የካቲት 12 /1929 ዓም አዲስ አበባ ከ ሰላሳ ሺህ በላይ ነዋሪዎችዋ በ አንዲት ጀንበር ሰማአትነት የተቀበሉባት ቀን ነበረች። ይህ ታሪክ አስተማሪነቱ ዘርፈ ብዙ ነው።የሀገራችን ፖለቲካ የየካቲት 12 አይነት ታሪኮችን ለትውልዱ በማስተማር በተለይ ከታሪክ አንፃር ብዙ ቁም ነገር ሊሰራበት ይገባል። ለመሆኑ የዛሬ ስማንያ አራት ዓመት አዲስ አበባ ምን ሆነች? ብዙዎቻች ታሪኩን የምናውቀው የሚመስለን ግን አውቀነውም ቁምነገሩን እና አንደምታውን ችላ ያልነው ጥቂቶች አይደለንም።
የዛሬ ሰማንያ አራት ዓመት አብርሃም፣ሞገስ እና ስምዖን በግራዝያን ላይ ባቀናበሩት የ ቦንብ አደጋ (ጣልያን አሸባሪ ብሏቸው የነበረ መሆኑን ሳንረሳ) የጣሉበት እና አዲስ አበባ በ ደም ጎርፍ የታጠበችበት የ መከራ ቀን፣የካቲት 12/1929።
የዛሬ ሰማንያ አራት ዓመት አብርሃም፣ሞገስ እና ስምዖን በግራዝያን ላይ ባቀናበሩት የ ቦንብ አደጋ (ጣልያን አሸባሪ ብሏቸው የነበረ መሆኑን ሳንረሳ) የጣሉበት እና አዲስ አበባ በ ደም ጎርፍ የታጠበችበት የ መከራ ቀን፣የካቲት 12/1929።
አብርሃም ደቦጭ፣ሞገስ አስገዶም እና ስምዖን አደፍርስ እነማን ናቸው?
የአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1936 (1929 ዓም ) የዓለም ፖለቲካ ብዙ አዳዲስ ክስተቶች የታዩበት ነበር።
- የጣልያኑ ፋሺሽት መሪ ሞሶሎኒ የሮማ 'ኤምፓየር' አዲስ መሬት አዲስ አበባን መያዙን ያሳወቀበት፣ ቀደም ብለው ተግባሩን በስውር ሲደግፉ የነበሩ ሀገሮች ማንነታቸው የለየበት፣
- የብሪታንያ ዜና አገልግሎት' ቢቢሲ' የመጀመርያ የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን
የጀመረበት፣
- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡበት ፣
- የጃፓን ባህር ኃይል የ ቻይናን ሻንጋይ ክፍለ ሀገር የወረረበት እና ባጠቃላይ ጊዜው ዓለም ወደ ሁለተኛው ታላቁ ጦርነት ለመግባት አራት አመታት ብቻ ቀርቷት የምትታትርበት ጊዜ ነበር።
አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ከሐማሴን አና አካለጉዛይ (የአሁኗ ኤርትራ)ተነስተው በፋሺሽት እጅ የወደቀችው የሀገራቸውን የኢትዮጵያ አርበኞች ሊቀላቀሉ መጡ።
ከለበሱት ልብስ ውስጥ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አጥፈው ይዘዋል።ህልማቸው፣ሳጋቸውን እየተናነቀ የሚይዛቸው የሀገራቸው መከራ እረፍት ነሳቸው።
በወቅቱ ከነበሩት ትምህርት ቤቶች ጣልያንኛ ተምረው ስለነበር የቅኝ ግዛት ችግርን በ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣውን አንደምታ ከ ጊዜው ፖለቲካ ጋር አዛምደው መረዳታቸው ሌላው የእግር ውስጥ እሳት ነበር።በእዚህ ጊዜ ነበር እንደነሱ በሀገሩ ጉዳይ ውስጡ ይንተከተክ የነበረውን ስምዖን አደፍርስን ያገኙት።
