ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, June 9, 2023

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ ኢትዮጵያን በደን ለማልበስ የጀመሩትን በጎ ጅምር በማስቀጠላቸው ሀገራዊም፣ዓለም አቀፋዊ ሽልማት ይገባቸዋል። • ማመስገን ''አድርባይ'' በሚያስብልበት ዘመን ላይ ብንሆንም።ይህንን መልካም ስራ ሳያመሰግኑ ማለፍ ግን ፈጽሞ አይቻልም።
 • የዳግማዊ ምንሊክ የደን ልማት
 • አሁን ኢትዮጵያ እያለማች ያለችው የደን ልማት አጀማመር፣
 • የሚተከሉት ችግኞች ቁጥር እንዴት ታወቁ?
 • ዘንድሮ ለመትከል የታሰበው ምን ያህል ነው?

ማመስገን ''አድርባይ'' በሚያስብልበት ዘመን፣መሳደብ ተከታይ በሚያበዛበት ዘመን ላይ ብንሆንም።መልካሙን ስራ ሳያመሰግኑ ማለፍ ፈጽሞ አይቻልም።
  
ይህንን የጉዳያችንን ገጽ የዛሬ 11 ዓመት ስጀምር የመጀመርያ ጽሑፌ የማመስገን ባሕላችን ምን ያህል እንደተጎዳ በሚገልጽ ጽሑፍ ነበር።ለእዚህም ማጠናከርያ የሆነኝን የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ መምህሬ ዶ/ር ማረው ዘውዴ ክፍል ውስጥ ስለ የማመስገን ባሕላችን የተናገሩት ነበር። የዛሬ 11 ዓመት የመጀመርያው የጉዳያችን ጽሑፍ ርዕስ እና ሊንክ ''የምስጋና አና የ ወቀሳ ባህላችን'' የሚል ነበር።

ዛሬ ላይ ለአንዳንዶቻችን መልካሙን ለማመስገን የሚያሳቅቅ፣መውቀስ (መውቀስ ተገቢ መሆኑ ሳይዘነጋ)፣መሳደብ እና ማጥላላት ግን ብዙ ተከታይ የሚያስገኝበት ጊዜ ነው።ብዙ ወቀሳ ካለ ሊዘለል የማይችለውን መልካሙን እና ዳግማዊ ምንሊክ ከአውስትራልያ ድረስ የበሃርዛፍ ችግኝ እያስመጡ ኢትዮጵያን በደን የማልበስ ግዙፍ ስራ ያስቀጠሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን በእዚህ የደን ልማት ስራቸው አለማበረታታት ፈጽሞ አይቻልም።

የዳግማዊ ምንሊክ የደን ልማት

ዳግማዊ ምንሊክ ኢትዮጵያን በደን የማልበስ እቅዳቸው ብቻ አይደለም አስደናቂ የሚያደርጋቸው።ከመቶ ዓመታት በፊት የአካባቢ ጥበቃ ሳይንስ ያላቸው ግንዛቤ እና የመጪው ዘመንን የኃይል ፍላጎት ቀድመው መተንበያቸው ነው።ንጉሱ ከአካባቢ ጥበቃ በላይ አስደናቂ የሚያደርጋቸው ተጨማሪ ሦስት ጉዳዮችም ናቸው

የእዚህ ጽሑፍ ርዕስ ወደሆነው የደን ልማት ጉዳይ ስንመጣ ንጉሱ ለኢትዮጵያ ያስተዋወቁት የበሃርዛፍ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የአበባ እና የፍራፍሬ ዛፍ ዝርያዎችን (ለምሣሌ የኮክ ፣ የእንጆሪና የወይን ) ከአውሮፓ እያስመጡ አራብተዋል። የባሕር ዛፍ ወደ ኢትዮጵያ በንጉሰ ነገስቱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ አድርገው እንዲራባ ባይደረግ ኖሮ በኢትዮጵያ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የኃይል ክፍተት ቢጠና የንጉሰ ነገስቱ ውሳኔ ምን ያህል ለውጥ እንዳመጣ በሚገባ ለመረዳት ይቻል ነበር።

ከዳግማዊ ምንሊክ በኋላ በንጉሱ ዘመንም ሆነ በወታደራዊ መንግስት ዘመን የደን ልማት ስራ በኢትዮጵያ ተከናውኗል። በተለይ በወታደራዊው መንግስት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘመቻዎች ተደርገው አሁን ድረስ የሀገሪቱ አሻራዎች ሆነው የሚታዩበት ማሳያ ቦታዎች አሉ።

