ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, October 4, 2022

''መታዘዝ ከመስዋዕትነት ይበልጣል...እልከኝነትም ጣዖትን እንደማምለክ ነው። '' 1ኛ ሳሙኤል - 15፣22-23 በውጪ ሀገር በሚገኙ አንዳንድ የኢ/ኦ/ተ/አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ስለቅዱስ ሲኖዶስ አና ሊቃነ ጳጳሳት የተዛቡ መረጃዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚያሰራጩ መኖራቸው ምዕመናን የቅዱስ ሲኖዶስንም ሆነ የሊቃነ ጳጳሳት ማዕረገ-ክህነት ሳያውቁ እንዲደፋፈሩ እና ከህገ ቤተክርስቲያን እንዲወጡ እያደረጋቸው ነው።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ አጥብያ ቤተክርስቲያን ያለው መዋቅር

=================
በአዚህ ጽሑፍ ስር ከሚያገኙት ርዕሶች ውስጥ  - 
  • ቅዱስ ሲኖዶስ አንዴት ተጀመረ? ከቅዱስ ሲኖዶስ ውጪ የሆነች ቤተክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ትባላለች?
  • የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ የጀመሩ ከጌታችን እግር ስር የተማሩት ሐዋርያት ናቸው።
  • የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔያት ሃይማኖታችንን አፅንተዋል።
  • ቅዱስ ሲኖዶስ እግዚአብሔር ሃሣቡን ፈቃዱን ለልጆቹና ለቤተ ክርስቲያን የሚያስተላልፍበት መንፈሳዊ ጉባዔ ነው፡፡
  • ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ ምን ምን ይገኛሉ?
  • ቅዱስ ሲኖዶስ ይሳሳታል? ቢሳሳት የሚስተካከለው አንዴት ነው?
  • ሀገረ ስብከት ምንድነው?
  • የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ
  • ቃለ አዋዲ ምንድነው?
  • የቃለ ዓዋዲው ተቀዳሚ ዓላማ
  • ቃለ አዋዲውን ሙሉ ይዘት ለማንበብ የሚችሉበት ማስፈንጠርያ (ሊንክ) ያገኛሉ።


መግቢያ 

በውጭ ሀገር የሚገኙ አንዳንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የሥርዓት አካሄድ ለቅስፈት አንዳይዳርግ የሚያስፈራበት ሁኔታ ላይ ነን።አለማወቅን በመማር፣እልህን በትሕትና መለወጥ ከአገልጋይም ከምዕመናንም ይጠበቃል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ሰዎች አንደፈለጉ የደነገጉት አይደለም።የሚያጸድቅና የሚያስኮንን ነው።ሁሉም ሰው ሲወለድ ጀምሮ የቤተክርስቲያን መሰረታዊ ትምሕርቶች አብረውት አልተፈጠሩም።በአርግጥ ፀጋውን ያደላቸው ለተመረጡት ይህ ተደርጎ ይሆናል።የቀረው ምዕመን አና አገልጋይ ግን በቤተክርስቲያኒቱ የትምሕርት ሥርዓት ስር አልፎ ወይንም ከመምህራን ጉባዔ ተምሮ አልያም አንብቦ ትክክለኛውን የቤተክርስቲያንቱን ትምሕርት መማር ይችላል።ይህ ያለንበት የ21ኛው ክ/ዘመን ደግሞ ማንኛውንም ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የደቂቃዎች ጊዜ ቢፈልግ እንጂ ብዙ ውስብስብ አይደለም።ዋናው ቁምነገር ትክክለኛ ምንጩን ማወቅ ነው።

አሁን ባለንበት ዘመንም አንዳንድ አገልጋዮች ቀለል አድርገው የሚያቀርቡት ምዕመናንም ሳያውቁ ችላ ያሉት ጉዳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ሰማያዊ ክብር አና የሊቃነ ጳጳሳት ስልጣን ነው።ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ የሊቃነ ጳጳሳት ስልጣነ ክህነት ሰማያዊ እና እራሱ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስርቶ፣ከጌታችን የተማሩት ሃዋርያት ያስፋፉት እና ሊቃውንት ያመሰጠሩት ነው።

