ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, January 21, 2019

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአውሮፓ አህጉረ ስብከት ከስኖዶሳዊ አንድነት በፊት የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ ነው።(ጉዳያችን ዜና)

  • ለረጅም ጊዜ የቆየው  የጣልያን ሀገረ ስብከት ችግር አዲስ በተሾሙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሕርያቆስ ብርቱ ጥረት በቅርቡ ተፈትቷል፣
  • የግሪክ ጉዳይ እልባት ለማግኘት ሂደት ላይ ነው፣
  • በጀርመን ያሉ አብያተ ክርስትያናትም የአንድነት ሀገረ ስብከት አዋቅረዋል።
በአቡነ ሕርያቆስ የደቡባዊ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የተመራው ስብሰባ ሮም፣ኢጣልያ ሲካሄድ 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጡን ተከትሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች የረጅም ጊዜ ፀሎት  እና በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ብርቱ ክትትል እና ጥረት ለሃያ ሰባት ዓመታት  የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ አንድነት ከከፈለ በኃላ በቅርቡ ሲኖዶሳዊ አንድነቱ ተፈጥሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ አንድነቷን ለማስጠበቅ መቻሏ ይታወቃል።

በእዚሁም መሰረት ከስኖዶሳዊ አንድነቱ በኃላ የመጀመርያውና በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጳጳሳት ጉባኤ የተደረገበት የሲኖዶስ ጉባኤ ባለፈው ጥቅምት ወር 2011 ዓም አዲስ አበባ ቤተ ክህነት መደረጉ ይታወሳል።የሲኖዶስ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ስለሚደረግ ቀጣዩ ስብሰባ በመጪው ግንቦት ወር (ለርክበ ካህናት) እንደሚደረግ ይታወቃል።
በአቡነ ሕርያቆስ የተመራው  ከሮሙ ጉባኤ ተሳታፊ አባቶች በከፊል 

የጥቅምቱ የሲኖዶስ ጉባኤ ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አህጉረ ስብከት ድልድል ሲሆን በእዚህም መሰረት ለአውሮፓ ደቡባዊ ክፍል ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የኦስሎ፣ኖርዌይ መካነ ቅዱሳን ወአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የኖርዲክ ሀገሮች እና ሰሜን አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የጀርመን እና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የእንግሊዝ ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በመሆን መመደባቸው ይታወሳል።

የደቡባዊ አውሮፓ ማለትም ኢጣልያ፣ፈረንሳይ፣ግሪክ፣ቱርክና ቤልጅየም  ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሕርያቆስ በአጭር ጊዜ ከሁሉም ሀገረ ስብከት ካህናት እና ምእመናን ጋር በአካል እና በስልክ በመገናኘት ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ለዓመታት የቆየ ችግር የነበረባቸው የኢጣልያ እና የግሪክ ሀገረ ስብከት ችግሮችን ለመፍታት በአካል በመገኘት ቀናት የፈጀ ውይይት እና የቆዩ ቁርሾዎችን ለመፍታት ባደረጉት ጥረት በኢጣልያ የነበረው ችግር ካህናቱን በመሸምገል እና ሀገረ ስብከቱ ለዓመታት የነበረበትን መዋቅራዊ አሰራር ወደ አንድ እና ወጥ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ ችለዋል። 

በእዚህም መሰረት ጥር 3 እና 4/2011 ዓም ሮም ላይ ከኢጣልያ፣ፈረንሳይ፣ግሪክ፣ቱርክና ቤልጅየም በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመጡ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች የሀገረ ስብከቱን ጠቅላላ ሰባካ ጉባዔ ስብሰባ የተደረገ ሲሆን በስብሰባው ላይ በበርካታ የሀገረ ስብከት አገልግሎት ሂደት እና አሰራር ላይ ከመነጋገሩም በላይ የአስተዳደር ጉባኤ መርጧል፣የክፍለ አህጉረ ስብከቱን መዋጮ መጀመር ላይ ወስኗል እንዲሁም የ2011 ዓም የአገልግሎት ትኩረት አቅጣጫ ላይ ለመወሰን ችሏል። ቀደም ብሎ በኢጣልያ ለረጅም ጊዜ የቆየ እና ምዕመናንን  በከፍተኛ ሁኔታ ሲያውክ የነበረው በሁለት አጥብያዎች መካከል የነበረው አለመግባባት በአቡነ ሕርያቆስ አባታዊ ምክር እና ልመናም ጭምር ጉዳዩ በይቅርታ መፈታቱ ምዕመናንን ያስደሰተ ተግባር ሆኖ አልፏል።

