ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, September 29, 2022

ኢትዮጵያ ፬ ቁልፍ ጉዳዮችን የቅድምያ ቅድምያ ካልሰጠች ያሰጋኛል።

 
==========
ጉዳያችን
=========

ዓለም እየገባችበት ስላለው ማጥ በሚገባ አልተነገረንም

ዓለማችን አሁን ያለችበት ሁኔታ የትኛውም ሚድያም ምሑርም ሆነ ተንታኝ በሚገባ እየነገሩን አይደለም።ምሑራዊ ብልግና፣ጋዜጠኛዊ አድርባይነት እና ተንታኛዊ አሽቃባጭነት በዝቷል። የምዕራቡ መገናኛዎች በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ከነበሩበት ወርደዋል።የዩንቨርስቲ ምሑራን ለሰው ልጅ እና ለትውልድ ቀጣይነት የሚያስቡ እና እውነቱን የሚያወጡ ሳይሆኑ የጥናት ጽሑፎቻቸው ሁሉ በአዋጪ የገንዘብ ጥቅም ላይ ተመስርተው ማሰብ አናውዟቸዋል። ስለሆነም ዓለም ወደ ከባዱ እና የማይቀረው ታላቅ ጦርነት ለመግባት ዳር ዳር እያለች ነው። የዩክሬኑ ጉዳይ ጧት እና ማታ ይነገራል እንጂ የግሪክ እና የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ጧት ማታ የሚያወሩት የቱርክ ድሮኖች የግሪክን ድንበር ጥሰው መግባታቸው፣ግሪክ ቱርክ ለወረራ እየተዘጋጀች እንደሆነ ነው። የሰርብና የክሮሽያ፣የአዘርባጃንና አርመን በየቀኑ ያሉ ውጥረቶች የት እንደደረሱ ገና አልሰማንም።መጪው የሚፈራው የባልካን አገሮች በተለይ ሰርብያ በሩስያ ድጋፍ የቀድሞ የዩጎዝላቭያ ግዛት ግጭት እንደ አዲስ ተወጥሯል።አውሮፓ እና ሩስያ የገቡበት የጋዝ እቀባ ሁሉ የዋናው ግጭት ዳር ዳርታ ናቸው።ይህ ሁሉ በያዝነው እና ባለፈው ሳምንት ያሉ እና እያደጉ የመጡ ውጥረቶች ናቸው እንጄ የቆዩ አይደለም።በዓለም ዜና ላይ ግን የሉም።

አገር መሆን ያቃታቸው እና እንደአገርነት አሉም እንዳል በዓለም መድረክ የማይታዩ መንግስታት ፈልገን ያላገኘንላቸው፣የሉም እንዳንል ለጊዜው የጦርነቱ ቋያ የበረደ የመሰለላቸው፣ውሏቸው እና አዳራቸውን የማናውቅላቸው ሊብያ፣ኢራቅ፣የመን፣ሶርያ እና ሱማሊያ የዓለም ''ፖሊስ'' አገሮች ባደረሱባቸው ግፍ ቂም አርግዘው ኖረው በደረሰበት ሲብከነከን ያደገው አዲስ ትውልድ ለአቅመ ትውልድ ደርሶ የደረሰበትን ከእነማን ጋር ተሰልፎ ምን እንደሚያደርግ ማወቅ አይቻልም።

ሩስያ ከዩክሬን ጦርነት የምዕራቡ የመረረ ምላሽ ተምራ መጪው ጊዜ ከኔቶ ጋር የሚኖራት ግጥምያ ከሚገባው በላይ እያሰበችበት እንደሆነ ግልጽ ነው። ቻይና በታይዋን ጉዳይ ብቻ አይደለም የምጣኔ ሃብት ጦርነቱ በንግድ ሥራ ብቻ ሳይሆን በጦር ሜዳ የበላይነትም እንደሚፈታ አልገባትም ማለት ጅልነት ነው።ኔቶም ሆነ የምዕራቡ ዓለም ምጣኔ ሃብቱ ብቻ ሳይሆን ሁሉም መንገዶች ወደ ጦርነት እየተጓዘ እንደሆነ ገብቶታል።ነገር ግን ሚድያዎቹ እውነቱን አፍረጥርጠው እንዲያወሩ አይፈቅድላቸውም።ከእዚህ ይልቅ ህዝቡን የንግስት ቀብር ወይንም ሌላ ጉዳዮች ካሉ በእዚያ ህዝቡን ወጥሮ ከጭንቀቱ ማስታገስ ነው የተመረጠው።  አሁን ያለው ዓለም ኃያላኑ በአንድ ጊዜ ወደ አጠቃላይ ጦርነት የሚገቡበት አይደለም።ነገር ግን በየቦታው ቀደም ብለው በለኮሷቸው ጦርነቶች እነርሱ ከጀርባ ሆነው ይዋጋሉ።በመቀጠል ወደ አጠቃላዩ ግጭት ይገባሉ።አንዳንዴ ማርክስ ''ኢምፔራሊዝም ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ሲደርስ የጥሬ ዕቃ እና የገበያ ሽምያው ዓለምን ወደ ጦርነት ይመራታል'' ያለውን ደግሞ ማየት ያስፈልግ ይሆን? ያስብላል። 