በቅዱስ ሲኖዶስ ላይ ከምዕነናን ወይንም አገልጋዮች የሚቀርብ ቅሬታ፣አቤቱታ፣ጥያቄ በየትኛውም መልክ መኖሩ በራሱ ችግር አይደለም።ያልገባውን መጠየቅ ኃጢአት አይደለም።አምላካችንም የመጠየቅ፣ባልገባን መልክ አቤቱታ ማቅረብ አልከለከለንም።በመፅሐፈ ዕዝራ ላይ አንደምናነበው ዕዝራ ከአግዚአብሔር ጋር አሞግታለሁ ብሎ ተነስቶ ነበር።አግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ስለሆነ የዕዝራ መጠየቅን ከኃጢአት አልቆተረበትም።ይልቁንም መልአኩ ቅዱስ ዑራእልን ልኮ ያሉትን ጥያቄዎች ሁሉ መለሰለት።ስለሆነም ጥያቄ መጠየቅ አምላካችንም አልከለከለም። ሕጉን አና ሥርዓቱን መጣስ ግን አልፈቀደልንም። ይህም የምንጎዳበት ስለሆነ አንጂ አርሱ ሊከብርበት አይደለም።

የዘመናችን አካሄድ ግን ከአዚህ አየተለየ ነው።ትውልዱ የቅዱስ ሲኖዶስን ክብር አና የሊቃነ ጳጳሳት ስልጣን ዝቅ አድርጎ ለማቅረብ የማይኬድበት መንገድ የለም።የታዘዙትን ካለመስራት አንስቶ አስከ የአውደ ምሕረት እና አንድ በአንድ ግንኙነት ላይ ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስን አና ጳጳሳትን አንዳንድ ነገሮች አየነቀሱ ትውልዱ አንዲጠላቸው የሚደረገው ድርጊት መልሶ ቤተክርስቲያንን አንደሚጎዳ በተለይ በውጭ ያሉ አብያተክርስቲያናት ሊገነዘቡት ይገባል።የፕሮቴስታንት እምነት ሲጀመር የካቶሊክን እምነት አባቶች የማስጠላት ትልቅ ዘመቻ ላይ ነበር።ይህ ተግባር ምእመኑ ላይ ያመጣው ውጤት ግን የካቶሊክ አባቶችን መጥላት ብቻ ሳይሆን ክርስትና የተባለ እምነትን በሙሉ የሚጠላ ትውልድ ዛሬ አንደምናየው ወልዶ ቁጭ አለ።የካቶሊክ አባቶች ብቻ ይጠላሉ ብሎ ዘመቻ የከፈተው የፕሮቴስታንት ዓለም ፕሮቴስታንትንም ማንንም የማያምን ኢ-አማኒ ትውልድ ፈጥሮ ሁሉንም ሜዳ ላይ አንሳፎ ዓለማችንን ወደ ጥፋት ይዞ ነጎደ።

ዛሬም በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት አባቶችም ሆኑ አገልጋዮች በምንም መልኩ ለምዕመናንም ሆነ ምዕመናን ለልጆቻቸው ቅዱስ ሲኖዶስ አና ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ነቁጥ ስነቅሱ መዋሉ ፅድቅ ሳይሆን ኩነኔ መሆኑም ማወቅ አለባቸው።አባቶቻችን አንደኛው የሰው ባሕሪ የተላበሱ ናቸው።የቤተክርስቲያን ስርዓት ሲጣስ ያሳለፉት ለቤተክርስቲያን ታዛዥ የነበረ ያለፈ ትውልድን በአኛ ደፋር አነጋገር ተተክቶ ሲመለከቱ ይበሳጫሉ፣ይቆጣሉ።ይህ የሰው ከአሳት ባሕሪ የመፈጠሩ ተፈጥሮ አንጂ አነርሱ ከአኛ የበለጠ ኃጢአተኞች ሆነው ከመሰለን ተሳስተናል።ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስም በቤተመቅደስ ሲሸጡ አና ሲለውጡ ተመልክቶ ጅራፍ አንስቶ ሰዎችን ገርፏል፣ንግዳቸውን አነ ሸቀጣቸውን ገልብጦታል።ይህ ግን የባህሪ አምላክነቱን ለሰው ልጅ ያለው ፍቅርን የሚቀንስ አይደለም።አባቶቻችንም አንዲሁ ናቸው።በአኛ ሲናደዱ ይቆጣሉ፣ነገር ግን በርህራኄ መልሰው ስለኛ ይፀልያሉ።ብዙዎች ምዕመናን ከአባቶች ጋር ቀርቦ የማወቅ ዕድል ስላላገኘን አሩቅ ለማየት አግዶናል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት።የቅዱስ ሲኖዶስ ስርዓትን፣የካህናት አና ጳጳሳት ስልጣናትን የተማረችው በቅድምያ ከጌታችን አና ከጌታችን ከተማሩት ከሐዋርያት ነው።ሊቀካህን እየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ልስጣነ ክህነት ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ አሁን ያለንበት ደረጃ ደርሷል።ይህንን ስልጣን ያከበረ ይከብራል።ያላከበረ ግን አይከብርም።

