ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, April 4, 2017

የኢትዮጵያ ጉዳይ እጅግ አደገኛ የሚባል ደረጃ ደርሷል።የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚሰማችሁ የስርዓቱ አካላት፣የተቃዋሚ ኃይሎች እና መላ ህዝብ ኢትዮጵያ መንግስት እንዲኖራት በቶሎ መነሳት ይጠበቅባቸዋል።ምን ይደረግ? ባለ ሰባት ነጥብ ሃሳቦች ቀርበዋል።(የጉዳያችን ወቅታዊ ሃሳብ)



ጉዳያችን /Gudayachn 
መጋቢት 27፣2009 ዓም (April 5,2017)

መግቢያ 

አሁን በስልጣን ላይ ያለው የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ጎማ ከእዚህ በላይ ኢትዮጵያን ሊያሽከረክር አይችልም።ኢትዮጵያ ካለ አንዳች ለውጥ አንዲት ቀን መቆየት የማትችልበት ደረጃ ላይ ነች።በሀገር ውስጥ እና ዙርያዋን እየሆነ ያለው ሁሉ መንግስት የሌላት ሀገር የሚል ስም የሚያሰጥ፣ስርዓት አልበኝነት ከምንገምተው በላይ የሚሄድበት ትልቅ ዕድል አለ።ሕወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያን የመምራት አቅም አይደለም እራሱን ብቻ ተሸክሞ መራመድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።እራሱን መሸከም አለመቻል ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱ በገባው ቅራኔ መንገዱ ሁሉ ታጥሮበታል።የውስጥ ቅራኔው መስፋት ቀድሞ ከነበረው ደካማ አቅም በባሰ እጅግ ደካማ በሆነ የሰው ኃይል ከወዲያ ወዲህ ያለ አንዳች ሥራ እየተንገላወደ ነው።

ይህ ከአቅም በታች የሆነ የሰው ኃይል ከዋናው የህወሓት አስኳል ጋር በመሆን ኢትዮጵያን በአራቱም ማዕዘን ዘረፋውን አጧጡፈውታል።የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የልማት ባንክ በቢልዮን የሚቆጠር  ገንዘብ ዕዳ ውስጥ ገብቷል።ስርዓት አልበኞቹ ባለስልጣናት ከአቶ ሃይለማርያም ጀምሮ ኢትዮጵያን የግል ንብረታቸው አድርገው የመንግስት ስራን  ከሚገመተው በላይ አቡክተውታል።በአባይ ወልዱ የሚመራው የትግራይ ክልል (በእራሱ ለማዕከላዊ መንግስት ባለፉት አመታት ሲያደረገው እንደነበረው ሁሉ) የእራሱ የዘመነ መሳፍንት ዓለም ፈጥሮ በእያንዳንዱ የኢትዮጵያዊ መንግስታዊ እና የግል ድርጅቶች የውስጥ ጉዳይ ሁሉ  እየገባ እያመሰ እና እየዘረፈ ነው። የስርዓቱ አስተዳደር መዋቅር ተበጣጥሶ ሁሉም የእራሱን ሕግ በሚገዛው ቀበሌ ውስጥ ገዢ ሆኗል።የአዲስ አበባ አስተዳደርን ብቻ ብንወስድ እታች ቀበሌ ያለውን ሥራ የመምራትም ሆነ የመቆጣጠር አቅሙ ወርዶ ሰዎች ከሰሜን በመጣ እና ባልመጣ አነጋገር እየተለየ  ያልነበረሕግ የሚሰራበት ደረጃ  ላይ ተደርሷል።

ኢትዮጵያ እየፈረሰች ነው ክልሎች በባእዳን እጅ የመግባት መጥፎ ዕድል አላቸው 

የሱማሌ ክልል ከአዲስ አበባ ጋር ከሚያደርገው ግንኙነት ይልቅ ከሞቃዲሾ የሚመጡ ኮብራ መኪናዎች ይቀርቡታል።ክልሉ የኢትዮጵያን የቁም ከብት እና ጫት እንዲሁም ፍራፍሬ እየሸጠ በምትኩ የጦር መሳርያ እየሸመተ ነው።ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያን ድንበር ከፓኪስታን እና ከአፍጋኒስታን የመጡ አሸባሪዎች ሳይቀሩ እንደፈለጉ የሚገቡበት እና የሚወጡበት የውሃ መንገድ አስደርጎታል።አቶ ሃይለማርያም ኢትዮጵያን የመምራት አይደለም ፒያሳ ስላለው ጉዳይ አያውቁም።ከጀርባ እየመራ ነው የሚባለው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እርስ በርሱ ለመመታታት ሰዓታትን እየጠበቀ ነው።አቦይ ስብሐት እራሳቸው ግራ ተጋብተው ደጋግመው የሚወዱትን ሬድ ሌበል ውስኪ ከመጎንጨት በቀር የሚሰሩት ግራ ገብቷቸዋል። 

