ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, January 11, 2019

የህወሓት የጎሳ ጥብቆና የጠባብነት ቀለበት ወራሾች

ጉዳያችን / Gudayachn
ጥር 3/2011 ዓም (ጃንዋሪ 11/2019 ዓም)



ኢትዮጵያን ትልቅ ሀገር ለማድረግ ከህወሓት በፊት የነበሩት መሪዎች የራሳቸውን አሻራ እያስቀመጡ ሄደዋል። ለኢትዮጵያ ጥብቆ ያሰፋ እና የጠበበ ቀለበት ውስጥ ያስገባት ህወሓት ለመሆኑ ክርክር የሚያነሳ የለም።ዛሬ ላይ ቆመን ልናነሳ የሚገባን ጥያቄ የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ህወሓት በሰፋለት ጥብቆ እና ቀለበት ውስጥ ነች ወይንስ አይደለችም? የሚለው ነው።


ህወሓት ለኢትዮጵያ ያሰፋው ጥብቆ እና ቀለበት

ታሕሳስ 7/1953 ዓም  መንግስቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ የመሩት የመፈንቅለ መንግስት እንቅስቃሴ ላይ እኩለ ቀን ሲሆን በኢትዮጵያ ራድዮ ሲታወጅ እንዲህ የሚል ቃል ተነበበ።
''...አሁን በቅርብ ጊዜ ነፃ የወጡት የአፍሪካ አገሮች ከቀን ወደ ቀን በኢኮኖሚ፣በትምህርትና በኑሮ መሻሻል ፈጣን እድገት አድርገው ኢትዮጵያን አልፈዋት ሄደዋል።'' ካለ በኃላ የራድዮ መልዕክቱ ሲደመድም '' የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ አንድነትህ ከብረት የጠነከረ ይሁን! የዛሬዋ ዕለት ለኢትዮጵያ አዲስ ጎህ መቅደዱን ለመላው ዓለም የምታበስር ናት!'' ይላል።

ይህ የራድዮ መልዕክት በኢትዮጵያ ራድዮ ከተላለፈ ሃምሳ ስምንት ዓመታት አለፉ።ጥያቄው ግን አሁንም አለ።ለነፃነታቸው የቆምንላቸው የአፍሪካ ሀገሮች በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት የወደቁበት ደረጃ ቢለያይም ቢያንስ በነፍስወከፍ ገቢ ትተውን የሄዱት የአፍሪካ ሀገሮች ቁጥር ቀላል አይደለም።በድህነት እና ኃላ ቀርነት ሀገራችን የኖረችበት ዋናው ምክንያት የፖለቲካው ጉዳይ አለመስተካከል መሆኑ የታወቀ ነው።ኢትዮጵያ ግን በብዙ ውጣ ውረድ አልፋም ቢሆን በሀገርነት ኖራ እዚህ ደርሳለች።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በቀደሙ ዘመናት ከገጠማት ፈተና ሁሉ የከፋው በህወሓት የተሰፋላት የጎሳ ጥብቆ እና የጠባብነት  ቀለበት ውስጥ ሀገሪቱ የገባችበት መከራ ነው።ጥብቆው ስለ ጎሳህ ብቻ እንድትዘምር እና በጠበበ ቀለበት ውስጥ እየኖርክ ሰለ ትልቅ ኢትዮጵያ እንዳታስብ የሚከለክል እኩይ መመርያ አለው።

ይህ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲገባበት የተሰፋለት የጎሳ ጥብቆ እና  የጠባብነት ቀለበት አሁን ባለው የኢትዮጵያ የለውጥ ፖለቲካ ላይም የራሱን ጥላ አጥልቷል። ለውጡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ አቶ ለማ እና አቶ አንዳርጋቸው ቡድን እውን ሲሆን በመጀመርያ ግብግብ የገጠመው ህወሓት ለኢትዮጵያ ያሰፋውን የጎሳ ጥብቆ እና የጠባብነት  ቀለበት የመስበር እንቅስቃሴ ላይ ነው። ይህንኑ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መጋቢት 24/2010 ዓም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር ሲረከቡ ባደረጉት ንግግር ጥብቆው እና ቀለበቱ ላይ ያነጣጠረ ሰፊዋን ኢትዮጵያ ደግሞ በመደመር የስሌት ቀመር  ህወሓት ለኢትዮጵያ ያሰፋውን የጎሳ ጥብቆ እና  የጠባብነት ቀለበት በአደባባይ እርቃኑን አስቀሩት።

