Tuesday, April 18, 2017

በዋልድባ ገዳም ላይ ህወሓት ያደረገው ምስጢራዊ ስብሰባ እና ገዳሙን ለማፍረስ ያደረጋቸው እኩይ ተግባራት

አቶ ገብረመድህን አርአያ 

ከአቶ ገብረመድህን አርአያ 
የህወሓት መስራች፣ የፖሊት ቢሮ አባል እና የፋይናንስ ኃላፊ የነበሩ 
አሁን በስደት በአውስትራሊያ ነዋሪ 

የዋልድባ ገዳም በህዋሓት መሪዎች በዓይነ ቁራኛ የወደቀው ገና ትገሉ እንደተጀመረ ነው። የዋልድባ ገዳም የህወሓት መሪዎች እንዲወድም ሃሳብ ያቀረቡት በ1973 መጨረሻ አካባቢ ሲሆን፣ አቅማራ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በውቅቱ የህወሓት መናኸሪያ ነበር። በተመቤን ውስጥ የሚገኘው ቦታ በፕሮፓጋንዳ ጽ/ቤት ተሰብስበው ወሰኑ፤ በስብሰባ የነበሩት አመራር ፖሊት ቢሮው በሙሉ ነበር። እነሱም፣ ስብሃት ነጋ፣ አረጋዊ በርሄ፣ ገደይ ዘርአጽዮን፣ አባይ ፀሃየ፣ ስዩም መስፈን እና መለስ ዜናዊ ነበር። በወቅቱ ማ/ኮሚቴ የነበሩ ናቸው።Ato Gebremedhin Araya former TPLF leadership member
በዚህ ስብሰባቸው የዋልድባን ገዳም እጣ ፈንታ ወሰኑ። ዋልድባ እንዲወደም የወሰኑት በዚህ ስብሰባቸው ነበር። የዋልድባ ገዳም ለብዙ መቶ ዘመናት የቅዱሳን፣ ብፁአን፣ ባህታውያን፣ ቀሳውስት፣ አባቶች፣ ደናግል፣ ዲያቆናት ወዘተ ሰፈር በመሆን በኢትዮጵያ ቅዱስና በታሪክ ትልቅ ምእራፍ የያዘ ገዳም ነው። ይህ ቅዱስ ገዳም የቅዱሳን ማረፊያ በመሆኑ በታላቅነቱ የሚታወቅ ነው። ገዳሙ የታነጸው በ12ኛው ክፍለ ዘመን በብፁእ ወቅዱስ አቡነ ዮሴፍ ነው። ቅዱሳን ወደኢትዮጵያ እንደገቡም ያረፉበት፣ የተሰባሰቡበት ቦታ እንደሆነ በርካታ አማንያን ይናገራሉ። ዋልድባ ገዳም ታሪካዊ ቅርሶች፣ የግዕዝ ብራና፣ ታላላቅ መጻሕፍት፣ ጥናታዊና ታሪካዊ መዛግብት የሚገኙበት ስፍራ ነው።

የህዋሓት ሴራ በዋልድባ ገዳም ላይ
ከዚህ ቀጥየ የማቀርበው ፀረ ዋልድባ ገዳም የሆኑትን፣ ከላይ ስማቸው የተዘረዘረውን የህዋሓት ፖሊት ቢሮ መሪዎች በ1973 በአቅማራ፣ ተምቤን የወጠኑትን ፀረ ዋልድባ ሴራ ነው። በብዙ ታጋዮች የሚታወቅ፣ በይበልጥም ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት መሪዎች፣ የስለላ ታጋዮች፣ የክፍል መሪዎች ወዘተ በትክክል የሚያውቁት ሴራ ነው። በስብሃት ነጋ ተነግሮናል፣ ስለዚህ ድብቅ ምስጢር አይደለም። ለሕዝብና ለተራ ታጋይ ግን ድብቅ ምስጢር ነበር።
ከላይ የተጠቀሱት የህወሓት መሪዎች የዋልድባን ገዳም በተመለከተ ብዙ ከተነጋገሩበት በኋላ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በሚከተሉትን ምክንያቶች አድርገው ወሰኑ፤

