈው ምርጫ ኢህአዴግ አሸነፍኩ ካለው የ ምክር ቤት  ወንበር ብዛት መካከል ያለው ልዩነት የ ደርግ ከ አንድ ፐርሰንት በታች የሚበልጠው መሆኑ ነው። ይሄውም ደርግ መቶ ፐርሰንት ሲያሸንፍ አህአዴግ ግን ዘጠና ዘጠኝ ነጥብ ምናምን ፐርሰንት ማሸነፉ ነው።
ሃይማኖት ና መንግስት በ ዘመነ ኢህአዴግ

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በጣም የሚፈራቸው (ሊገቡት ስላልቻሉ ሊሆን ይችላል) ግን ሊፈራቸው የማይገባው የነበሩ ሁለት ነገሮች አሉ። እነርሱም- የመጀመርያው ''ምርጫ'' ሲሆን ሁለተኛው '' ሃይማኖት'' ነው።የ ምርጫው ይቆየንና ሃይማኖትን ግን ለምን ይፈራዋል? ብለን ስንጠይቅ ስለ  ሁለት ምክንያቶች መሆኑ  ይታዩኛል። እነርሱም :-



፩- ኢህአዴግ በመዋቅሩ የ ሃይማኖት አስተምሮቱም ሆነ ትምህርቱ ያላቸው ሰዎች በ አመራር ደረጃ አለመኖር
ኢህአዴግ በ ከፍተኛ አመራሩ ደረጃ ያሉት አባሎቹ ማለ- ሊግ ፣ግምገማ ና የራስን እድል በራስ መወሰን፣ወዘተ በሚሉ ሃሳቦች አንጂ የ ሞራልም ሆነ ሃይማኖታዊ መሰረቶች ቦታ የላቸውም። አዚህ ላይ ለማስረጃ ቢሆነን ባለፈው በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ አና አቡነ ጳውሎስ መካከል በተነሳው ውዝግብ መንግስት ቢያንስ ቤተክርስትያንቱን የሚያውቁ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የተመሰከረላቸው ባለስልጣን ስላላገኘ ሊቃነ ጳጳሳቱ ፊት ጠረንዼዛ አየደበደበ የሚያስፈራራ ሰው ልኮት አረፈው።አባቶችን አክብሮ ትህትና በተሞላ ማአነጋገ ሃይማኖተኛነትን ሳይሆን ኢትዮጵያነት ማስረጃ  ነው።ሌላው ማሳያ የ ቤተክርስትያንቱን ጉዳይ በተመለከተ ሁሉ የምያማክራቸው የ ''እኔ  ናቸው '' ብሎ የሚያስባቸውን የ ቤተክህነቱን ፊታውራሪዎች ብቻ አንጂ ከስር ምን ችግር አንዳለ ህዝቡ ምን እንደምያስብ ያወቀ ቢመስለውም አንዳላወቀ ተግባሩ እና ለነገሮች የሚሰጠው ምላሽ ያሳብቅበታል።