አሁን ኢትዮጵያ እያለማች ያለችው የደን ልማት አጀማመር 
 • ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 'አረንጓዴ አሻራ' በሚል ዘመቻ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች በአገር አቀፍ ደረጃ የችግኝ ተከላ መርሐግብር በይፋ ተጀመረ።
 • ከእዚህ ዘመቻ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባዘጋጁት 'ገበታ ለሸገር' የእራት ግብዣ ላይ በሕንድ ተይዞ የነበረውን በመላ አገሪቱ ዛፍ የመትከል ክብረ ወሰን ለመስበር የሚያስችል ዘመቻ ለማካሄድ ማሰባቸውን በንግግራቸው ለመጀመርያ ጊዜ ይፋ አደረጉ።
 • ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው "ሕንድ 100 ሚሊዮን ዛፍ በመትከል ክብረ ወሰኑን ይዛለች። እኛ በመላ አገሪቱ ሁለት መቶ ሚሊዮን ችግኝ ለምን አንተክልም?" በሚል አባባል ገልጸውት ነበር።
 • በእዚያው የክረምት ወቅት የክረምት ወቅትም 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቋመ።
 • ለእዚሁ ለሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም የዛፍ ተከላ ዘመቻ በኦሮሚያ 126 ሚሊዮን፣ በአማራ 108 ሚሊዮን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል 48 ሚሊዮን፣ በትግራይ ዘጠኝ ሚሊዮን ችግኞች ሊተከሉ እቅድ ተይዞ፣ ቦታ ተመርጦ፣ ጉድጓድ ተቆፍሮ ተዘጋጀ።
 • የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በሁሉም ወረዳዎች 3 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችለው ዝግጅት አደረገ።
 • "የአራዳ ልጅ ዛፍ ይተክላል" በሚል በትዊተር ላይ የተጀመረ ዘመቻ ተቀጣጠለ። የዚህ ዘመቻ አስተተባሪዎች "ዛፍ መትከል ጤናን መገብየት ነው" በሚል በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ዛፍ ለመትከል ጥሪ አቀረቡ።
 • ሐምሌ 22 ቀን በአንድ ጀንበር 200 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ለተያዘው እቅድ 54 ሚሊየን ብር መመደቡ ተግለጸ የሚያስተባብረው ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ስራውን ማቀላጠፍ ጀመረ።
 • ከተመሰረተ ከ30 ዓመታት በላይ የሆነውና የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዎርጊስ መስራች የሆኑበት የኢትዮጵያ የአካባቢና ልማት ማኅበር የረጅም ጊዜ ህልሙ የሆነው ስራ መጀመሩ አስደሰተው ለተግባራዊነቱም ከግንባር ቀደምቶቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ ደጋፊ ሆነ።
 • በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በአፈር አጠባበቅ ላይ እየሠሩ የነበሩት አቶ መሀመድ እንድሪያስ ስለ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ማሽቆልቆል በወቅቱ ለቢቢሲ ሲያብራሩ በ1990ዎቹ አካባቢ የአገሪቱ የደን ሽፋን መጠን 15 ሚሊዮን አንድ መቶ አስራ አራት ሔክታር ነበር የሚሉት መምህሩ፤ በ2000 ላይ 13 ሚሊዮን ሰባት መቶ አምስት አካባቢ መሆኑን በመጥቀስ፤ በ2010 ላይ አስራ ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ዘጠና ስድስት፤ በ2018 ላይ ደግሞ አስራ ሁለት ሚሊዮን 147 ሔክታር አካባቢ ሽፋን መኖሩ ጠቅሰዋል።

የሚተከሉት ችግኞች ቁጥር እንዴት ታወቁ?