ከአዚህ በታች ስለቅዱስ ሲኖዶስ፣ሀገረ ስብከት ምንነት አና ተያያዥ ጉዳዮች መሰረታዊ ግንዛቤ በአንዳንድ የውጭ ሀገራት በሚገኙ ምዕመናን ዘንድ ባለመኖሩ ጉዳያችን ከልዩ ልዩ የቤተክርስቲያናችን የትምሕርት ገፆች ላይ ያገኘችውን ለማቅረብ ትሞክራለች።መረጃዎቹን በሚገባ አንብበን መጠቀም የአኛ ፈንታ ነው።ጽሑፎቹ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ከማኅበረ ቅዱሳን ገፆች አና አቡነጎርጎርዮስ ካልዕ ''የቤተክርስቲያን ታሪክ'' መፅሃፍ የተወሰዱ ናቸው። 

ቅዱስ ሲኖዶስ አንዴት ተጀመረ? 
ከቅዱስ ሲኖዶስ ውጪ የሆነች ቤተክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን ትባላለች?

ቅዱስ ሲኖዶስ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስለቤተክርስቲያን ዶግማ ቀኖና ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም አስተዳደር የሚመክሩበት በመንፈስ ቅዱስ የሚቃኝ ጉባዔ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ የበላይ መንፈስቅዱስ ነው።የሚመራውም መንፈስ ቅዱስ ነው።ይህም «ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ፓትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳትና ኤጲስ  ቆጶሳት የሚያደርጉት ዓቢይ ጉባዔ ነው፡፡» ተብሎ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የተገለፀው ነው፡፡ /ሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 2(2)/፡፡በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቻ አይደለም።በመላው ምሥራቃውያን አብያተክርስቲያናት ውስጥ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕይታ፣ቁጥጥር እና ትዕዛዝ ውጪ የሆነ ቤተክርስቲያን ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስቲያን አትባልም።ይህ ቤተክርስቲያናችን በክርስቶስ መስራችነት መመስረቷን፣በሃዋርያት ትምህርት መሰበኳና በሰማዕታት ደም መጽናቷ መገለጫ ነው።

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ የጀመሩ ከጌታችን እግር ስር የተማሩት ሐዋርያት ናቸው።

ሊቃውንት የቅዱስ ሲኖዶስን ሥርዓት አጀማመር ጌታ ከሐዋርያት ጋር ያደረጋቸው ስብሰባዎች መነሻ አድርገው ያመጣሉ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው የሚገኙ ሦስት ጉባዔያትን አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያው በይሁዳ ምትክ አንድ አባት መርጠው ሐዋርያ ለመሾም ያደረጉት ጉባዔ ነው፡፡/የሐዋ 1፥15-16/ ሁለተኛው ሰባቱን ዲያቆናት ለመሾም የተደረገው ጉባዔ (ሲኖዶስ) ነው፡፡ /የሐዋ 6.1-6/ የመጨረሻው ከአሕዛብና ከአይሁድ ወደ ክርስትና በመጡት መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተደረገው ነው፡፡/የሐዋ.15፥1/

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔያት ሃይማኖታችንን አፅንተዋል።

በጉባዔ ኬልቄዶን ምክንያት የሃይማኖት መከፋፈል ከመጀመሩ በፊት የአካባቢ ሲኖዶሶች እምብዛም የተለመዱ አልነበሩም፡፡ ዛሬ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሦስቱ ጉባዔት ብቸኞቹ ዓለም አቀፍ ጉባዔያት ናቸው፡፡ እርሱም በኒቅያ በ325 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ በ381 ዓ.ም እንዲሁም በኤፌሶን 431 ዓ.ም የተካሔዱት ናቸው፡፡

