ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, September 4, 2018

ስልት ግብ አይደለም።የጎሳ ፖለቲካን እንደ ስልት የያዙ ግባቸው ላይ መድረስ አይችሉም።



ጉዳያችን/Gudayachn
ነሐሴ 29/2010 ዓም (ሴፕቴምበር 4/2018)
======================

የትም ፍጭው ስልጣኑን አምጭው 

 ስልት (ስትራቴጂ) ወደ ዋና ግብ የሚያደርስ የእቅድ ወይንም የእቅዶች አፈፃፀም ሂደት ነው። ቃሉ በአስራዘተነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ ሀያኛው አጋማሽ ድረስ በወታደራዊው ዓለም የገነነበት እና የጦር አመራሮች ብቃት የሚለይበት መንገድ እንደሆነ ይነገራል።ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኃላ ግን ስልት (ስትራቴጂ) የሚለው ቃል ለንግድ አስተዳደር እና ለተለያዩ የማኅበራዊ ሳይንስ ማስፈፀምያነት መዋል ጀመረ።አሁን ባለንበት ዓለም በፖለቲካው ዓለም በውጭ ፖሊሲ እና በፖለቲካ ፕሮግራሞች ማስፈፀምያነት ሥራ ላይ እየዋለ ይገኛል።

ወደ ሀገራችን ፖለቲካ ስንመጣ ከ1966 ዓም አብዮት ወዲህ በነበሩ የፖለቲካ ስልጣን የትግል ሂደት ላይ የነበሩ ተዋናዮች ሁሉ የሚያተኩሩት የስልጣን ወንበሩ ላይ ለመድረስ የሚደረገው የትግል ሂደት ላይ እንጂ ግብ ብለው የሚያስቀምጡት የስልጣን  ወንበሩን (በምንም አይነት የሰው እና የንብረት ወጪ ክፍያ) መቆጣጠርን ነው።ስለሆነም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ፣ታሪካዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ሁኔታ በሚገባ ሳያጠኑ እና ሳያስጠኑ ወደ ትግል መስመር ውስጥ ይገቡ እና መርሐግብራቸውን ወይንም ፕሮግራማቸውን እንደፈለጉ እየቀየሩ ተንገታግተው የስልጣን ወንበሩ ላይ ለመድረስ ይሞክራሉ።

እነኝህ የስልጣን እርከኑን ለመቆጣጠር እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ነባራዊ ሁኔታም ሆነ ዓለም አቀፍ እና አካባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ  ሂደት ላለፉት አርባ ዓመታት ሲያራምዱ ከኖሩት ውስጥ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና  የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ድርጅቶች የተለያዩ ስለሆኑ) መጥቀስ ይቻላል።ቤተ መንግስቱ ድረስ የገባው ህወሓት ስለሆነ የእርሱን ስልት እና ግብ መመልከት አሁን ላሉት የጎሳ ፖለቲካ ( ሲቆላመጥ የማንነት ፖለቲካ ይሉታል) አራማጆች የፖለቲካ ትርፍ እና ኪሳራውን ለመለካት እንደ አንድ አይነተኛ ናሙና ይረዳል።


በትግራይ ለአርባ አምስት ዓመት የተቀነቀነው የጎሳ ፖለቲካ (ሲቆላመጥ የማንነት ፖለቲካ) ከትግራይ ሕዝብ የፈለቀ ሳይሆን ተማሪዎች የጫኑበት የትግል ስልት ነው 

የ1960 ዎቹ መጨረሻ እና የ1970ዎቹ መጀመርያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁለት መሰረታዊ መንደርደርያዎችን ይዞ ይነሳል።እነርሱም ብሔርተኛ እንቅስቃሴንና የእንቅስቃሴው አባት የግራ ክንፍ ፖለቲካ ናቸው።የብሔርተኝነት እንቅስቃሴን ህወሓት አራት ኪሎ ላይ በትግራይ ተማሪዎች ማኅበርነት ጠንስሶ ትግራይ ደደቢት ላይ ስዘራው የትግራይ ገበሬ እንግዳ ነገር እንደወደቀበት መረዳት ይቻላል።የትግራይ ሕዝብ የብሔር ፖለቲካን ከውስጡ አብቅሎ ያካሄደው አብዮት ሳይሆን አዲስ አበባ የትግራይ ተወላጅ ጥቂት ተማሪዎች ተሰብስበው የጫኑበት እንደሆነ ለመረዳት በቅርቡ የወጣው የቀድሞ የህወሓት መስራች እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ግደይ ዘረዓፅዮን '' ከትግል ትዝታዎቼ የደደቢት አብዮት በሰረኞች መቀጨት'' በተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ ወደ ብሔር ፖለቲካ የመራቸው አንዱ ምክንያት አወዛጋቢው የዋለልኝ በጎሳ ፖለቲካ ዙርያ የፃፈው ፅሁፍ እንደነበር ይጠቅሳሉ።