፪-ሁለተኛው ሃይማኖትን የሚፈራበት ዋነኛ ምክንያት የ ቤተክርስትያትያን  አደረጃጀት ና አስተምሮ ከኢህአዴግ ክልልን መሰረት ያደረገ አሰራር በተከተለ መልክ  ቤተክርስትያኒቱም  እንድትቀኝ   መመኘቱ ነው።ቤተክርስትያን ከሞያሌ አስክ ደብረዳሞ ከሐረር አስክ ኢልባቦር ድረስ ቅዳሴዋ፣አስተምሮቷ ሁሉ ዘር ና  ቋንቋ ሳትለይ ለ ሁሉ እናት መሆኗ፣ የ ቀደመው የሀገሪቱ ታሪክ፣ትምህርት፣ፍልስፍና፣ነፃነት ሁሉ በ አሻራነት መያዝዋ -ኢህአዴግ አዲስ ታሪክ ለመፍጠር ከሚሞክረው ሙከራ ጋር እየተጋጨ ብዙ ጊዜ ስላነጠረበት ቤተክርስትያንን በበጎ አይን ከማየት በሂደት ወደሚፈልገው አካህያድ  እንድትሄድ በ ቤተክህነት፣በ አጥብያ አብያተክርስትያናት እና በ መንፈሳዊ ማህበራት ውስጥ  ጭምር ካድረዎቹን እያስገባ  ምእመናንን ቁም ስቅል ማሳየት ተያይትዞታል።
ለ ዚህም ማሳያው በ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተጠመቁ ካድሬዎች ቤተክህነቱን እንደፈለጉ ስንፈላሰሱ፣የ ሊቃነ ጳጳሳትን ማደርያ በር እየሰበሩ ሲያስፈራሩ ፣የ ስልክ ዛቻ ሲፈፀም ሁሉ  ጉዳዩን ለምርመራ አቅርቦ ለሕዝብ ከማሳየት ይልቅ እንደዋዛ ማለፍ የተጠቀመበት የ  አጉል ብልጣብልጥነት  መንገድ ነበር።

''ኢትዮጵያ -የ እግዚአብሔር የምስጢር ሀገር''

በ ኢትዮጵያ  ሁኔታ ሃይማኖት የ እድገት ትልቅ መሳርያ የሚሆንበት ብዙ አይነት  እድሎች ነበሩ። የ ኢትዮጵያ ቤተክርስትያን በመዋቅር ደረጃ  ብንመለከት ከቤተመንግስት እስክ ገጠር መንደር ድረስ መዋቅር ያላት፣ በ ሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ የያዘች፣በያንዳንዱ ሰው ዘንድ የመሰማት እና ተፅኖ የመፍጠር  አቅም   ያላት ፣የሀገሪቱን የ ቱሪዝም እንዱስትሪ ከሰማንያ በመቶ በላይ ድርሻ ያላትን ትልቅ ተቋም  በ ፍርሃት ማየት ና የ ልማት አጋር አለማድረግ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን በሚፈለገው መንገድ ለመቅረፅ የመሞከር አጅግ አስፈሪ ተግባር ነው።እርግጥ ነው ቤተክርስትያን የአስተዳደራዊ መዋቅር ችግሯ ሁሉ ከኢህአዴግ ችግር ብቻ የሚነሳ ነው  ለማለት አይቻልም። ግን በነበረው ችግር ላይ ቤተክርስትያን መፍትሄ እንድትፈልግ እድል   ከመስጠት ይልቅ የባሰ ሌላ የቤት ሥራ መስጠት ምን የሚሉት ፈልጥ ይሆን?

''ኢትዮጵያ የ አግዚአብሔር የምስጢር ሀገር'' ይህን የተናገሩት በ 1982 ዓም በ መኪና አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ብፁእ  አቡነ ጎርጎርዮስ ነበሩ። ለእዚህም ምክንያት ነበራቸው።  ሀገራችን ከ ክርስቶስ ልደት በፊት በ ህገ -ልቦና (ሰዎች አምላካቸውን በ ልቦናቸው ያወቁበት)፣በ ህገ ኦሪት (በ ሙሴ አስርቱ ትዛዛት ሕግ ስር  አክብራ የኖረች መሆኗ) እና በ ህገ- ወንጌል አምልኮተ- አግዝያብሔርን ስትፈፅም የነበረች አሁንም ያለች ሀገር ነችና አንዲሁም የሚወዱትን ና  የሚሳሱለትን ነገር በ ሚስጥር ቦታ እንደሚሸሽጉት ታቦተ ፅዮንን ከ አስራኤል አምጥቶ፣ ሃብተ ንግስናን ከ ዳዊት አምጥቶ፣ሃብተ ትንቢትን ከ ነቢያት አምጥቶ፣ሐዋርያነትን ከ ቅዱስ ፊልጶስ  ዝማሬ መላአክትን በ ቅዱስ ያሬድ አምጥቶ ሸሽጎባታልና የ ሚስጥር ሃገሩ ትባላለች። ይህ ብቻ አደለም ክርስትናን በ ዓለም  ላይ ከ ምድረ እስራኤል ቀጥላ ጌታችን ገና  ባረገ በ ዓመቱ በ 34 ዓም የተቀበለች (በ ጃንደረባው አማካይነት)  ሀገርም  ነችና የ እግዚያብሔር የሚስጥር ሀገር ትባላለች።
ይህች ሀገር የራሷ የሆነ የ አኗኗር፣አመጋገብ፣አለባበስ፣አነጋገር፣ሰላም አፈጣጠር፣እራሷን የመከላከል ብልሃት ፣ሀገርኛ የሆነ አሸመጋገል ና የመንግስት አስተዳደር ባህል ያላት ሀገር ነች።ኢትዮጵያን ለማወቅ መጀመርያ ኢትዮጵያዊ ሆኖ መፈጠር አለበለዝያ ህብረተሰቡ ውስጥ እየተከባበሩ ማደግ የግድ የሚሉት ሁለቱ መስፈርቶች ናቸው። ከ እዚህ ውጭ ግን ሁል ጊዜ ጉዳዩ ሁሉ ''ሾላ በድፍን'' እንደሆነ መቅረት ደግሞ  ሌላው  እድል ሊሆን ይችላል።