1. በሰሜን ኢትዮጵያ የክርስትና መስፍፋት ዋና መሰረቱ በዋልድባ ገዳም እየተማሩ የሚወጡት ናቸው። በተለይ በትግራይ የሚገኙት አብያተ ክርስትያናት መሪዎች በዚሁ ገዳም የተማሩ ናቸው። ቀሳውስት፣ ዲያቆናት በዚሁ ገዳም የተማሩ ናቸው። ይህ ገዳም እያለ የክርስትና ሃይማኖት ከትግራይ ውስት ለማስወገድ አይቻልም። ለወደፊቱ ከድል በኋል ለምናቋቁመው የትግራይ መንግሥት ትልቅ መሰናክል የሚሆኑት የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖቶች ናቸው። ስለሆነም ዋልድባ ገዳም የክርስትና ሃይማንቶት መፈልፈያ ስለሆነ ከምንጩ ማድረቅ አለብን በማለት የህወሓት ፖሊት ቢሮ አባላት፣ ማለትም፣ ስብሃት ነጋ፣ አረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘርአጽዮን፥ አባይ ፀሃየ፣ ስዩም መስፍን እና በወቅቱ ማ/ኮሚቴ የነበረው መለስ ዜናዊ በገዳሙ ላይ ውሳኔ አስተለለፉ። ውሳኔውም፤
2. በገዳሙ ተንቀሳቃሽ ንብረትና የማይንቀሳቀስ ንበርት ላይ ጥናት ማካሄድ፤
3. የገዳሙ ሃላፊዎችን ስም ዝርዝር ማጥናትና ማሳወቅ፣
4. የዋልድባ ገዳም ግምጃ ቤት ውስጥ የሚገኙትን ቅርሳ ቅርስ፣ ጥንታዊ መጽሐፍትና መዛግብት በዝርዝር ማጥናት፣
5. የገንዘቡን ክምችትና ቦታውን አጥንቶ ማሳወቅ። ይህንን ሁሉ በረቀቀ ስለላ ማጥናትና መከታተል የፖሊት ቢሮው ሃላፊነት ይሆናል ተብሎ ተወሰነ።
ለዚህ ጥናት ወደ ዋልድባ ገዳም አስርገን የምንልከው ታጋይ ቢያንስ ቢያንስ የድቁና ማእረግ ያለው፣ የቤተክረስቲያን ትምህርት ያለውና ያጠናቀቀ ታጋይ መሆን አለበት በማለት የህወሓት አመራር በአቅማራው ስብሰባ ወሰኑ። በዚህ ስብሰባ ሃላፊነቱ የተሰጠው ለስብሃት ነጋና ለግደይ ዘርአጽዮን ነበር። ሁለቱ የፖሊት ቢሮ አባላት፣ የህወሓት ሊቀመንበር እና ም/ሊቀመንበር ናቸው። በውሳኔው መሰረት ወደ ሥራቸው ተሰማሩ። ይህን የሥራ ሃላፊነት የተረከቡት የቤተ ክህነት ብቁ እውቀት ያለው ሰው ማግኘት ካባድ ቢሆንባቸውም፣ በየዞኑ የሚገኙትን የሕዝብ ግንኙነት ታጋይ ሃላፊዎችን በማነጋግር በምስጢር ደብዳቤ በመላላክ ብዙ ጊዜ ፈጁ። 

በ1974 መጨረሻ አካባቢ በተምቤን አውራጃ ጣንቋ አበርገሌ ውስጥ የድቁና ማእረግ ያለው ብቁ ወጣት ዲያቆን ተገኘ። አበርገሌ ተወልዶ ያደገ፣ የቤተ ክህነት ትምህርቱን ያጠናቀቀ ቀዳሽ ነው። ዘመናዊ ትምህርት የለውም። የዞኑ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረውና አራት ጓዶቹን አሰባስቦ ድርጅታችን ህወሓት እናንተን ለትግል ይፈልጋችኋል ተብለው ተገደው ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ (02) ተላኩ። ይህ የቤተ ክህነት ድቁና ያለው ወጣት ልዩ ዳብዳቤ ለአስገደ ግብረስላሴ ተላከለት። በደብዳቤው የተካተተው ለልዩ ሥራ ስለሚፈለግ ጥሩ እንክብካቤ እንዲደረግለት የሚል ነበር። የ02 አስልጣኞችም በተላከው ደብዳቤ መሰረት ተንከባክበው ያዙት። የአንድ ወር ወታደራዊ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ይህ ታጋይ በርሄ መብራህቱ ይባላል። 

በርሄ መብራህቱ ከማሰልጠኛው ጣቢያ አስወጥተው ሰው በማያገኘው አንድ ገበሬ ቤት ደበቁት። በዚሁ ድብቅ ቦታ የሚገናኘው ከኪሮስ ሃይለ (ወዲ ሃይለ) ጋር ብቻ ነበር። ኪሮስ ሃይለ የወታደራዊ ማሰልጠኛ አስትዳዳሪ ሃላፊ ነው። አስፈላጊ እንክብካቤም አደረገለት። ከአስር ቀናት በኋላም ካንድ ትልቅ አመራር ጋር እንደሚገናኝ ነገረው። ከማንም ሰው ጋር እንዳይገናኝ አስጠነቀቀው። እንዲሁ እያለ ከ13 ቀናት በኋላ ስብሃት ነጋ መጥቶ እዛው ድብቅ ቤት ተገናኙ። ስብሃት ነጋና በርሄ መብራህቱ ለ9 ቀናት አብረውት በመቆየት ስብሃት ታጋይ ዲያቆን በርሄ መብራህቱ ወደ ዋልድባ ገዳም ለስለላ እንደሚላክና እገዳሙ ወስጥ ገብቶ የስለላ ጥናቱን እንደሚያካሂድ፣ ምን ምን መስራት እንዳለበት አሰለጠነው። የሚፈጸሙትን ተግባራትም በዝርዝር አስጠናው። ከሚፈጽማቸው ተግባራት መካከል፣ በዋልድባ ገዳም ያሉትን ጥናታዊ ቅርሶች፣ የብራና መጻህፍት፣ መዛግብት፣ የገዳሙን የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት፣ ዋና ግምጃ ቤቱ ወስጥ ያለውን ወርቅ ወዘተ የሚቀመጥበትን፣ የዋልድባ ገዳም ሃላፊዎችን ስም ዝርዝር፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ሌሎች አስፈላጊ ናቸው የምትላቸውን ስም ማሳወቅ ወዘተ ተብሎ ተነገረው። ይህንን ጥናት ወደኛ ለማስተላለፍ ጥሞናና ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን ማወቅ አለብህ። መኖሪያህ ገዳሙ ውስጥ ነው። ቀናት የፈጀ ገለጻውን ትምህርቱን ሲጨርስ ከሳምንታት በኋላ እንገናኛለን ተባለ። ግደይ ዘርአጽዮን መጥቶ ያነጋግርሃል በማለት ለጊዜው ተሰናበተው። ግደይ ዘርአጽዮን ከሁለት ቀን በኋላ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመሄድ ኪሮስ ሃይለን በማግኘት ኪሮስ ሃይለም ታጋይ በርሄ መብራህቱን ወደተደበቀበት ቦት ይዞ በመሄድ አገናኘው። ግደይም ለቀናት ታጋይ በርሄ መብራህቱን ስለ ስለላ ሥራው አሰለጠነው። መገናኛው የምስጢር ቃል ኮድ መሆኑን አስረግጦ አስተማረው። ከማን እንደሚገናኝ፣ የምስጢር ኮዱ ስብሃት ተመልሶ ስለሚገናኝህ ይነግርሃል በማለት ተሰናበተው።