ስምዖን አደፍርስ
''በመናደድ ብቻ መቆም የለብንም ወሳኝ የሆነ ሥራ መስራት አለብን ፋሽሽትን ደሞ ከትጥቅ ትግል በቀር ምንም ሌላ መንገድ የሚዋጋው የለም'' ይላቸው ነበር። ስምዖን አደፍርስ ገና የከተማ መልክ አየያዘች በነበረችው አዲስ አበባ ውስጥ ጅቡቲ ይኖር ከነበረው ወንድሙ በተላከለት ታክሲ ሥራ ላይ ነበር። በ ስራው ላይ አያሌ የ ፋሺሽት ጣልያኖች ግፍ ና በደል እና የሃገሩ የወደፊት እጣ ሲያስበው ንዴት ፣ውርደት ና አልገዛም ባይነት አንድ ላይ ተደባልቀው ውስጡን አናውጠውታል። ይህን ስሜት ይዞ ነበር ሌሎቹ የ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ፍቅር ያንገበገባቸውን ሁለቱን ወጣቶች አብርሃም ደቦጭ ና ሞገስ አስገዶምን ያገኛቸው።
እልል! በሉ ልዕልት ተወለደች
አብርሃም፣ሞገስና ስምዖን በአዚህ ሃሳብ ላይ ሳሉ ነበር የሞሶሎን የኢትዮጵያ ሹመኛ ግራዝያን'' ልእልት ተወለደች ተሰብሰቡ፣ቸርነቴን ተመልከቱ ላብላችሁ፣ላጠጣችሁ''ብሎ በአሁኑ የስድስት ኪሎ ዩንቨርስቲ የየያኔው የአፄ ኃይለስላሴ ገነተ ልዑል ቤተመንግስት የአዲስ አበባን ሕዝብ የጠራው። ይህ አጋጣሚ ለእነ አብርሃም ታላቅ አጋጣሚ ሆነ።በ ድግሱ ላይ ንግግር እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ግራዝያን ላይ የእጅ ቦንብ ወርውረው መግደል የሚል አቅድ አዘጋጁ።ለእዚህ ሃሳብ ደግሞ የእጅ ቦንብ አጠቃቀም መማር ያስፈልጋል።ስምዖን የደጃዝማች አፈወርቅ ወታደሮች በድብቅ አንዲያስተምሯቸው ሁኔታውን አመቻቸ። በየቀኑ ወደ ስፍራው ከ አዲስ አበባ ውጭ ከሁለት ሰዓት በላይ በታክሲው እየወሰደ አስተማራቸው ቀኑ ደረሰ።በአቅዳቸው መሰረት ሞገስ እና አብርሃም ግራዝያንን በቦንብ ከ ገደሉ በሁዋላ በ አሁኑ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን አጥር በኩል ይዘሉና ቆሞ የሚጠብቃቸው ስምዖን ታክሲ ውስጥ ገብተው ከአዲስ አበባ መውጣት ቀጥለውም ሰሜን ሸዋ ላይ በውጊያ ላይ ካለው የራስ አበበ አረጋይ አርበኛ ጦር ጋር መቀላቀል እና መዋጋት የሚል ታላቁ አቅድ ብለው መከወን ተግባራቸው ሊሆን' ቃል ለምድር ለሰማይ 'መሀላቸው ነበር።
የካቲት ከገባ ገና አስራ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።የ አዲስ አበባ አየር ደመናማ ነበር። የተለመደው የበልግ ዝናብ ሊመጣ ዳር ዳር የሚል ይመስላል። አዲስ አበባ መንገዶች በጣልያን ወታደሮች ይታመሳል። ሰሜን ሸዋ ላይ የሚዋጋው አንዳንዴም አዲስ አበባ መግብያ በር ደረሰ እየተባለ የሚወራለት የ አርበኛው የራስ አበበ አረጋይ ሰራዊት በየ ጠጅ ቤቱ በ ቅኔ አዘል ግጥም ይሞገሳል። ቅኔው የገባቸው ባንዳዎችም አዝማሪውን እየጠቆሙ ፍዳውን ያሳዩታል። አዝማሪው ገና አለ ገና በሚል መልክ ውግያው ይቀጥላል የሚል ቃና ያለው ግጥም ያንቆረቁራል-
'' የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፣
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ''
እየተባለ ሴት ወንዱ ለውጊያ የተዘጋጀበት አርበኛ ሆኖ መሞት የተናፈቀበት ጊዜ ነበር። የስድስት ኪሎ የያኔው ቤተመንግስት የአሁኑ ዩንቨርስቲ ከአዲስ አበባ በግድም በውድም በተሰበሰቡ ባብዛኛው ሴቶች ና ሕፃናት ተሞላ። እብሪት የተሞላበት የግራዝያኒ ንግግር ተጀመረ። በንቀት ያየው ሕዝብ ላይ ስለ ''ታላቂቱ ጣልያን'' መደስኮር ጀመረ። ግን ብዙ አልቆየም አብርሃም እና ሞገስ ሕዝቡን ጥሰው ከፊቱ ደረሱ ሰባት ቦንቦችን አከታትለው ወረወሩበት፣ግራዝያን ቆሰለ፣ የአየር ኃይሉ ኃላፊ ተገደለ። አብርሃም እና ሞገስ በ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን በኩል ባለው የ ቤተመንግስቱ የጋራ አጥር ዘለው ወጡ እና ታክሲ ይዞ ወደሚጠብቃቸው ስምዖን ገሰገሱ፣ ስምዖን በታክሲ ወጣቶቹን ይዞ ነጎደ፣ እንጦጦ ተራራ ላይ ውጥተው አዲስ አበባን ቁልቁል አይዋት፣ ግራዝያን በቆሰለበት ሆኖ አዋጅ አውጆ ለካ የ አዲስ አበባ ወንድ ከሴት ሕፃን ከአዋቂ ሳይባል በ ጥይት፣በ አካፋ እና በዶማ በተገኘው ሁሉ መፈጀት ተጀምሯል።
ሶስቱ ወጣቶች ተቃቅፈው ተላቀሱ።ጊዜው እስኪመሽ ጠበቁ እና ስምዖን ወደ ደብረሊባኖስ ይዟቸው ነጎደ።ለ ሰሜን ሸዋ ራስ አበበ አረጋይ ቅርብ የሆነችው -ደብረሊባኖስ አመቺ መስመር እንደሆነች ሁሉም አምነውበታል። ስምዖን ተልኮውን ፈፅሞ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። አብርሃም ና ሞገስ ከ ራስ አበበ አረጋይ ጦር ጋር ተቀላቀሉ።
የካቲት አስራ ሁለት ቀን በአዲስ አበባ ብቻ ከ ሰላሳ ሺህ በላይ ነዋሪዎችዋ ሰማአትነት ተቀብለዋል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለዋል። ግድያው በመንገድ ላይ የተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ ሲሆን ለመግደል የሚፈለገው መስፈርት ኢትዮጵያው መሆኑ ብቻ ነበር።
በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ የሚገኘው የየካቲት 12 የሰማዕታት ሃውልት
ሞግስ አስገዶም፣አብርሃም ደቦጭ እና ስምዖን አደፍርስ ፍቅር እስከ መቃብር
ስምዖን አብርሃም እና ሞገስን ደብረሊባኖስ ወደ ሰሜን ሸዋ መንገድ ከሚያውቃቸው አርበኞች ጋር አገናኝቶ ተመለሰ።ብዙም አልቆየ በፋሽስቱ ጥቁር ለባሾች ተይዞ በብዙ መከራ እና ስቃይ ተገደለ። የታሪክ ምሁራን እንዳስቀመጡት ስምዖን የእጁም ሆነ የእግሩ ጥፍር በጉጠት እየተነቀለ ጣቶቹን እየሰባበሩ አሰቃይተው ገደሉት።
አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም
አብርሃም ደቦጭ ና ሞገስ አስገዶም ከራስ አበበ አረጋይ የአርበኞች ጦር ጋር ከተቀላቀሉ በኃላ ራስ አበበ አረጋይ ልዩ እንክብካቤ እንዲያገኙ አደረጉ።ቆይተው ግን የነበራቸውን የትምርት ደረጃ በመረዳት ከሀገር ውጭ ወጥተው ለሀገራቸው ቢሰሩ ይጠቅማሉ ብለው በማሰብ ከስንቅ እና ገንዘብ ጋር ወደ ሱዳን እንዲሄዱ መከሯቸው። ሆኖም ግን በጉዞአቸው ላይ ሱዳን ሊገቡ ትንሽ ሲቀራቸው ፎቶዋቸው በገጠር ባሉ የፋሺሽት ወታደሮች ሁሉ ተናኝቶ ነበርና በፋሺሽቶች ተይዘው በስቅላት ሰማዕት ሆኑ።በኃላ ግን አፄ ኃይለሰላሴ በ ሱዳን በኩል ጣልያንን ከእንግሊዝ ሰራዊት ጋር ሆነው ድል ሲያደርጉ የ አብርሃም እና የሞገስ አስከሬን ተቆፍሮ ወጥቶ አሁን አዲስ አበባ በሚገኘው የ ቅድስት ስላሴ አርበኞች ሃውልት ስር እንዲያርፍ አድርገዋል።
ዘመኑን ዋጁት
'
ዛሬ ላይ ሆነን የዛሬ ሰማንያ አራት ዓመታት የነበሩትን ወጣቶች ስናስብ እና ሐማሴን እና አካለጉዛይ ከእኛ ኢትዮጵያውያን የተለዩ አስመስለው ሊያወሩን ለሚፈልጉ ከመረብ ማዶም ሆነ ከመረብ ወዲህ ላሉት ባለ ጊዜዎች ትንሽ ጊዜ ወስደው እንዲያስቡ ማረግ ተገቢ ነው።የመረብ ማዶውን ከመረብ ወዲሁ የተለያየው በታሪክ፣በዘር፣ በሃይማኖት አይደለም።ከእዚህ ይልቅ '' ውሸት ሲደጋገም እውነት የመሆን እድል ይኖረዋል'' የሚለውን ብሂል ሁል ጊዜ የሚሰራ የሚመስላቸው ወገኖች በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ብቻ ነው።
ፅሁፌን ከመጠቅለሌ በፊት አንዲት ሃሳቤን የምታሳርግልኝ የታዋቂው አሜሪካዊውን የሀገራችን ታሪክ አዋቂ እና ስለ ኢትዮጵያ በመፃፍ የሚታወቁት ፣አማርኛም አቀላጥፈው የሚናገሩት ፕሮፌሰር ዶናልድ ለቪን ከስምንት ዓመታት በፊት ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በተናገሩት ንግግር ልደምድም።እንዲህ ነበር ያሉት :-''ኢትዮጵያን በአሁኑ ሰዓት የሚያስተዳድሯት የሀገሪቱን ታሪክ በሚገባ የማያውቁ ናቸው።ስለዚህ የምመክረው ታሪክን በደንብ ይረዱ .......እናንት ኢትዮጵያውያን የችግሮቻችሁ ሁሉ መፍቻ ታሪካችሁ ላይ አለ በደንብ ተረዱት'' ፕሮፌሰር ዶናልድ ለቪን ።
ጉዳያችን Gudayachn
www.gudayachn.com
ማሳሰብያ - ይህ ፅሁፍ ከአራት ዓመታት በፊት ለመጀመርያ ጊዜ በእዚሁ ገፅ ላይ ወጥቶ ነበር።በሌሎች ድረ-ገፆችም ከእዚህ ገፅ ተወስዶ ተለጥፎ ነበር።
የፅሁፉ መርጃዎች
፩/ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ http://www.ethioobserver.net/forgoten_heroes.ሕትም
፪/ኢሳት ራድዮ የካቲት 11/2004 ዓም ዝግጅት
፫/ ግሎባል አልያንስ ኢትዮጵያ http://www.globalallianceforethiopia.org