ጉዳያችን ዜና /Gudayachn News
መጋቢት 25፣2009 ዓም (March 3,2017)
የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከአሜሪካው አቻቸው ጋር በዋይት ሃውስ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 25፣2009 ዓም ተገናኝተዋል።በቀይ ምንጣፍ ስነ-ስርዓት ሞቅ ያለ አቀባበል የጠበቃቸው የግብፁ ፕሬዝዳንት ፕሬዝዳንት ትራምፕን አግራሞት እና አድናቆት በተላበሰ እይታ ተመልክተዋቸዋል።በአፀፋውም ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአክብሮት ሰላምታ መለሱ።አልሲሲ ከአረብ ሀገሮች የመጀመርያው ለትራምፕ ስልክ ደውለው ደስታቸውን የገለጡ ሲሆኑ ትራምፕም መጀመርያ መልሰው ከደወሉላቸው የዓለም መሪዎች የግብፁ ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ነበር።
´´ያንን ነገር አብረን እናደርገዋለን! ሽብርተኝነትን እና ሌሎች ነገሮችን አብረን እንዋጋለን" ("we will do that thing together. We will fight terrorism and other things together") አሏቸው ትራምፕ የግብፁ አቻቸውን አተኩረው እየተመለከቱ። ትራምፕ "ያንን ነገር" ያሉት ፀረ ሽብር ዘመቻውን እንደሆነ ተገምቷል። "ሌሎቹ ነገሮች" ያሏቸው የትኞቹን ነገሮች እንደሆነ አላብራሩም።አልሲሲ በሃሳቡ ከተስማሙ በኃላ ትራምፕን "ልዩ ስብዕና የተላበሱ ሰው" በማለት አሞካሿቸው። ትራምፕ ፈገግ አሉ።ዓለም በሙሉ ትራምፕ የሚለውን ስም በሚወቅስበት ሰዓት ከግብፁ አቻቸው ይህንን ሙገሳ ማግኘት እልም ባለ በረሃ ላይ አንድ ብርጭቆ ቀዝቃዛ ውሃ የማግኘት ያህል ውድ ነበር ለትራምፕ። ትራምፕ ቀጠሉ "ለእረጅም ጊዜ ወዳጅ እንደሆንን እንቆያለን" "We will become friends for a long time," አሏቸው።አልሲሲ በፈገግታ መለሱላቸው።
የግብፅ ፕሬዝዳንት ዋይት ሃውስን ለመጨረሻ ጊዜ የጎበኘው እ.ኤ.አቆጣጠር በ2010 ዓም በፕሬዝዳንት ሁስኔ ሙባረክ ወቅት ነበር።በወቅቱ ኦባማ የግብፅን ጉዳይ በጣም ቀዳሚ እና አንገብጋቢ አጀንዳ አላደረጉትም ነበር።
ይህ በእንዲህ እያለ የግብፁ ፕሬዝዳንት ከትራምፕ ጋር ባደረጉት የዛሬ ንግግር ግብፅ ቀዳሚ ´የፀጥታ እና የደህንነቴ ስጋት´ ብላ የምትቆጥረው የውሃ ጉዳይ እና በኢትዮጵያ እየተሰራ ነው በተባለው የዓባይ ግድብ ዙርያ እንዲሁም በሕወሓት መንግስት ጉዳይ እና የደቡብ ሱዳን ሁኔታ ዙርያ ለትራምፕ ምንም ነገር ሹክ አላሉም ማለት አይቻልም።
ኢትዮጵያ በሕዝብ ተቀባይነት ያላቸው፣በእውቀት እና ችሎታ ላይ የተመሰረቱ ባለስልጣናት ቢኖራት ኖሮ በአካባቢው ላይ ተፅኖ የመፍጠር አቅሟ ባደገ እና በዛሬው የአልሲሲ ቦታ ላይ የኢትዮጵያ መሪ በክብር በተገኘ ነበር።ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ መልሳ አትነሳም ማለት አይደለም።በዘር ላይ የተመሰረተ መንግስት ፍፃሜውን ማፋጠን ማለት ኢትዮጵያን መልሶ ማንሳት ነው።ላለፉት 26 አመታት ሕወሓት ከመግደል እና ከማሰር እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን እንዲሰደዱ እና አንጡራ ሀብታቸው ለባዕዳን ከመሸጥ ያለፈ አንዳች ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም።ወደፊትም አይችልም።በቂም እና በመንደር ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ከአዲስ አበባ ዋይት ሃውስ ድረስ የሚደርስ ዓለም አቀፋዊ ተፅኖ የመፍጠር አቅም የለውም። ስለ አድዋ እና መቀሌ ብቻ የሚያስቡ መሪዎች ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅ ሀገር የማስተዳደር አቅምም ሆነ ችሎታ የላቸውም።ይልቁንም ኢትዮጵያን ለማንሳት ኢትዮጵያውያን ትልቅ ርእይ ይዘው መነሳት ካለባቸው ጊዜው አሁን ነው።የእራሳችንን ጉዳይ ሌሎች እንዲነጋገሩበት እና አጀንዳ እንዲያደርጉት ዕድል ልንሰጣቸው አይገባም።
የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በዋይት ሃውስ ከትራምፕ ጋር የሰጡት መግለጫ ከእዚህ በታች ባለው ቪድዮ ይመልከቱ። የግብፁ ፕሬዝዳንት እንግሊዝኛ ስለማይችሉ አይደለም በሀገራቸው ቋንቋ የሚናገሩት። ኢትዮጵያ ባለስልጣናቷ እስከ ደረግ ዘመን ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ሳይቀር የሚናገሩት በሀገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ነበር።
የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በዋይት ሃውስ ከትራምፕ ጋር የሰጡት መግለጫ ከእዚህ በታች ባለው ቪድዮ ይመልከቱ። የግብፁ ፕሬዝዳንት እንግሊዝኛ ስለማይችሉ አይደለም በሀገራቸው ቋንቋ የሚናገሩት። ኢትዮጵያ ባለስልጣናቷ እስከ ደረግ ዘመን ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ሳይቀር የሚናገሩት በሀገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ነበር።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com