ስብሃት ነጋ ከሳምንት በኋላ ተመልሶ መጣ። ሲመጣም በቀረጢት የተቋጠሩ እቃዎችን ይዞ መጣ። ከረጢቱን ፈትቶ ለታጋይ በርሄ መብራህቱ አሳየው፤ መስቀል፣ የቄስ ጥምጥምና ቆብ፣ የቄስ ዘንግ፣ መቁጠሪያ፣ ጭራ፣ ሙሉ የቄስ ልብስ፣ ጋቢ ወዘተ ለአንድ ቄስ የሚያስፈልገውን ሁሉ በተሟላ ሁኔታ ሰጠው። ታጋይ በርሄ መብራህቱም የመጣለትን ተረከበ። ከአሁን በኋላ ስምህ አባ ገብረሥላሴ ነው። ዋልድባ ገዳም ስትገባ አባ ገ/ሥላሴ መሆንህን አስተዋውቅ። በርሄ መብራህቱን እርሳው ተባለ፣ በጉዳዩም ላይ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው። ከኔም ሆነ ከግደይ ዘርአጽዮን ጋር የምትገናኝበት የምስጢር ኮድ ይህ ነው ብሎ ሰጠው። የሚላኩልህን መልእክቶች ተቀበል፣ የተሳሳተ ኮድ ከሆነ አትቀበል፣ የሚመጣውን ሰው ሁሉ አታነጋግር ተባለ። ከአንተ ጋር የሚገናኘው ብስራት አማር ብቻ ነው። ሲመጣ አስተዋውቅሃለሁ። በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ትገናኛላችሁ። የተገኘውን ምስጢር ሁሉ ጽፈህና አሽገህ ትልክልናለህ። ከኔም ሆነ ከግደይ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በምስጢር በአካል በደብቅ ቦታ እንገናኛለን ተብሎ መመሪያ ተሰጠው።

አሁን የለበስከውን ልብስ ለብሰህ እስከ ተከዜ ትሄዳለህ። ተከዜን ከተሻገርክ በኋላ የለበስከውን ልብስ አውልቀህ ሙሉ የቄስ ልብስህን ትለብሳለህ። የዱሮው ልብስህን ተመልሰህ እኛን ለመገናኘት ስትመጣ የቄስ ልብስህን ደብቀህ የዱሮ ልብስህን ለብሰህ እንገናኛለን። ሰው በማያገኘው ጥሩ ቦታ ደብቀው ተባብለው በዚሁ ተለያዩ። አባ ገ/ሥላሴም ዋልድባ ገዳም ገቡ። ታጋይ በርሄ መብራህቱ (አባ ገ/ሥላሴ) ገዳም ገብተው ሰፈሩ። ከ1975 እስከ ሐምሌ 1983 ለ8 ዓመታት ዋልድባ ገዳም የኖረው ታጋይ በርሄ መብራህቱ ሰላዩ በዋልድባ ገዳም የሚታወቀው አባ ገ/ሥላሴ ሲሆን የተሰጣቸውን የስለላ ተግባር በተሳካ ሁኔታ ቀጠሉበት። በዋልድባ ገዳም አባ ገ/ሥላሴን የሚያውቋቸው የገዳሙ አባላት በርካታ ናቸው። ቢሆንም፣ ገዳሙን ለማጥቃት በህወሓት የተላኩ ሰላይ መሆናቸውን ግን አያውቁም። ስምንት ዓመት በገዳሙ ሲኖር ማንነቱ እንዳይታወቅ በጥንቃቄ የኖረ ሰላይና መልእክተኛ ነው። ታጋይ በርሄ መብራህቱ (አባ ገ/ሥላሴ) በዋልድባ ገዳም ባካሄደው የስለላ ጥናቱ ለስብሃት ነጋና ለግደይ ዘርአጽዮን በማስተላለፍ ዋልድባ ገዳምን ለካባድ ጥፋትና ውድመት የዳረገ ሰው ነው። ከግደይ ዘርአጽዮን በማለሊት ምስረታ ጉባኤ በሃሐምሌ 1977 ቢባረርም፣ ሰላዩን በተገቢው መንገድ አሰጥኖታል። 

አባ ገ/ሥላሴ (ታጋይ በርሄ መብራህቱ) በሚያስተላልፈው የስለላ መልእክቶች በብስራት አማረ እጅ በመላክ ለስብሃት ነጋና ለውውይት ለዘርአጽዮን ይደርሳል። ከዚሁ በመነሳት የሚፈለገውን ጥቃት ሁሉ በስምንት ዓመታት ቆይታው ገዳሙ ከሚጠቀምባቸው የምንጭ ውሃ እስከ እርሻ መሬት፣ በብዛት የጋማ ከብትና ማንኛውንም ሃብት በዝርዝር አሳልፈው የሰጡና ያስተላለፉ ሰላይ ዛሬ ገዳሙ እየደረሰበት ያለው መፍትሄ የሌለው ውድቀትና ችግር የአባ ገ/ሥላሴ (ታጋይ በርሄ መብራህቱ) የስለላ ውጤቶች ናቸው። በወቅቱም ቢሆን በብስራት አማረ የሚመራው አፋኝና ሽብርተኛ ገዳይ ቡድን አድፍጠው በመጠባበቅ ብዙ ብፁአን አባቶችን፣ ቀሳውስቶችን፣ በርካታ ዲያቆናትን ደብዛቸውን አጥፍቷል። ሙታኖችን ገዳሙ ይቁጠራቅቸው። ለዚህ ሁሉ ወንጀል ተጠያዎቹ ስብሃት ነጋና ግደይ ዘርአጽዮን ናቸው።
ዛሬ በዋልድባ ገዳም ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋትና ውድመት በስብሃት ነጋና በግደይ ዘርአጽዮን በታቀደ የስለላ መረብ ምክንያት ነው። በጠቅላላ ለጥንታዊውና ባለታሪኩ ገዳም መውደም ተጠያዊዎቹ የህወሓት ከፍተኛ መሪዎች ናቸው። ለጥፋት ውሳኔው ዋናዎቹ ተባባሪዎች፣ አረጋዊ በርሄ፣ አባይ ፀሃየ፣ ስዩም መስፈን እና በወቅቱ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል የነበርው መለስ ዜናዊ ናቸው። በዋልድባ ገዳም ዛሬ እየደረሰ ላለው ውድመት የገዢው ስርዓት ህወሓት ሙሉ ለሙሉ በሃላፊነት ተጠያቂ ናቸው። ወንጄሎቻቸውም፤

1. ታላቅና ባለ ታሪክ የሆነውን የዋልድባን ገዳም አውድመዋል፣
2. ብዙ ብፁአን አባቶችን፣ ባህታዊያንን፣ ቀሳውስትን ገድለዋል፣ አጥፍተዋል፣
3. የዋልድባን ገድም ጠቅላላ ሃብታና ንበረት ዘርፈዋል አስዘርፈዋል፣
4. ጥንትዊ የብራና መጽሐፍት፣ የታሪክ መዛግብትን ወዘተ ዘርፈዋል፣ አስዘርፈዋል፣
5. የገዳሙን ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ሃብትና ንብረት፣ የጋም ከብቶች፣ የእርሻ ቁሳቁሶችን ወዘተ በህወሓት ባለሥልጥናት በጉልበት ወስደዋል።

በሥልጣን ላይ ያለው ፋሽስትና ሽብርተኛ ህወሓት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛቱ ሰር ከጣላት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዋልድባ ገዳም እየደረሰ ያለው ፋታ የሌለው ጥቃት ስብሃት ነጋና ግደይ ዘርአጽዮን በሸረቡት ተንኮል የዋልድባ ገድማ ጥፋት እንደቀጠለ ነው። ዛሬ የዋልድባ ገዳም በውድመት አፋፍ ላይ ተንጠልጥሎ ይገኛል። ክብሩና እና ህልውናው ተገፎ የባንዳዎችና የህወሓት አመራር የግል ንብረታቸው አድርገውታል።

የዚህ ቅዱስ ቦታ ጥቃትና ውድመት፣ ሃብታና ንብረት መዘረፍ፣ የብፁአን አባቶች ሕይወት መጥፋት ወዘተ ተጠያቂው ህወሓት ነው። የዚህ ፋሽስትና ዘራፊ መሪዎች ሁሉ ለቅዱስ ገዳሙ መጥፋት በሕግ ተጠያቂዎች ናቸው።

ከአቶ ገብረመድህን አርአያ 
የህወሓት መስራች፣ የፖሊት ቢሮ አባል እና የፋይናንስ ኃላፊ የነበሩ 
አሁን በስደት በአውስትራሊያ ነዋሪ 

ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

Tuesday, April 4, 2017

የኢትዮጵያ ጉዳይ እጅግ አደገኛ የሚባል ደረጃ ደርሷል።የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚሰማችሁ የስርዓቱ አካላት፣የተቃዋሚ ኃይሎች እና መላ ህዝብ ኢትዮጵያ መንግስት እንዲኖራት በቶሎ መነሳት ይጠበቅባቸዋል።ምን ይደረግ? ባለ ሰባት ነጥብ ሃሳቦች ቀርበዋል።(የጉዳያችን ወቅታዊ ሃሳብ)



ጉዳያችን /Gudayachn 
መጋቢት 27፣2009 ዓም (April 5,2017)