ህወሓት የጎሳ ፖለቲካን ከህዝቡ የመጣ እና የመነጨ ለማስመሰል በ1935 ዓም የተነሳውን የመጀመርያ የገበሬዎች አመፅ ይጠቅሳል።ሆኖም ግን ገበሬዎች በግብር ዕዳ አመጽ ሲያነሱ የማንነት ጥያቄ አነሱ ማለት አይደለም። በንጉሡ ዘመን የገበሬዎች አመፅ በጎጃም፣በባሌ እና ሌሎች አካባቢዎች ሲነሳ እና ሲከስም ኖሯል። እነኝህ አመፆች ግን የማንነት ጥያቄዎች ነበሩ ማለት ትክክል አይደለም።


ስልት ግብ አይደለም።የጎሳ ፖለቲካን እንደ ስልት የያዙ ግባቸው ላይ  መድረስ አይችሉም።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ የጎሳ ፖለቲካ እንደ የስልጣን መወጣጫ እቅድ መጠቀም የተለመደ አዙሪት እየሆነ ነው።ይህ ስልት በስሜት ህዝብን ለመኮርኮር፣ ሁሉንም በደሎች የእገሌ ብሔር ስለሆንክ ነው ይህ የደረሰብህ ብሎ ቅራኔዎችን ለማክረር ይጠቅም ይሆናል።ለምሳሌ ህወሓት እስከ 1979 ዓም ድረስ ከአስራ ሁለት ዓመታት በላይ ውጤት ያላመጣው እና የትግራይን ሕዝብ በሚገባ ለማንቀሳቀስ እና ለማሰለፍ ባለመቻሉ የብሔር ስሜትን በማጋል እና በሐውዘን የህዝብ እልቂት ሴራ በማራመድ የትግራይን ሕዝብ ለመኮርኮር ጠቅሞታል።ይህንን የድርጅቱ አባል እና የፋይናንስ ኃላፊ የነበሩት አቶ ገብረመድህን አርአያ በተለያዩ ጊዜዎች በሰጧቸው መግለጫዎች ያረጋገጡት ሐቅ ነው።

በተመሳሳይ መንገድ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወደ ስልጣን የመውጫ ዋነኛ ስልት አድርጎ የተነሳው አሁንም የጎሳ ፖለቲካን በማራገብ ከብሔራዊ ስሜት ይልቅ የኦሮምኛ ተናጋሪዎች የጎሳ ፖለቲካ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ነው።በተቆላመጠው የማንነት ፖለቲካው ላይ የኦነግ ፖለቲካ አራማጆች እራሳቸውን እንደ ልዩ ማኅበረሰብ ከማየት እስከ ፌዴሬሽን ሁሉ በየመድረኩ አስተጋብተዋል።አቶ ሌንጮ ለታ በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ ''ከኢትዮጵያ ጋር መደራደር እንፈልጋለን'' በማለት አዲስ አበባ ላይ ሲናገሩ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ይዘው ነበር።

የጎሳ ፖለቲካን ለስልትነት ተጠቅመን ወደ ስልጣን ወንበሩ ላይ ስንጠጋ ቀስ ብለን አንሸራተን ሌላ መታወቂያ እንይዛለን ብለው የሚያስቡ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች ቀድሞውንም ግባቸውን ደብቀው ስለኖሩ በስሜት የተሰባሰበው የጎሳቸው አባል ባስተማሩት የከረረ የጎሳ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሐሳባቸውን ያስረዋል።ህወሓት የሆነው ይሄው ነው።ለስልት ብሎ ያከረረው ብሔርተኝነት አንዴ ወልቃይት ላይ እናቶችን ክላሽ እያስያዘ ሰልፍ ሲያስወጣ፣ ሌላ ጊዜ ባህር ማዶ የትግራይ ማኅበር እያለ እየደገሰ ሲያበላ ከርሞ የጎነታለቸው እና በብሔር ፖለቲካ የወጋቸው የአማራ እና ኦሮሞ ማኅበረሰብ እርሱ በመጣበት መንገድ አክርሮ ስመጣ ማጣፍያው አጠረ። 