ከዚያ በኋላ ግን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በየራሣቸው መንበር የአካባቢ ሲኖዶስ ማድረግ ቀጥለዋል፡፡ እነሆ የእኛም ቤተ ክርስቲያን በራሷ ሲኖዶስ መመራት ከጀመረች ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ሆኗል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋነኛ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መገለጫ ነው፡፡ በየጊዜው በሚወለዱ ክስተቶች ዶግማዊ ቀኖናዋ ሥርዓቷ ትውፊቷ እንዲሁም አስተዳዳሯ እንዳይፈታ መጠበቂያ ነው፡፡ በዚህም በመሠረት እምነቷ ላይ ጥያቄ ሲነሳ ማብራሪያ መስጠት አዳዲስ አስተምህሮዎች ሲመጡ በዶግማዊ መሠረት ማረቅ ማቅናት የጾም የጾሎት ሥርዓትን መሥራት ልጆቿን የሚመሩ አበው ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋነኛ ተግባራት ናቸው፡፡

አስቀድመን እንደገለጽነው ክርስትና በማኅበር የሚኖርበት በማኅበር ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ይህ ማኅበር በአንዳች ምክንያት እንዳይበተን የአንድነት መገለጫው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

ምዕመናን ሁል ጊዜ ሊሰሙት የሚገባው የቤተ ክርስቲያን ድምጽ ይህ የአንድነቷ መገለጫ ከሆነው ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጣው ድምጽ መሆን አለበት፡፡ አንድ ክርስቲያን በአኗኗሩ ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሚደነግጋቸው ድንጋጌዎች ተገዢ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ አልተስማማኝም ይህ ጐረበጠኝ ብሎ በግልም በቡድንም መጓዝ ከሕይወት መንገድ ይለያል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ እግዚአብሔር ሃሣቡን ፈቃዱን ለልጆቹና ለቤተ ክርስቲያን የሚያስተላልፍበት መንፈሳዊ ጉባዔ ነው፡፡

ለእስራኤል ዘሥጋ ሥለ አንድነታቸው ስለአኗኗራቸው በነሊቀነብያት ሙሴ በኩል ሥርዓትን የሠራ እግዚአብሔር በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ክርስቲያኖች እስራኤል ዘነፍስም ሥለ አንድነታችን ማኅበራችን እንዴት በሥርዓት ልንኖርበት እንዲገባ ሥርዓቱን የሚሠራልን በብጹአን አበው አማካኝነት ነው፡፡ በዚህም ከመንጋው ተለይቶ ላለመቅበዝበዝ የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ መስማት ተገቢ ነው፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ 

ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠውን ሃይማኖት መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ሕግ ማውጣትና ማስፈጸም፣ ትልልቅ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን መመርመርና ዘመኑን በዋጀ ሥርዓት ትውልድን መምራት፣ በገዛ ደሙ በዋጃት የእግዚአብሔር በተክርስቲያን ጳጳሳት አድርጎ ለሾማቸው መንፈስ ቅዱስ በመታመን ለራሳቸውና ለመንጋው መጠንቀቅ ይጠቀሳሉ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ይሳሳታል? ቢሳሳት የሚስተካከለው አንዴት ነው?

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ ፍጹምና የማይሳሳት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሲኖዶስ ተሳሳተ ተብሎ ሌላ አቋራጭ መንገድ መከተል ደግሞ የበለጠ ለጥፋት የሚዳርግ ነው፡፡ ሲኖዶስ ቢሳሳት የሚስተካከለው በራሱ በሲኖዶሱ ሥርዓትና ደንብ ብቻ ነው፡፡ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መገዛት የማኅበረ ምዕመናን አባልነት በዚህ ምድር ያላችው የእግዚአብሔር መንግሥት ነዋሪነት መገለጫ ነው፡፡

ሀገረ ስብከት ምንድነው?

ሀገረ ስብከት ሀገረ ስብከት ቤተ ክህነቱን ወክሎ የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ ሃይማኖቱን እና ቀኖናውን ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ፣ ከክርስቶስ ጀምሮ የመጣውን ሀብተ ክህነት ለመጠበቅ እና ለማስተላለፍ፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ ገዳማት እና አድባራት እንዲረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተከሉ፣ ምእመናን ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መብት እንዲከበር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ወጥ እና ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን፣ የካህናት አስተዳደር እና አገልግሎት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት እንዲሆን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት እና ንብረት በሕግ እና በሥርዓት መሠረት እንዲጠበቅ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና እንዲሰጡ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ተግባሮቹ ናቸው፡

