አዲሱ 2008 ዓም ከገባ ስድስተኛ ወር ላይ ነን።የካቲት ወር ለኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በርካታ ገጠመኞችን ይዟል።በባርነት ቀንበር ልንወድቅ አፋፍ ላይ ሆነን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ እና ጣይቱ ጋር አድዋ ላይ ተሞ ጣልያንን ድል ያደረገው በየካቲት 23 ቀን ነበር።በየካቲት 12/1929 ዓም ደግሞ ኢትዮጵያን ዳግመኛ የወረረው ኢጣልያ በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ የፈፀመበት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድ ሴቱ ከአርበኞች ጋር ይበልጥ እንዲሰለፍ የቆረጠበት እለት ነው።በሌላ በኩል የካቲት 1966 ዓም የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጀመርያ ግብታዊ አብዮት ያቀጣጠለበት ወር ነበር።በእዚህ አብዮትም አሁን ድረስ ላለው ላልሰከነው የአገራችን ፖለቲካ መነሻ ሆኖ ቀጥሏል።ይህ የያዝነው የካቲት ወርም ከሰሜን እስከ ደቡብ የሕዝብ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጥያቄ ዳግም የተነሳበት ነው።
ህወሓት የገመደችው የጎሳ ፖለቲካ ጅራፍ እራሷን መግረፍ ጀመረ
ህወሓት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መለያ ከሆነው አደገኛ መንገድ ውስጥ ዋናው አገሪቱን በጎሳ መከፋፈል ነው።ህወሓት የኢትዮጵያ የሆኑ ነገሮችን በጎጥ ያልከፋፈላቸው እና በጎሳ በሽታ ያለከፋቸው እሴቶች የሉም። ከዋናው የአገሪቱ ምክርቤት ጀምሮ ሰንደቅ አላማ፣የእራድዮ እና የቴሌቭዥን ጣቢያ፣የሚኒስቴር መስርያ ቤቶች፣ ወዘተ በኢትዮጵያ ስም ሳይሆን በጎጥ እንዲከፈሉ አደረገ።እዚህ ላይ የጎጥ ክፍፍልን ከፈድራል አስተዳደር ጋር ለማመሳሰል መሞከር ፈፅሞ የተሳሳተ ነው።ፌድራል አስተዳደር ዓላማ አገርን በጎጥ የመከፋፈል ሳይሆን ሕዝብ እራሱ በመረጣቸው መሪዎች የመምረጥ እና የመተዳደር መብትን እና በማዕከል የተያዘውን አስተዳደር እታች ላለው ሕዝብ በቅርቡ አገልግሎቱን እንዲያገኝ ማድረግ ነው። የጎሳ ፈድራሊዝም ግን የበለጠ ሕዝብ አስጨናቂ እና ብጥብጥ ፈጣሪ ሆኗል። ይህ ደግሞ ላለፉት 24 ዓመታት በአገራችን ተፈትኖ የወደቀ ነው።
ይህ ህወሓት የገመደው የጎጥ ጅራፍ እንደ ህወሓት አስተሳሰብ ሌላውን ኢትዮጵያዊ እየገረፈ ሊኖርበት እንጂ እራሱን የሚገርፍ ጅራፍ ይሆናል ብሎ አላሰበም ነበር።በፈድሬሽን ምክርቤት ጎሳዎች ሲጣሉ (ህዝቡ በእራሱ በመረጣቸው ሽማግሌዎች የሚፈታውን ችግር ) በመካከል እየገባ በርካታ የአገሪቱን ችግሮች በመንደር ደረጃ አወሳስቦታል።
ህወሓት ስልጣን እንደያዘ በርካታ ምሁራን በቅንነት የጎሳ ፖለቲካ ውሎ አድሮ ችግር እንደሚያስከትል ሲናገሩ ነበር። ህወሓት ግን አንድ ጊዜ ነፍጠኞች፣ሌላ ጊዜ የደርግ ርዝራዥ እያለ ሁሉንም አራቃቸው።ህወሓት ስልጣኑን ለመረከብ ብቃት እንደሌለው ነገር ግን በአገሪቱ የነበረው ሁኔታ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታው ስልጣኑን ካለምንም ተቀናቃኝ እንዲረከብ እንዳደረገው ዘነጋው እና በእውቀት፣በምክንያታዊ እና በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ መንግስት መመስረት አቃተው። አቶ መለስ ተቃዋሚዎቻቸውን በመሳርያ ኃይል ማራቃቸው የፈለጉትን የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ላይ ማስፈን ብቸኛ የስልጣን ዋስትና አድርገው ተመለከቱት።ስለሆነም የጎሳ ጅራፉን ገመዱት እና የእኛ አይደለም ባሉት ሕዝብ ሁሉ ላይ ያሳርፉት ጀመር።