ኢትዮጵያ!

ኢትዮጵያ አሁን ያለውን የዓለም አካሄድ በደንም መረዳት ያለባት ጊዜ ነው።መሪዎቿም ሆኑ ህዝቧ እውነታውን ጥርት አድርገው ማወቅ አለባቸው።ዓለም ወደጦርነት የመግባቱ አደጋ ግልጽ ነው።ይህንን ሲኤንኤን በማየት አይገመትም። ምክንያቱም ሚድያዎቹ እንደዘመኑ 'የፊት ሜክአፕ' ብዙ ነገሮች ተቀባብተው ጓዳቸውን ሸሽገው ነው የሚቀርቡት።በሩስያ ላይ የተደረገው የእቀባ መጠን እና ስፋት ብቻ ሳይሆን አሁን ላለው የየትኛውም የዓለም ጦርነቶች የሚዳኛ አንድም አቅም ያለው ተቋም የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የለም።ይህ ብቻ አይደለም ጦርነቶች እንዳይደረጉ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የሰላም እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ከአርባ እና ሃምሳ ዓመታት እንደነበሩት ዓይነት የተራው ህዝብ ንቅናቄዎች የሉም።ስለሆነም በማንኛውም ሰዓት የሚሆነውን የምናየው ከሆነ በኋላ ነው።

ይህ የዓለም መጪው ሁኔታ እና ኢትዮጵያ በውስጧ ያለውን ችግሮች ለመፍታት፣የውጭው ማዕበል እንዳይመታት የውስጥ ሞገድ እንዳያናውጣት መንግስቷም ህዝቧም ተስማምተው መስራት የሚገቧቸው ፬ ቁልፍ ጉዳዮች አሉ።