ቀደም ብሎ በታህሳስ /2011 ዓም እንዲሁ በግሪክ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን የጎበኙት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ እና የስካንድንቭያ እና ሰሜን አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ በአቴንስ ከተማ የሚገኙ አጥብያ ቤተክርስቲያናት ያሉባቸው ችግሮች ዙርያ ከተወያዩ እና አባታዊ ምክር፣ግሳፄ እና ትምህርት ከሰጡ በኃላ፣እዚያው የሚፈቱትን ጉዳዮች ውሳኔ ከሰጡባቸው በኃላ  ሲኖዶሳዊ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮችን ወደዝያው እንደተመሩ ከምዕመናን የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።በግሪክም ሆነ በኢጣልያ ብፁዓን አባቶች የቤተ ክርስቲያንን ችግር ለመፍታት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሁሉ የኢትዮጵያ ቆንስላ እና ኤምባሲ ኢትዮጵያን እንደመወከላቸው እና ቆንስላ እና አምባሳደሯ  አባቶችን ከመቀበል እና ችግሩን እንዲፈታ በማገዝ በኩል በጎ ተግባር እየፈፀሙ እንደሆነ መሰማቱ ሌላው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የሆኑት አሻራዎች ላይ ሁሉ አለኝታነቱን የማሳየቱ ጅማሮ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።

በተመሳሳይ መንገድ በብፅዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የሚመራው የጀርመን እና አካባቢው ሀገረ ስብከት የምሥረታ ጠቅላላ ጉባኤውን በፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ማካሄዱን ለማወቅ ተችሏል። ይህ ጀርመንን፣ ስዊዘርላንድን፣ ኦስትሪያን እና ሆላንድን የሚያጠቃልለው ሀገረ ስብከት በቁጥር ከ 30 በላይ የሚሆኑ አጥቢያዎችን የሚያስተዳድር ሲሆን ለዚህ ጉባኤ ከአብዛኛዎቹ አጥቢያዎች የመጡ የአድባራት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የሰበካ ጉባኤ፣ የካህናት እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች በአጠቃላይ ከ 90 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል። 
በጀርመን ሀገረ ስብከት ጉባኤው በአቡነ ድዮናስዮስ እየተመራ ሲካሄድ።

ባጠቃላይ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ከስኖዶሳዊ አንድነት ወዲህ ሁለት ቦታ የነበሩትን ሀገረ ስብከቶች በአንድ በማካተት እና አስተዳደራዊ አካል እንደገና በአንድነት በማዋቀሩ ሥራ ላይ አመርቂ ሥራ እየተሰራ ነው።በአስተዳደራዊ አንድነት ሂደት ላይ ከመዋቅር በዘለለ ተግባራዊ አንድነት እና ምዕመናንን በአንድነት የማገለገል ተግባር ከእዚህ በፊት ክፍተት የሚያሳዩ ደንቦችን በማሻሻል እና በማረቅ ለበለጠ አገልግሎት መትጋት አሁንም ከሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ይጠበቃል። ዛሬ ዓለም በተለይ አውሮፓ ከእምነት በራቀ አሳዛኝ ሕይወት ውስጥ ይገኛል።የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ተስፋ የጠፋበት አህጉር እንዴት ልትደርሰው ትችላለች?እነቅዱስ ጳውሎስ አውሮፓን የሰበኩት እንደዛሬው ኢንተርኔት ሳይኖር በእግራቸው እየሄዱ ነበር።ዛሬም ቤተ ክርስቲያን መንገዷ ረጅም መሆኑን ከአሁኑ ማወቅ አለባት።ለእዚህም በርካታ ውስጣዊ ስራዎች ይጠበቁባታል።የመጀመርያው ተግባር ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሙስና በፀዳ መልክ የሰው፣የገንዘብ እና የንብረት ሐብቷን በቶሎ ማደራጀት ነው። ጊዜ የለም።



ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments: