ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, October 16, 2022

ወቅቱ በውጪም ሆነ በሃገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን የባዕዳን መግቢያ ቀዳዳዎችን መድፈን ላይ ማትኮር የሚገባቸው ወሳኝ ጊዜ ነው።


=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

ኢትዮጵያን ለመበተን የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዘው የተነሱባት ጠላቶቿ ዛሬም ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ የዘለቀ ዕቅዳቸውን ለማሳካት እየሮጡ ነው። ኢትዮጵያውያን የሚዘናጉበት ጊዜ አይደለም። እያንዳንዱን ክስተቶች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ዘለቄታዊ አደጋዎችን በደንብ የመረዳት አቅም ከሚድያዎች ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ ያስፈልጋል። ስለሆነም ወቅታዊ ሁኔታዎችን በሚገባ መትሮ የመረዳት አቅምን በተለይ ለአዲሱ ትውልድ ማስታጠቅ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያን እየወጉ ያሉት ባዕዳኑም ናቸው

በትግራይ ከሽብርተኛው ህወሃት ጋር የተደረገው ጦርነት ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተደረገ ጦርነትም ጭምር ነው።ግብጽ ለህወሃት ከሁለት ሚልዮን ዶላር ከመስጠቷ በላይ የጦር መሳርያዎች እና ሌሎች የሎጀስቲክ ድጋፎች ማድረጓ በቅርቡ የወጣው አዲስ መረጃ አመልክቷል።ከእዚህ በተጨማሪ በየሁለት ሳምንቱ ግማሽ ሚልዮን ዶላር ለህወሃት ሽብርተኞች እየተከፈለ እንደሆነ ነው መረጃው የሚያመለክተው።ከእዚህ በተጨማሪ አድሏዊ በሆነ የፕሮፓጋንዳ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንዲሁም የሳተላይት መረጃዎች የሚሰጡ አንዳንድ የምዕራብ ሃገሮችን ጨምሮ ጥቅማችንን ያስከብራል ለሚሉት ለህወሃት የውክልና ጦርነት ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ ተወርውረውም የኢትዮጵያ ህዝብ ባሳየው ቁርጠኝነት፣የመከላከያ እና የጥምር ኃይሉ ተጋድሎ ህወሃት ከባዕዳን ጋር ገጥሞ በኢትዮጵያ ላይ የቃጣውን ወረራ በሚገባ ተቀልብሷል። በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ህዝብ ከህወሃ ነጻ ለመውጣት ዋዜማው ላይ ይገኛል።ይህ ማለት ግን ሥራዎች ሁሉ አብቅተዋል ማለት አይደለም።የኢትዮጵያውያን (በውጪም ሆነ በውስጥ ያሉ) ከመቼውም ጊዜ በላይ ለኢትዮጵያ የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው።

ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለው ከሽብርተኛው ህወሃት እና ሸኔ ጋር ብቻ አይደለም።እነርሱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ወይንም ለማዳከም እንዲረዱ ከመደገፍ ባለፈ ዋና ዓላማው የኢትዮጵያን አንጡራ ሃብት ለባዕዳን የሚያስረክብ ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የተመቸ መንግስት አራትኪሎ ላይ ማቆም ነው።በአፍሪካ የምሥራቅ አፍሪካን መሪዎች ጨምሮ በቀጥታ ለአንዳንድ የምዕራብ ሃገሮች የሃገራቸውንም ሆነ የጎረቤቶቻቸውን የማዕድን ሃብት ለባዕዳን ኩባንያዎች በማቀበል የስልጣን ዘመናቸውን የሚያራዝሙ ናቸው።ለእዚህም የኮንጎ የሰላም እጦት አንድ መነሻ ይሄው መሆኑን መጥቀሱ እና ለሰላሟ መጥፋት እና ማዕድኗን እያዘረፉ ለባዕዳን አንዳንድ የምዕራብ ኩባንያዎች በማቀበል የሩዋንዳ እና የዩጋንዳ መንግስታት ይታማሉ።የሽብርተኛው ህወሃትን ለመደገፍ ተፍ ተፍ ሲሉ የነበሩ አንዳንድ የአፍሪካ መንግስታት ታይተው የነበሩት መንግስታቱ ሲመሰረቱም የአፍሪካን አንጡራ ሃብት በማስመዝበር ብቻ የስልጣን ዘመናቸው ስለሚራዘም ነው።ኢትዮጵያ ከእዚህ ሁሉ ጋር ነው አሁን ገጥማ የምትገኘው። ሽብርተኛው ህወሃትም ኢትዮጵያን ለመሸጥ የሚሮጥበት ደረጃ በእዚህ ያህል የከፋ መሆኑን ማወቅ እና ከጀርባው ያለው የቀጥታ እና የእጅአዙር ቅኝ አገዛዝን ማስፈን ይህ ካልሆነ ግን ሃገሩ ተበትኖ ባዕዳን በቀጥታ የሚገቡበትን መንገድ ማሰላሰል ነው የተያዘው። 