                                                     ገዳማዊ አባት
                                                        

''ስኳር አንፈልግም ብለን ገዳም  ብንመጣ
ዛሬስ ከነ አካሉ  ስኳር ታጥቆ መጣ '' የ ዋልድባ ገዳም  አባቶች

ከላይ ከተውሱት ጉዳዮች አንፃር በ  ዋልድባ ገዳም ጉዳይ  የ ሰሞኑ የመንግስትን  ተግዳሮት  ስንመለከተው የ እስካሁኑ ተከታይ ግን ከወትሮው በበለጠ ድፍረት ና ተጠያቂነት ያጣ ና ግራ ና ቀኙን ያላገናዘበ የ ይድረስ ይድረስ ሥራ መሆኑ የ አደባባይ ምስጢር ነው ።ጉዳዩን እንደምናውቀው መንግስት የ ገዳሙን (ዋልድባ ገዳም)  አንድኛውን ክፍል በነካ መልክ የ ስኳር ፋብሪካ አቆማለሁ ብሎ ለ ፋብሪካው የሚረዱ ስራዎችን እየሰራሁ ነው ማለቱ ና  የ ገዳሙ አባቶች ደግሞ ''ቦታው የ ቃል ኪዳን ቦታ ነው ገዳሙ ሀጥያት የማይሻገርበት ፣ዘር የማይዘራባት፣እህል የማይበላባት ቦታ ነው'' ማለታቸው ይታወሳል። በ ገዳሙ አባቶች የተፈረመ ደብዳቤ እስክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ  ድረስ መድረሱን እስካሁን ግን መንግስት በ ቴሌቭዥን መነኮሳቱን በ ''ፖለቲካ አስተሳሰብ የተወጠሩ'' በማለት ለ አንድ የ ሃይማኖት አባቶች መስጠት የሚገባውን ክብር እረስቶ 'እንክያ ሰላምታ' ውስጥ መግባቱ ይታወቃል። አለማዊ ኑሮ ና ምግብ ይቅር ብለው በመነኑ ያ የፈሩትን የ ዓለም ሁካታና፣ ሆይሆይታ  ለማምጣት ብሎም  ክፋብሪካው ተከላ ጋር ተያይዞ የሚመሰረተው ከተማ  ገዳምሙን  መጠጋት ለ ዋልድባ አባቶች ታሪካዊ ስህተት መሰራቱን ያሳየ ክስተት ነበር ።