በጎሳ ፖለቲካ ጅራፍ ሺዎች ከቀያቸው ተባረዋል፣ንብረታቸው ተወርሶ ተመፅዋች ሆነዋል፣እንደ እብድ ጫካ ለጫካ እየተባረሩ እንደ ውሻ ተገድለዋል፣ብዙዎች በጎሳ ፖለቲካ ከስራቸው ተፈናቅለዋል፣ከአገር ተሰደዋል።በጉርዳፈርዳ የተባረሩ አማርኛ ተንጋሪ ኢትዮጵያውያን፣በምስራቅ ሐረር በሱማሌኛ ተናጋሪዎች የተባረሩ በሺህ የሚቆጠሩ የኦሮምኛ ተናጋሪዎች፣በእልባቦር እና ከፋ ከቀያቸው ተባረው በጥይት የተገደሉት ወዘተ ቤቱ ይቁጠራቸው።እነኝህ ሁሉ የህወሓት የጎሳ ፖለቲካ ጅራፍ ያረፈባቸው ናቸው።በደላቸውን ወደ መንግስት አቤት ለማለት ሲመጡ የህወሓት መንግስት ኢፍትሃዊ መልስ ሲሰጣቸው ቆይቷል።ጅራፉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጅራፍ ላይ አረፈ።ሆኖም ግን ችግሩ በእዚህ ብቻ አልቆመም።
ህወሓት ሰራሹ የጎሳ ጅራፉ አደገ ተመነደገ እና ነቃ! ለካ ህወሓት ቢሰራውም እራሱ ሰሪውን መግረፍ ይችላል። ህወሓት የኢትዮጵያን ፓርላማ መስከረም ወር ላይ ሲከፍት ኢትዮጵያዊ ለዛን አጥፍቶ የተጣፈ ሱሪ የመሰሉ በርካታ የክልል ባንዲራ የያዙ ሕፃናትን እያስያዘ የኢትዮጵያን የነበረ ሰንደቅ አላማ ስያኮስስ መኖሩ ይታወቃል።በትግራይ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በበለጠ ሕዝብ የህወሃትን አርማ የያዘ ጨርቅ የበለጠ እንዲከበር ሲያደርግ ታይቷል።አቶ መለስም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ''ጨርቅ ነው ከጨርቁ በስተጀርባ'' እያሉ ለማናናቅ የሞከሩት የህወሓት አርማን ለማጉላት የታሰበ ሃሳብ አካል ነው።
ዛሬ ግን የህወሓት ጅራፍ አድጎ ጥያቄ አነሳ! በኦሮምያ በተነሳው ሕዝባዊ አመፅ የጅራፍ ገማጁን የአቶ መለስን ፎቶ ግራፍ አውርዶ የኦነግ አርማ የያዘ ጨርቅ ተሰቀለ።የጎሳ ፖለቲካ ጅራፍ ሲሆን መጀመርያ አለመግመድ ጥሩ ነበር።ከገመዱም ቶሎ አቁሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ መከፋፈል ማቆም እና የአገሪቱን አንድነት የሚጠብቅ ሥራ ላይ ማትኮር፣ዲሞክራሲን በእውነት ማስፈን፣ ሕዝብ የመናገር እና ሃሳቡን የመግለጥ መብቱን ማክበር ለእዚህ ጊዜ ይጠቅም ነበር።
ባጭሩ ህወሓት የጎሳ ፖለቲካ ጅራፍ ገምዳ የኢትዮጵያን ሕዝብ እገርፍበታለሁ ብላ አሰበች።ጅራፉ ግን አድጎ እና ተመንድጎ እራሷን ሕወሃትን አደጋ ላይ ጣላት።ቅንነትን መሰረት ያደገ፣ የሕዝብን አንድነት የሚጠብቅ እና ከጎጥ ፖለቲካ የራቀ ፖለቲካ መከተል ጥቅሙ ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም ለእራሷ ለሕወሃትም ይበጃት ነበር።ክፋቱ ግን ህወሓት የገመደው ያቀጣጠለው የጎሳ ፖለቲካ ጅራፍ ለኢትዮጵያም ሌላ ፈተና እንዳያመጣ አሁንም ሁሉም ወገኖች የማንነት ክብርን ጠብቆ የዜግነት ፖለቲካን ማራመድ ብቸኛው መውጫ መሆኑን ማወቅ አለባቸው።ዛሬ ላይ ሆነው የጎጥ ጅራፍ የሚገምዱቱም ነገ እንደህወሓት መልሶ እንደሚገርፋቸው ማወቅ አለባቸው።ከማትወጡበት ማጥ ከመግባት በፊት ከህወሓት ከእራሷ ተማሩ።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
የካቲት 15/2008 ዓም (ፈብሯሪ 23/2016)
No comments:
Post a Comment