የውስጥ አጀንዳ ፈልፋዮች

የኢትዮጵያን ጉዞ ለማደናቀፍ እና ከውስጥ ለመቦርቦር በአገር ላይ ከሚሸረበው ተንኮል አንዱ አጀንዳ ፈጥሮ ህዝብን ከመንግስት ጋር ማጣላት ነው።በእዚህ ሂደት ደግሞ ከሽብርተኛው ህወሃት ጀምሮ መተዳደርያቸው የጎሳ ግጭት እንዳይበርድ የሚፈልጉት እና በኦፌኮ እና ሸኔ ስር ያሉ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር እንደሚሰሩ ከድርጊታቸው እና ከአጀንዳዎቻቸ ሁሉ ለመረዳት ቀላል ነው። ይህ ብቻ አይደለም በአማራው ማኅበረሰብ ስም ከሚነግዱት የዩቱበር ተዳዳሪዎች እስክ ሌሎች የማኅበራዊ ሚድያ አቀንቃኞች ሁሉ ኢትዮጵያውያንን የሚከፋፍሉ አጀንዳዎች ለመፍጠር እና ለማሰራጨት ከሚሞክሩት ውስጥ ናቸው።በመሆኑም የውስጥ አጀንዳ እየፈጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል የሚፈልጉትንም ሆነ የባዕዳንን ጣልቃ ገብነት ለመቋቋም ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሊሰሯቸው የሚገቡ ሥራዎች አሉ።

ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች አሁንም መስራት ያሉባቸው ወቅታዊ ሥራዎች ውስጥ 

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በቀጣይ ከባዕዳን የሚሰነዘሩትን ማናቸውም የፕሮፓጋንዳ እና የተጽኖ መፍጠር ሙከራዎችን እና የግጭት አጀንዳ ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎችን ለማክሸፍ ዛሬም ወገባቸውን ጠበቅ ማድረግ ሊሰሯቸው ከሚገቡት ሥራዎች ውስጥ -

  • በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዲፕሎማሲ ዘመቻውን መቀጠል።በተለይ የአሜሪካ የምክርቤት ምርጫ ከመድረሱ አኳያ ኢትዮጵያውያን ተጽዕኖ የሚፈጥሩበትን መንገድ እንደገና ማንቀሳቀስ፣ተከታታይ ሰልፎች በማድረግ በውጭ የሚኖረው ቀረጥ ከፋይ ህዝብ የራሳቸው መንግስት የሚሰራው የተሳሳተ የውጭ ፖሊሲ ማሳወቅ።

  • አዲስ አጀንዳዎች በኢትዮጵያ ጠላቶች ሲፈጠሩ አጀንዳዎቹን በሚገባ ሳይረዱ ከስሜታዊነት መራቅ እና ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ባገናዘበ መልክ መረዳት፣ከአጀንዳዎቹ ጀርባ ያሉትን የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍላጎት መረዳት።

  • በርካታ የዜና ዩቱቦች እየተከፈቱ ነው።ከእነኝህ ዩቱቦች ውስጥ ህወሃትን የሚነቅፉ ዜናዎች የሚያቀርቡ ግን በመሃል ድብቅ የህወሃት አጀንዳ የሚይራምዱ ዜናዎችን አልፎ አልፎ የሚለቁትን በጥንቃቄ መመልከት። አንዳንዶቹ በቀጥታ በባዕዳን መንግስታት የደህንነት ቢሮዎች የሚተዳደሩ እና በተሻለ የአቀራረብ ጥራት እና የአማርኛ ዜና አነባበብ ሁሉ የሚለቀቁ ስለሆኑ፣በሂደት ሥራዎቻቸውን በማጤን መከታተል እንደሚያስፈልግ መረዳት።

  • በትዊተር የኢትዮጵያን ጥቅም የሚቃረኑ ጽሑፎችን መቃወም እና እውነታውን ለዓለም የሚያሳዩ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ መጻፍ መቀጠል ከኢትዮጵያውያን የሚጠበቅበት ጊዜ ነው።
===========///==========

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።