Monday, July 17, 2023

ጳጳሳት ከቡድናዊ ስሜት ወጥተው በውጭ ያሉ አጥብያዎችን ምዕመናንን ሁሉንም እኩል በማየት ዝቅ ብለው ወርደው የአጥብያዎችን፣ የምዕመናንን እና የካህናትን ችግር እንዲፈቱ እራሱ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ እንዳስተማራቸው ለአፍታም ሊዘነጉት አይገባም።


  • በውጭ ያለችው ቤተክርስቲያን የፍትሕ እጦት ብዙ መዘዝ እንዳያስከትል ያስፈራል።
  • ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ''እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉ (ሁሉ የሚለው ተሰምሮበት) እና ለራሳችሁ  ተጠንቀቁ! ያለው ሁልጊዜ መታወስ ያለበት ቅዱስ ቃል ነው።''

ይህ መልዕክት ነው።በእዚህ ዘመን በውጭ ሀገር ምዕመናን ተሳቀው፣ወጥተው ወርደው ያገኙትን ጥሪት አውጥተው የገዟቸውን አብያተክርስቲያናት መጥቶ የሚባርክላቸው፣በልጅነት ያጠፉትን እንደ አባት ወርዶ ይህ እንዲህ ይስተካከል፣ ያንን እንዲህ አድርጉት ብሎ አብሮ የሚመራቸው አባት እንጂ በቡድናዊ ስሜት ውስጥ ገብቶ አንዱን ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ አድርገው እንዲያስተዳድሩ መንፈሳዊም ሆነ ምድራዊ ሕግ አይፈቅድም። አንዳንድ ድርጊቶች ግን ምዕመናን ቤተክርስቲያንን የሚያዩበት ዓይን ብቻ ሳይሆን እምነታቸው እስኪፈተን ድረስ አደገኛ አካሄድ እየተፈጠረ ነው። የእዚህ ዓይነት የአስተዳደራዊ በደሎች ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን ሀገርንና ትውልድን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ስም የሚያጠለሽበት ደረጃ ደርሷል።

በውጭ ሀገር ባሉ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ለመልካም ስራ ከሚያወጡት ይልቅ ለባዕዳኑ ፍርድ ቤት አንዱ አንዱን ለመክሰስ የሚያወጡት ገንዘብ በደንብ ተጠንቶ ቢቀርብ እጅግ ልብ የሚያደማ ነው። የክሶቹ መነሻዎች ደግሞ ተራ እልህ እና እንዲህ ብሎኝ እንዲያ አድርጎኝ የሚሉ ከመሆናቸው አልፎ ጳጳሳት ዝቅ ብለው የአብያተ ክርስቲያናትን ችግር ምዕመኑ ጋር ወርደው ለመፍታት ያደረጉት ጥረት እዚህ ግባ የማይባል የመሆኑ ውጤት ነው። ምዕመናንን ሁሉ እኩል አይቶ ማስተዳደር፣ ከአድመኝነትና እልህ ስሜት ወጥቶ ርቱዕ በሆነ መንገድ ቡድናዊነት በማይታይበት መልኩ ዝቅ ብሎ ወርዶ ምዕመኑን ማነጋገር ያስፈልጋል።በስማ በለው የሚሰራ ስራም ሆነ አገልግሎት የለም።አይደለም ስለ ብዙ ምዕመናን፣ስለ አንድ ምዕመን ህይወት መጠየቅ አለ። የምዕመናን እንባም አጥቦ ይወስዳል። ለአንድ ቡድን ወግኖ የቤተክርስቲያንን ጥቅም ሜዳ ላይ በትኖ እንዴት ለአንድ ቀንስ እንቅልፍ ይተኛል? በጎቼን ጠብቅ ብሎ አደራ የሰጠ አምላክ ስለ መንጋው አይደለም ስለ አንድ ምዕመን ሀዘን ይገደዋል።

