ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, September 13, 2018

የብሔራዊ ፖለቲካ አንዱ መገለጫ የሆነውን የአዲስ አበባን ጉዳይ ማድበስበስ አይጠቅምም::የመጪው ቅዳሜው የዳውድ ኢብሳን አቀባበል አስመልክቶ የአዲስ አበባ ሕዝብ ማድረግ የሚገባው

አዲስ አበባ በምሽት 

ጉዳያችን/Gudayachn 
መስከረም 4/2010 ዓም (ሴፕቴምበር 14/2018 ዓም)

የአዲስ አበባ ጉዳይ የብሔራዊ ፖለቲካው አካል ነው 

አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሀገሪቱ እንብርት፣ከግማሽ በላይ የንግድ ገቢ ቀረጥ የሚሰበሰብባት እና ሁሉም የኢትዮጵያ ነዋሪ የሚወከልባት (ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ) የሚገኝባት፣ በዓለም ላይ ካሉ በርካታ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ከሚገኝባቸው ከኒውዮርክ፣ጄኔቭ እና ዋሽንግተን ቀጥሎ በአፍሪካ የቀዳሚነት ቦታ የያዘች ከተማ ነች።አዲስ አበባ የ20ኛው ክ/ዘመን የለውጥ እንቅስቃሴ ማዕከልም ነበረች።በየካቲት 12፣1929 ዓም በግራዚያኒ ላይ የቦንብ ጥቃት የተፈፀመባት እና ጥቃቱን ተከትሎ ከሰላሳ ሺህ በላይ የከተማው ነዋሪዎች የተጨፈጨፉባት፣ የ1953 ዓም የመንግስቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያስተናገደች፣የየካቲት 1966 ዓም አብዮት የተተነሳባት፣የ1997 ዓም የመጀመርያው ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ፈንጥቆ የጨለመበት ምርጫ የተደረገባት ከተማ አዲስ አበባ ነች።


አዲስ አበባ የብሔራዊ ፖለቲካው አካል ነች።በብሔራዊ ደረጃ የሚተገበረው ፖለቲካ አዲስ አበባ ላይ በቀጥታ ይንፀባረቃል።አንዳንዶች የአዲስ አበባን ጉዳይ የማንሻው ጊዜ አሁን አይደለም የሚሉ አሉ።ሆኖም ግን የመናገር ነፃነት በአንፃራዊ መልኩ በተለቀቀበት ወቅት አለመወያየት አይቻልም።የአዲስ አበባ ነዋሪ በከተማው የመኖር ልዕልናውን ለመጋፋት የሚሞክር ንግግር የሚናገሩ ሰዎች በጊዜው ተገቢው ምላሽ አለማግኘታቸው ዘግይቶ ጥፋት መሆኑ እየታየ ነው።የጎሳ ፖለቲካው ትንፋግ ለአዲስ አበባም ተርፏታል።የአዲስ አበባን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያን ጎሳን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ከጎሳ ይልቅ ሀገራዊ አንድነትን ያስቀደመ መሆኑ ወሳኝ ነው።ስለሆነም አዲስ አበባን ያገለለ፣ የአዲስ አበቤን ነዋሪ ህልውና እና መብት ያላከበረ ስርዓት ሊኖር እንደማይገባ ግልጥ ነው።ይህ ማለት የአዲስ አበባ ነዋሪን ''ሰፋሪ፣መጤ'' የሚሉ በእርስ በርስ ግጭት አስነሽነት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።አሁን ባለንበት ዘመን አይደለም በአንድ ሀገር የሚኖር ሕዝብ በሌላ ሀገር የሚኖር ሕዝብ ''መጤ ወይንም ሰፋሪ'' ብሎ መጥራት በሕግ የሚያስከስስ ንግግር ነው። አዲስ አበባዎችም ቢያንስ የራሳቸውን የኢትዮጵያዊነት መብት በሕግ ማስከበር ተፈጥሯዊ መብት ነው።


ኦነግ ስንት ነው? 