ከዋልድባ ገዳም ንትርክ የ ኢህአዴግ  ፖለቲካዊ  ትርፍና  ኪሳራ ሲሰላ

 ሮብ መጋቢት 12/2004  ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በ አዲስ አበባ አቆጣጠር የ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተለመደ ''ጆሮ የሚጠልዝ'' ዜና አሳየን። በ ሰሜን ጎንደር የተካሄደ  አቶ አባይ ፀሐዬ የመሩት  በ ፊልሙ ላይ አንደምታየው ወደ አራት ብቻ  የሚጠጉ መነኮሳት  ና ሌላ ጥቁር ለባሽ የተሰበሰቡበት ስብሰባ ታየ። ሁለት ሰዎች የ ስኳር  ፋብሪካውን አንደደገፉ ሲናገሩ ተሰማ። ''የማይመስል ነገር ለ ምንትስ አትንገር'' ይላሉ ይሄው ነው። በዚህ የመገናኛ አገልግሎት በፅፋፋበት ጊዜ የዚህ አይነት የ ዜና ልዩነት ማንበብ በራሱ ግራ መጋባት ነው። ቀጥሎ አባይ ፀሐዬ አርገውት የማያውቁትን  የቴሌቭዥን ጣቢያ ዜና አንባቢው ጎን ተቀምጠው ማብራርያ ሰጡን '' ገዳሙ ውስጥ አልገባንም ከዳር ነው ያለነው----ወዘተ''። ከዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ነገር መንግስት አንድ ስለ ገዳማት ያልተገነዘበው ነገር መኖሩን ነው። ይሄውም  ገዳማት (የ ዋልድባን ገዳም በልዩ ሁኔታ ቃል ኪዳን ስላለበት አይዘራበትም፣አይታረስም አንጂ)  ሥራ የ ምንኩስና ሕይወት አንዱ አካል ምሆኑና ''መፅሐፈ መነኮሳት'' የተሰኙት መፃህፍትም  ስራን ወደ ሀጥያት ላለማምራት አንዱ ተራጅ መንገድ  መሆኑን  ነው።
ዋልድባ ያለው አንዱ ጥያቄ በገዳሙ ክልል የመግባት አና አለመግባት ጉዳይ ብቻ አይደለም ከዚህ በዘለለ የገዳሙ መንፈሳዊ ሕይወት ከግንዛቤ መግባት ይገባው ነበር።ይህ ብቻ አይደለም በ ሰሞኑ የመንግስት ንትርክ የሚከተሉት ነጥቦች አለመታወቃቸው ወይንም ግንዛቤ አለማግኘታቸው ያስገርማል። አነርሱም-
  • በ አካባቢው ሸንኮራ አደጋ መትከል አደለም ድምፅ ማሰማት የተከለከለ ነው።
  • ዶዘር ና ትራክተር ማርመስመስ አደለም ድምፅን ከፍ አርጎ  ማውራት አይገባም።
  • ብዙ የስውራን ና ቅዱሳን አባቶች ቦታን  (ሃይማኖት ባይኖረን ከሞራል አንፃር ለማየት ቢሞከር ) ለ ዓለም አንድፀልዩ  ብንተ ውላቸው?  
  •  የ ፀለምት ወረዳ አስተዳዳሪ በ አሜሪካ ድምፅ አማርኛው ክፍልም አንዳረጋገጡት ና ገዳማውያኑም አንደተናገሩት የ ቆዩ የ ቅዱሳን ና ምመናን አፅም አየተፈነቀለ ወደ ሌላ ቦታ መዛወሩ ና ''ቤተሰብ ወደፈለገው ቅዱስ ቦታ ተወሰደ'' ብሎ  መናገር ምን አይነት ሞራላዊ ንግግር ይሆን? 
ኢህአዴግ ከአዚህ ሂደት አንድን ነገር ድርቅ ብሎ ሃሳብን ባለመቀየር ወደፊት ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ አስተማሪ ይሆናል በሚል ግምት ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ያስባል። ጉዳዮችን ሁሉ  ''ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ'' ፍልስፍና አንፃር ብቻ ከታየ ያውም ለ ሺ አመታት የፀናን ሃይማኖት በ መገዳደር አና መንግስትን ያህል ተቁአም ከዋናከተማ በ ብዙ መቶ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ካለ ገዳም ጋር ቦታ መጋፋት ለ ቤተክርስትያኒቱ ሌሎች ይዞታዎች ሊተላለፍ የተፈለገው መልክት ከመንግስት በኩል  መኖሩን የሚያሳይ ይመስለኛል። ይሄ ድርጊት ግን ሕዝቡን ወደ አንድ የግዴታ ጥግ እየመራው ነው። ይህ ደግሞ ቀልድ አይደለም ያ ጥግ ምንድነው? ቢባል አሁን ላይታወቅ ይችላል። አንድ ሰው የራሱን ድመት በር ዘግቶ ባይገርፍ ይመረጣል።ብችል በሩን ገርበብ አርጎ መግረፍ ይሻላል።ድመትቱ ለተወሰነ ጊዜ የ ክፍሉን ዙርያ አየዞረች ለመሸሽ ትሞክራለች።ዱላው ሲበዛባት ግን ገራፍዋ ጉሮሮ ላይ ለመቆም ትገደዳለች። ዛሬ ለ ኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የማያዝንላት የለም።አናት ስትጎሳቆል ና ስትገፋ ማን የማያዝን አለ?