ጆሮ ያለው ይስማ! መንገድ ላይ የሚጮህ ''እብድ '' አይደለም ህጻናት ሲጫወቱ እርስ በርስ የተነጋገሩትን ''ይህች ንግግር ለእኔ ነች  ወዮልኝ!'' ብለው እያነቡ ወደ ገዳም የሄዱ አባቶች ያሏት ቤተክርስቲያን በተራ እልህ እና  የአንድ ቡድን ስሜት ይዞ በመሄድ ቤተክርስቲያንን መጉዳት በእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚያስጠይቅ ለማስረዳት ጥቅስ መደርደር አያስፈልግም።

ከሊቀ ካሕን ክርስቶስ የሚበልጥ ጳጳስ የለም። ካህኑ ዔሊ ከ40 ዓመታት በላይ ታቦተ ጽዮንን ማገልገሉ በኋላ ባሳየው ቸልተኛነትና ቡድናዊ ስሜት ከመቀጣት አላዳነውም። ምዕመናን መፍትሄ የሚሰጣቸው ቤተክህነት እና ሊቀ ጳጳስ ይፈልጋሉ። ችግሮች የሚፈቱት በባዕዳን ፍርድቤት የቤተክርስቲያንን አጀንዳ ይዞ በመዞር አይደለም።የምዕመናንን ገንዘብ በየባዕዳኑ ፍርድቤት እየበተኑ ኃላፊነት ባልተሰማ መንገድ ምዕመናን ሲበተኑ ቆሞ በማየት ሊሆን አይችልም።ስለእዚህ ጉዳይ የማይገደው ማንም ክርስቲያን የተባለ ሊኖር አይገባም።

ዝቅ ብሎ ምዕመኑ ጋር ቀርቦ ችግሩን መፍታት፣ሸክሙን መሸከም የተሰጠ አደራ ነው። እግዚአብሔር ከማደርያው ሆኖ የሚፈጸሙትን የግፍ እና የአድሏዊ አሰራሮች ይመለከታል። ተመልክቶ ግን ድንገት በቃ ብሎ ይነሳል። ይህንን መጠን ያለፈ መንጋውን በፍቅር ሳይሆን በኃይል ለምግዛት የመሞከር አካሄድን አለመናገር በራሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቃል።መጽሐፍ ያስተማረው ጳጳሳት መንጋውን በኃይል ሳይሆን በፍቅር እንዲመሩ ነው። 

በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያለው የሲኖዶስ መከፈል በኋላ ቀድሞ የነበሩ የአጥብያዎች የእርስ በርስ ችግሮች ውስጥ ስንት ችግሮች በውጭ ባሉ ጳጳሳት ተፈታ? ስንቶቹ አሁንም ድረስ ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ሲሄዱ ጳጳሳት አንተም ተው! አንተም ተው! ብለው ሲሆን አልቅሰው እና ምዕመኑ መሃል ቀርበው ፈቱ? ስንቶቹ ጋር በአንዱ ቡድን ውስጥ እየገቡ ችግሮቹ ተባባሱ? በእዚህ ላይ እስኪ ቤተክህነት ጥናት ያጥና እና እነኝህን ችግሮች ይፍታ! ችግሩ ጣርያ ደርሶ ሀገር ሲታመስ ከመሮጥ ዛሬ ላይ ቀድሞ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል። የቤተክርስቲያን ጉዳይ የጳጳሳት ጉዳይ ብቻ፣ወይንም የዲያቆናት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ምዕመናን የራሳቸው ድርሻ አላቸው።መንጋውን በኃይል እንዲገዛ የተፈቀደለት እረኛ እንደሌለ መጽሐፍ ነግሮናል።በፍቅር፣ዝቅ ብሎ ምዕመናን እና ካህናቱ መሃል ቁጭ ብሎ የመነጋገር እና የመፍታት ለእዚህም የሚመጣ ማናቸውንም ፈተና ለመቋቋም የእያንዳንዱ እረኛ ግዴታ ነው።ቁራም ይጮሃል፣እብድም ይናገራል።ይህች ንግግር ለእኔ ነች ብሎ የሚሰማ ይስማት።የማይሰማ ንቆ ይተዋት። ይህ የሰማይ ደጅ ጉዳይ ነው።በሰማይ ደጅ ጉዳይ ነው።ምዕመኑ የሰማይ ደጁን ጉዳይ ጳጳሳት ዝቅ ብለው ወርደው እንዲፈቱ አሁንም ይለመናሉ።እግዚአብሔር ሳይነሳ ሰውም ሳያመር ትናንት የነበሩበትን አስታውሶ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብለው ችግሮችን እንዲፈቱ ይለመናሉ።

''በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ!'' ሐዋ ስራ 20፣28

===============/////፟=============

Wednesday, July 12, 2023

የትግራይ ክልል ጳጳሳት የካሕኑ ዔሊን ድፍረት በታቦተ ጽዩን ፊት ለመፈጸም ቀጠሮ ይዘዋል።ከአርባ ዘመን በላይ ያገለገለውን ካሕኑ ዔሊን ከመቅሰፍ ያልተመለሰ የአምላክ ፍርድ ዛሬም በታቦቷ ፊት የሚፈጸመውን የድፍረት ኃጢአት ዝም አይልም።


  • ለሹመት ብለው የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን የከዱ፣ታቦተ ጽዮንን ከመሸጥ አይመለሱም።

=========
ጉዳያችን ምጥን
=========
የትግራይ ክልል ጳጳሳት ከቅዱስ ሲኖዶስ ፍቃድ እና እውቅና ውጪ በሕገወጥ መንገድ ኢጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ይህንንም የድፍረት ኃጢአት በታቦተ ጽዮን ፊት በአክሱም ለመፈጸም ለሐምሌ 9 ቀጠሮ ይዘዋል። ይህንን የድፍረት ኃጢአት እንዳይፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ለማግባባት ብቻ ሳይሆን ባልተለመደ መንገድ ላላጠፋው ጥፋት ሁሉ ይቅርታ ከመጠየቅ አልፎ ቅዱስ ፓትርያሪኩ አቡነ ማትያስ መቀሌ ድረስ ሔደው ጳጳሳቱን ለማግኘት ቢሞክሩም ፖለቲከኞችን ለመቀበል መቀሌ አሉላ አባነጋ አየርማረፍያ ይጋፉ የነበሩ ጳጳሳት ቅዱስ ፓትርያሪኩ ላይ ቤተክርስቲያን ዘግተው ተደብቀው ውለዋል።

አሁን ምንም ሀተታ አያስፈልገውም።የድፍረት ጥጉ ልክ አልፏል።ታቦተ ጽዮን ጥንት የነበረችው ነች። የነበረው የእግዚአብሔር ክብርም ዛሬም አለ። ካህኑ ኤሊ ከበደሉ ባለመመለሱ የቀጣ አምላክ ዛሬም ለፍርድ በቦታው አለ።የኃጢአት ቀጠሮው እና የሚያስከትለውን ቅስፈት የት ድረስ እንደሚደርስ የምናየው ነው።

ስለሞተው አታልቅሱ ለገዛ እራሳችሁ እንጂ



በግሪክ አቴንስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ገዳም ዙርያ የኢቢኤስ ሪፖርት ሰኔ 2፣2015 ዓም EOTC Monastery in Greece, EBS TV Report


Saturday, July 8, 2023

አቡነ ሰላማ ያከበሩትን፣የቀደሙ የአክሱም ነገስታት ያልተዳፈሩትን የቅዱስ ሲኖዶስ ክብር እያቃለሉ በአቡነ ሰላማ ስም የሚነግዱቱ የትግራይ ጳጳሳት ድፍረት ቅስፈት እንዳያመጣ ያሰጋል።የትግራይ ገዳማት ህገወጦቹን ጳጳሳት ሊገስጹ ይገባል።


በትግራይ ጳጳሳት በህገወጥ መንገድ እየተዟዟረ የሚገኘው ኢጲስ ቆጶስነት ለመሾም የምትፈልጉ መነኮሳት ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3 ተመዝገቡ የሚለው የጉድ ማስታወቂያ።



