ጉዳያችን ምጥን
==========
በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ሽብርተኛው ህወሃት በኢትዮጵያውያን ላይ ግፍ ያደረሰም ሆነ ኢትዮጵዊነቱን ሙሉ በሙል ክዶ ከባዕዳን ጋር ከባዕዳን በላይ ሆኖ ኢትዮጵያን የሸጠ አንድም ኢትዮጵያዊ ኃይል በታሪካችን አልገጠመንም። ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሃብት አሟጦ ከግል የውጭ የመንደር ባንኮች ሳይቀር ኢትዮጵያን አስይዞ መበደር ደረጃ የደረሰ እና የተበደረውንም እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፍሰት አጥኚ ከ11 ቢልዮን ዶላር በላይ ከኢትዮጵያ ያሸሸ የኢትዮጵያ ጠላት ነው።
ሽብርተኛው ህወሃት በትግራይ የትኛውም ቦታ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይሰቀል አድርጎ በራሱ እራፊ ቀይሮ ትግራይን ለባዕዳን አስማምቶ የትግራይ መንግስት እያለ እራሱን የሚጠራ ወንጀለኛ ቡድን ነው።ስለ ቡድኑ ብዙ ተብሏል።እዚህ ላይ ማንሳት የተፈለገው ግን አንድ ጊዜ በአፍሪካ ህብረት አልዳኝም ካለ በኋላ መልሶ ደግሞ በባዕዳኑ ምክር ተመርቶ ከፌድራል መንግስት ጋር እነጋገራለሁል በማለት ትናንት መግለጫ ልኳል።
'አሁን መንግስት በ ''ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ'' ዓይነት ንግግር ከሽብርተኛው ህወሃት ጋር ካደረገ ሃገር ከመሸጥ ጋር እኩል ሥራ ከመስራት ጋር አንድ ነው።አሁን ህወሃትን የትግራይ ህዝብ ደገፈው አልደገፈው ስሌት ውስጥ የሚገባበት ጊዜ አይደለም።በሽብርተኛው ህወሃት በር ከፋችነት ባዕዳን ከሚገባው በላይ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እየፈተፈቱ ነው።ይህ ብሔራዊ አደጋ ነው።ማንም ሃገር የማይፈቅዳቸው እና ማንም መንግስት በግዛቱ ውስጥ እንዲሆን ማየት አይደለም መስማት የማይፈልጋቸው ጉዳዮች በሽብርተኛው ህወሃት በኩል በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረጉ ነው።እነርሱም
1/ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን አውርዶ በራሱ እራፊ የሚንቀሳቀስ ክልል በትግራይ ተፈጥሯል።
2/ በራሱ ክልል ውስጥ የራሱን ታጣቂ ይዞ የሚንቀሳቀስ ኃይል በትግራይ ተፈጥሯል።
3/ እራሱን እንደ አንድ መንግስት የሚጠራ ክልል በትግራይ ተፈጥሯል።
እነኝህ ሦስት ጉዳዮች እጅግ አደገኛ ብቻ ሳይሆኑ ማንም መንግስት በሚገዛው ክልል ውስጥ የሚፈቅደው አይደልም።ኢትዮጵያ መንግስት ጠንክሮ እነኝህን ጉዳዮች አንስቶ እና ሳይስተካከሉ ድርድር የሚባል ነገር እንደሌለ በግልጽ ለኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ለውጭ የህወሃት አጫፋሪ መንግስታት ማስታወቅ አለበት። ይህንን የኢትዮጵያ መንግስት በማድረጉ ደግሞ ማንም መንግስት በስውር እንጂ በግልጽ ዲፕሎማሲ ሊቃወም አይችልም።አሜሪካንም በምታወራው እና በምታወጣቸው መግለጫዎች ደጋግማ ያለችው ጉዳይ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት እንደምታከብር ነው።በመሆኑም ቢያንስ በግልጹ ዲፕሎማሲ እንዲህ ዓይነት አቋም ካንጸባረቀች የኢትዮጵያ መንግስትም የጠነከረ አቋም ለመያዝ የሚያግደው ምን ጉዳይ አለ?
ከእዚህ በኋላ ከህወሃት ጋር ለንግግር እቀመጣለሁ የሚል መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት መሰረታዊ የአገር ምሰሶዎች የሚገዘግዝ ሥራ ከመስራት ያነሰ አይደለም።ኢትዮጵያን አላውቅም ካለ ሽፍታ ጋር ድርድር አይሰራም።ከእዚህ በተሻለ የትግራይን ክልል አስተዳድራለሁ የሚል አዲስ አደረጃጀት ካለ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ባከበረ እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ከመንግስት ጋር የሚደራደር አዲስ ቡድን ማገዝ እና የትግራይን ህዝብ ከመርዳት መለስ ከህወሃት ጋር የሚደረግ ማናቸውም ድርድር ኢትዮጵያን የማፍረስ የዳርዳርታው ጅማሮ ነው። ጆሮ ያለው ይስማ! ''ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ'' ዓይነት ንግግር ከሽብርተኛው ህወሃት ጋር ማድረግ ሃገር ከመሸጥ እኩል ነው።አሁን ህወሃትን የትግራይ ህዝብ ደገፈው አልደገፈው ስሌት ውስጥ የሚገባበት ጊዜ አይደለም።ህወሃትን ትጥቅ የማስፈታት ጥብቅ አቋም ከመንግስት ያስፈልጋል!
No comments:
Post a Comment