በ1960ዎቹ የብሔር ፖለቲካን ተከትሎ ከተመሰረቱት ድርጅቶች ውስጥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አንዱ ነው።ኦነግ ከተመሰረተ 50ኛ ዓመቱን ቢደፍንም፣ብዙዎች እስካሁን የጎላ ሚና አለማድረጉ እሙን ነው።ኦነግ ወደ ሀገር ቤት ሲገባ ከ1983 ዓም ወዲህ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ማለት ነው።እርግጥ ነው ዛሬም ድረስ የኦነግን ዓርማ አንዳንዶች ሲመለከቱ የበደኖው እልቂት፣የአርባጉጉ ጭፍጨፋ ትዝ የሚላቸው አሉ።ይህ ስሜት ለምን ተፈጠረ? ማለት አይቻልም።እርግጥ ነው ኦነግን እንደሚወክሉ የሚናገሩ አካሎች እነኝህ እልቂቶች የኦነግ ተግባራት አለመሆናቸውን በተለያዩ ሚድያዎች ገልጠዋል።ይህንን ለታሪክ አጣሪዎች እንተወው።ጥያቄው ግን ኦነግ ስንት ነው? የሚለው ነው።በቅርቡ  በኦነግ ስም አቶ ዲማ ነጎ እና ሌንጮ ለታ ወደ ሀገር መግባታቸው ይታወሳል።አሁን የሚገባው በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ሌላው የኦነግ ክፍል ነው ማለት ነው።ይህ ማለት ኦነግ ስንት ነው? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው።


ቄሮስ ስንት ነው? 


ቄሮ (ወጣት) የሚለው ቃል ላለፉት ሁለት ዓመታት በኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያውያን ውስጥ ስሙ ደጋግሞ ተነስቷል። ቄሮን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያውቀው ባህርዳር ድረስ ሄዶ የጣናን አረም ስነቅል፣ እኛ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቆምን አይደለንም ብሎ አዳማ (ናዝሬት) ላይ መፈክር ሲያሰማ ነው። አሁን የምናየው  ግን ከእዚህ በፊት የምናውቀው ቄሮ አይደለም።ሻሸመኔ ላይ ሰው ከነቁሙ የሚሰቅል፣ አዲስ አበባ መሐል ገብቶ መሐል አስፋልት ላይ የኦነግ አርማን በቀለም የሚስል፣ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ድንጋይ የሚወራወር ቄሮ የትኛው ቄሮ ነው? ቄሮ ስንት ነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ መሆኑን  እነኝህ ሁነቶች የሚጠቁሙ ናቸው። 


ሐጂ ጃዋር ኦነግ ነው?


የኦሮምያ ሚድያ ኔትዎርክ ሥራ አስኪያጅ ጃዋር መሐመድ (በያዝነው ወር ወደ ሳውዲ ዓረብያ ተጉዞ ሐጂ መባሉን ለማወቅ ተችሏል) ጃዋር ኦነግ ነው? ይህንን ጥያቄ ብዙዎች ይጠይቃሉ።እርግጥ ነው ሐጂ ጃዋር ወደ ፖለቲካ መሪነት መምጣት እንደማይፈልግ ነገር ግን በጋዜጠኛነት መቀጠል እንደሚፈልግ ተናግሯል።ሐጂ ጃዋር የኦሮምያን ፖለቲካ የሚያቀነቅነው ፅንፍ የያዘ የእስልምና አካራሪ እንቅስቃሴ አፍቃሪ በመሆኑን ነው በማለት የሚያሙት አሉ።እነኝህ ወገኖች ለእዚህ አባባል የመነሻ ነጥባችን ብለው የሚጠቅሱት ሐጂ ጃዋር በአሜሪካ በአንድ ወቅት ባደረገው ንግግር (የሜጫ ንግግር በሚል አንዳንዶች ይጠቅሱታል) የእስልምና እንቅስቃሴ መሰረቱ ማድረግ ከሚገባው የኅብረተሰብ አካል ውስጥ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ዋናው ሊሆን እንደሚችል የገለጠበት አገላለጥ አንዱ ሲሆን። በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮምያ ሚድያ ላይ የአረብኛ ተናጋሪ እምብዛም ለሆነባት ኢትዮጵያ የአረብኛ መርሐግብር እንዲኖር የሄደበት መንገድ እንደ ማስረጃዎች ያነሳሉ። ሆኖም እስካሁን ለእነኝህ አገላለጦች ማስረጃዎች አልተገኙም።በዛሬው እለት ግን ሐጂ ጃዋር የኦነግ አቀባበል ''እጅግ ከፍተኛ'' እንደሆነ የገለጠበት መግለጫ የሰሙ ሐጂ ጃዋር የኦነግ አባል ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች እያየሉ ነው።ሐጂ ጃዋር ኦነግ የመሆንም ሆነ  በጋዜጠኝነት መቀጠል መብቱ ነው።ሆኖም ግን ሐጂ ጃዋር ከሁሉም በባሰ የሚወቀስበት አንድ ነጥብ አለ።ይሄውም የሻሸመኔ ጉብኝቱ ወቅት በእርሱ ሳብያ ከወጣው ሕዝብ መሐል በቄሮ ስም በጠራራ ፀሐይ ሰው ሲሰቀል ድርጊቱን ለመውቀስ መግለጫ ሳይሰጥ፣በዛሬው የአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ፈጥኖ ወደ ሚድያ መምጣቱ ብዙዎችን አነጋግሯል።    