መግቢያ 

አሁን በስልጣን ላይ ያለው የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ጎማ ከእዚህ በላይ ኢትዮጵያን ሊያሽከረክር አይችልም።ኢትዮጵያ ካለ አንዳች ለውጥ አንዲት ቀን መቆየት የማትችልበት ደረጃ ላይ ነች።በሀገር ውስጥ እና ዙርያዋን እየሆነ ያለው ሁሉ መንግስት የሌላት ሀገር የሚል ስም የሚያሰጥ፣ስርዓት አልበኝነት ከምንገምተው በላይ የሚሄድበት ትልቅ ዕድል አለ።ሕወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያን የመምራት አቅም አይደለም እራሱን ብቻ ተሸክሞ መራመድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።እራሱን መሸከም አለመቻል ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱ በገባው ቅራኔ መንገዱ ሁሉ ታጥሮበታል።የውስጥ ቅራኔው መስፋት ቀድሞ ከነበረው ደካማ አቅም በባሰ እጅግ ደካማ በሆነ የሰው ኃይል ከወዲያ ወዲህ ያለ አንዳች ሥራ እየተንገላወደ ነው።

ይህ ከአቅም በታች የሆነ የሰው ኃይል ከዋናው የህወሓት አስኳል ጋር በመሆን ኢትዮጵያን በአራቱም ማዕዘን ዘረፋውን አጧጡፈውታል።የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የልማት ባንክ በቢልዮን የሚቆጠር  ገንዘብ ዕዳ ውስጥ ገብቷል።ስርዓት አልበኞቹ ባለስልጣናት ከአቶ ሃይለማርያም ጀምሮ ኢትዮጵያን የግል ንብረታቸው አድርገው የመንግስት ስራን  ከሚገመተው በላይ አቡክተውታል።በአባይ ወልዱ የሚመራው የትግራይ ክልል (በእራሱ ለማዕከላዊ መንግስት ባለፉት አመታት ሲያደረገው እንደነበረው ሁሉ) የእራሱ የዘመነ መሳፍንት ዓለም ፈጥሮ በእያንዳንዱ የኢትዮጵያዊ መንግስታዊ እና የግል ድርጅቶች የውስጥ ጉዳይ ሁሉ  እየገባ እያመሰ እና እየዘረፈ ነው። የስርዓቱ አስተዳደር መዋቅር ተበጣጥሶ ሁሉም የእራሱን ሕግ በሚገዛው ቀበሌ ውስጥ ገዢ ሆኗል።የአዲስ አበባ አስተዳደርን ብቻ ብንወስድ እታች ቀበሌ ያለውን ሥራ የመምራትም ሆነ የመቆጣጠር አቅሙ ወርዶ ሰዎች ከሰሜን በመጣ እና ባልመጣ አነጋገር እየተለየ  ያልነበረሕግ የሚሰራበት ደረጃ  ላይ ተደርሷል።

ኢትዮጵያ እየፈረሰች ነው ክልሎች በባእዳን እጅ የመግባት መጥፎ ዕድል አላቸው 

የሱማሌ ክልል ከአዲስ አበባ ጋር ከሚያደርገው ግንኙነት ይልቅ ከሞቃዲሾ የሚመጡ ኮብራ መኪናዎች ይቀርቡታል።ክልሉ የኢትዮጵያን የቁም ከብት እና ጫት እንዲሁም ፍራፍሬ እየሸጠ በምትኩ የጦር መሳርያ እየሸመተ ነው።ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያን ድንበር ከፓኪስታን እና ከአፍጋኒስታን የመጡ አሸባሪዎች ሳይቀሩ እንደፈለጉ የሚገቡበት እና የሚወጡበት የውሃ መንገድ አስደርጎታል።አቶ ሃይለማርያም ኢትዮጵያን የመምራት አይደለም ፒያሳ ስላለው ጉዳይ አያውቁም።ከጀርባ እየመራ ነው የሚባለው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እርስ በርሱ ለመመታታት ሰዓታትን እየጠበቀ ነው።አቦይ ስብሐት እራሳቸው ግራ ተጋብተው ደጋግመው የሚወዱትን ሬድ ሌበል ውስኪ ከመጎንጨት በቀር የሚሰሩት ግራ ገብቷቸዋል። 

ከጎንደር እና ጎጃም በእየሰዓቱ  የሚመጣው ዜና የኢህአዴግ/ህወሓት ወታደር የሆነ ሁሉ ጥቃት እየተፈፀመበት እንደሆነ ነው።ሰራዊቱ እራሱ ጎንደር ላይ ለመዝመት አንዳች ፍላጎት የለውም።ምክንያቱም ዘመቻው እራሱ ምክንያታዊ ሳይሆን በሕወሓት እብሪት የተፈጠረ እሳት መሆኑን ሰራዊቱ ይስማማበታል።ይህ ሁሉ ጉዳይ ያስጨነቀው ሕወሓት የሱዳኑን ፕሬዝዳንት ዛሬ አዲስ አበባ ድረስ ጠርቶ ማናገር ይዟል።የሱዳኑ ፕሬዝዳንት አልበሽር እራሳቸው አዲስ አበባን ሲረግጡ ከእዚህ በፊት ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሲመጡ የሚያውቁት ሀገር አልሆነባቸውም።አሁን ለውጥ ለውጥ የሚል ሽታ እና የስርዓቱ ባለስልጣናት አቶ ኃይለማርያምን ጨምሮ የተደናገጠ ፊት ብቻ ነው የተመለከቱት።ጉብኝታቸው ሁሉ የውሸት ስለሆነባቸው የሚያደርጉት ውል ሁሉ የማይረጋ መሆኑን ስሜታቸው እንደነግራቸው ከፊታቸው ይነበባል። 