፩/ የብቁ ዜጋ ስልጠና (የቀድሞው ብሔራዊ ውትድርና) መጀመር
 • ኢትዮጵያ የመቶ አስር ሚልዮን ሕዝብ ነች።አስፈሪነቷ በህዝቧ ቁጥር ብቻ አይደለም።የስድስት ወርም የውትድርና ስልጠና የወሰደ ወጣት መኖሩ ብቻ የኃይል ሚዛኗን በቀጠናውም በዓለምም የሚያስደምጣት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ውትድርና ወስዶ ቢያንስ ለስድስት ወራት የሰለጠነ ወጣት ሲኖራት ነው። የአገሮች የኃይል ሚዛን በበኛ ሰራዊቱ ብቻ አይለካም በሰለጠነው ወጣት እና ተጠባባቂ ኃይልም ጭምር ነው። ስለሆነም የሰለጠነ የሰው ኃይል በሰላም ጊዜ ብቁ ዜጋ ማፍርያ፣በቀውጢ ጊዜ ጉልበተኛ ማስታገሻ ነው። ኢትዮጵያውያን በቀድሞ ዘመን ልጁን ተኩስ እና ጉግስ ሳያስተምር የማያልፍባት ኢትዮጵያ ዛሬ በዘመናዊ መልክ ልጆቿን የብቁ ዜጋ ስልጠና መስጠት አለመጀመሯ አደጋ አለው።
 • ስልጠናው በግድ ከሚሆን ይልቅ በፈቃደኝነት የስልጠና ግዴታቸውን የተወጡ የተሻለ የሥራ እና የትምህር ዕድል እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን ልዩ የመጠርያ የክብር ተቀጥላ ስም መስጠቱ እና በሕብረተሰቡ ውስጥ ልዩ ክብር እንዲያገኙ በማድረግ እና ስሙን ጥሩ ያልሆነ ሥም ከተለጠፈበት ብሔራዊ ውትድርና ወደ የብቁ ዜጋ ስልጠና መቀየሩ የራሱ የሆነ በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
 • የብቁ ዜጋ ስልጠና ወይንም ብሔራዊ ውትድርና ግዴታ ያልሆነበት የአውሮፓ አገር ማን ነው? ኖርዌይ፣ስዊድን፣ጀርመን እና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ወጣቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ለወታደራዊ ስልጠና መግባት ቅድመ ሁኔታ ነው።ወደ ስልጠናው የገባ የዩንቨርስቲ መግብያ ነጥብ ብቻ ሳይሆን ሥራ ለማግኘት ቅድምያ አለው።
 • እነኝህ የአውሮፓ አገሮች አሁን ያላቸው ሰላም እያለ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላም ወጣቶቻቸውን የሚያሰለጥኑት ከውትድርና ክህሎቱ ጋር ስልጠናው በራሱ ብቁ የሆነ ዜጋ ማፍርያ እንደሆነ ስለሚያምኑበት ነው።
፪/ የሥራ ባሕል እንደ የባሕል አብዮት መጀመር አለበት።
 • ማንም እጅ እና እግር ያለው በቀን አንድ ሥራ ሳይሰራ የማይውልበት የባሕል አብዮት ያስፈልጋል።
 • ኢትዮጵያ ከጎረቤት የአፍሪካ አገሮች ጋርም ሲነጻጸር የከተሜው ወጣት የሥራ ባሕል መቀየር አለበት።
 • ትምሕርት ቤት፣የሃይማኖት ተቋማት፣ሚድያውና ወላጆች በልዩ መልኩ ሊመክሩበት ይገባል።
 • ሥራ ሲባል ከቤት ያለው የቤተሰቡ የቀን ከቀን ሥራዎች እስከ ማንኛውም ድረስ ለሥራ ያለው ክብር ብቻ ሳይሆን ባሕል መሆን አለበት። ይህ ደግሞ ከስነ ልቦና ዝግጅት እና ማነቃቃት ጀምሮ የሚሰራ ሥራ ነው።
 • አገር በወታደር አይወረርም የሥራ ባሕል እንዳይኖረው ጫት እና ሕልመኛ ብቻ እንዲሆን ግን ባዕዳኑም በረቀቀ መልኩ ሰርተውብናል፣እኛም ችላ ብለነዋል።ጉዳዩ ግን አገር ይሰራል፣አገር ያፈርሳል።
፫/ ቤተ ዕመንቶች ያለባቸው የአስተዳደር ብልሹነት እና ንቅዘት እጅግ በቶሎ መስተካከል አለበት 
 • ይህ ካልሆነ እንደ ኢትዮጵያ ላለ አማኝ ህዝብ ላላት አገር የብዙ ምጣኔ ሃብታዊ፣ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሁም የጸጥታው የተለየ መታወክ ሁሉ የቤተ ዕምነቱ ንቅዘት ውስጥ ተሸሽጓል።
 • ይህንን በቶሎ አለማድረግ ኪሳራው ቀላል አይደለም።አዲስ የሚመጣው ትውልድ ግዙፍ እና ስሜታዊ ግብግብ ከዕመነት ተቋማቱ ጋር ገብቶ ለማስተካከል ሊነሳ ይችላል።ይህ ደግሞ በራሱ ይዞ የሚመጣው ጥፋት አለ።
 • ስለሆነም ቀድሞ ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ 
፬/ የተረሳው የአነስተኛ እና ጥቃቅን ንግድ ማስፋፍያ ልዩ ድጋፍ 
 • ነስተኛ እና ጥቃቅን በምጣኔ ሃብት ኢመደበኛ ምጣኔ ሃብት የሚለው ይተካከለዋል።አነስተኛ እና ጥቃቅን የሚለውም አሉታዊ ዕሳቤ ጥሎ ስላለፈ ወደፊት ስሙ ተቀይሮ መቅረብ ሊያስፈልገው ይችላል።
 • የአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ዘርፍ የህወሃት/ኢሃዴግ መንግስት አበላሽቶት ከማለት ይልቅ አተረማምሶት ሄዷል።
 • ዘርፉ ግን ያደጉ አደጎችም ኢመደበኛ ዘርፍ በሚል በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሥራ ዕድል የፈጠረ ዘርፍ ነው።
 • በኢትዮጵያ ደግሞ በከፍተኛ ትምሕርት ገብቶ ከተማረው ውጭ ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠርያ ብቻ ሳይሆን በልምድ እና በሚሰራው አነስተኛ ንግድ ክህሎት ከፍተኛ ዕውቀት ያለው ህዝብ ያለበት ነው።ነገር ግን የካፒታል፣የሂሳብ አያያዝ፣የፈጠራ ክህሎት ማዳበርያ እና የመሬት ድጋፍ ከመንግስት እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ይፈልጋሉ።
 • የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ጉዳይ ሲነሳ የኢኮኖሚ አማካሪዎችም እየረሱት የመጡት እና ሚናውን ማሳየት የተዉት እንዲሁም መንግስት በዘርፉ ዙርያ አለመስራቱ የአገር ውድቀት መሆኑን የሚያሳይ የምጣኔ ሃብት አማካሪ ብዙም አይሰማም።
 • ህወሃት/ኢህአዴግ ዘርፉን የፖለቲካ መጠቀምያ ብቻ ሳይሆን ዘርፉ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያን አነስተኛ ንግድ ወደ መካከለኛ እና ከፍተኛ ደረጃ አሳደገው ወይ? ብለን ብንጠይቅ የሚጨበጥ ነገር የለም።ሁሉም ከፕሮፓጋንዳ ያላለፈ እንደ ሳሙና አረፋ ኩፍ ብሎ ታይቶ የጠፋ ጉዳይ ሆኗል።
 • አሁን መንግስት የተቸገሩትን በበዓል ሲደጉም በቴሌቭዥን ከሚያሳየው የበጎ አድራጎት ሥራ በተለየ ወጣቱን ከፖለቲካ ተጽዕኖ በተለየ እና ህወሃት/ኢህአዴግ ከሄደበት ስህተት የታረመ የአነስተኛ እና የጥቃቅን ንግዶች እና ማምረቻዎች እንዲስፋፉ ፖሊሲውን በሚገባ መከለስ እና የገንዘብ ተቋማትም ሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመጋጋቢ ሥራ እንዲሰሩ ማድረግ ያዋጣል።
 • የእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እና በአዲስ አበባ ከተማ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደመስራቱ የዘርፉ ወሳኝነትና የህወሃት/ኢሃዴግ ስህተት ምን እንደነበር የመረዳት ዕድሉ ገጥሞታል። በመሆኑም ዘርፉ ክብር ተሰጥቶት እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ዘርፉን እንዲደግፉ ቢመደቡ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅሙ  ከፍተኛ እንደሆነ ያምናል።ዘርፉ ከኢትዮጵያ ባሕል እና አኗኗር አንጻር የተለየ ጥናት ማድረግም የሚፈልግ ነው እንጂ የዓለም ባንክ ባለሙያዎች ባስቀመጡት አሰራር ብቻ መሔድ ለሁሉም በሽታ አንድ አይነት ኪኒን የመስጠት ያህል የቀደመው አካሄድ አያዋጣም።
 • በኢትዮጵያ የከተማ ከንቲባዎች ለተወሰኑ ምስኪኖች የሚበላ እና መጠለያ ሲሰጡ መታየታቸው በጎ እና ሊበረታታ የሚገባው ነው።ነገር ግን ከእዚሁ ጋር የአነስተኛ እና ጥቃቅን ንግድ ማስፋፍያ ሥራዎች አብዛኛውን ወጣት አቅፎ መንቀሳቀስ አለበት።
 • ዘርፉን ባለሃብቶች እንዲደግፉት ማድረግ እና ልዩ የሃገር ውስጥ ፈንድ ከተሞች እንዲሰበስቡ እና ለወጣቶች ሥራ ማስጀመርያ እንዲያግዙ ማድረግ ያስፈልጋል።
 • ዘርፉ ከፍተኛ ዕውቀት፣ልምድ እና አቅም ያለው የሰው ኃይል የሚመራው እንጂ እንደ ህወሃት/ኢሃዴግ በካድሬ መቀለጃ ሆኖ እንዲያልፍ ማድረግ አገርን ደግሞ መግደል ነው። 
ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱት ፬ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ በፍጥነት ካልሰራች የብዙ ችግሮቿ መተብተብያ ክር ለመፍታት እንዳትቸገር ያሰጋኛል።

================///===========  


No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...