=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓለም ቀደምት ክርስትናን ካስፋፉት አብያተክርስቲያናት ቀዳሚዎቹ ውስጥ ነች። ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከእርገት በኋላ በዓመቱ በ 34 ዓም በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማክይነት መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያት ሥራ ምዕ 8 ላይ የተጻፈ ነው። ኢትዮጵያ ክርስትናን በጃንደረባው አማካይነት ብትቀበልም በብሔራዊ ደረጃ የታወጀው ግን በ4ኛው ክ/ዘመን ነበር። የመጀመርያው ጳጳስ ደግሞ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ነበሩ።

አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን በሦስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በሕዳር 26/ 245 ዓ.ም ከአባታቸው ቅዱስ ምናጦስና ከእናታቸው ቅድስት ማርያም ሰናይት በጢሮስ /ግሪክ/ ተወለዱ። የመጀመሪያ ስማቸው ፍሬምናጦስ ይባላል። አቡነ ሰላማ የ12 ዓመት ልጅ እያሉ ሜሮጵዮስ የተባለ ነጋዴ /ፈላስፋ/ ይዟቸው ወደ አገራችን በእግዚአብሔር ፈቃድ መጣ። ከእርሱም ጋር ኤድስዮስ የተባለም አብሮት እንደነበረ ይታወቃል። እነዚህን ሁለት ወጣቶች አስከትሎ የመጣው ሜሮጵዮስ በቀይ ባሕር አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በጣሉለት አደጋ በዚሁ እንደ ሞተ ታሪክ ይነግረናል። ፍሬምናጦስና ኤድስዮስ ግን በወቅቱ የአክሱም ንጉሥ የነበረው ንጉሥ ታዜር ጋር አድገዋል። ንጉሡ በአእምሮ መብሰላቸውን ተመልክቶ ፍሬምናጦስ በጅሮንድ ኤድስዮስም ጋሻ ጃግሬው አድርጎ ሾማቸው።

ከዚያ በኋላ ንጉሥ ታዜር ሲያርፍ ወደ ፈለጉበት እንድሄዱ ነፃ ስለተለቀቁ ኤድስዮስ ወደ አገሩ ተመልሶ ሄዷል። አባታችን አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ግን በጨለማ የሚኖረውን ሕዝብ ትቼ ወደ አገሬ አልመለስም በማለት እንደቀሩ ታሪክ ያስረዳናል። 

በዚያን ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ ስርዓተ ንስሐ፣ ስርዓተ ጥምቀት፣ ስርዓተ ቅዳሴ፣ ስርዓተ ቅዱስ ቁርባን የሚያከናውን ጳጳስ ስላልነበረ ይህን የተመለከቱ ነገስታት ኢዛናና ሳይዛና ጵጵስና እንዲያመጡ አባታችን አቡነ ሰላማን ወደ ግብጽ ላኳቸው። አባታችንም ወደ ግብጽ በመሄድ ስርዓቶቹን በመማር በቅዱስ አትናትዮስ አንብሮተ እድ ˝ኤጲስ ቆጶስ” ተብለው ጵጵስና ተቀበሉ። ወደ አገራችን ከተመለሱ በኋላ መጀመሪያ ነገስታት ኢዛናና ሳይዛናን አጥምቀውና አቁርበው አብርሃ ወአጽበሃ በማለት ስመ ክርስትና ሰጧቸው። በመቀጠልም በመላው አገራችን እየተዘዋወሩ በማስተማር ስርዓቱን ፈጽመዋል። 


ዛሬ በአቡነ ሰላማ ስም እየተነገደ ነው።አቡነ ሰላማ ኢጲስቆጶስነትን ለመቀበል በሱዳንና ግብጽ በረሃ ተንከራተው ሹመቱን ይዘው መጡ እንጂ እንደየዘመኑ በስማቸው እንደሚነግዱባቸው የትግራይ ጳጳሳት በጉልበት እና ፍጹም ትዕቢት በተሞላበት መንገድ ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና እና ፈቃድ ውጪ አልሄዱም።የዘመናችን የትግራይ ጳጳሳት ግን ኢጲስ ቆጶሳት ለመሾም የምትፈልጉ ተመዝገቡ የሚል ማስታወቂያም እስከማውጣት ተደርሷል የሚል ዘገባም በማኅበራዊ ሚድያ ሲዘዋወር ታይቷል። አቡነ ሰላማ በስማቸው እየተነገደ ፍጹም ድፍረት ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ለህወሃት አመራር የሚታዘዙት የትግራይ ጳጳሳት ህገወጥ ድርጊት ለበለጠ ቅስፈት እንዳይዳርግ በእጅጉ ያስፈራል።