የኢትዮጵያ ዙርያ ያሉ መሬቶች በአረብ ሀገር ወታደሮች እየተከበቡ ነው።ከሱማሌ እስከ አሰብ ድረስ ጂቡቲን ጨምሮ ከእዚህ በፊት ሰራዊታቸውን ከሀገራቸው ውጭ አስፍረው የማያውቁ የአረብ ሀገሮች በሙሉ የኢትዮጵያን በሕወሓት ደካማ እና በዘር ላይ የተመለከተ መንግስት እጅ መውደቅ ተመልክተው  ዙርያችን ሰፍረዋል።የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ጉዳይ ተሞክሮ እዚህ ግባ የማይባል ልምድ በሌላቸው ግለሰብ እጅ በመውደቁ ሚንስትሩ  ዛሬ ለምክር ቤት ያለፈ የስድስት ወር ሪፖርት ሲያቀርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደረጃ መነገር የማይገባቸው ቃላት ሲጠቀሙ መመልከት የብስለት ብቻ ሳይሆን  የዓለም አቀፍ እውቀት እና ልምድ ማነስ ምን ያህል ኢትዮጵያን አፈር ድሜ እንዳስገባ ለመረዳት ቀላል ነው።

የህዝቡ የጉስቁልና ደረጃ በቀላሉ በማንኛውም የውጭ ኃይል የመማረክ መጥፎ እጣ ያሰጋዋል።

የምጣኔ ሃብቱ ድቀት የድሀውን እና የደሞዝተኛውን የመግዛት አቅም ከተጠበቀው በታች አውርዶታል።በመምህራን ደረጃ የመኖር እና አለመኖር ግብግብ ውስጥ ስለገቡ ሰልቫጅ ልብስ መንገድ ላይ በመሸጥ ከማስተማር ሙያቸው በተጨማሪ  የሚሰሩ መምህራን አዲስ አበባ ላይ መኖራቸው የእዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ሰምቷል። በእዚህ ወር የዋጋ ግሽበቱ መጨመሩን ሮይተርስ በለቀው ዘገባ አረጋግጧል።የዓለም ባንክ ከውሃ እና ፍሳሽ ጋር በተያያዘ በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ብድር መፍቀዱ ትናንት ቢሰማም ብድሩን ለማግኘት በእራሱ ብዙ ደረጃዎች አሉት።ስለሆነም ለአሁኑ የህወሓት የውጭ ምንዛሪ ጥማት ሊደርስለት አይችልም።የዓለም ባንክ ይህንን የሚያደርገው የቻይና እጅ በበለጠ እንዳይረዝም ከማሰብ ውጭ የብድር መመለስ አስተማማኝ ዋስትና ኖሮት አይደለም። 

እነኝህ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ኢትዮጵያን በደርግ ዘመን ከነበረችበት ደረጃ እና አሁን በሕወሓት ዘመንም  ካለንበት አስከፊ ደረጃ በባሰ ሁኔታ ሀገሪቱን ይዞ የሚወርድ አደገኛ ደረጃ ነው።ስለሆነም ምን መደረግ አለበት? ሙስናው የኢትዮጵያን ሀብት እየዘረፈ፣ባእዳን ጥርሳቸውን እያሳዩን ሀገራችንን ሲያጠፉ እንመልከት? ወይንስ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚጠበቅብንን  ለመስራት በቁርጠኝነት እንነሳ? ደግሞስ ማን ምን ይስራ? 

ኢትዮጵያን ለማዳን አሁን  ምን ያድርግ?

የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ምጣኔያዊ ሀብት እና ማኅበራዊ ሁኔታ ላለፉት 26 አመታት በኢህአዴግ/ሕወሓት እጅጉን ቆስሏል።ይህ ቁስል ለመጠገግ ቢያንስ ሁለት ዓመታት ይፈልጋል።ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከሕወሓት መውደቅ በኃላ ወድያው ጤናማ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ማሰብ በእራሱ ሞኝነት ነው።ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያን ለማዳን ደረጃ በደረጃ ምን ይደረግ?

1ኛ/ ከኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት፣ከኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ከስርዓቱ ጋር ያልተነካኩ እና የቆሸሸ ስም የሌለባቸው የሃይማኖት ተወካዮች፣ምሁራን፣ከበሬታ ከህዝብ ያገኙ ዜጎች ያቀፈ ጊዚያዊ የኢትዮጵያ መንግስት በቶሎ አዲስ አበባ ላይ መመስረት አለበት።ይህ ጊዜያዊ መንግስት ለሁለት አመታት የሚቆይ (ዓመቱ ግምት ነው። ሊያንስ ይችላል) መሪ የዜጎች የጋራ መርህ ያወጣል።

ይህ እንዴት ይችላል? ሕወሓት ስልጣን ይለቃል ወይ? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ የተረዱ የሰራዊቱ አባላት እና የህዝብ ንቅናቄ ሁሉ ሕወሃትን ማስገደድ አለባቸው።ይህ እንደሚሆን እራሳቸው ህወሐቶችም በሚገባ ያውቁታል።በማንኛውም ደረጃ የሚነሳ የስልጣን ነጠቃ እንደሚኖር ያውቃሉ።አሁን የቀረው መረረኝ ብሎ የቆረጠ የሰራዊቱ አባል እና ሕዝብ እራሱን ባጭር ጊዜ አደራጅቶ የመነሳቱ ጉዳይ ብቻ ነው።

