ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, June 15, 2023

የምስኪኖች ዕንባ ተንጠባጥቦ አይቀርም።ግፈኞችን ገና ዋጋ ታስከፍላለች።


ዶ/ር ተሾመ አዱኛ
  • ''ሸገር ከተማ ውስጥ እያሉ ድሃም ህገወጥም ናቸው።አሁን (ከመሬቱ ካስለቀቅናቸው በኋላ) ቢያንስ ድሃ ሆነው ህጋዊ ናቸው።''የሚለው የሸገር ከተማ ከንቲባ ግፍ የተሞላበት ንግግር የኢትዮጵያውያንን ልብ የባሰውን አድምቷል።
========
ጉዳያችን
========
''ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ'' የሚለው አባባል ቀላል አባባል አይደለም። ኢትዮጵያውያን በታሪካችን በቅኝ ገዢ ያልተገዛች ሀገር የመሆኗን ያህል የጎሳ ፖለቲከኞች ያደረሱብንን ያህል ተሰምቶ የማይታወቅ የግፍ ዓይነት አላየንም።በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን ከጉርዳፈርዳ እስከ ወለጋ ህዝብ ተፈናቅሏል።ከ2010 ዓም በኋላ ደግሞ መፈናቀሉ ከገጠር እስከ ከተማ ሆኗል።በተለይ በኦሮምያ ክልል እጅግ አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ዜጎች ከይዞታቸው ተፈናቅለዋል፣ተገድለዋል፣ንብረታቸው ተዘርፏል።

ይህ በእንዲህ እያለ ሸገር ከተማ በሚል አዲስ ከተማ መመስረቱን የተናገረው የኦሮምያ ክልል ፍጹም ፋሺሽታዊ በሆነ መንገድ ቤታቸውን ላፈረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ካሳ መክፈል እና ህጋዊ ይዞታ የላቸውም የሚላቸው ካለ ቀድሞ የሚያርፉበትን ምትክ ቤት መስጠት ሲገባው አሁንም ለተፈጸመው ግፍ ሌላ የህዝብ ቁስል የሚወጋ ንግግር የሸገር ከተማ ከንቲባ እና የሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ ውጤት የሆኑት ዶ/ር ተሾመ አዱኛ ''ብርቱ ወግ '' ለተሰኘው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥኝ መርሐግብር ሰሞኑን ሰጥተዋል። ስለ የሸገር ከተማ ዝርዝር መረጃ ጉዳያችን ከሦስት ወር በፊት በየካቲት ወር ላይ ''ሦስት ሳምንት ያልሞላት አራስ እናትን ቤት በግሪደር አፍርሶ በከተማ ዙርያ ከተማ ልመሰርት ነው ያለው የኦሮምያ ክልል ፕሮጀክት፣እውን የከተማ ፕሮጀክት መስፈርት ያሟላል?'' በሚል ርዕስ የጻፈችውን ይመልከቱ።

ዶ/ር ተሾመ በእዚሁ ቀጣይ ክፍል አለው በተባለው የኢቲቪ ቃለ መጠይቃቸው ለሚጠየቁት ጥያቄ የሚሰጡት የምላሽ አሰጣጥ በተፈጸመው ግፍ እየተኩራሩ ብቻ ሳይሆን ስላቅ በቀላቀለ አገላለጽ ለመመለስ ሲሞክሩ መመልከት ልብ ያደማል። ኢቲቪ ካቀረበላቸው ጥያቄ ውስጥ 
  • ወዴት ይሂዱ ብላችሁ አባረራችኋቸው? 
  • በግዢ ባገኙት ቦታ ላይ የገነቡት እና አሁን ያባረራችኋቸው ኢትዮጵያውያን ግዢውን ሲፈጽሙ ሕጋዊ እንዴት አይባልም? ባለው ሕግ መሰረት ሂደቱን ታውቁ ነበር፣ሻጩን ህገወጥ ያላለ፣ገዢውን ብቻ ለይቶ ህገወጥ እንዴት አላችሁ?
  • ይህንን ውሳኔ ስታሳልፉ በምን ህጋዊ መሰረት ነው?
  • ልማት ለሕዝብ የሚሰራ ነው።ሕዝብን በማፈናቀል ሕዝብ የተቀበለው ፕሮጀክት ነው ለማለት እንዴት ይቻላል?
  • የተፈናቀሉት የሌላ ሀገር ዜጋ አይደሉም።የሌሎች ዜጎችን ህዝብ እየተቀበልን እነኝህ ኢትዮጵያውያንን እየተፈናቀሉ ለማን ነው ልማት እየሰራን ነው ያላችሁት?
  • ህዝብ በእዚህ ደረጃ ሳይፈናቀል ከተማ መስራት አይቻልም ወይ?
እና ሌሎች ጥያቄዎችም የቀረበላቸው ከንቲባ አንድም አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡም። ይልቁንም እዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ ሲዋሹም ተደምጠዋል። ከእዚህ በፊት በህገወጥ ሽያጭ ማስፈጸም ተግባር ላይ የተሰማሩ የክልሉ ባለስልጣናት በሕግ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ ወይ? ሲባሉ መጀመርያ እስከ 400 ታስረው ነበር ካሉ በኋላ፣ ለፍርድ ቀርቦ የተፈረደበት አንድ ሰው አለ ወይ? ብሎ ኢቲቪ ሲጠይቃቸው መልሰው በሕገወጥ መንገድ የተደረገ ነገር ለማጣራት ከባድ ነው በሚል የተፈረደበት እንደሌለ ለመናገር ሞክረዋል።

