ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, August 1, 2015

''ሉዓላዊነት ማለት በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊን መብት ማስክበርም ጭምር ነው''።ለአውራምባው ድረ-ገፅ አቶ ዳዊት እና ለ''ቲጂ'' ''ዩቱዩብ'' አዘጋጅ አቶ መስፍን በዙ የተዘጋጀ ምላሽ (የጉዳያችን ማስታወሻ)



 ''በባህር ማዶ ኢህአዴግን የሚቃወሙ ከ9 እስከ 10 የሚሆኑ ናቸው።ብዙዎቹን በአካል አውቀዋቸዋለሁ።በታክሲ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው'' የአውራምባ ድረ-ገፅ አዘጋጅ አቶ ዳዊት

 ''ሰልፍ የሚወጡት ሰዎች እየተከፈላቸው ነው'' አቶ መስፍን በዙ የቲጂ ''ዩቱዩብ'' አዘጋጅ 

ኢትቪ ዶክመንተሪ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 25/2007 ዓም በውጭ የሚኖሩ የሀገራቸው ጉዳይ እንደ እሳት የሚያንገበግባቸው ኢትዮጵያውያንን የሚዘልፍ ፕሮግራም አስተላልፏል።ፊልሙ የአውራምባ ድረ-ገፁን አቶ ዳዊትን፣አቦይ ስብሐት፣መስፍን በዙ ሲናገሩ ያሳያል።አቶ ሬድዋን ልብስ ሊገዙ ሱቅ ሲገቡ የዘለፏቸውን ሰዎች እና ኢሳት ድንቁን ጋዜጠኛ መሳይ መኮንንን አክትቪስቶቹን ሲያወያይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳያል።እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሳትን በኢቲቪ ሲመለከት ''አንበሶቹ መጡ'' ሲል በአይነ ህሊና ይታያችሁ።አቶ መስፍን በዙ አሜሪካ የሚገኘው የቲጂ ዩቱዩብ (ለአቅመ ቲቪ አለመድረሱን የማይስማማ የለም) ''ሰልፍ የሚወጡት ሰዎች እየተከፈላቸው ነው'' ብሉ ሲናገር  የኢትቪ ጋዜጠኛ ነጠቅ አደረገና ''ማን ነው የሚከፍላቸው?'' ሲል በርቀት ተሰማ (ኤዲት ሳይደረግ መሆን አለበት) አቶ መስፍን እንዳልሰማ አለፋት። የአውራምባ ድረ-ገፅ አዘጋጅ አቶ ዳዊት''በባህር ማዶ ኢህአዴግን የሚቃወሙ ከ9 እስከ 10 የሚሆኑ ናቸው።ብዙዎቹን በአካል አውቀዋቸዋለሁ።በታክሲ ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው'' በማለት ለማቃለል ሲሞክር በጣም ያሳፍራል።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላ አቶ ዳዊት ቀደም ብሎ ''በአሜሪካ ያሉት ተቃዋሚዎች  ከ 9 እስከ 10 የሚሆኑ ናቸው'' ያለውን እረሳው መሰለኝ  ''የሚቃወሙት በኢሳት ዙርያ ናቸው'' አለ እና የማይገናኝ ነገር ማውራት ጀመረ ''የኢሳት አማካሪዎች እነ ካሳ ከበደ  እና ሻለቃ ወልደ ጊዮርጊስ ናቸው'' በማለት አስቂኝ ንግግሩን ቀጠለ።አላማው ''ኢሳት የደርግ ነው'' የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው።እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ሁሉንም ነገር ደርግ ደርግ  እያላችሁ ደርግን የማያውቀውን ትውልድ ደርግን አስወድዳችሁት ይሄው ባለፈው ግንቦት በሊብያ ላለቁት ወገኖቻችን አዲስ አበባ ሰልፍ የወጡ ወጣቶች ''መንጌ ና!'' እያሉ እንዲዘፍኑ አደረጋችሁ።ኢሳት ደርግ ነው ካሉ ደርግ ጥሩ መንግስት ነበር።ብለው የሚያስቡ ኢህአዴግ ከገባ የተወለዱ ብዙ ወጣቶች አሉ።ዛሬ አቶ ዳዊት ኢሳትን የሚያማክሩ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው ሲል ተሰማ።እዚህ ላይ ግን ህወሃት የቤላሩስ የአየር ኃይል አብራሪ እየቀጠረ ሀገር እየጠበኩ ነው የለን የለም እንዴ? በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የደርግ መኮንኖች ያላቸውን በልመና ከየሀገሩ እየሰበሰበ አማክሩኝ ማለቱን አቶ ዳዊት አላወቁ ይሆን? ኢሳት የሚተዳደረው በሕዝብ የምመከረውም በሕዝብ መሆኑን በአንድ ወቅት አቶ ዳዊት በምድረ አሜሪካ ስለ ኢሳት ታላቅነት በአሜሪካ ለኢሣት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ እንዲህ ብሎ ነበር ''ኢሳት ሲጀምር ሀገር ቤት ነበርኩ።መንግስት የተገለበጠ ነበር የሚመስለው።ትልቁ ትግል መሆን በሚድያ ነው።ኢሳትን መደገፍ አለብን'' ብሎ ነበር።የአቶ ዳዊትን ከሁለት ዓመት በፊት ውዳሴ ኢሳት ያሰሙበት የፊልም ድርሳን ለመስማት ይህንን ይጫኑ።

የዛሬ የኢቲቪ ፕሮግራም ቀጠለ። አቶ ዳዊትም እንዲህ አለ '' እነኝህ (ተቃዋሚዎችን ማለታቸው ነው) ዜግነት የቀየሩ ናቸው እና ስለ ኢትዮጵያ ምን አገባቸው?''። ዳዊት አሁን 'ወጥ' ቢጤ እረገጠ።አቶ ዳዊት ጋዜጠኛ በመሆኑ  በመጠኑም ቢሆን የውጭውን ዓለም አይቶታል የሚል ያነበብኩ መስሎኝ ነበር። በምሳሌ ላስረዳው መሰለኝ።ለመረጃ ያህል በውጭ ሀገር ብዙ ኢትዮጵያዊ  ''የአምነስቲ ኢንተርናሽናል'' አባል አለ።እኔም እራሴ አባል ነኝ። አምነስቲ በርማ ለታሰረው ለማላውቀው ወንድሜ ድምፄን እንዳሰማ ይጠይቀኛል።ጠይቆኛልም።እኔም ሳላቅማማ ድምፄን አሰማለሁ፣ፔቲሽን እፈርማለሁ፣ ካስፈለገ ሰልፍ እወጣለሁ።ሌላ ምሳሌ ልጥቀስለት በኖርዌይ ቀይ መስቀል አባልነቴ ደግሞ ለሶርያ ሕፃናት በኦስሎ ጎዳና ''የሶርያ ሕፃናትን እርዱ'' እያልኩ ገንዘብ አሰባስቤ ሰጥቻለሁ።እና እንደ አውራ አምባው ዳዊት በአንዱ ክፍለ ዓለም ያለው ጉዳይ ሌላው ዓለም አያገባውም ሊለን ነው።ትውልደ ኢትዮጵያዊ ስለ በርማ ነፃነት፣ስለ ሶርያ ሕፃናት እልቂት አያገባውም ሊለን ነው።

የዳዊት በእርግጥ ደፈር ይላል።ዳዊት ትውልደ ኢትዮጵያዊው እትብቱ ስለተቀበረባት ኢትዮጵያ አያገባውም የሚል የትምክህት ንግግር ነው በማን አለብኝነት ያሰማን።አቶ ዳዊት ይህንን ዘመን አለፍነው እኮ! አሸባሪ እና ህዝብን በጎሳ የሚከፋፍል መንግስት ከስልጣን መውረድ አለበት ብሎ መጮህ ዓለም አቀፍ ግዴታን መወጣት ነው።አይደለም በደሉ የተፈፀመበት ሀገር ተወላጅ ቀርቶል ዳዊትን የምጠይቀው ኢህአዴግ/ህወሓት ለምንድነው አንዴ ሱማሌ፣ሌላ ጊዜ ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ወጣቶች እየላከ በጦርነት የሚማግደው? በእዚህ አነጋገር ፕሬዝዳንት ኦባማም አፍሪካ ህብረት ላይ ቆመው የአራት ኪሎ ቅምጥሎችን ''ስልጣን ልቀቁ ለአዲሱ ትውልድ አስተላልፉ'' ብለው እስከአንገታቸው የነገሯቸው ኢትዮጵያዊ ሆነው እንዴ? አቶ ዳዊት ዓለም ተቀየረ። አራት ኪሎዎች በጎሳ ሲከፋፍሉት ዓለም አንድ ሆነ።እዚህ ላይ ፕሬዝዳንት ኦባማ ሉሲን ካለነገራቸው የጎበኙት የጎጥ ፖለቲካ ድንቡሽት ላይ እንደተሰራ  ለወቅቱ ባለሥልጣኖቻችን  ለመንገር መሆኑን መጠርጠሬን መደበቅ አልችልም።ሉሲን ከጎበኙ በኃላ በንግግራቸው ''ሁላችን ቅድመ ምንጭ ሉሲ'' በማለት የጎጥ ፖለቲካን ''አንድነት 101'' ኮርስ መስጠት እንደፈለጉ የገባን ገብቶናል። 
ዳዊት ግን አቶ ኦባማን እርስዎ አሜሪካዊ ነዎት ስለ አፍሪካ ምን አገባዎት ብሏቸው ይሆን? ይህ ማለት አቶ መለስ የሱማልያ ፓስፖርት ነበራቸው።ይህ ማለት በስህተት ነው ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ማለት ጋር እኩል ነው።