ከጎንደር እና ጎጃም በእየሰዓቱ  የሚመጣው ዜና የኢህአዴግ/ህወሓት ወታደር የሆነ ሁሉ ጥቃት እየተፈፀመበት እንደሆነ ነው።ሰራዊቱ እራሱ ጎንደር ላይ ለመዝመት አንዳች ፍላጎት የለውም።ምክንያቱም ዘመቻው እራሱ ምክንያታዊ ሳይሆን በሕወሓት እብሪት የተፈጠረ እሳት መሆኑን ሰራዊቱ ይስማማበታል።ይህ ሁሉ ጉዳይ ያስጨነቀው ሕወሓት የሱዳኑን ፕሬዝዳንት ዛሬ አዲስ አበባ ድረስ ጠርቶ ማናገር ይዟል።የሱዳኑ ፕሬዝዳንት አልበሽር እራሳቸው አዲስ አበባን ሲረግጡ ከእዚህ በፊት ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ሲመጡ የሚያውቁት ሀገር አልሆነባቸውም።አሁን ለውጥ ለውጥ የሚል ሽታ እና የስርዓቱ ባለስልጣናት አቶ ኃይለማርያምን ጨምሮ የተደናገጠ ፊት ብቻ ነው የተመለከቱት።ጉብኝታቸው ሁሉ የውሸት ስለሆነባቸው የሚያደርጉት ውል ሁሉ የማይረጋ መሆኑን ስሜታቸው እንደነግራቸው ከፊታቸው ይነበባል። 

የኢትዮጵያ ዙርያ ያሉ መሬቶች በአረብ ሀገር ወታደሮች እየተከበቡ ነው።ከሱማሌ እስከ አሰብ ድረስ ጂቡቲን ጨምሮ ከእዚህ በፊት ሰራዊታቸውን ከሀገራቸው ውጭ አስፍረው የማያውቁ የአረብ ሀገሮች በሙሉ የኢትዮጵያን በሕወሓት ደካማ እና በዘር ላይ የተመለከተ መንግስት እጅ መውደቅ ተመልክተው  ዙርያችን ሰፍረዋል።የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ጉዳይ ተሞክሮ እዚህ ግባ የማይባል ልምድ በሌላቸው ግለሰብ እጅ በመውደቁ ሚንስትሩ  ዛሬ ለምክር ቤት ያለፈ የስድስት ወር ሪፖርት ሲያቀርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደረጃ መነገር የማይገባቸው ቃላት ሲጠቀሙ መመልከት የብስለት ብቻ ሳይሆን  የዓለም አቀፍ እውቀት እና ልምድ ማነስ ምን ያህል ኢትዮጵያን አፈር ድሜ እንዳስገባ ለመረዳት ቀላል ነው።

የህዝቡ የጉስቁልና ደረጃ በቀላሉ በማንኛውም የውጭ ኃይል የመማረክ መጥፎ እጣ ያሰጋዋል።

የምጣኔ ሃብቱ ድቀት የድሀውን እና የደሞዝተኛውን የመግዛት አቅም ከተጠበቀው በታች አውርዶታል።በመምህራን ደረጃ የመኖር እና አለመኖር ግብግብ ውስጥ ስለገቡ ሰልቫጅ ልብስ መንገድ ላይ በመሸጥ ከማስተማር ሙያቸው በተጨማሪ  የሚሰሩ መምህራን አዲስ አበባ ላይ መኖራቸው የእዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ሰምቷል። በእዚህ ወር የዋጋ ግሽበቱ መጨመሩን ሮይተርስ በለቀው ዘገባ አረጋግጧል።የዓለም ባንክ ከውሃ እና ፍሳሽ ጋር በተያያዘ በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ብድር መፍቀዱ ትናንት ቢሰማም ብድሩን ለማግኘት በእራሱ ብዙ ደረጃዎች አሉት።ስለሆነም ለአሁኑ የህወሓት የውጭ ምንዛሪ ጥማት ሊደርስለት አይችልም።የዓለም ባንክ ይህንን የሚያደርገው የቻይና እጅ በበለጠ እንዳይረዝም ከማሰብ ውጭ የብድር መመለስ አስተማማኝ ዋስትና ኖሮት አይደለም። 