እውነታው ግን የቀድሞው ኦህዴድ አሁን ብልጽግና ሆኖ የተከሰቱት ባለስልጣናት ከገላን እስከ ቡራዩ ዙርያ አዲስ አበባ ያሉ የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ካርታ እያባዙ መሬቱን ሲቸበችቡ እንደነበር የኦሮምያ ክልል ህዝብ ምስክር ነው።ዛሬ እንደ ንጹህ አባራሪ እና አፈናቃይ ሆነው ''ዐይናቸውን በጨው አጥበው'' ብቅ አሉ።

በሸገር ከተማ ዙርያ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሩብ ሚልዮን በላይ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ብቻ ከ100 ሺህ ተፈናቃዮች አቤቱታዎች ደርሶኛል በማለት ለቪኦኤ አማርኛ ገልጾ ነበር።

የኦሮምያ ክልልን እያለማን ነው ያሉት የሸገር ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ ክልሉን እያፈረሱ መሆናቸው ምናልባት በሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ ውስጥ ያለ አንድም መጽሐፍ አልነገራቸው እንደሆነ አይታወቅም እንጂ የኦሮምያ ክልል ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ የባሰ የስርዓተ አልበኝነት፣የኢንቨስተሮች መሸሽ እና ይህንን ተከትሎ ከፍተኛ የስራ አጥ ችግር ውስጥ ተወጥሯል።ችግሩ ምናልባት የክልሉን ቅምጥል ባለስልጣናት አይመለከት ይሆናል እንጂ ክልሉ በርካታ ከዕውቀት የራቁ ፕሮጀክቶች እና የታይታ የፕሮፓጋንዳ ቅብ ልማት የሚመስሉ ህዝብን ማታለያ የውሸት የመዝረፍያ ፕሮጀክቶች ናቸው።ሪፕርተር ባለፈው ዕሁድ ባወጣው ዘገባ ብቻ ብንመለከት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ከኦሮምያ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ጋር በጋራ ባጠናው ጥናት በክልሉ ስራ ለመጀመር ፍቃድ ከወሰዱት ውስጥ 57% የሚሆኑት ወደ ስራ ለመግባት ያልቻሉና 43% ስራ ጀምረዋል የተባሉትም በሙሉ ኃይላቸው የማይሰሩ መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል።

በ''እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ '' እንዲሉ ክልሉ ከፍተኛ ምስቅልቅል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጎጥ አጥር የታጠሩ፣ሙስናና ህገወጥነት የሚያስተባብሩ ባለስልጣናት የሚመሩት በመሆኑ ከክልሉ አልፎ የመላዋ ኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር አሁን ካለበት ሁኔታ በላይ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።የኦሮምያ ክልል ህዝብ ከሩብ ሚልዮን በላይ ያውም በከተሞች እያፈናቀለ እና ከተማ እያፈረሰ ከተማ እሰራለሁ የሚሉ የሲቪል ሰርቪስ ምሩቆች ሀሳብ የተሞላ ስለሆነ ከአሁኑ በባሰ የኢትዮጵያ ዕዳ የመሆን አደጋው አሁንም ግልጽ ነው።

በመጨረሻም ለህዝብ አሳቢ መንግስት ኢቲቪ ''ወዴት ይሂዱ ብላችሁ አባረራችኋቸው?'' ብሎ እንደጠየቀው።እውነተኛ ለህዝብ የቆመ መንግስት ህዝብ አማራጭ መኖርያ ሳያዘጋጅ ከአንድ ቦታ አያፈናቅልም። በሸገር ከተማ የታየው ግን ለጆሮ ለማመን የሚከብድ ነው። ክልሉ ያባረራቸውን ሌሎች እንዳያከራዩ ማስፈራርያ ከእዚያም ባለፈ እስር ሁሉ ያስተናገዱ አከራዮች መኖራቸው ነው የተሰማው። ይህ ግልጽ የሆነ የጥላቻ ተግባር ነው። ከእዚህ በፊትም በአንድ ጽሑፍ ላይ እንደጠቀስኩት፣ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እንደተናገሩት ጣልያን ኢትዮጵያውያንን ፒያሳን የነጮች ብቻ ከተማ ለማድረግ አልሞ ከፒያሳ አካባቢ የአዲስ አበባ ህዝብን ማፈናቀል ጀምሮ ነበር። ነገር ግን ጣልያን ሲያፈናቅል፣ፕሮፌሰር መስፍን አንድ ወቅት እንደተናገሩት ከማፈናቀሉ በፊት መርካቶ አካባቢ የጭቃ ቤት ሰርቶ ቀድሞ አዘጋጅቶ ወደእዚያ ያስገባ ነበር እንጂ አባሮ ሜዳ ላይ ይውደቁ ብሎ አልጣለም። የኦሮምያ ክልል ሸገር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ ግን ''የት ይሂዱ ብላችሁ አባረራችኋቸው?'' ሲባሉ ''ሸገር ከተማ ውስጥ እያሉ ድሃም ህገወጥም ናቸው።አሁን (ከመሬቱ ካስለቀቅናቸው በኋላ) ቢያንስ ድሃ ሆነው ህጋዊ ናቸው።'' በማለት ተሳለቁበት።የምስኪኖች ዕንባ አንዲት ጠብታ መሬት ላይ በከንቱ ተንጠባጥባ አትቀርም።ግፈኞችን ገና አሳር አበሳ የበዛበት ዋጋ ታስከፍላለች።

============///=========

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...