በተመሳሳይ መንገድ  በኦሮሞ እና አማራ ማኅበረሰብ ውስጥም ህወሓትን ለመምታት የህዝብን ስሜት በጎሳ መቀስቀስ በሚል የተጀመረው ስልት ግቡ ስልጣን ላይ መውጣት ብቻ እንጂ ሌላው ቀርቶ የቡድን መብት የሆነውን ጎሳውን ለይቶ መንከባከብ እንደማይቻል፣ቢሞከር ደግሞ የሚያናጋው የፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ታሪካዊ መስተጋብር ሁሉ ቀድሞ አልታየም ነበርና ሌላው ምስቅልቅል ሆኖ ይገኛል።ለእዚህ አብነት አሁንም የህወሓት እና ኦነግ የአርባ ዓመት የትርምስ ፖለቲካ መመልከት ነው።ህወሓት የጎሳ ፖለቲካው ሰሜን ወሎ እና ጎንደርን እንደማያሻግር ዘግይታም ቢሆን ስላወቀች ከቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የተማረኩ ወታደሮችን በመጀመርያ ''የመኮንኖች ዲሞክራሲያዊ ግንባር'' (መቼም መሳቅ ነው እንዴት ይህንን ስም እንደፈጠሩለት) በመቀጠል የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ወዘተ እያለ ኢትዮጵያ የሚመስል ቅርፅ በመያዙ እና በማዕከላዊ መንግስት ውስጥ ያለው የውስጥ ቅራኔ ብቻ አዲስ አበባ ድረስ እንዲመጣ እረዳው እንጂ  የጎሳ ፖለቲካውን እንደያዘ በህወሓት ስም ልራመድ ቢል እንደ ኦነግ እስካሁን ድረስ አንዴ በአስመራ ሌላ ጊዜ በባሌ እንደ ቱሪስት እየተዘዋወረ ይኖር ነበር።

ዘመነኞቹ ምን ይማሩ? 

አሁን ባለንበት ዘመንም የአርባ ዓመቱ የተሳሳተ የፖለቲካ ስልት መድገም አለብን የሚሉ እየታዩ ነው።ህወሓት ባለበት እያረጀ ሲሄድ በአማራ እና በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ አዲስ የጎሳ አደረጃጀቶች የብሔራዊ አንድነት እና በግለሰቦች የዜግነት ፖለቲካ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ለማጥላላት ይሞክራል።የሚያሳዝነው  አሁንም የጎሳ ፖለቲካ በስልትነት ተጠቅሞ የፖለቲካ የበላይነትን ለማግኘት መጣር ላይ እንጂ  ለሀገራችን ዘለቄታ የጋራ ተጠቃሚነት፣እኩልነት እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህልን ማስፈን ላይ ትኩረት አለመስጠት ይታያል።ይህ ታሪክን በአሳዛኝ መልኩ የመድገም መጥፎ አባዜ ነው።ለፖለቲካ ስልት ሲባል ሺዎች  እረገፉ፣ሚልዮኖች ተሰደዱ፣ኢትዮጵያ የዛሬ አርባ ዓመት ከነበረችበት ዓለም አቀፍም ሆነ አካባቢያዊ ተፅኖ ፈጣሪነት ደረጃ በእጅጉ አወረዳት።

ዛሬም ግን የጎሳ ፖለቲካን እንደ ስልት አስቀምጦ ግብን ደብቆ የመሄድ መንገድ ሕዝብ እንዲከተል ጥረት ይደረጋል።ይህ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ አሁን ያለው ትውልድ የጎሳ ፖለቲካን ለመዋጋት እና እንደ ስልት እየተጠቀሙ ግን ግቡ ጎሳውን መጥቀም ነው እያሉ የሚዋሹትን ኃይሎች ማጋለጥ ሕዝብ በኢትዮጵያዊ መንፈስ ለመብቱ እና ለዲሞክራሲ ሂደት ጤናማነት እንዲደራጅ ማድረግ አስፈላጊ ነው።መልሰን መጭበርበር የለብንም።ያለፈው አርባ ዓመት እልቂት ይበቃናል።ህወሓት እና ኦነግ  ከአርባ አምስት ዓመት የጎሳ ፖለቲካ በኃላም የደረሱበትም ሆነ ያስቀመጡት ግብ የለም።የተወሰኑ የጎሳው አባላት ዘርፈው ሀብት ማካበታቸው ግብ ሊሆን አይችልም።ግባቸው ስልጣን መያዝ ነበር።ስልጣን ከያዙ በኃላ የሚያስቀምጡት ግብ ስሌላቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ፣ልማታዊ መንግስት እያሉ ለማታለል ሞከሩ።እርሱም አልተቻለም።ሌላ የጎሳ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ከሕዝባዊ አመፅ ጋር ተደባልቆ ጠራረጋቸው።ፖለቲካ ስልቱን ሲያስቀምጥ ግቡን ሀገራዊ እና ሁሉን የሚያሳትፍ፣የሚጠቅም እና ተጠያቂነትን መሰረት ያደረገ ከሆነ ሚልዮኖች አብረውት ስለሚሰለፉ በቀላሉ አይገፋም።የጎሳ ፖለቲካ በአንፃሩ በስልትነት የተነሳበትን የጎሳ ቅስቀሳ ወደ ስልጣን ከመጣ በኃላ ይደናበራል።በሌላ ኃይል ሲገፋ ደግሞ ቀድሞም በግቡ እና በዓላማው ዙርያ አምኖ የተሰለፈ ስለሌለ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደገባ ውሻ ተክለብልቦ ይባረራል።

ማጠቃለያ 

የጎሳ ፖለቲካ ስልጣኑን ለማስጠበቅ የሚጠቀመው ግድያ፣እስር እና የራሱን ጎሳ ከሌላው ጋር በማጋጨት እርሱ ብቸኛ የጎሳው ተከላካይ በመሆን ድጋፍ ለማግኘት በመጣር ነው። የጎሳ ፖለቲካን በስልትነት የሚጠቀሙም ሆኑ የመገናኛ ብዙሃናቸውን በጎሳቸው ስም የሚጠሩ ሁሉ ኢትዮጵያዊነት በሁሉም መልክ የተቀጣጠለ ጊዜ የራሳቸው ጎሳ ስለሚከዳቸው እልቄት ከመፈፀም ውጭ አማራጭ አልባ ይሆናሉ። 

የጎሳ ፖለቲካን እንደ ስልት የያዙ ግባቸው ላይ  መድረስ አይችሉም።ሕዝብ ከማስፈጀት እና ከማቃቃር ያለፈ ውጤት የላቸውም የምለው።ኦነግ እስከአሁን ድረስ የኦሮሞ ማኅበረሰብን ሳይቀር ከማስፈራራት እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይዙ ከማሳቀቅ ባለፈ ለሕዝቡ ያስቀመጠው ሕዝቡን አንድ እርምጃ የሚወስድ ግብ ለመናገር ያልቻለው።ይህንን የጎሳ ስሜትን ማቀንቀን እና እስከመገንጠል ድረስ መሔድ ስልት እንጂ ግብ አለመሆኑን ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና አንድ ወቅት ለኢሳት ራድዮ ሲናገሩ አረጋግጠዋል።ፕሮፌሰር መራራ ሲቆላመጥ የማንነት ፖለቲካን እስከ መገንጠል የሚለውን አባባል ''የኦነግ ድርጅት ምናልባት ቢጠቀምበት እስከ ቤተ መንገስት ድረስ ነው።ከእዝያ በኃላ አይጠቀሙበትም'' በማለት ገልጠዋል።