በትግራይ ጳጳሳት እየሄዱበት ያለውን የተሳሳተ መንገድ ለመመለስ ቅዱስ ሲኖዶስ ብዙ እርቀት ከመሄድ አልፎ፣ቤተክርስቲያን ይቅርታ ጠየቀች የሚል ዜናም ተሰምቷል። አንድ የትግራይ አባት ይህንን ሰምተው ምዕመን ቤተክርስቲያንን ይቅርታ ይጠይቃል እንጂ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ነው ምዕመንን የምትጠይቀው? በማለት የጉዳዩን ተገላቢጦሽነት ገልጸውታል።እየሆነ ያለው መንፈሳዊነት ሽታ የሌለው ከቅሌት ያለፈ በፈጣሪ ላይ የሚደረግ ድፍረት ነው።አሁን የትግራይ ገዳማት አስተዳዳሪዎች ምን ይላሉ? የመገናኛ ብዙኃን በጳጳሳቱ ሕገወጥ አካሄድ ላይ ምን ይላሉ? የህወሃትን ማስፈራራት አሸንፈው የጳጳሳቱን ድርጊት የሚያወግዙ ገዳማውያን እነማን ናቸው? ይህ የመገናኛ ብዙኃኑ ሊያሰሙን እና ሊያሳውቁን የሚገባ ቀዳሚ ተግባር ነው።

===============///==============





Friday, June 30, 2023

የዘመኑ ምሑር ችግር፣ትልቁን ሀገራዊ ስዕል ትቶ በጥቃቅን የመንደር ጉዳዮች የመዋጥ ችግር ነው።


=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች።በእኛ ዘመን እንደገባችን መጠንም ብቻ አይደለችም።ከ20ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የተነሳው ትውልድ የገጠመው የዕውቀትም ሆነ መጪውን የሚያመላክተው የኮከብ ምሑራን እጦት በእጅጉ ጎድቶታል። ከ1960 ዎቹ የተነሳው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የመሩት ሐያዎቹን ያልዘለሉ፣በስሜት እና ከውጭ የግራ ክንፍ ጽሑፎች ባነበቡት የኢትዮጵያን ታሪክ ለመገልበጥ የሞከሩ መሆናቸው በቀጣይ ሀገሪቱን ወዴት እንደመራት እና ዛሬ ድረስ የእዚህ ሁሉ ውጤት ለጎሰኛ እና ስርዓት አልበኛ የፖለቲካ ድርጅቶች መፈልፈል አሳልፎ ሰጥቶትን ብዙ ነገሮች እንዲበላሹ አድርጎ ኢትዮጵያን ጎድቷል።

አሁን ያለው ምሑር ችግር ትልቁን ሀገራዊ ስዕል ትቶው በጥቃቅን ጉዳዮች መዋጥ። ትውልድ የሚያሻግረውን አጀንዳ ጥሎ ከከንፈር እስከ አፍንጫ የሚደርስ አጀንዳ አንጠልጥሎ መብረር እንደ አዋቂ እያስቆጠረ ነው።ይህ የሀሳብ ልዕልና የመውረድ ችግር በጊዜ ካልተገታ አጠቃላይ ውድቀት ያስክትላል። የሚድያ ውይይቶቹ፣ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚቀርቡት የወቅታዊ ጉዳይ ተብለው የሚነሱት ርዕሶች ትውልዱ ትልቅ እና ተሻጋሪ ሃሳቦችን ላይ እንዲያሰላስል የሚያደርጉ ሳይሆኑ፣እገሌ የተባለው ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የወጣው መረጃ ተብሎ ምሑራን ሃሳብ ይስጡበት ተብሎ የሚጠየቅበት፣ከተጨባጭ መረጃዎችና የጥናት ውጤቶች ይልቅ ''እየተወራ ያለው '' ተብሎ የሀገር ፖለቲካ የሚተነተንበት ሂደት ይህንን ትውልድ ከማስደንበር እና መጪውን ጊዜ አጨልሞ እያየ እንዲባንን ከማድረግ በላይ የነገዋን ኢትዮጵያ ፈጽሞ አይገነባም።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ስናነሳ የምናነሳበት ጥግ በጣም ደካማና የመንደር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ከመሆኑ የተነሳ ኢትዮጵያን አስፈንጥረው የሚያነሱ አንኳር ጉዳዮችን ለትውልዱ ለማሳየት እና አጀንዳ ለመፍጠር ምሑራንም ሆኑ ጋዜጠኞች ሲጥሩ አይታይም። ለእዚህ ደግሞ ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው። አንዱ ከፍተኛ የአቅም ማነስ እና ልዩነት ይታያል።ወቅታዊውን ጉዳይ አብስሎ የመከታተል፣የማንበብ፣ለማወቅ የመጣርና፣ያወቁትን እውነት ለማንጠር ያለመቻል ችግር በግልጽ ይታያል።ይህ አቅም ደግሞ በድንገት በአንድ ምሽት የሚመጣ አይደለም።ልምድ፣ዕውቀትና አንጥሮ የመለየት አቅም ማዳበር ላይ ብዙ ይቀረናል። ሁለተኛው ምክንያት ለተከታታይ ዓመታት በጠባብ የጎሳ አስተሳሰብ ስርዓት ውስጥ ተነክሮ የመውጣት ችግር ነው። ይህ ሁለተኛው ችግር በተለይ አጥብቦ የማየት ችግር በመሆኑ የተሻለ ነገር ለማማተር ስንኩል የሆነ አካሄድ አስከትሏል።

ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች።መጪው ትውልድ ደግሞ የዛሬ ጋዜጠኞች እና ምሁራን በሚያነሱት የአስተሳሰብ ልክ በየቀኑ እየተቀረጸ ይሄዳል። የዛሬ ምሁራን እና ጋዜጠኞች የሚያነሱት ትልቁን የኢትዮጵያ ጉዳይ ሳይሆን ጥቃቅን እና የመንደር ወሬዎች ላይ ባተኮሩ ቁጥር ለትልቋ ኢትዮጵያ የሚቆም ትውልድ እና የቱ የሀገሪቱ ትልቅ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የማያውቅ ትውልድ ማፍራት ይጀመርና ኢትዮጵያን ወደ የባሳ አደጋ ይዟት ይሄዳል። የሀሳብ ልዕልና የመውረድ ችግር በጊዜ ካልተገታ አጠቃላይ ውድቀት ያስክትላል።ስለሆነም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የምትወያዩ፣ የምትጽፉ እና ወቅታዊ ጉዳዮች በሚል የሀገር ጉዳይ ላይ የምትናገሩ ሁሉ ከትናንሽ አጀንዳዎች ወጥታችሁ፣ ትልቁ፣ሀገራዊና ትውልድ ተሻጋሪ በሆኑ ሀሳቦች ላይ አትኩሩ።ትልቅ ሀገርን የሚመጥን አጀንዳ ከወሬ እና ከይመስለኛል ሀሳቦች የራቀ ጠንካራ እና ውስጥን የሚሰረስር ትውልድ የሚያነቃ ነው። 
==========///==========

በጠ/ሚ/ዐቢይና ሙ/ጥ/ዲ/ዳንኤል ላይ በውሸት ወሬ የዘመቱት ''አፈ-ጊንጦች'' በቴዲ አፍሮ ዘፈን ሊሸሸጉ ሲሞክሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየሳቀባቸው ነው።

ጠ/ሚ/ዐቢይ አሕመድ እና ሙ/ጥ/ዲ/ዳንኤል ክብረት በታላቁ የዓባይ ግድብ ምርቃት ቀን። ======== ጉዳያችን ምጥን ======== አፈ ጊንጥነቱ እና የውርደት ካባው ''አፈ ጊንጥነት'' የሚለውን ...