''አሳ ለ ገዳማውያኑ!?''  ለምን አያሳዝን?
  • የ ቤተክርስትያን ከፍተኛው አካል ቅዱስ ሲኖዶስን የሚመራው በ ቅዱስ መንፈስ ነው። በ ቅዱስ መንፈስ የሚመራ ቅዱስ ሲኖዶስ (ባልፈው ሳምንት የ ኢህአዴግ ባለስልጣን በ አሜሪካ ድምፅ ራድዮ እንደ  ምክርቤት አባል አጠራር 'ክቡር ሲኖዶስ' አያለ  ሲናገር ነበር) የሚያሳልፈው ውሳኔ ፓትራርኩ ሊሽረውም ሆነ ሊያሻሽለው አይችልም። ቅዱስ ሲኖዶስ በ ሃያ ቀን ይፍረስ ያለው የ አቡነ ጳውሎስ ሃውልት ይሄው ሳይፈርስ ሁለት ዓመት ሊሞላው ሲሆን ማዘን ይነስ?
  • በ ቤተክህነቱ (በመንግስት ሹመኞች ጋር በተሞዳሞደ መልኩ) ከፍተኛ ሙስና ተስፋፍቶ ሙስናው ቅጥ አጥቶ የ ካህናት ምደባ በ ሙስና የተበላሸ ሲሆን ማዘን ይነሰን?
  • በ ቤተክርስትያኒቱ አስተምሮ የተመሰከረላቸው ሊቃውንት በ ሙስና በተቀጠሩ ቅጥረኞች እየተሰደቡ፣እየታዘዙ ሙሰኞቹ ሲሻቸው ስያባርሯቸው ቤቱን የ ወንበዴዎች ዋሻ ሲያደርጉት ማዘን ይነስ?
  • ነጋ ለ ፀሎት ሲመሽ ለ ፀሎት በሚጠጉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብስባ ላይ ተሰብስበው በወሰኑት ውሳኔ ምሽት በራቸው እየተሰበረ፣ የማስፈራርያ ማስጠንቀቅያ እየተሰጠ '' ይሄ የተለመደ ሁኔታ  ነው'' ተብሎ ካለ አንዳች  ምርመራና ውጤት ይሄው ሁለት ዓመት ሲሆን ማዘን ይነሰን?
  • ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን እንደ   ክፍል ውስጥ ተማሪ መንግስት ከፍተኛ ባለስትጣኑን ልኮ ጠረንጴዛ እየደበደበ ሲያስፈራራ  ሲውል ማዘን ይነስ?
  • በአሰቦት ና ዝቁላ ገዳም እሳት ተነስቶ ቤተክህነት ለምን በቶሎ አልደረሰም ሲባል ''እሳት የትም ይነሳል ምነው ቤተክርስትያን ሲሆን እንዲህ ይጋነናል?'' በ አራዳ አነጋገር '' ለምን ታካብዳላችሁ?'' መሰል መልስ ሲሰጥ ምነው አያሳዝን?
  • የ  ዋልድባ ገዳም  መንግስት እሰራዋለሁ በሚለው   የ ስኳር  ፋብሪካ ገዳማውያኑ 'ከቁአፍ ስር 'ሌላ እንደማይበሉ  እየታወቀ  ለ ፋብሪካው በምንገድበው ግድብ ገዳማውያኑ አሳ በመብላት እንድጠቀሙ  እናደርጋለን  ተብሎ ስሾፍ  አንዴት አያሳዝን?
  • ''የ ዋልድባ ገዳም የ አርምሞ፣የዝምታ ፣የ ቃልኪዳን ቦታ ነው ሀጥያት የማይሻገርበት፣ዘር የማይዘራበት ቅዱስ ቦታ ነው'' ብለው በተናገሩ በ ገዳሙ አበምነት ተወክለው በመጡት  አባት ላይ ''የ ፖለቲካ አላማ አላቸው፣መንኩሴ አደሉም '' ብሎ መሳለቅ ሲፈፀም ለምን አናዝን?

