ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, August 16, 2015

ሰበር ዜና - ''በምግብ እራሳችንን ችለናል'' ብለው የነበሩት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ ካለፈው የካቲት/2007 ዓም ጀምሮ እንደነበር ዛሬ እሁድ ነሐሴ 10/2007 ዓም አመኑ (የጉዳያችን አጭር ጥንቅር)

ፎቶ - የዓለም ምግብ ፕሮግራም

ኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ እንደተጋረጠባት የሰሞኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መግለጫዎች እና የዜና አውታሮች ያረጋገጡት ሀቅ ነው።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የሁለት አሃዝ እድገት ላይ ነኝ ያለው የኢህአዴግ/ህወሓት ስርዓት ስለ ስጋቱም ሆነ ሊከሰት ስለሚችለው አደጋ አንዳችም ማብራርያ አልሰጠም።ይልቁንም በየካቲት ወር ላይ የህወሓት 40ኛ ዓመት በሚል በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከሀገሪቱ ካዝና ወጥቶ መባከኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ዛሬ ነሐሴ10/2007 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ''የዲያስፖራ ድግስ ማጠቃለያ'' በተባለ ዝግጅት ላይ ከትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ድርቁን አስመልክቶ በተጠየቁት ጥያቄ ላይ የሰጡትን ምላሽ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በምሽት የዜና እወጃ መርሃ ግብሩ ላይ አቅርቦታል።በዘገባው መሰረት የድርቁ አደጋ ከየካቲት ጀምሮ የተከሰተ መሆኑን አቶ ሃይለማርያም በንግግራቸው ወቅት ጠቁመዋል።ቀደም ብለው  ስለድርቁ አንዳችም ያልተነፈሱት አቶ ሃይለማርያም በዛሬው ንግግራቸው ላይ ግን  ''ድርቅ ካሊፎርንያም አለ (ተሰብሳቢው አጨበጨበ)፣አውስትራሊያም ድርቅ አለ'' (አሁንም ግራ በሚያጋባ ሁኔታ አጨበጨበ በማጨብጨብ ችግር ይፈታ ይመስል)  አቶ ሃይለማርያም ቀጠሉ  ''ከየካቲት እስካሁን ድረስ ድርቁ ቢኖርም አንድም ሕፃን ወደ እርዳታ ካምፕ አልገባም '' ሲሉ ተደምጠዋል።ይህ የአቶ ሃይለማርያም ንግግር ስርዓታቸው ድርቁን ከአለፈው የካቲት ጀምሮ መከሰቱን በትክክል ያውቅ እንደነበር እና ለሕዝብ ይፋ ሳያደርግ መቆየቱን በማያሻማ ሁኔታ አመላካች ነው።

አቶ ሃይለማርያም በዛሬው ንግግራቸው ላይ ሁለት የተምታቱ ነገሮችም ተናግረዋል።በአንድ በኩል ድርቅ ቢኖርም ረሃብ አልተከሰተም የሚል መልእክት ካስተላለፉ በኃላ መልሰው ''ከፍተኛ የዝናብ መቆራረጥ በምሥራቃዊው ክፍል ከላይ እስከታች አጋጥሞናል መንግስት ውሃ በማሰባሰብም ጥረት እያደረገ ነው'' ሲሉ ግራ አጋብተውናል። በድርቅ ወቅት የትኛውን ውሃ ነው መንግስታቸው እያሰባሰበ ያለው? ''መንግስት ውሃ ለማሰባሰብ እየሞከረ ነው'' ማለት በራሱ ምን ማለት ነው? 

አቶ ኃይለ ማርያም ይህንን ይበሉ እንጂ እውነታው ግን የተለየ ነው።በምስራቃዊ፣ደቡባዊ እና ሰሜን ምስራቃዊ የኢትዮጵያ ክፍል በከፍተኛ የዝናብ እጥረት ውስጥ እንደሚገኙ እና በተለይ ከእዚህ ወር በኃላ አመታዊ የክረምቱ የዝናብ ወቅት ያላገኙ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚጠቁ የሰሞኑ አለማቀፍ ዘገባዎች ያመለክታሉ።''ኦል አፍሪካ ዶት ኮም'' ባለፈው አርብ ነሐሴ 8/2007 ዓም ድርቁን አስመልክቶ ባወጣው ዜና ላይ የአፋር ክልል ብቻ ከ300 ሚልዮን ዶላር በላይ የአፋጣኝ እርዳታ ጥያቄ ማቅረቡን ይገልፃል።በእዚህ ሳምንት ታዋቂው የአሜሪካ ''ኤን ኤ ቢሲ'' የተሰኘው የቴሌቭዥን ጣቢያ ቀዳሚ አርእስቱ ውስጥ የኢትዮጵያ ረሃብ አንዱ እና ዋናው የዜና አርስቱ ነበር።''ኤን ኤ ቢሲ''  ቪድዮ ለመከታተል ይህንን ይጫኑ።