 በእዚሁ የቅዳሜው ኢቲቪ ፊልም ላይ ዋሽንግተን መጥቶ የተወቀሰ ባለስልጣን ሁሉ እንዳይቀር የተባለ ይመስል አቦይ ስብሃትም ታድመው ነበር። ለሚሉት ነገር ጠያቂ እና ተቆጪ  የሌለባቸው አቦይ ስብሐት ''እነኝህ ሰዎች (ተቃዋሚዎች ማለታቸው ነው) የሚናቁ አይደሉም'' ብለው ፈርጠም ብለው ተናገሩ።የአቦይ ይሻላል።ቢያንስ አቦይ በተደጋጋሚ መግለጫ የሚሰጡበትን ኢሳትን አልተሳደቡም። ተቃዋሚዎችን የሚናቁ አይደሉም ሲሉ ግን የተቃዋሚዎችን አቅም እንደሚፈሩትም ከፊታቸው ይታይ ነበር።

በእዚሁ ፊልም ላይ አስቂኝ የኢቲቪ አዘጋገብም ትመለከቱ እና አሁን ማንን ነው የሚያታልሉት? የሚያስብል ትዕይንት ታያላችሁ።ቴሌቭዝኑ የኦባማን ንግግር እየቀነጠበ ሲያቀርብ የአፍሪካ ህብረት ንግግራቸውን አንዲት ቃል አላሰማም።የአፍሪካ ህብረት የፕሬዝዳንት ኦባማ ንግግር አሁንም ድረስ በአምባገነኞቹ ጆሮ በምሽትም ያስገመግማል መሰል።በጣም ሲፈሩት ያስታውቃል።ኢቲቪ ፕሮፓጋንዳ አልተሳካለትም። አቦይ ስብሐት፣አቶ ሬድ ዋን እና የሱማልያው ክልል ፕሬዝዳንት ተጠያቂነት አለባችሁ ያሉ አክትቪስቶች በአሜሪካ ሆቴሎች በግልፅ ሲጠይቁ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳየው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ''ለካ እዚህ አንበሳ ትመስላላችሁ ውጭ ስትሄዱ ግን...'' እንዲል አደረገው።በነገራችን ላይ አክቲቪስቶች የሀገራቸውን መሪዎች እና ባለስልጣናት በውጭ ሀገር ሲያገኙ ማሸማቀቃቸው በኢትዮጵያ የተጀመረ አይደለም በርካታ የአፍርካ እና የእስያ መንግሥታት ያጋጠማቸው ነው።የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቡሽ ይልቁንም በአደባባይ ጫማ ተወሯሮባቸዋል።ሆኖም አንዳቸውም ተደፈርን ብለው አልፎቀሩም እንደ ኢቲቪ በውጭ የሚኖር ዜጋቸውን ዝቅ የሚያደረግ ፕሮግራም አላዘጋጁም።ውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በሆነ ባልሆነ ከመስደብ እና ዝቅ አድርጎ ከመመልከት (አቶ ሃይለማርያም ዶሮ ላደርስ ጀርመን ሄጄ ያሉትን ጨምሮ) እና የስድብ ናዳ ከማውረድ በሊብያ ለተሰዉት ወገኖቻችን ሰልፍ የወጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ይዘው የወጡት መፈክር መጥቀስ እፈልጋለሁ።''ሉዓላዊነት ማለት በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊን መብት ማስክበርም ጭምር ነው''።  


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ሐምሌ 26/2007 ዓም (ኦገስት 2፣2015)

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...