በ ኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ላይ የተሰራው ግፍና የማናጋት ሥራ እጅግ አደገኛ ብቻ ሳይሆን ነገ የተደገሰውንም አመላካች ሥራ ነው።
ባጠቃላይ የዋልድባው ጉዳይ የዋልድባን ችግር  ብቻ የሚያሳይ  አደለም። ይልቁንም  የ እያንዳንዱ አጥብያ ቤተክርስትያን ይዞታ ጉዳይ ነው። አንደምታው ለሁሉም ነው። ዋልድባ የ እፍታው ማሳያ ነው። እፍታው ከተገላለጠ በኋላ  ዋናው ወጥ ገና እየተሰራ ወይንም ተሰርቶ ሊወጣ መሆኑን አመላካች ነው። ጉዳዩንም እግዝያብሔርን አውቃለሁ የሚል በሙሉ ሊቃወመው ቢያንስ ገዳማውያኑ በዚች ዓለም በ አርምሞ፣በዝምታ ከአምላክ ጋር ለመነጋገር ፀጥ ያለው ዋልድባ ውስጥ የመፀለይ ና የማልቀስ ሰዋዊ   መብታቸውን ባይነፈጉ ።እንደ ሰው ማሰብ ተጀመረ ማለት ነበር።




በ ዋልድባ ገዳም ላይ የ አሜሪካ ራድዮ ያቀረባቸው ዘገባዎች ያዳምጡ

1. Waldibba Monastery  Reportage by VOA Radio http://www.youtube.com/watch?v=JLiJ2ADUh_k&feature=related

2. Waldibba Monastery  Reportage by VOA Radio http://www.dejeselam.org/2012/03/waldibba-monastery-3rd-reportage-by-voa.html


አበቃሁ
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ











7 comments:

Anonymous said...

that is all right and true.

pkk said...

wow wow!!!!
very analytical and acadamic essay!!
betam tiru new gecho

Anonymous said...

Berta!!

Henok said...

Your titls and sub titls are non-forgetable. This will indicates me as you have fantastic capacity. The way how you link issues are also tremendous. I really like it.Last you need to edit some letters like 'A'.But my general view is very good.keep on it.

ርብቃ said...

ከ ሃገር ውስጥ ብዙ ሰው ብሎግህን ያነባል።በርታ በትንሽ ጊዜ ብዙ ተማርኩበት። ቀጥልበት። ብሎግህን ሊንክ ብታደርግበት ደግሞ ቆንጆ ነው።
ርብቃ

Anonymous said...

You expressed my internal feelings in a very fantastic way. May God Bless you

Anonymous said...

Thank you - You did a great job! You speak out what is in our mind.

May God be with you.

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።