አቶ ሃይለማርያም ዝናቡን ያስቀረው ስርዓታቸው አለመሆኑን ለማስረዳት ''መሃላ ቀረሽ'' ንግግራቸው ተቀንጭቦ በቀረበበት ክፍል ላይ ''ዝናብን የአውስትራሊያ መንግስትም ማምጣት አይችልም'' በማለት ዝናብ አውርዱ የተባሉ የሚመስል ንግግር በመናገር ጉዳዩን ለማድበስበስ ሲሞክሩ ትዝብት ላይ ወድቀዋል።አሁንም ድርቁ የውሃ እጥረት ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ/ወያኔ የተሳሳተ የእርሻ  እና የመሬት ፖሊሲ በአንድ በኩል እና በሌላ በኩል ገበሬውን ከመሬቱ በማፈናቀል ገበሬው ዋስትና እንዲያጣ የማድረግ ተግባር ሁሉ ድምር ነው።ድርቅ በማንኛውም ሀገር ይከሰታል።ሆኖም ግን አንድ እራሱን መንግስት ብሎ የሚጠራ አካል የሚወቀሰው ለምን ዝናብ አላወረድክም ተብሎ እንዳልሆነ አቶ ኃይለ ማርያም ከጠፋቸው ሌላው አሳዛኝ ገፅታቸው ነው ማለት ነው።ጥያቄው ድርቅ ስመጣ ከሌላ የሀገሪቱ ክፍል ምርቱ ተገዝቶ ለተጠቃው ሕዝብ ማከፋፈል የአንድ መንግስት ግዴታ ሀሁ ነው።

እዚህ ላይ አቶ ኃይለ ማርያምን መጠየቅ የምፈልገው ''በምግብ እራሳችንን ችለናል'' የሚል ንግግር ከተናገሩ ገና አንድ ዓመት ማስቆጠሩ ነው።ዛሬ ስለ ድርቁ የሚነግሩን መልሰው ደግሞ ''ጥረት ይደረጋል'' እና ሌሎችም ቃላት የሚያሰሙን ለምንድነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚራበው በዝናብ እጥረት ብቻ አይደለም የሀገሪቱን ገንዘብ ለህወሓት፣ኦህዴድ ወዘተ እያላችሁ በሚልዮን የሚቆጠር ሀብት ስለምታባክኑ እና ብሔራዊ ባንክ የስንዴ መግዣ መስጠት ስለማይችል ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚራበው በካድሬ የሚመራው መንግስትዎ ለችግሮች ቅንጣት ታክል መፍትሄ የማምጣት አቅም ያላቸው ስብስብ ስላልሆነ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚራበው በሙስና የተተበተቡ ባለስልጣናት በሕግወጥ መንገድ ሀብት እያሸሹ ሀገሪቱ በእራሷ መንገድ እንዳትቆም ስላደረጉ ነው።በመጨረሻም ከአቶ ኃይለ ማርያም ንግግር በኃላ ኢቲቪ ለድርቁ የእንግሊዝ ሰንደቅ አላማ የታተመበት የእርዳታ እህል በማዳበርያ ተጭኖ ሲወርድ ያሳያል።ይህ የሆነው ''የዲያስፖራ በዓል'' ብለው ከሸራተን በውድ ዋጋ በመጣ ምግብ እና ውስኪ የሀገሪቱን ሀብት ሲያባክኑ በከረሙ ተመሳሳይ ሳምንት ውስጥ ነው።ይህ ብቻ አይደለም ይህ የሆነው ቀደም ብለው አቶ ሃይለማርያም ''ወዳጆቻችን የውጭ ሀገር መንግሥታት ''እስኪ እንያቸው'' ብለው  ዳር ቆመው እየተመለከቱን ነው'' ማለታቸው በተሰማ በደቂቃዎች ውስጥ ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

ነሐሴ 11/2007 ዓም (ኦገስት 17/2015)

No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...