ከመጋቢት 24/20110 ዓም የጠቅላይ ሚኒስትር  ዓብይ ንግግር በኃላ ሚልዮኖች ኢትዮጵያውያንን ከጎናቸው አሰለፈ።ከገጠር እስከ ከተማ ሕዝብ ደስታውን የገለጠበት ነጥብ የህወሓት የጭቆና ሰንሰለት መበጠሱ ብቻ አይደለም።የህወሓት የጎሳ ጥብቆና የጠባብነት ቀለበት መበጠሱ ነው ከሁሉም በላይ ህዝብን ያስደሰተው።እውነታው ይህ ነው።ሆኖም ግን የጎሳ ጥብቆውና የጠባብነት ቀለበት በቀላሉ የማይነቀል የሃያ ሰባት ዓመት ትክል መሆኑን ያወቁት የለውጥ ኃይሉ መሪዎች ጥብቆውን እና ቀለበቱን በአንድ ጊዜ ከመቅደድ እና ከመስበር ይልቅ በሂደት በማስተማር እና እራሳቸውን  በአንድ ጊዜ ጥብቆውን አውልቀው ከመቅደድ የታቀቡበት ምክንያት መሬት ላይ ያለውን የጥብቆ እና የቀለበት ትክል በሂደት ለመንቀል ነው።

የጥብቆው እና የቀለበቱ ወራሾች የለውጡ ረባሾች

የህወሓት የጎሳ ጥብቆ እና የጠባብነት ቀለበት ለውጡ ከመጣ በኃላም ሊጠፋ ያልቻለበት ዋናው ምክንያት የህወሓት ወራሾች የጎሳ ጥብቆውን እና  የጠባብነት ቀለበቱን ይዘው ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ መንገድ እየመሯት ነው።ጥብቆውና ቀለበቱ የሕዝብ ፍላጎት አይደለም። ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትም ሆነ ባሳለፍናቸው ጥቂት የለውጥ ወራት ውስጥ ሁሉ የጎሳ ጥብቆው እና የጠባብነት ቀለበቱ ኢትዮጵያን እንደሀገር ከማቆርቆዝ ባለፈ የብዙ ዜጎች ሕይወት በጥብቆው እና ቀለበቱ አፍቃሪዎች  እረግፏል። አስገራሚው ጉዳይ የጎሳ ጥብቆውና የጠባብነቱ ቀለበትን ከህወሓት የወረሱት ቡድኖች በዓማራ፣በኦሮሞ፣በትግራይ እና በሌሎች ስም እየማሉና እየተገዘቱ እንዲሁም ለመንደራቸው ዘብ የቆሙ መሆናቸውን በማወጅ የህወሓት ውላጆች መሆናቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ።በኢትዮጵያ ውስጥ አንዳች ችግር ሲፈጠር የእነርሱን መንደር ካልነካ ላይጮሁ፣ የመንደራቸው ልጅ ከተነካ ግን  የጎሳ ጥብቆ እና የጠባብነት ቀለበታቸውን ይዘው በመውጣት ፍጅት ያውጃሉ።

ጥብቆውን የቀደደ እና ቀለበቱን የሰበረ ዋንጫውን ይወስዳል

የኢትዮጵያ ሕዝብ በህወሓት የጎጥ ጥብቆ እና የጠባብነት ቀለበት ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ቡድኖች ላይ የሚነሳበት ቀን እሩቅ አይደለም።አንዳንዶች ይህ ውሸት ይመስላቸዋል።ጉዳዩ ግን የጊዜ ጉዳይ ነው።እስካሁንም ያልተነሳበት ስለ ሁለት ምክንያት ነው።አንዱ፣ የሲቪክ ድርጅቶች እና አክትቪስቶች ኢትዮጵያዊነትን በሚገባ አለማንቀሳቀሳቸው እና ብሔራዊ ፀረ የጎሳ ጥብቆ እና የጠባብነት ቀለበት ንቅናቄ ባለመደረጉ ሲሆን ሁለተኛው ህወሓት የዘራው የእርስ በርስ የጎሳ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ከህወሓት ባላነሰ መልክ ውላጅ ወራሾቹ የዘሩት ዘር ነው።

በመጪዋ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ አረፋ ኩፍ ያሉቱ የጎሳ ጥብቆ እና የጠባብነት  ቀለበት አራማጆች ቦታቸው እየጠበበ እንደሚመጣ ለመረዳት ብዙ ምርምር አይጠይቅም።የጥብቆው እና የጠባብነት ቀለበት አራማጆች ትግራይ የሚኖረውን ሕዝብ ዓማራ ጠላትህ ነው፣ኦሮሞ ደመኛህ ነው ይሉታል፣ዓማራው ውስጥ ያሉት የጎሳ ጥብቆው እና የጠባብነት ቀለበት ወራሾች ዓማራ ታራራውን እና ወንዙን ሳይቀር ዓማራ የሚል ቀለም እንቀባው ቀረሽ ቅራኔ እየፈጠሩ ሕዝቡን  የማገት ያህል ሌላ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዳይኖረው ቢያስብም እንደማይፈቀድለት ለመንገር ሲዳዳቸው ይታያሉ። በኦሮምያም ያሉት የጥብቆው ወራሾች ከስደት የመጡት የፖለቲካ ድርጅቶቻቸው የጥብቆው እና የጠባብነት ቀለበቱን ይዘው በሕዝቡ ላይ ለመንዛት እየተንገታገቱ ነው።ይህ ሁሉ የጎጥ እና የጠባብነት ወራሽ ደግሞ የለውጥ ሂደቱን ለማወክ በጎሳቸው ስም እየተገዘቱ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመዘወር የሚያደርጉት ከንቱ ሙከራ ሁሉ በሕዝብ ንቅናቄ ፈፅሞ እንደሚከሽፍ ፈፅሞ አያንጠራጥርም።