የሀገረ ስብከት ቅድመ ታሪክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ ምዕራፍ ስድስት፣ ዐንቀጽ ሠላሳ ስምንት እስከ አርባ አምስት ድረስ በተዘረዘረው መሠረት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መሠረት የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት መሥርቶ እና አጠናክሮ መሥራቱ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡

በእንግሊዝኛው «ዳዮሰስ» የሚለው ቃል dioikesis ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡  በመሆኑም ሀገረ ስብከት ማለት በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ አንድ አካባቢ ማለት ነው፡፡
ሀገረ ስብከት ለመጀመርያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችንን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተከፋፍለው ለማስተማር በወጡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ይመቻል፣ አይመችም ሳይሉ በተሠማሩበት ሀገረ ስብከት ገብተው አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል፣ ምእመናንን አስተምረው በማጥመቅ፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን በመሾም የወንጌልን ቃል ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሀገረ ስብከቱ፣ ዮሐንስ ወንጌላዊው በታናሽ እስያ ሀገረ ስብከቱ፣ ቶማስ በሕንድ ሀገረ ስብከቱ፣ማርቆስም በእስክንድርያ የሠሩት ሥራ ለዚህ ማስረጃችን ነው፡፡
በቃለ ዐዋዲው ዐንቀጽ አርባ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ እንደ ተገለጠው «የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያትና ለወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ነው»

ቃለ አዋዲ ምንድነው?

ቃለ ዓዋዲ ቀጥተኛ ትርጉሙ “የአዋጅ ነጋሪ ቃል” ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ብሎ የተነበየለት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ነበር፡፡ /ኢሳ.40፥1፵፥፩/ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዊ ልደት ስድስት ወራትን ቀድሞ የተወለደው ቅዱስ ዮሐንስ ጥርጊያውን እያስተካከለ ሰዎችን ለንስሐ እየጠራ ለአማናዊው በግዕ ለኢየሱስ ክርስቶስ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብም /ቃለ ዓዋዲ/ ሦስቱ ጾታ ምእመናንን/ ካህናት፣ ወንዶች እና ሴቶች/ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እየተመሩ ሕይወታቸውን እንዲጠብቁ ስለሚያውጅ ቃለ ዓዋዲ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ቃለ ዓዋዲ የተባለው መጽሐፍ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን አስተዳደራዊ መዋቅር ያካተተ የሕግ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰን ከምእመናን ጀምሮ እስከ ካህናት ድረስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መብትና ግዴታ በውሉ የሚያስገነዝብ መመሪያም ነው፡፡

ቃለ ዓዋዲ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበት የሕግ መጽሐፍ ነው ሲባል፤ ቃለ ዓዋዲ ከመኖሩ በፊት ቤተ ክርስቲያን በምን ትተዳደር ነበር? የሚል ጥያቄ ያስነሣ ይሆናል፡፡ ይህንን ጥያቄ የምንመልሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ለረዥም ዘመን በሓላፊነት አገልግለው በሞተ ሥጋ የተለዩንን የአባ አበራ በቀለን የአንድ ወቅት ቃለ ምልልስ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አባ አበራ በቀለ እንዳሉት “ቃለ ዓዋዲ ከመፈጠሩ በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ትመራበት የነበረ አስተዳደራዊ መዋቅር አላት ከኒቂያ ጉባኤ በፊትም ቢሆን የአስተዳደር ሥርዓት ነበራት፡፡ ከሁሉ በፊት ግን እንደ ሕግ ሆኖ የሚመራት ዋናው የሕግጋት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ እርሱም የሃይማኖትና የሥነ ምግባርን ሕግ የያዘ ነው፡፡ በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ዘመን አባቶቻችን በዚህ ሲገለገሉ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይመሰክራል ወደ ሀገራችንም ስንመጣ ፍትሐ ነገሥቱ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ መንግሥት ከአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ ንግሥ ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ድረስ አንድነት ነበራቸው፡፡ ቤተ መንግሥት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ይገባ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ወደ መንግሥት አስተዳደር ትገባ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ፍትሐ ነገሥቱ በሁለቱም ወገኖች ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በዓፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ አዳዲስ ሕጎች ሲወጡ ፍትሐ ብሔሩና ወንጀለኛ መቅጫው ሲወጣ የፍትሐ ነገሥቱ አሠራር እየቀዘቀዘ በአዲስ እየተተካ ሄደ፡፡ እንደሚታወቀው ፍትሐ ነገሥት ሁለት ክፍል አለው እርሱም፡-