 የመጪው ቅዳሜው የዳውድ ኢብሳን አቀባበል አስመልክቶ የአዲስ አበባ ሕዝብ ማድረግ የሚገባው


ዶ/ር ዓብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት የኦነግ አንጃዎች ውስጥ በኤርትራ የነበረው በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን በመጪው ቅዳሜ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የአቀባበል ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተገልጧል።ኮሚቴው መግለጫ ሲሰጥ በሰሜን አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና በኦነግ ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር።የግጭቱ መንስኤ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለአሜሪካ ድምፅ ራድዮ የአማርኛ አገልግሎት እንደገለጠው ''ግጭቱ የተፈጠረው የኦነግ አርማ አትስቀሉ በሚል አይደለም።ሰሞኑን ሲሰቅሉ ማንም ምንም አላላቸውም።ይልቁን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እየነቀሉ በኦነግ አርማ ሲቀይሩ እና በአስፋልት ላይ ቀለም ሲቀቡ ነው ግጭት የተነሳው።አስፋልቱ የጋራ የህዝብ ሀብት ነው።'' በማለት አብራርቷል።ከእዚህ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ  ሕዝብ ማድረግ የሚገባው 


 ሀ) የአዲስ አበባ እና የኦሮምያ ወጣቶች በእርቅ መንፈስ መነጋገር።


አሁን የአዲስ አበባ ወጣቶች ከኦሮምኛ ተናጋሪ ወጣት ኢትዮጵያውያን ጋር በመረጡት መንገድ መወያየት፣ሐሳባቸውን መለዋወጥ፣መከባበር እና የነበረውን ግጭት የሚያጠፋ ግንኙነት መፍጠር አለባቸው።ይህ ደግሞ ለወጣቶቹ አስቸጋሪ አይደለም።በነገው እለት አርብ ይህንን ማድረግ ይችላሉ።ለአራዳ ልጅ እና በአዲስ አበባ ዙርያ ለሚኖር ወጣት ይህንን ያህል ነገሮችን አያካርርም የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አለ።


) የቅዳሜ የዳውድ ኢብሳ አቀባበል ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች የሚወክሉ አቀባበሉ ላይ መገኘት።


በቅዳሜው የዳውድ ኢብሳ አቀባበል ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች የሚወክሉ ወጣቶች በአዘጋጅ ኮሚቴው እውቅና  የፈለጉትን ሰንደቅ ዓላማ እና አለባበስ ለብሰው እንዲገኙ መፍቀድ፣እና ይሄውም በመገናኛ ብዙሃን ቀድሞ እንዲነገር ቢደረግ ጥሩ ነው። 


ሐ) 
በቀጣይ ጊዜ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና የኦሮምያ ወጣቶች እራሳቸው በመረጡት ጊዜ እና አደባባይ የጋራ የሙዚቃ እና የምሳ ዝግጅት እንዲደረግ ማድረግ

በቀጣይ ጊዜ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና የኦሮምያ ወጣቶች እራሳቸው በመረጡት ጊዜ እና አደባባይ የጋራ የሙዚቃ እና የምሳ ዝግጅት እንዲደረግ ማድረግ ለእዚህም መንግስት በውጪ መጋራት እንዲያግዛቸው ቢደረግ ከመደበኛ ግንኙነት በላይ ኢ- መደበኛ ግንኙነቶች በማኅበራዊ ግንኙነት ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል።

ባጠቃላይ በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶች ይጠይቃል።አንዳንዶቹ ጉዳዮች ዛሬ የተፈጠሩ ድንገቴዎች ሳይሆኑ ቀናቸውን እየጠበቁ የነበሩ ጥያቄዎች ናቸው።ሁሉንም ጉዳይ መንግስት ይፍታው ማለት ከባድ ነው።ሕዝብ በባለቤትነት ተቀብሎ የመንግስትን ሥራ መስራት ይችላል።ሕዝብ ሕግን አክብሮ በትዕግስት እስከሄደ ድረስ ምንም ጉዳይ ከእጅ የወጣ አይሆንም።ለጉዳዮች ከዳር ሆኖ መመልከት አደገኛ ነው።የአዲስ አበባ ጉዳይም የብሔራዊ ፖለቲካ አካል ነው የሚባለው ለእዚህ ነው።የአዲስ አበባ ነዋሪ የራሱ ማኅበራዊ መስተጋብር እስካለው ድረስ ሕግ አክብሮ የራሱንም መብት ከማናቸውም ኃይል መከላከል ተፈጥሯዊ መብቱ መሆኑን ፈፅሞ መዘንጋት የለበትም።


ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

No comments: