ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, August 20, 2015

በአንደኛ ዙር 14 ሚልዮን ርሃብተኛ አምራቹ የኢህአዴግ/ወያኔ የትራንስፎርሜሽን እቅድ በሁለተኛው ዙር ስንት ሊያመርት አቀደ? እና አቶ ኃይለ ማርያም፣እውነት ለርሃብ መንስኤ የአየር ንብረት ለውጥ ብቻ ነው? (ጉዳያችን GUDAYACHN )

????????????????????

ሰሞኑን የአራት ኪሎ ቅምጥሎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለሌላ ዙር የጥፋት ተግባር ለመሰማራት ደፋ ቀና እያሉ ናቸው።ርሃቡን በአየር ንብረት ሰበብ የጥፋት ተግባራቸውን ማጠብያ ሰበብ አድርገው በማቅረብ እና 14 ሚልዮን ርሃብተኛ ያፈራውን የመጀመርያ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተብዬ በሌላ ማደናገርያ ሁለተኛ ትራንስፎርሜሽን እቅድ በሚል ማደናገርያ ለመተካት።

በአንደኛው የትራንስፎርሜሽን እቅድ ውጤት መሰረት 14 ሚልዮን ርሀብተኛ አመረታችሁ። በሁለተኛውስ ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስንት ርሀብተኛ ልታፈሩ አቀዳችሁ? 

የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጧት ማታ ኢትዮጵያ አደገች እያለ እንደሚለቀው ተራ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የ2015 ዓም እ አ አቆጣጠር የሰው ልማት ሪፖርት የሚያሳየው ከ186 የዓለም ሃገራት ውስጥ ኢትዮጵያ  173ኛ መሆኗን እና ከአብዛኛዎቹ የሳሃራ በታች ካሉ ሃገራት አንፃርም መጨረሻ ላይ መሆኗን ነው። ''Even though Ethiopia is one of the 10 countries globally that has attained the largest absolute gains in its HDI over the last several years, it still ranks 173rd out of 186 countries in the latest UNDP Human Development Report.'' UNDP National Human Development Report 2015 Ethiopia.

ይህንን ውርደታችንን ለእሩብ ክ/ዘመን ማሻሻል ያልቻለው ወያኔ በምርጫው 100% አሸነፍኩ እያለ አይን ያወጣ ፕሮፓጋንዳውን በሚነዛባት ሀገር ለሌላ ድህነት ሕዝቡን ለመዳረግ ''ሁለተኛ የትራንስፎርሜሽን እቅድ'' እያለ ማደናገር ይዟል።እውነታው ግን ከቅኝ ግዛት ከተላቀቁ ሃገራት አንፃር ሲታይም በካድሬ ምሁር ነን ባይ እቅድ የሚነደፍልን እኛ በብዙ ደረጃ ወደኃላ የቀረን መሆናችንን ነው።ለምሳሌ በ 2014 እአውሮፓውያን አቆጣጠርም በወጣው ዘገባ መሰረት አንዳችም ለውጥ አለማሳየታችን የዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት ዘገባም ያሳያል።በእዚህም መሰረት- 
ሱዳን  በሰባት ደረጃ ቀድማን 166ኛ፣
ጋና በሰላሳ ሰባት ደረጃ ቀድማን 138ኛ፣
ኬንያ በሃያ ስድስት ደረጃ ቀድማ 147ኛ፣
ዑጋንዳ በዘጠኝ ደረጃ ቀድማ 164ኛ፣
ናሚብያ በአርባ ስድስት ደረጃ ቀድማን 127ኛ፣ይቀጥላል። ዝርዝሩን ይህንን በመጫን ይመልከቱ። 

እውነታው ይህ ሆኖ ነው እንግዲህ የመጀመርያው ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተብዬ ጥቂት የስርዓቱን ሰዎች በሀብት ማዕበል ውስጥ መክተቱ እና ነውራቸው ለዓለም አደባባይ ተርፎ በለንደን አየር መንገድ ሳይቀር በእዚህ ሳምንት መጀመርያ በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች እንደተዘገበው ከ5 ሚልዮን የእንግሊዝ ፓውንድ በላይ በግለሰቦች ቦርሳ ተይዞ ሲወጣ እየታየ አቶ ሃይለማርያም ''አይናቸውን በጨው አጥበው'' ስለ ''ሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን'' እያሉ መስበክ ጀምረዋል።ስለሀገር አስተዳደርም ሆነ ስለልማት አንዳች በማያውቁ የካድሬ ስብስብ የተዘጋጀው ሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢትዮጵያን ለበለጠ መቀመቅ ለመክተት ካልሆነ በቀር ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንዳች የማይፈይድ ለመሆኑ ብዙ እማኝ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል።


ኢትዮጵያን የሚያህል በርካታ የተማረ የሰው ኃይል ያላትን ሀገር ምሁራኑን በእስር ቤት አጉራችሁ የቀረውን ከሀገር አሰድዳችሁ ከመሰል ካድሬዎቻችሁ ጋር የአምስት ዓመት እቅድ እያላችሁ ስትዘባበቱ መስማት በእራሱ የሀገሪቱን የውርደት ደረጃ አመላካች ነው።የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት፣ፖለቲካ፣እና ማህበራዊ ሕይወት ዘረኛ ለሆነ ርኩስ መንገዳችሁ እንዲመች እያደረጋችሁ መቀየሳችሁን እናንተ ብቻ የምታውቁት ከመሰላችሁ መሳሳታችሁን እወቁት።በወረደ አስተሳሰብ ውስጥ ተዘፍቃችሁ በኢትዮጵያ ስም በአደባባይ ላይ ስትናገሩ ከመስማት በላይ ምን ውርደት አለ? ሰሞኑን አቶ ኃይለ ማርያም የከሸፈውን ያለፈውን እቅድ እያድበሰበሱ ስለመጪው ማውራት ሰሞኑን የተያዘ አዲሱ ፋሽናቸው ሆኗል።ለመሆኑ የሚቀጥለውን የአምስት ዓመት እቅድ የሚቀይሱት ምሁራን ሳይሆኑ ካድሬዎች መሆናቸውን ''ሪፖርተር ጋዜጣ'' በአንድ ወቅት የዘገበውን መመልከት በእራሱ ነገሩ ሁሉ ''ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ'' መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም።ለሌላ 5 አመታት የ90 ሚልዮን ህዝብን ዕጣ እንወስናለን ብለው ሁለተኛ ትራንስፎርሜሽን እቅድ እናቅድላችሁ ያሉንን ባለ ጊዜዎች ይህንን በመጫን ተመልከቱ። 

በልማት ጥናት ዘርፍ እቅድ አዘገጃጀት ልምድ ያላቸው ምሁራን እና የሀገሪቱን ሕዝብ ማወያየት 100% አሸነፍኩ ላለን እፍረተ ቢስ ምኑ ነች?  ከሁለት ሳምንት በኃላ ኢህአዴግ አዲስ እቅድ አወጣ ብለው እየተዘጋጁ እና መስከረም ላይ ምክርቤቱ አፀደቀው ሊሉን አፋቸውን እያሟሹ ባለበት ወቅት ሕዝብ አወያየን ለማለት አቶ ሃይለማርያም ዛሬ ነሐሴ 13/2007 ዓም ኢቲቪ ላይ ቀርበው ግራና ቀኛቸውን ያልለዩ ምልምል ካድሬዎች ሰብስበው በሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ተወያዩ የሚል ፌዝ አይሉት ቀልድ ማስደመጣቸው ነው።''ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ያፅናሽ'' ማለት የእዚህ ጊዜ ነው።የሀገር ሀብት በጥቂት ካድሬዎች ያውም በዘር እና በጎሳ በተጠራሩ እጅ መውደቁ ይዘገንናል።

አቶ ኃይለ ማርያም እውነት ለርሃብ መንስኤ የአየር ንብረት ለውጥ ብቻ ነው? 

የዓለም ምግብ ፕሮግራም (FAO) በድረ-ገፁ ላይ ''ለረሃብ ምክንያት የሚሆኑት ምክንያቶች ምንድናቸው? '' በሚል ርዕስ ስር ባሰፈረው ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ የአየር ንብረት መዛባት አንዱ ምክንያት እንጂ ዋናው አለመሆኑን ያብራራል።በዓለም አቀፍ የልማት ጥናት ባለሙያዎች ገለፃ መሰረት ርሃብ ሰው ሰራሽ ክስተት እንደሆነ ያስረዳሉ።ይህ ማለት ግን የአየር ንብረት መዛባትን የሰው ልጅ ያስተካክለዋል ማለት ሳይሆን ከአየር ንብረቱ መዛባት በላይ የመንግስት  ቸልተኝነት እና ከሁሉም በላይ የተዝረከረከ አሰራር ውጤት መሆኑን የዓለም ምግብ ድርጅት ይገልፃል።

በእዚህም መሰረት በዓለም ምግብ ድርጅት ማብራርያ መሰረት የርሃብ ምክንያቶች በርካታ መሆናቸውን እና በዋናነት ግን ስድስት መሆናቸውን ይገልፃል። በቅድምያ ፅሁፉ በመግቢያነት የሚይስቀምጠው ነጥብ ''ዓለም ለ7 ቢልዮን የዓለማችን ሕዝብ በቂ ምርት ያመርታል'' በማለት ይጀምርና ስድስቱን በአንድ ሀገር ላይ ርሃብ የሚከሰትባቸውን ምክንያቶች ይዘረዝራል።

1/ ድህነት (Poverty trap)

2/ በእርሻ ላይ በቂ መዋለ ንዋይ አለመመደብ ( Lack of investment in agriculture)

3/ የአየር ንብረት ለውጥ ( Climate and Weather)

4/ ጦርነት እና የህዝብ ከስፍራው መፈናቀል (War and displacement)

5/ ያልተረጋጋ የምግብ ገበያ ( Unstable Market) 

6/ የተረፈ ምግብ ብክነት ( Food Wastage)
ዝርዝሩን ለማየት ይህንን ይጫኑ።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የርሃብ አደጋ እንዳንዣበበባቸው በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች መዘገቡ ይታወሳል።አቶ ኃይለ ማርያምን ለናሙናነት ያስቀመጠው የወያኔ መንግስት ግን ለሕዝቡ ትክከለኛውን የአደጋውን ጥልቀት ከማስረዳት ይልቅ ''ድርቅ በአሜሪካም፣አውስትራልያም አለ'' እያለ ከመግለፅ ያለፈ ተግባር ሲፈፅም አይታይም።የሰው ሕይወትን የማዳን ሥራ ከመስራት ይልቅ የማደናገርያ ቃላትን መደርደር ከተጠያቂነት አይድንም።አቶ ሃይለማርያም የድርቅ መንስኤ የአየር ንብረት መዛባት ብቻ እንደሆነ አድርገው የገለፁበት ንግግር ባለፈው ሳምንት ስሰማ አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚናገረው ንግግር አይመስልም።በሃያ አንደኛው ክ/ዘመን ላይ ተቀምጠው ህዝብን ለማታለል ለሚታትር ያውም በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የተቀመጠ ሰው ከማየት የበለጠ ምን ያሳፍራል? 

ከላይ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከዘረዘራቸው ምክንያቶች ውስጥ አምስቱ የማን ተግባራት ናቸው? ለአቶ ሃይለማርያም እና ለአራት ኪሎ ቅምጥል ባለስልጣናት የሚቀርብ ጥያቄ ነው።የተረጋጋ የምግብ ገበያ መፍጠር የማን ሥራ ነው? የህዝብ መፈናቀልን መከላከል የማን ሥራ ነው? (አፈናቃዩ በመንግሥትነት የተሰየመ መሆኑ ደግሞ ሌላው አስደንጋጭ ጉዳይ መሆኑን ሳንረሳ)፣ጦርነት እና የጦርነት ስጋት እንዳይኖር ማድረግ የማን ሥራ ነው?  በእርሻው ዘርፍ ላይ በቂ መዋለ ንዋይ እንዲኖር ማድረግ የማን ሥራ ነው? ድህነትን መቀነስ የማን ሥራ ነው?  

ባጠቃላይ ኢህአዴግ/ህወሓት የሩብ ክ/ዘመን ተግባሩ ከበቂ በላይ ማንነቱን እና ሀገር የመምራት ደካማ አቅሙን ብቻ ሳይሆን በመጪው ዓመታት ኢትዮጵያን ሊከታት ያሰበበት ትልቅ አዘቅት መጠን በትክክል እየታየ ነው።የመጀመርያ፣ሁለተኛ ትራንስፎርሜሽን እያሉ ማደናገር ጊዜ ያለፈበት የፈዘዘ እቅድ ነው።ለርሃቡ የአየር ንብረትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ደግሞ የበለጠ ምን ያህል ከሳይንስ የራቁ ቅምጥሎች እየመሩን እንዳሉ አመላካች ነው።በእርግጥ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ይህንን ስርዓት የምትገላገልበት ጊዜ መፋጠን እንዳለበት አእምሮ ላለው ሰው ሁሉ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በእራሳቸው በቂ ናቸው።


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ነሐሴ 14/2007 ዓም (ኦገስት 20/2015) 

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...