ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, September 12, 2018

የድርጅትህን ዓርማ በፈለክበት ቦታ ማውለብለብ ትችላለህ።የሉዐላዊት ሀገር ኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውርደህ በድርጅት ዓርማ ለመቀየር መሞከር ግን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን አላውቅም ከማለት እኩል ነው።



ጉዳያችን/Gudayachn
መስከረም 3/2010 ዓም (ሴፕቴምበር 13/2018 ዓም)

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ዛሬ በነፃነት የሚውለበለበው ኢትዮጵያውያን ከወለጋ እስከ ሱማሌ፣ከሞያሌ እስከ ትግራይ፣ከመተማ እስከ አፋር የሚኖር ሕዝብ ደሙን አፍስሶ እና አጥንቱን ከስክሶ መሆኑን  ማንም ሊክደው የማይችለው ሐቅ ነው።የፖለቲካ ዓላማህን በፈለክበት ቦታ እና ጊዜ ልታንፀባርቅ ትችላለህ።ይህ ግን በኢትዮጵያ ክበብነት ውስጥ እንጂ ''ኢትዮጵያን አላውቅም፣ሰንደቅ ዓላማዋን መሬት ላይ እጥላለሁ'' በሚል ጀብደኝነት ሊሆን ፈፅሞ አይችልም።የድርጅትህን አርማ ከአንገትህ በላይ አድርገህ ማውለብለብ ትችላለህ።የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከትምሕርት ቤቶች ግቢ፣ከመንግስታዊ ድርጅቶች ግቢ ውስጥ እየገባሁ አወርዳለሁ ብለህ ሙከራ የምታደርግ ከሆነ ግን ከባዕዳን ወረራ እኩል መላው ኢትዮጵያዊ የሚንቀሳቀስበት ቁልፍ ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚነካ ማንም ሊያልፈው የማይፈቀድለት ቀይ መስመር ነው።

ሰሞኑን 'ቄሮ' ለሁለት የተከፈለ በሚመስል መልኩ እየታየ ነው።ይሄውም በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መብት የሚያከብር እና ለለውጡ ሁሉም ያደረገውን አስተዋፅኦ የሚያከብር  ሲኖር በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሕዝብን ''የምንሊክ ሰፋሪ! መጤ!'' በሚል የሚዘልፍ ከሕግ እና ከሥርዓት ውጭ የሆነ በቄሮ ስም የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው።ይህ ''መጤ እና ሰፋሪ'' የምትለው  የበታችነት ስሜት ያለበት ንግግር ከአሁን በኃላ ፈፅሞ የሚናገር ሰው በሕግ ሊቀጣ ይገባል።ወደ ''ሰፋሪ'' ትርክት ከመጣን ብዙ ታሪክ (ምናልባት አላስፈላጊ ሊሆን ይችላል) ከአስራ አምስተኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ብቻ ታሪክን መቃኘት ይችላል።በኢትዮጵያ ማንም ''ሰፋሪ'' የሚባል መርዘኛ ''የጀኖሳይድ'' ንግግር እንዲናገር ሊፈቀድለት አይገባም።ታሪክን ወደ ኃላ ከሄድን የሰሜን ሸዋ፣የባሌ ሱማልያ፣የደቡብ ሕዝብ ብዙ ታሪክ ዛሬ ''ሰፋሪ'' እያሉ በሚዘልፉ ወገኖች እንደተገፉ የሚናገሩት ብዙ ታሪክ አለ።ይህንን ፋይል መክፈት ስለማይጠቅም እና ተገቢም ስላልሆነ በጋራ ጉዳይ ላይ ማተኮር ይገባል ከሚል መተዉን ሁሉም ሊረዳው ይገባል።ሂሳብ መተሳሰብ በተለይ በታሪክ ላይ ብዙ የሚያመጣው ጉዳት አለ።የወደፊቱ ላይ ማተኮሩ ጠቃሚ ነው። አዲስ አበባ ከአምስት መቶ ዓመት በፊት የት ነበረች? ዛሬ ''ሰፋሪ!'' የሚሉት ወገኖች ያን ጊዜ የት ነበሩ? ይህ ስሌት ለትውልዱ ይጠቅመዋል? ብዙ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል። ስለሆነም ማንም ዛሬ ላይ ቆሞ ማንንም ''ሰፋሪ እና መጤ'' እያለ እንዲናገር ሊፈቀድለት አይገባም።ዲሞክራሲ ማለት ህዝብን መስደብ ማለት አይደለም።

አሁን የመጣው ለውጥ ተጠቃሚ ማንም አይደለም።ትግራይን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።ለውጡን መንከባከብ ደግሞ የአንድ ወገን ብቻ ሊሆን አይገባም።የሁሉም ወገን ኃላፊነት ነው።ይህ ለውጥ እንዳይረበሽ የሚፈልግ ወገን ስላለ ማንም አይቃወመኝም በሚል የተሳሳተ እሳቤ ብቻ ህዝብን ''ሰፋሪ'' በሚል ስድብ በማወክ እና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውረድ ለውጡን ለማወክ መሞከር በእራስ ላይ ፍም የመጫር ያህል ነው።ሕዝብ የባሰ ደረአ ላይ ከሆነ ለመጪዎቹ ዓመታት ሕልውናውን እና የጋራ አንድነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ለመታገል አይደክመውም።ብቸኛው አማራጭ ከሆነ ትግል የኖረበት ነው።ከእዚህ አዙሪት የመውጣት አስተሳሰብ እናዳብር ሲባል ሕልውናችንን አጥተን እንኑር ማለት አለመሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት።

በመጪው ቅዳሜ ከአስመራ አዲስ አበባ የሚገቡት የኦነግ መሪ ዳውድ ኢብሳ ወደ ሀገራቸው በክብር መግባታቸው ላይ ማንም ጥይቄ ያለው ዜጋ የለም። በሀገራቸው በኢትዮጵያ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከእነሙሉ ክብራቸው ሕዝብ ወጥቶ ይቀባላል።ይህ ማለት በፖለቲካ መርሃቸው አለመስማማት መብት እንደሆነ ሁሉ መስማማትም መብት ነው።ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያንሉዓላዊነት፣ሰንደቅ ዓላማ እና ሕዝብ የመረጠው ቦታ የመኖር መብቱን የሚገስ  አካሄድ አሁንም ሌላው የቀይ መስመር ነው።ኢትዮጵያን አልፈልግም ያለ አለመፈለግ መብቱ ነው። ኢትዮጵያን የሚፈልጉትን እንዲጋፋ ሊፈቀድለት አይገባም።መከባበር፣የእራስን ዓላማ ማራመድ (ሉዓላዊነትን በማይጣረስ መልኩ) ይቻላል። አሁን በኦሮምያ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)፣ የኦፌኮን እና ኦነግ አርማዎች ይውለበለባሉ።በመላዋ ኢትዮጵያም ድርጅቶች የተለያየ ዓርማ አላቸው።የድርጅት አርማቸውን ግን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ በመቀየር ያልሰለጠነ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን አንድ የባዕድ ኃይል ሊፈፅምባት የሚችለውን የመጨረሻ የሉዓላዊነት ጥሰት በሚያሳይ መልኩ መንቀሳቀስ ምንም አይነት እሹሩሩ የማያስፈልገው ጉዳይ ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያለ መሬት አዲስ አበባን ጨምሮ ''መጤ ሰፋሪ'' ተብሎ የሚጠራ ሕዝብ የለበትም።ይህንን የሚሉ በሙሉ ለፍርድ መቅረብ ይገባቸዋል።የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከተሰቀለበት ለማውረድ የሚሞክር ግለሰብ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመረረ እርምጃ አይወስድም ብሎ መገመት ሕዝቡን እንደሕዝብ ካለማወቅ የሚመጣ ደካማ እይታ ነው።

በመጨረሻም በአዲስ አበባ በቄሮ ስም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በጉለሌ አካባቢ የሚገኙትን የመንገድ ማካለያዎች በኦነግ አርማ ቀለም ለመቀባት ሲሞክሩ ግጭት መፈጠሩ ሌላው የዛሬ ዜና ነው።የአዲስ አበባ መንገዶች እና ማካለያዎች ሕዝብ በጋራ በከፈለው ቀረጥ የተሰሩ እንጂ የአንድ ድርጅት የግል ንብረት አይደሉም።በቀለም መቀባቱ ላይ የግለሰቦች አጥሮች ሳይቀሩ ለመቀባት ተሞክሯል።ይህ ስልጣኔ ያልጎበኘው እጅግ ኃላ የቀረ አስተሳሰብ ነው። ሆን ብሎ ፀብ የመጫር ሙከራም ነው።አሁን ባለቸው ኢትዮጵያ ከአራት ወር በፊት በነበረው ስሜት ሕዝብ የሚያንቀሳቅሱ የሚመስላቸው አካሎች ጊዜውን በሚገባ መተንተን ቢችሉ ጥሩ ነው።በስሜት ለመቆስቆስ የሚደረገው ሙከራ እዝያኛውም ቤት እጅግ በትዕግስት የተሞላ ነገር ግን ሀገራዊ፣ ሁሉም በከፍተኛ ስሜት ለሰንደቅ ዓላማ መቆም እና ''መጤ እና ሰፋሪ'' ለሚል የወረደ አጠራር ሕዝብ በከፍተኛ ቁጣ ምላሽ እንደሚሰጥ መረዳት አስፈላጊ ነው።
ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ፍቃድ ውጭ የተቀባው የመንገድ ማካፈያ 

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...