መጪዋ ኢትዮጵያ  ህወሓት የሰፋላትን የጎጥ ጥብቆ ቀዳዳ ትጥላለች።የጠባብነት ቀለበት ሰብራ ትጥላለች።የህወሓት የጎሳ ጥብቆ ለብሰው ኢትዮጵያን  በመንደራቸው ልክ ለማጣበቅ የሚፈልጉ እና በጠባብ ቀለበት ውስጥ ለማስገባት እና ኢትዮጵያን ወደየማያባራ የእርስ በርስ ግጭት ለመምራት የተዘጋጁ ኃይሎች በቀጥታ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የሚፋጠጡበት ወቅት ደርሷል። የጎሳውን ጥብቆ ተርትሮ እና የጠባብነት ቀለበቱን ሰብሮ በኢትዮጵያዊ ሰገነት ላይ የቆመ ደግሞ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የክብር ዋንጫውን ይቀበላል።ይህ ማለት የጥብቆው እና የጠበብነት ቀለበት ወራሾች መንገጫገጭ አይፈጥሩም ማለት አይደለም።መንገጫገጩ የህዝብ ሕይወት ይቀጥፋል።ሲሆን ጥብቆውና እና ቀለበቱን ጥለው ወደ ሰፊው ሃገራዊ ሜዳ ቢመጡ የበለጠ ባማረ ነበር።የጥቅም፣የስልጣን እና የመተዳደርያ ጉዳይ ከሆነ ግን ጥብቆውን እና ቀለበቱን እንደያዙ ሕዝብ ይደርስባቸዋል።

ለማጠቃለል ጥብቆውን መቅደድ እና ቀለበቱን መስበር የወቅቱ ጥያቄ ነው።የለውጡ ሐዋርያዎችም በድፍረት የመቅደዱን እና የመስበሩን ተግባር በዓላማ ደረጃ እንዳስቀመጡ ሁሉ ተግባሩን መጀመር ግን አለባቸው።የጎሳ ጥብቆ እና የጠባብነት ቀለበት ኢትዮጵያን እንደ ግመል ሽንት ወደኃላ የሚጎትታት ክፉ የዘመን ነቀርሳ ነው።ሰሆነም ሰዎቹን ትተን ሀሳባቸው ካልመከነ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ነች።ምንም አይነት ስም ቢሰጠው፣ ሃያ ሰባት ዓመት የተተከለ የጎሳ ጥብቆ እና የጠባብነት ቀለበት የህወሓት ስሪት መርዝ ነው።ኢትዮጵያ ትቀጥላለች።ጥብቆውን የሚቀድላት፣ ቀለበቱን የሚሰብርላትን እየጠበቀች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ፣አቶ ለማ እና አቶ አንዳርጋቸው እና የለውጡ ኃይል በአንድነት ጥብቆውን የማውለቅ እና ቀለበቱን የመስበር ሥራ በይፋ ጀምሯል።የጥብቆው እና የቀለበቱ ወራሾች ግን በተቃዋሚ ስም ከህወሓት ያልተናነሰ የጎሳ ፖለቲካ እና የጠባብነት ቀለበታቸውን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በአዲስ መልክ ለመጫን የሚሞክሩ ሁሉ ሀሳባቸው መና ካልሆነ አሁንም አደጋ ላይ ነን።የለውጡ ኃይል ጥብቆውን መቅደድ፣ቀለበቱን መስበር ኢትዮጵያዊነትን ማንገስ መሆኑን በግልጥ በጅማሮው አሳይቶናል።አቀዳደዱን እና አሰባበሩን ግን በጥንቃቄ ለማድረግ ቅዳጁም ሆነ ስባሪው የኢትዮጵያን ሕዝብ እግር እንዳይወጋ እየተጠነቀቀ እንዳለ ይገባናል።የሁሉም አካል እገዛ ግን ያስፈልጋል።የጎሳ ጥብቆውን የቀዳደደ እና የጠባብነት ቀለበቱን የሰበረ የዋንጫው ባለቤት ነው።የዋንጫው ሸላሚ ደግሞ ሕዝብ እና ሀገር ነው።

ጉዳያችን / Gudayachn 
www.gudayachn.com


































































ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com


No comments: