ከእዚህ በታች የሚገኘው ፅሁፍ የተወሰደው ከማኅበሩ ድረ-ገፅ http://eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1495-2014-06-21-08-20-51 ላይ ነው ።
''በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል የኦሮምኛ ድረ ገጽ አገልግሎት በቅርቡ እንደሚጀምር የዋና ክፍሉ ሓላፊ ዲያቆን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ገለጹ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊት የጠበቁ ትምህርቶችን በኦሮምኛ ቋንቋ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ዘዴዎች ለምእመናን ለማሰራጨት እቅድ ከያዘ መቆየቱን የገለጹት ዲያቆን ዶ/ር መርሻ፤ የድረ ገጽ አገልግሎቱ ቅድሚያ ተሰጥቶት ለምእመናን ተደራሽ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም መሠረት “በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የኦሮምኛ ድረ ገጽ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፤ ወደፊት የኅትመትና የብሮድካስት ዝግጅቶችን ለምእመናን ለማዳረስ ማኅበሩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
የኦሮምኛ ዝግጅት ንዑስ ክፍል አስተባባሪ ዲ/ን መዝገቡ ከፍያለው ለኦሮምኛ ድረ ገጽ መከፈት ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ሲገልጹ “በኦሮሚያ ክልል ምእመናን ስለ እምነታቸው በቋንቋቸው መማር አለመቻላቸው፤ በቋንቋው የተዘጋጁ ሃይማኖታዊ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ውጤቶች አለመኖር እና ምእመናን በሌሎች የእምነት ተቋማት መወሰዳቸው ነው” በማለት ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት እና ያሉትን ምእመናን ለማጽናት፤ የጠፉትንም ለመመለስ እንዲቻል ከዐውደ ምሕረት ስብከት በተጨማሪ በመገናኛ ብዙኀን ዘዴዎች ወደ ምእመናን ለመድረስ አዲስ የተዘጋጀው ማኅበራዊ ድረ ገጹ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡
በድረ ገጹም ትምህርተ ሃይማኖት፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ነገረ ቅዱሳን፤ ስብከት፤ ለጥያቄዎች ምላሽ /ከምእመናን ለሚጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት/፤ መዝሙር እና ኪነጥበብ ወዘተ. . . የተካተቱበት ሥራዎች እንደሚቀርቡ ዲ/ መዝገቡ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የድረ ገጹ አድራሻ፡- www.eotcmk.org/afaanoromo
በተያያዘ ዜና ከዚህ ቀደም ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝኛ ድረ ገጽ በቅርቡ የሚጀምር ሲሆን፤ የድረ ገጹ አድራሻ፡- www.eotcmk.org/site-en መጎብኘት ይቻላል፡፡''
No comments:
Post a Comment