=========
ጉዳያችን ምጥን
=========
ጌታቸው ረዳ በትግርኛ ማምሻውን መግለጫ ሰጥቷል። ጋዜጠኞቹ ይችን ምሽት ጌታቸው አጠገብ መቀመጥ እንዳስጨነቃቸው ከጠያቂዎቹ መርበትበት ለመረዳት የስነ ልቦና ጠቢብ መሆን አይጠይቅም። ቢጨነቁም ምክንያት አላቸው። የህወሃት ባለስልጣናት ባሉበት ሁሉ እያነፈነፈች ድንገት የምትመጣው ድሮን በእዚህ ምሽት አትመጣም ብለው እንዴት አይፈሩም? ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ወደ ጌታቸው የተደበቀበት ኮንቴይነር የተላኩት ጋዜጠኞች አንተ ሂድ አንተ ሂድ ሳይባባሉ አይቀሩም። ጌታቸውም ተጨንቋል።ራሱን ሳይበላው የግራ እጅ ጣቶቹን ወደ ጸጉሩ ጋር ይልክና መልሶ ያወርደዋል።
ወጣት ጋዜጠኞቹ መጀመርያ መግለጫ አለ ሲባል ህወሃት አዲስ ነገር ይናገራል።ህዝቡን አላስፈጅም ስልጣኔን እለቃለሁ። የትግራይ ህዝብ እራሱ በመረጠው ይተዳደር ይላል ብለው ጠብቀው ነበር።ጋዜጠኞቹ ወጣቶች ናቸው።ለእነርሱ የናፈቃቸው መከላከያ መቀሌ ገብቶ መብራት መጥቶ ወላጆቻቸው በሰላም እንጀራ ጋግረው እፎይ ብለው ማየት ነው። ወጣቶቹ የናፈቃቸው መከላከያ መቀሌ ገብቶ የመቀሌ ጎዳናዎች በታክሲ እና መኪና ተጣበው ከጓደኞቻቸው ጋር ሳባ ካፌ ቁጭ ብለው መሳቅ ነበር። ጌታቸው ግን ምንም አዲስ ነገር አልነገራቸውም። ያንኑ ኢሳያስ፣ አቢይ፣ እያለ ያደርቃቸው ያዘ። ፊታቸው ከመቼውም ጊዜ በባሰ ተስፋ ቆረጠ። አንዷ ጋዜጠኛ የጌታቸውን ፊት መመልከት ስላስጠላት የሚጻፍ ሳይኖር አቅርቅራ የሆነ ነገር መሞነጫጨር ላይ ብቻ አተኮረች።ወንዶቹ ጋዜጠኞች ዛሬ ህወሃት አዲስ ነገር ይናገራል ህዝቡን ከእልቂት ያድናል ብለው ሲጠብቁ ጌታቸው በእርዳታ እህል የተብለጨለጨ ፊቱን እያሳየ አደረቃቸው።በተለይ በቃለመጠይቁ መሃል ላይ የነበረው ሳል የድሮን ጥቃት እየመሰለው ጌታቸውም ሆነ ጋዜጠኞቹ ሲደነግጡ ቃለ መጠይቁ ላይ ይታይ ነበር።
ጌታቸው በዛሬው የትግሪኛ ቃለ መጠይቁ የኢሳያስ ጦር በሙሉ አቅሙ ወሮናል፣የትግራይን ህዝብ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ነው ወረራው ካለ በኋላ ህወሃት ለሰላም እየሰራ ነው በማለት የትግራይን ህዝብ ለመደለል ሞክሯል። ጌታቸው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ለወራት ከምንዋጋ አስር ዓመት ብንደራደር ይሻላል ያለውን። ሦስት ሳምንት ከምንዋጋ ሦስት ወር ብንደራደር ይሻላል። በማለት አሁንም የትግራይን ህዝብ ለማታለል ሞክሯል።
ጌታቸው በዛሬው መግለጫ ምንም አዲስ ነገር የለውም።ከእዚህ ይልቅ የቃለ መጠይቁ ምክንያት ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ የተሻለ ነው። ከቃለ መጠይቁ የምንረዳው ሽንፈቱ ከእዚህ በፊት ከሚያውቀው ሽንፈት እጅግ ስልታዊ እና ከመቀሌ ወጥቶ ደደቢት ለመግባት የማያስሽል። የኢትዮጵያ መከላከያ የአሁኑ አመጣጥ ህወሃቶች ቀድመው የሚገቡበትን ዋሻ በመያዝ ወደ መቀሌ የሚያመራ መሆኑ ነው።ከእዚህ በላይ የትግራይ ህዝብ እንደተነሳባቸው ብቻ ሳይሆን አሁን የሚያሳምኑበት ቃል እንዳለቀ ነው። ድሮም እናንተ በአፋር እና በወሎ በኩል ጦርነት የከፈታችሁ ለትግራይ ህዝብ ብላችሁ ሳይሆን የተወሰደባችሁን ፎቅ ለማስመለስ ነው እንጂ ለህዝብ አይደለም የሚለው ድምጽ በመላዋ ትግራይ እያስተጋባ ነው።ስለሆነም የጣረ ሞት የጌታቸው መግለጫ በትግሪኛ የሆነ ነገር ማለት ስላለበት ማይክራፎኑ ፊት ተሰየመ።ከእዚህ መግለጫ በፊት ጌታቸውም ሆነ የጠየቁት ጋዜጠኞች ዛሬ ቀን በኢቲቪ የታዩት እና ለመከላከያ እጃቸውን የሰጡት ምናልባትም ጋዜጠኞቹ በሰፈራቸው የሚያውቋቸው ልጆች ሁሉ ተማርከው አይተው ወደ ቃለ መጠይቁ መጥተው ይሆናል። ጌታቸው ግን አሁንም ያንኑ ዘፈን ይዘፍናል ብለው አልጠበቁም።ቢያንስ በእዚህ ጊዜ ህዝቡን ለማዳን አንድ ነገር ይለናል ብለው ጠብቀው ነበር። ያው ''የሞኝ ዘፈን ሁሌ አበባዬ '' እንደሚባለው ጌታቸው ያንኑ ኢሳያስ፣ ዐቢይ የሚለውን ዘፈን ዘፍኖ አሰናበታቸው። የትግራይ ህዝብ ህወሃትን አሁንም ዛሬም ተነስቶ በቃህ ካላለው ህወሃት ለስልጣኑ ህዝቡን ይዞ ወደ የበለጠ እልቂት እንደሚወስደው ዛሬ ላይም ያልተረዳ ይኖር ይሆን? ጥያቄ ነው።
==============
No comments:
Post a Comment