2ኛ/ ይህ ጊዜያዊ የኢትዮጵያ መንግስት በቅድምያ የኢትዮጵያን ሰራዊት ከሁሉም የሀገሪቱ ግጭቶች ገለልተኛ የሆነ የሁሉ ጠባቂ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ስራዎችን ይሰራል።ምክንያቱም ግዝያዊ መንግስት ሲመሰረት በአንዳንድ ክልሎች አንዳንድ ግጭቶች ዕለቱን አይቆሙም።ለምሳሌ በሰሜን ጎንደር እና ትግራይ፣በኦሮሞ እና ሱማሌ መካከል ያሉት ግጭቶች እና መስል ግጭቶች ሕወሓት ወለድ እና ቀደም ብሎ የነበረ ታሪካዊ ሂደት ስላላቸው ሰራዊቱ የሁሉንም ችግር የሚያዳምጥ እና የሚጠብቅ በቅድምያ ግን የኢትዮጵያን አንድነት እና ድንበር ጥበቃ አስተማማኝነት ላይ ያተኩራል።

3ኛ/ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ስር ሆነው ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን ይመሰርታሉ።ለምሳሌ የሀኪሞች ባለሙያዎች፣የግብርና ሙያ ባለሙያዎች ወዘተ በእየሀገሩ ይደራጃሉ ወይንም የነበረ አደረጃጀታቸውን ያስመዘግባሉ። ሁሉም አደረጃጀቶች ጊዜያዊ የኢትዮጵያ መንግስት በሚያወጣው የዜጎች የጋራ መርህ ይመራሉ።

4ኛ/ ጊዚያዊ የኢትዮጵያ መንግስት ዋናው መንግስት መጣም አልመጣም ነፃ ከመሆን የሚያግዳቸው የማይኖረው የፍትህ አካላት እና የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ለሁሉም የቆመ መሆኑ ላይ አበክሮ ይሰራል።ነፃ የምርጫ ቦርድ የመመስረት፣ የፕሬስ ሕጉ ለሁሉም የሚሰራ መሆኑ ላይ እና የህዝቡ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሕይወት በሽግግር ጊዜው ወቅት እንዳይታወክ አበክሮ ይሰራል።ይህ ማለት በከፍተኛ ደረጃ እርስ በርስ መቃቃር ያቆሰለውን ሕዝብ በበጎ የእርስ በርስ ግንኙነቶች እንዲዳብር በሁሉም መስክ ይሰራል።

5ኛ/ ዚያዊ የኢትዮጵያ መንግስ ነፃ ምርጫ (እንደ እዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ) እንዲደረግ የምርጫ ቦርዱ በነፃ እንዲያስደርግ  ሙሉ እገዛ ያደርጋል። የፕሬዝዳንት ምርጫ እንደ ኢትዮጵያ ትልልቅ ብሔሮች ላሉባት እና ሌሎች በርካታ ውሁዳንም ለሚኖሩባት ሀገር  ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት፣ልምድ እና ስነ-ምግባር የተላበሰ  አቅም ያለው ፕሬዝዳንት ከየትኛውም ብሔር ቢመጣ እና በዙር ለሌላውም ሲደርሰው ላለፉት 26 አመታት የተዘራውን መርዝ ያረክሰዋል።

6ኛ/ የኢትዮጵያ ዋናው ምክር ቤት በነፃ ምርጫ ይመሰረታል፣የኢትዮጵያ መጪ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ፣ የውጭ ፖሊሲ እና የአጠቃላይ የልማት አቅጣጫ ይቀየሳል።በመካከለኛው ምስራቅ፣አፍሪካ እና ሌሎች አለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የሚገቡበት አግባብ ይቀየሳል፣በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ቅራኔዎች እንዳይኖሩ የይቅርታ እና የኢትዮጵያዊነት ቀን ይታወጃል። በሀገር ላይ ከፍተኛ በደል የፈፀሙ ግልፅ በሆነ መንገድ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያደርጋል።

7ኛ/ የኢትዮጵያውያን የጋራ ተቋማት ግንባታ ላይ ያተኮሩ ስራዎች፣የስራ ዕድል ፈጠራዎች፣የስነ-ጥበብ እና ኪነ-ጥበብ እድገት ላይ ያተኮሩ ስራዎች እና ኢትዮጵያን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚችሉ ስራዎች ወደ ተግባር ይቀየራሉ።

ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች የሕልም ወሬ ያህል የምንገምተው እንኖራለን።ሆኖም ግን አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ጠቃሚው እና እንደ ሀገር የመቀጠል እድላችንን የሚያጎላ ነው።የግድ ካልሆነ ከእንጦጦ ጀምሮ እስከ አራት ኪሎ ድረስ መንገዱ በመድፍ እየታረሰ መገባት ላይኖርበት ይችላል።በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሕዝብ፣ሰራዊቱ እና ተቃዋሚዎች ልብ ለልብ መገናኘት በቂ ነው።ከእዚህ ሲዘል ደግሞ የስርዓቱ አቀንቃኞች ይህ ለመቸውም ቢሆን ከስህተቱ የማይታረም ስርዓት ለማስወገድ እና ለልጆቻቸው የሚተርፍ የደስታ ዘመን ለማስተላለፍ ቁርጠኝነት የተላበሰ ውሳኔ ብቻ ነው የሚፈልገው።ውሳኔ ሕልምን እውን ያደርጋል።ኢትዮጵያን ለማዳን እንወስን ወስኑ !


ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

Monday, April 3, 2017

የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ዛሬ ከትራምፕ ጋር በአካል ተገናኙ።አልሲሲ ትራምፕን "ልዩ ስብዕና የተላበሱ ሰው" በማለት አሞካሽተዋቸዋል።

ጉዳያችን ዜና /Gudayachn News
መጋቢት 25፣2009 ዓም (March 3,2017)

የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከአሜሪካው አቻቸው ጋር በዋይት ሃውስ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 25፣2009 ዓም ተገናኝተዋል።በቀይ ምንጣፍ ስነ-ስርዓት ሞቅ ያለ አቀባበል የጠበቃቸው የግብፁ ፕሬዝዳንት ፕሬዝዳንት ትራምፕን አግራሞት እና አድናቆት በተላበሰ እይታ ተመልክተዋቸዋል።በአፀፋውም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአክብሮት ሰላምታ መለሱ።አልሲሲ ከአረብ ሀገሮች የመጀመርያው ለትራምፕ ስልክ ደውለው ደስታቸውን የገለጡ ሲሆኑ ትራምፕም መጀመርያ መልሰው ከደወሉላቸው የዓለም መሪዎች የግብፁ ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ነበር።

´´ያንን ነገር አብረን እናደርገዋለን! ሽብርተኝነትን እና ሌሎች ነገሮችን አብረን እንዋጋለን"  ("we will do that thing together. We will fight terrorism and other things together")  አሏቸው ትራምፕ የግብፁ አቻቸውን  አተኩረው እየተመለከቱ። ትራምፕ "ያንን ነገር" ያሉት ፀረ ሽብር ዘመቻውን እንደሆነ ተገምቷል። "ሌሎቹ ነገሮች" ያሏቸው የትኞቹን ነገሮች እንደሆነ አላብራሩም።አልሲሲ በሃሳቡ ከተስማሙ በኃላ ትራምፕን "ልዩ ስብዕና የተላበሱ ሰው" በማለት አሞካሿቸው። ትራምፕ ፈገግ አሉ።ዓለም በሙሉ ትራምፕ የሚለውን ስም በሚወቅስበት ሰዓት ከግብፁ አቻቸው ይህንን ሙገሳ ማግኘት እልም ባለ በረሃ ላይ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ የማግኘት ያህል ውድ ነበር ለትራምፕ። ትራምፕ ቀጠሉ "ለእረጅም ጊዜ ወዳጅ እንደሆንን እንቆያለን" "We will become friends for a long time," አሏቸው።አልሲሲ በፈገግታ መለሱላቸው።

የግብፅ ፕሬዝዳንት ዋይት ሃውስን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኘው እ.ኤ.አቆጣጠር በ2010 ዓም በፕሬዝዳንት ሁስኔ ሙባረክ ወቅት ነበር።በወቅቱ ኦባማ የግብፅን ጉዳይ በጣም ቀዳሚ እና አንገብጋቢ አጀንዳ አላደረጉትም ነበር።

ይህ በእንዲህ እያለ የግብፁ ፕሬዝዳንት ከትራምፕ ጋር ባደረጉት የዛሬ ንግግር ግብፅ ቀዳሚ ´የፀጥታ እና የደህንነቴ ስጋት´ ብላ የምትቆጥረው የውሃ ጉዳይ እና በኢትዮጵያ እየተሰራ ነው በተባለው የዓባይ ግድብ ዙርያ እንዲሁም በሕወሓት መንግስት ጉዳይ እና የደቡብ ሱዳን ሁኔታ ዙርያ ለትራምፕ ምንም ነገር ሹክ አላሉም ማለት አይቻልም።

ኢትዮጵያ በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው፣በእውቀት እና ችሎታ ላይ የተመሰረቱ ባለስልጣናት ቢኖራት ኖሮ በአካባቢው ላይ ተፅኖ የመፍጠር አቅሟ ባደገ እና በዛሬው የአልሲሲ ቦታ ላይ የኢትዮጵያ መሪ በክብር በተገኘ ነበር።ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ መልሳ አትነሳም ማለት አይደለም።በዘር ላይ የተመሰረተ መንግስት ፍፃሜውን ማፋጠን ማለት ኢትዮጵያን መልሶ ማንሳት ነው።ላለፉት 26 አመታት ሕወሓት ከመግደል እና ከማሰር እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን እንዲሰደዱ እና አንጡራ ሀብታቸው ለባዕዳን ከመሸጥ ያለፈ አንዳች ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም።ወደፊትም አይችልም።በቂም እና በመንደር ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ከአዲስ አበባ ዋይት ሃውስ ድረስ የሚደርስ ዓለም አቀፋዊ ተፅኖ የመፍጠር አቅም የለውም። ስለ አድዋ እና መቀሌ ብቻ የሚያስቡ መሪዎች ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅ ሀገር የማስተዳደር አቅምም ሆነ ችሎታ የላቸውም።ይልቁንም ኢትዮጵያን ለማንሳት ኢትዮጵያውያን ትልቅ ርእይ ይዘው መነሳት ካለባቸው ጊዜው አሁን ነው።የእራሳችንን ጉዳይ ሌሎች እንዲነጋገሩበት እና አጀንዳ እንዲያደርጉት ዕድል ልንሰጣቸው አይገባም። 

የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በዋይት ሃውስ ከትራምፕ ጋር የሰጡት መግለጫ ከእዚህ በታች ባለው ቪድዮ ይመልከቱ። የግብፁ ፕሬዝዳንት እንግሊዝኛ ስለማይችሉ አይደለም በሀገራቸው ቋንቋ የሚናገሩት። ኢትዮጵያ ባለስልጣናቷ እስከ ደረግ ዘመን ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ሳይቀር የሚናገሩት በሀገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ነበር። 





ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com