እነኝህ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ኢትዮጵያን በደርግ ዘመን ከነበረችበት ደረጃ እና አሁን በሕወሓት ዘመንም  ካለንበት አስከፊ ደረጃ በባሰ ሁኔታ ሀገሪቱን ይዞ የሚወርድ አደገኛ ደረጃ ነው።ስለሆነም ምን መደረግ አለበት? ሙስናው የኢትዮጵያን ሀብት እየዘረፈ፣ባእዳን ጥርሳቸውን እያሳዩን ሀገራችንን ሲያጠፉ እንመልከት? ወይንስ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚጠበቅብንን  ለመስራት በቁርጠኝነት እንነሳ? ደግሞስ ማን ምን ይስራ? 

ኢትዮጵያን ለማዳን አሁን  ምን ያድርግ?

የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ምጣኔያዊ ሀብት እና ማኅበራዊ ሁኔታ ላለፉት 26 አመታት በኢህአዴግ/ሕወሓት እጅጉን ቆስሏል።ይህ ቁስል ለመጠገግ ቢያንስ ሁለት ዓመታት ይፈልጋል።ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከሕወሓት መውደቅ በኃላ ወድያው ጤናማ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ማሰብ በእራሱ ሞኝነት ነው።ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያን ለማዳን ደረጃ በደረጃ ምን ይደረግ?

1ኛ/ ከኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት፣ከኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ከስርዓቱ ጋር ያልተነካኩ እና የቆሸሸ ስም የሌለባቸው የሃይማኖት ተወካዮች፣ምሁራን፣ከበሬታ ከህዝብ ያገኙ ዜጎች ያቀፈ ጊዚያዊ የኢትዮጵያ መንግስት በቶሎ አዲስ አበባ ላይ መመስረት አለበት።ይህ ጊዜያዊ መንግስት ለሁለት አመታት የሚቆይ (ዓመቱ ግምት ነው። ሊያንስ ይችላል) መሪ የዜጎች የጋራ መርህ ያወጣል።

ይህ እንዴት ይችላል? ሕወሓት ስልጣን ይለቃል ወይ? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ የተረዱ የሰራዊቱ አባላት እና የህዝብ ንቅናቄ ሁሉ ሕወሃትን ማስገደድ አለባቸው።ይህ እንደሚሆን እራሳቸው ህወሐቶችም በሚገባ ያውቁታል።በማንኛውም ደረጃ የሚነሳ የስልጣን ነጠቃ እንደሚኖር ያውቃሉ።አሁን የቀረው መረረኝ ብሎ የቆረጠ የሰራዊቱ አባል እና ሕዝብ እራሱን ባጭር ጊዜ አደራጅቶ የመነሳቱ ጉዳይ ብቻ ነው።

2ኛ/ ይህ ጊዜያዊ የኢትዮጵያ መንግስት በቅድምያ የኢትዮጵያን ሰራዊት ከሁሉም የሀገሪቱ ግጭቶች ገለልተኛ የሆነ የሁሉ ጠባቂ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ስራዎችን ይሰራል።ምክንያቱም ግዝያዊ መንግስት ሲመሰረት በአንዳንድ ክልሎች አንዳንድ ግጭቶች ዕለቱን አይቆሙም።ለምሳሌ በሰሜን ጎንደር እና ትግራይ፣በኦሮሞ እና ሱማሌ መካከል ያሉት ግጭቶች እና መስል ግጭቶች ሕወሓት ወለድ እና ቀደም ብሎ የነበረ ታሪካዊ ሂደት ስላላቸው ሰራዊቱ የሁሉንም ችግር የሚያዳምጥ እና የሚጠብቅ በቅድምያ ግን የኢትዮጵያን አንድነት እና ድንበር ጥበቃ አስተማማኝነት ላይ ያተኩራል።