  • ፍትሕ መንፈሳዊና
  • ፍትሕ ሥጋዊ በመባል ይታወቃል፡፡

ፍትሕ መንፈሳዊ አሁንም በቤተ ክርስቲያን ተጠብቆ እየተሠራበት ነው፡፡ የሥጋዊ አስተዳደሩ ደግሞ በቤተ መንግሥት በኩል በሌላ አዋጅ ተተክቷል፡፡

በዓለመ መላእክት፣ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት፣ መላእክትና ሰዎች እግዚአብሔርን ያመልኩበት የነበረ ሥርዓት አለ፡፡ በዘመነ አበው፣ በዘመነ መሳፍንት፣ በዘመነ ነገሥት፣ በዘመነ ነቢያትና በዘመነ ሐዲስም ይህ ሥርዓት የጸና ነው፡፡ የሥርዓት አስፈላጊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ የተቀመጠ በመሆኑ አሁንም ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ለማኅበረ ምእመናን ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለ ሥርዓት፣ ያለ ሕግ፣ ያለ ደንብ፣ ያለ መዋቅር የምትሠራው ምንም ዓይነት አገልግሎትና ድርጊት የለም፡፡ ሊቀ ጉባኤ እንዳሉት የሕግ ሁሉ ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ በፍትሕ መንፈሳዊና በፍትሕ ሥጋዊ ተጣምሮ አገልግሎቱን ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ፍትሕ ሥጋዊ ወደ መንግሥት አስተዳደር ተጠቃልሏል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ራሷን ችላ የምትመራበት ሕግ እንዲጸድቅላት በጠየቀችው መሠረት ከምእመናን ምጣኔ ሀብታዊ ጋር በተገናዘበ መልኩ ሁሉንም የሚያሳትፍ መዋቅር በሁለተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና የመጀመሪያው ቃለ ዓዋዲ ጥቅምት 14/፲፬ ቀን 1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ታተመ፡፡ ቃለ ዓዋዲው ከመውጣቱ በፊት ረቂቁ  ለፓርላማ ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ለምእመናን እንዲደርስ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ በነጋሪት ጋዜጣ መልክ ወጣ፡፡ ይህ ቃለ ዓዋዲ ከ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም እስከ 1970/፲፱፻፸ ዓ.ም ለአምስት ዓመታት ያህል እንዳገለገለ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ አያይዘው ገልጠዋል፡፡

የቃለ ዓዋዲው ተቀዳሚ ዓላማ

ሀ. ቅድስት፣ ከሁሉ በላይ ሐዋርያዊትና አንዲት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ሓላፊነት የሚወጡት ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ድረስ የሚገኙት የሥራ ሓላፊዎች ናቸው፡፡

ለ. የካህናት የኑሮ ደረጃ የተሻለ ሆኖ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በትጋት እንዲወጡ ማድረግ፡፡

ሐ. የምእመናን ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እንዲጨምር እና ያሉትንም በምግባር በሃይማኖት ማጽናት፤ በመንፈሳዊ ዕውቀት እንዲበለጽጉ ማገዝ፤ ሁኔታዎችንም ማመቻቸት፡፡

መ. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲሻሻል የገቢ ምንጮችና ልማቶች ተበራክተው በገንዘብ አቅም የጎለበተች ቤተ ክርስቲያን ሆና ከተረጂነት እንድትላቀቅ ማድረግ ነው፡፡

እነዚህን ዓላማዎች ግቡ አድርጎ የተመሠረተው ቃለ ዓዋዲ አፈጻጸሙ እንዲሳካ ከምእመናን ጀምሮ ሥልጣነ ክህነት እስካላቸው አገልጋዮች ድረስ የሠመረ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ምእመናን ስለ ቃለ ዓዋዲ ያላቸው ግንዛቤ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዞ ምቹ መሆን የካህናት ድርሻ ብቻ የተሟላ አያደርገውም፡፡ የምእመናንም ድርሻ ከፍተኛውን ድርሻ መያዝ አለበት፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ለተወሰኑ አካላት ብቻ የማንተወው በመሆኑ የእነሱና የእነሱ ሓላፊነት ብቻ እንደሆነ ማሰብ የለብንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሦስቱም ጾታ ምእመናን ናትና ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