አሁን በአማራ ክልል የሚታየውም የጎሳ አደረጃጀትን በስልትነት አስፈላጊ ናቸው ብሎ  ከሚያነሳቸው ሁለት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሀገሪቱ ነባራዊ ፖለቲካ በብሄር ላይ የተመሰረተ ነው የሚል እና ሁለተኛው ደግሞ ለመከላከል ይጠቅማል የሚል ነው።ብሶት፣መጪውን ከመፍራት እና እስካሁን በጎሳ ማንነት ላይ ተመስርተው ከተነሱ ጥቃቶች አንፃር የአማራ የጎሳ አደረጃጀት ትክክል ስልት ይምሰል እንጂ ግቡ ግን ኢትዮጵያዊ እንደሆነ አደራጆቹ ይናገራሉ።እኔ እንደሚመስለኝ ግን የተገላበጠ ይመስላል።ኢትዮጵያዊነትን ይዞ የጎሳ ጥቃትን መከላከል እና ሃሳቡንም ድርጊቱንም መከላከል እና ማጥቃት ይቻላል እንጂ የጎሳ ማንነትን አክርሮ ኢትዮጵያዊነትን ማበልፀግ አይቻልም። ከሁሉም አስከፊው ደግሞ በስልትነት የተያዘው የጎሳ ፖለቲካ ስልጣን ላይ ከወጡ በኃላ ልመልስህ ቢሉት አለመቻሉ ነው።ምክንያቱም ለአመታት ለስልት ተብሎ የሌላው ብሔር ክፉነት እየተነገረው የቆየው የጎሳው ድርጅት አባላት መሪያቸው ከአመታት ጥፋት በኃላ የጎሳ ፖለቲካን እንተው ቢላቸውም በቀላሉ አይለቁለትም።ይልቁንም የጎሳ ፖለቲካ እንተው ያላቸውን መሪ ሊበሉት ይችላሉ።ስለሆነም ጥፋቱን እያወቀ አብሮ በማዳመቅ ለበለጠ እልቂት ህዝብን ያጋልጣል።



ህወኃትም ሆነ ኦነግ የሆኑት ይህንኑ ነው።ከሕወሓት የጎሳ ፖለቲካ የተቃወሙ እንደ አቶ ገብረ መድህን ያሉት እንደ ከሀዲ ሲቆጠሩ ከኦነግ ''ከኢትዮጵያ ጋር መደራደር እንፈልጋለን'' ያሉት አቶ ሌንጮ ከማንም ጋር ሳይጣጣሙ ወደ ሀገር  መግባቱን የመጨረሻ ግባቸው አደረጉት።ሌሎች ''ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ''  እንዲል አዳዲስ ምልምሎች ደግሞ  ተሞክሮ የከሸፈውን ዛሬ  ላይተነስተው እንደ አዲስ የጎሳ ፖለቲካን እያሞገሱ የዜግነት ፖለቲካ እያሳነሱ ሊነግሩን ይሞክራሉ።ይህ አደገኛ መንገድ ነው።ስልቱን አቆዩትና ግቡን በደንብ ተመልከቱት።የት እንደሚያደርሰን እንመርምር።ከሌላ ጥፋት በኃላ እንደ አቶ ሌንጮ የእርግና ዘመን ስንደርስ በተከዘ ስሜት ቁጭት ከማውራት፣ዛሬ ላይ ቆሞ የፖለቲካ ግብን ከስልት ጋር ያማከለ ሃገራዊ ፖለቲካ ለማራመድ መነሳት ያዋጣል። የማኅበራዊ ሳይንስ ከተፈጥሮ ሳይንስ የሚለየው በቤተ ሙከራ ውስጥ አስገብተው ሞክረህ የምታረጋግጠው ሳይሆን ከመሆኑ በፊት በቂ ጥናት ተደርጎ የሚነሳ መሆኑ ነው።ውጤቱ ሕዝብ ካስጨረሰ  በኃላ እቀይረዋለሁ አትልም።የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ የቤተ ሙከራ ቤትነት ገብቶ ተፈተነ፣አፋጀ፣አጫረሰ በመጨረሻም ሀገር እና ህዝብን ሕልውናቸውን ሊያጠፋ ደረሰ።በመሐል የለውጥ ኃይሉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ መሪነት ወደ መድረክ መጥቶ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ መሆናችንን እና እርስ በርሳችን የተነሳነስን መሆናችንን ደግሞ በመንገር የጎሳ ፖለቲካውን ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ በማዞር  ሀገር መልሶ እንዲረጋጋ ተደረገ።ቤተ ሙከራ ማለት ይህ ነው።የማህበራዊ ጥናት ቤተ ሙከራ ከእዚህ በላይ ከየት ይምጣ።ኢትዮጵያዊነት እና የዜጋ ፖለቲካ አዋጪ ለመሆኑ ሌላ ምስክር ከየት ይምጣ? 

ጌታቸው በቀለ ዳምጠው
getachewb221@gmail.com  
ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...