3ኛ/ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ስር ሆነው ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን ይመሰርታሉ።ለምሳሌ የሀኪሞች ባለሙያዎች፣የግብርና ሙያ ባለሙያዎች ወዘተ በእየሀገሩ ይደራጃሉ ወይንም የነበረ አደረጃጀታቸውን ያስመዘግባሉ። ሁሉም አደረጃጀቶች ጊዜያዊ የኢትዮጵያ መንግስት በሚያወጣው የዜጎች የጋራ መርህ ይመራሉ።

4ኛ/ ጊዚያዊ የኢትዮጵያ መንግስት ዋናው መንግስት መጣም አልመጣም ነፃ ከመሆን የሚያግዳቸው የማይኖረው የፍትህ አካላት እና የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ለሁሉም የቆመ መሆኑ ላይ አበክሮ ይሰራል።ነፃ የምርጫ ቦርድ የመመስረት፣ የፕሬስ ሕጉ ለሁሉም የሚሰራ መሆኑ ላይ እና የህዝቡ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሕይወት በሽግግር ጊዜው ወቅት እንዳይታወክ አበክሮ ይሰራል።ይህ ማለት በከፍተኛ ደረጃ እርስ በርስ መቃቃር ያቆሰለውን ሕዝብ በበጎ የእርስ በርስ ግንኙነቶች እንዲዳብር በሁሉም መስክ ይሰራል።

5ኛ/ ዚያዊ የኢትዮጵያ መንግስ ነፃ ምርጫ (እንደ እዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ) እንዲደረግ የምርጫ ቦርዱ በነፃ እንዲያስደርግ  ሙሉ እገዛ ያደርጋል። የፕሬዝዳንት ምርጫ እንደ ኢትዮጵያ ትልልቅ ብሔሮች ላሉባት እና ሌሎች በርካታ ውሁዳንም ለሚኖሩባት ሀገር  ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት፣ልምድ እና ስነ-ምግባር የተላበሰ  አቅም ያለው ፕሬዝዳንት ከየትኛውም ብሔር ቢመጣ እና በዙር ለሌላውም ሲደርሰው ላለፉት 26 አመታት የተዘራውን መርዝ ያረክሰዋል።

6ኛ/ የኢትዮጵያ ዋናው ምክር ቤት በነፃ ምርጫ ይመሰረታል፣የኢትዮጵያ መጪ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ፣ የውጭ ፖሊሲ እና የአጠቃላይ የልማት አቅጣጫ ይቀየሳል።በመካከለኛው ምስራቅ፣አፍሪካ እና ሌሎች አለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የሚገቡበት አግባብ ይቀየሳል፣በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ቅራኔዎች እንዳይኖሩ የይቅርታ እና የኢትዮጵያዊነት ቀን ይታወጃል። በሀገር ላይ ከፍተኛ በደል የፈፀሙ ግልፅ በሆነ መንገድ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያደርጋል።

7ኛ/ የኢትዮጵያውያን የጋራ ተቋማት ግንባታ ላይ ያተኮሩ ስራዎች፣የስራ ዕድል ፈጠራዎች፣የስነ-ጥበብ እና ኪነ-ጥበብ እድገት ላይ ያተኮሩ ስራዎች እና ኢትዮጵያን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚችሉ ስራዎች ወደ ተግባር ይቀየራሉ።

ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች የሕልም ወሬ ያህል የምንገምተው እንኖራለን።ሆኖም ግን አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ጠቃሚው እና እንደ ሀገር የመቀጠል እድላችንን የሚያጎላ ነው።የግድ ካልሆነ ከእንጦጦ ጀምሮ እስከ አራት ኪሎ ድረስ መንገዱ በመድፍ እየታረሰ መገባት ላይኖርበት ይችላል።በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሕዝብ፣ሰራዊቱ እና ተቃዋሚዎች ልብ ለልብ መገናኘት በቂ ነው።ከእዚህ ሲዘል ደግሞ የስርዓቱ አቀንቃኞች ይህ ለመቸውም ቢሆን ከስህተቱ የማይታረም ስርዓት ለማስወገድ እና ለልጆቻቸው የሚተርፍ የደስታ ዘመን ለማስተላለፍ ቁርጠኝነት የተላበሰ ውሳኔ ብቻ ነው የሚፈልገው።ውሳኔ ሕልምን እውን ያደርጋል።ኢትዮጵያን ለማዳን እንወስን ወስኑ !


ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)