በሐምሌ 22፣2011 ዓም በአንድ ጀንበር 200 ሚልዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደው ዕቅድ 300 ሚልዮን ችግኝ በመትከል የህንድን በሦስት እጥፍ የበለጠ ሥራ ተሰርቷል። ጥያቄው ቁጥሩ ትክክል ነው? እንዴት ተቆጠረ የሚለው ጥያቄ ነው። የችግኞቹ አቆጣጠር በተመለከተ 
 • የችግኝ ቆጠራውን በተመለከተ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ኃላፊነት ሲሆን በሥሩም አንድ ቡድን ተቋቁሟል። ቡድኑ የችግኝ ተከላዎችን አቆጣጠራቸውንና ምዝገባቸውን የሚከታተል ነው።
 • በሚኒስትር መስሪያቤቱ የበለጸገ ሶፍትዌር የተተከሉትን ችግኞች በመቁጠር ሂደት ወሳኝ ስራ እንደተሰራ በአንድ ወቅት መስርያቤቱ በሰጠው ማብራርያ ላይ ገልጿል።
 • ሶፍት ዌሩ በዛፍ መትከያ ቦታዎች ላይ የተከላውን ሂደት ለመቆጣጠር የተመደቡ ሰዎች ስልክ ላይ ብቻ የሚሠራ ሲሆን በአካል በመገኘት የቆጠሩትን ችግኝ ብዛት የሚያስተላልፉበት ሥርዓት አለው።
 • በዚህም መሠረት በተመደቡበት ቦታ ላይ ምን ያህል ችግኞች እንደተተከሉ ቁጥሩን ሲያስገቡ ሶፍት ዌሩ በተለያዩ ቦታዎች የሚደርሱትን አሃዞች በማጠቃለል እየደመረ ውጤቱን ይሰጣል። በመጨረሻ ላይም በአጠቃላይ በመላዋ ሃገሪቱ የተተከሉትን ችግኞች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እንደሚያሳውቅም ቢቢሲ አማርኛ ከአራት ዓመታት በፊት ሰፊ ዘገባ ሰርቶበታል።
 • እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ከተተከሉ በኋላ ምን ያህሉ እንክብካቤ እየተደረገ ነው? ለመትከል የተቋቋመው ግብረኃይል ያህል ለመንከባከብም ህብረተሰቡ እራሱ ሊያቋቁመው የሚገባ ግብረኃይል መኖር አይገባውም ወይ? የሚለው ጥያቄ አሁንም አለ።ከተተክሉት ምን ያህሉ እየጸደቁና የክረምት ዝናብ እስኪመጣ ለምልመው የመቆየት አቅም አዳበሩ? የሚለው በተመለከተ ተአማኒ ጥናት ተደርጎ መቅረብ ያለበት ነው።
ዘንድሮ ለመትከል የታሰበው ምን ያህል ነው?

ሁለተኛው የደን ልማት  ምዕራፍ ትናንት በአፋር ሲከፈት
 • የመጀመርያው የደን ልማት ምዕራፍ ከሐምሌ 22፣2011 ዓም እስከ ዘንድሮ ያለው ሲሆን፣ትናንት ሰኔ 1፣2015 ዓም በአፋር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣የክልል ፕሬዝዳንቶች እና የፈረንሳይ፣ጣልያንና ቻይናን ጨምሮ በርካታ በአዲስ አበባ ተቀማጭ የሆኑ ዲፕሎማቶች በተገኙበት የተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የደን ልማት (ችግኝ ተከላ) መርሐግብር አራት ዓመታት የሚወስድ ሲሆን በእነኝህ ዓመታት ውስጥ ደግሞ 25 ቢልዮን ችግኞች ለመትከል ስራ ተጀምሯል።
 • በመጀመርያው ምዕራፍም እንዲሁ ከ25 ቢልዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው ይታወቃል።
 • በእዚሁ በሁለተኛው ዙር  በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 60 በመቶ የጥምር ደን እርሻ ችግኞች፣ 35 በመቶ ደግሞ የደን ችግኞች ሲሆኑ 5 በመቶ ለከተማ ውበት የሚውሉ ችግኞች መሆናቸውን በማስጀመርያ መርሐግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አብራርተዋል።
ለማጠቃልል ይህ የደን ልማት ስራ ለኢትዮጵያ የህልውናዋ ወሳኝ እና ቁልፍ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ነው።የእዚህ ዓይነቱ ስራ ደግሞ የፖለቲካ እና ፖሊሲ አውጪው አካል የቁርጠኝነት ልክ በሚፈለገው ደረጃ ካልሆነ ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም። ለእዚህ ደግሞ ሀሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ በተከታታይ ለተግባራዊነቱ የፖለቲካ አመራር ቁርጠኛነት እንዲኖር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት መስጠት ወሳኝ ለመሆኑ ማንም ሊረዳው የሚገባ ነው። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አንዳንድ አክቲቪስቶች ሳይቀሩ የተከሉትን የዛፍ ቁጥር እየቆጠረ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽልማት ሲሰጥ ኢትዮጵያ ለምትሰራው ስራም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መስጠት የሚገባውን ያህል እውቅና አለመስጠቱ ብቻ ሳይሆን የዜና ሽፋኖችም ሆኑ በዛፍ የመትከል ስነስርዓት ላይ ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ወይንም ዋና ጸሐፊው ተገኝተው ኢትዮጵያን ማበረታታት ግዴታቸው ነበር። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምትተክለው ለእራሱ መተንፈሻ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጾ የሚያደርግ ነው። ለሁሉም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዳግማዊ ምንሊክ ኢትዮጵያን በደን ለማልበስ የጀመሩትን በጎ ጅምር በማስቀጠላቸው ሀገራዊም፣ዓለም አቀፋዊ ሽልማት ይገባቸዋል።
=============////==========

ማስታወሻ - 

ለእዚህ ጥንቅር ጉዳያችን ቢቢሲ አማርኛ፣ኢዜአ እና ፋብኮ ዘገባዎች ለመዳሰስ ሞክራለች 


No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...