ቃለ ዓዋዲ ተደንግጎ ጸድቆ ሰበካ ጉባኤ ተቋቁሞ በሥራ ላይ ውሎ አሁን ካለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ በ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶችን በመጥራት የመጀመሪያውን የቃለ ዓዋዲ ረቂቅ ለውይይት አቅርበዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በሸዋ ሀገረ ስብከት በዐሥራ አንድ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ስለ ቃለ ዓዋዲ ለካህናትና ለምእመናን ማብራሪያ በመስጠት አዲሱን እቅድ አስተዋውቀዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ልኡካንን መድበው በየአህጉረ ስብከት እየተዘዋወሩ እንዲያስተምሩ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሆኖም ካህናቱና ምእመናኑ ተወካዮችን መርጠው ሰበካ ጉባኤና ቃለ ዓዋዲ የሚባል በባህላችን የማይታወቅ አዲስ አሠራር መጣብን ብለው ለንጉሠ ነገሥቱ /ኀይለ ሥላሴ/ አቤቱታ እስከማቅረብ ደርሰው ነበር፡፡

ይህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ተሻግሮ በአገልግሎት ላይ የሚገኘው ቃለ ዓዋዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ከወጣበት ከ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ጀምሮ ለ5/፭ ዓመታት አገልግሎ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም የተለያዩ ማሻሻያዎች ታክለውበት ለሁለተኛ ጊዜ ታትሟል ከ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም እስከ 1991/፲፱፻፺፩ ዓ.ም መግቢያ ድረስ ለሃያ አንድ ዓመታት ያገለገለው ቃለ ዓዋዲ ዳግመኛ ተሻሽሎ ለሦስተኛ ጊዜ በ1991/፲፱፻፺፩ ዓ.ም ታትሟል፡፡

ሙሉውን ቃለ ዓዋዲን ለማንበብ ይህንን ሊንክ ይጫኑ።

ባጠቃላይ የቤተክርስትያናችንን ሥርዓት ሰማያዊ አንደሆነ ጠንቅቀን አንወቅ።አለማወቅ ከጥፋተኝነት አያድንም።አውቆ መጠቀም ደግሞ የሁላችንም ፈንታ ነው።ከእዚህ ውጪ ቅዱስ ሲኖዶስ ላይም ሆነ ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ለአንድ የሰፈር አዛውንት የሚሰጠውን ክብር ያህል መስጠት የተሳነው መልሶ መላልሶ የክርስትናው መሰረትን መመልከት ተገቢ ነው።አንዳንዶቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ላይ የሚዘመተው የማጥላላት ዘመቻ ተራ አለማወቅ አድርገን የምንመለከትበት ጉዳይ አደገኛ ነው።ከቅዱስ ሲኖዶስ የመነጠል ሂደት ግቡ ኦርቶዶክሳዊ ያልሆነች ቤተክርስቲያን የመቆርቆር አደገኛ አካሄድ ነው።በቅዱስ ሲኖዶስ ላይም ሆነ ከሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን በአክብሮት እና በታረመ አንደበት መጠየቅ እና ከአባቶች የሚነገረውንም በአንክሮ ማዳመጥ ተገቢ ነው። አንደበትን ከክፉ እና ከማይገባ ንግግር እርስ በርስ ስንነጋገርም ጭምር መጠበቅ እንደሚገባ መጽሓፍ ቅዱስ ያስተምረናል።

በያዕቆብ መልዕክት ምዕ 3፣5 እስከ 6 እንዲህ ይላል፡ 

''እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል።

አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል።''

=======================////=============


ከአዚህ በላይ ያሉት ጽሑፎች የተገኙት 


1/ ከአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ገጽ =  ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ-ገፅ 


2/ ከማኅበረ ቅዱሳን ድረገፆች ውስጥ


https://eotcmk.org/a/%E1%89%83%E1%88%88-%E1%8B%93%E1%8B%8B%E1%8B%B2-2/ 


3/ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርቲያን ቃለ ዓዋዲ 


https://static1.squarespace.com/static/5759a0b362cd94a47d9c6242/t/5c7d55cbe4966b9aba164a99/1551717869215/EOTC+-+%E1%89%83%E1%88%88+%E1%8B%93%E1%8B%8B%E1%8B%B2+%282009+Et.+Cal+Or+2017+Eur.+Cal%29.pdf 



No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...