ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, June 7, 2023

''ያንን ጉድጓድ ማን ማሰው? ያ! ሰው። ማን ገባበት? የማሰው።'' ኢትዮጵያዊነትን ቀና ለማድረግ የተኛህ ንቃ! የጀዋር የሌሊት ወፍ ፖለቲካና የኦነግ ሸኔ ኦሮምያን የመገንጠል ቅዠት።


በጅማ ጎዳናዎች ላይ ሰዎች ''አዕምሮውን ስቷል'' የሚሉት እርሱ ግን የራሱ ፍልስፍና እና አስቸጋሪ የህይወት ውጣ ውረድ ላይ ያለፈ ሰው ነው በቀይ ሽብር ጊዜ ለተፈጸመው ግድያ እና እርሱን ተከትሎ ለመጣው እልቂት በእየመንገዱ እየዞረ የሚናገር ሰው ነበር።ታሪኩ እውነተኛ ታሪክ ነው።ስሙ ለጊዜው ይቆይና ሸገር ኤፍኤም ሰሞኑን በስንክሳር ሳምንታዊ መርሐግብሩ ላይ የግለሰቡን እውነተኛ ታሪክ አስደምጦናል።ግለሰቡ በጅማ መንገዶች ላይ እየዞረ ይለፍፍ ከነበረው ውስጥ ''ያንን ጉድጓድ ማን ማሰው? ያ! ሰው። ማን ገባበት? የማሰው።'' የሚለው እዝነ ልቦናዬን የሳበው አባባል ነው።

ኢትዮጵያዊነትን ቀና ለማድረግ የተኛህ ንቃ!

ኢትዮጵያ ላይ ጉድጓድ የማሱባት ሁሉም እራሳቸው ገብተውበታል። ይህ ግን ዝም ብሎ በተዓምር ብቻ የመጣ አይደለም። ለኢትዮጵያ መስዋዕትነት የከፈሉ ለማንነቷ የቆሙ የእውነት ዜጎች ስላሏት ነው።ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ ብቻ በትንሹ ቆንጽለን ለማስታወስ ብንሞክር ከኡጋዴን በረሃ እስከ የኤርትራ በርሃዎች፣በምጽዋና አሰብ በር ላይ በጨበጣ ውግያ እየተሞሻለቁ ለኢትዮጵያ አንድነት ህይወታቸውን ከሰዉት እስከ የቅርቡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ መከላከያ ሰራዊቷ ላይ የተከፈተው የህልውና ዘመቻ ድረስ ሺዎች ለኢትዮጵያ ሞተዋል። ይህች ሀገር በቀልድ የተሰራች አይደለችም።በፌዝ እና በቧልትም የሚዘባበቱባት ምድር አይደለችም። የደም ዋጋ ነች። ሰንደቅ ዓላማዋን  ለመስቀል የሚነዝራቸው የባንዳ አስተሳሰብ ስንኩልነት ያጠቃቸው ሊያናንቋት እንደሚፈልጉት አይደለችም።የማንም ሀገር ህልውና በመሽሞንሞንና በዋዛ ተከብሮ አልኖረም። ኢትዮጵያዊነትም ኢትዮጵያዊነት የሚጠሉትን በማሽኮርመም አይከበርም።

የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን በከፍተኛ ግለት እና ማንነት እንዳያስከብር እንቅፋት የሆነው አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያውያንን በጎሳ የመከፋፈል ሴራ ነው። ኢትዮጵያዊነቱን ለማስከበር የተነሳ የእገሌ ጎሳ ፍላጎት ልታሟላ ነው እየተባለ ሲሸማቀቅ ኖሯል።ይህ ደግሞ እንደ ሀገር ከመጉዳት አልፎ ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ ቁልቁለት እየመራት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ከደቡብ እስከ ሰሜን፣ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በአንድነት ቆሞ ኢትዮጵያዊነቱን አጽንቶ እንዳይይዝ ምሑራን የተባሉቱ ሳይቀር በኦሮሞ፣አማራ፣ትግራይ ወዘተ የብሔር አስተሳሰብ ውስጥ ተሰንገው የእየብሔራቸው ተንታኞች ሆነው መክነው ቀርተዋል። ኢትዮጵያዊነት በእዚህ ሁሉ መሀል እየተጎሳቆለ እና እየደበዘዘ የመጣ እንዲመስል ሆኗል።ኢትዮጵያዊነት በሰሜን ቢበርድ ደቡብ ያቀጣጥለዋል፣ ምዕራብ ቢያቀዘቅዘው ምስራቅ ይዞት ይነሳል።በሁሉም ዘንድ ግን ኢትዮጵያዊነት እንደ የተዳፈነ ፍም በድንገት እንደቋያ እየተቀጣጠለ ይንቦገቦጋል።ለእዚህ ነው ዘላቂው ኢትዮጵያዊነት እንጂ እንደኩፍኝ የሚጠፋ ነገር ግን ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል የጎሳ ፖለቲካን ጭዳ ማድረጉ አይቀርም። ለእዚህ ግን ከምሑር እስከ ጨዋ፣ከሊቅ እስከ ደቂቅ ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን እንደገና ማቀጣጠል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው። እያንዳንዱ ጥቃቅን እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊነትን ለመነቅነቅ የሚደረጉ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች፣ጽሑፎች እና ሙከራዎች ሁሉ ላይ የማያዳግም አጸፋዊ ምት ለመስጠት ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከምር ካልተነሳን ኢትዮጵያን ለባንዳና ዱርዬ ሸኔ እና መሰሎቹ አስረክበን የታሪክ ተጠያቂ የመሆን ግዙፍ አደጋ ላይ ነን። 

የጀዋር የሌሊት ወፍ ፖለቲካና የኦነግ ሸኔ ኦሮምያን የመገንጠል ቅዠት።

ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የገባችበት የለውጥ ሒደት ውስጥ ያለፈችባቸው ውጣ ውረዶች ከውጭ የኢትዮጵያ ጠላቶች ብቻ የተፈበረኩ አይደሉም። ኢትዮጵያን ገልብጦ ለመስራት እና የነበረ ታሪኳን አፍርሶ የባዕዳን ተገዢ ለማድረግ የሚሮጡ የራሳችን ወገኖች የጥፋት ድግስ ውጤት ነው። የለውጦቹ ሒደቶች ኢትዮጵያዊነትን እያኮሰሰ መከፋፈል እና የሀሰት ትርክቶችን እያመነዠከ የሚኖር የጀዋር እና የኦነግ ሸኔ ኦሮምያን የመገንጠል ቅዠት ውስጥ በገቡ ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪዎች ሀገር ታውኳል። የእነኝህ የጥፋት ኃይሎች ሴል በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ገብቶ ፖሊሲ ለማጣመም ከመሞከር የጸጥታ ኃይሉ በቀጥተኛ ጭፍጨፋ ውስጥ እንዲገባ ሙከራ እስከማድረግ ደርሷል።

የጀዋር ፖለቲካ የሚለው በግለሰብ ስም ተጠቀሰ እንጂ ሃሳቡ በእርሱ አስተሳሰብ ውስጥ ተግተልትለው የሚጓዙ ሁሉ የሚመለከት ነው። ጀዋር ስለ ኦሮምያ ክልል ይጨነቃል ብሎ የሚያስብ ወይንም አጀንዳው የኦሮምያ ክልል የብሔርተኝነት ፖለቲካ የሚመስለው ካለ ተሳስቷል። የጀዋር የፖለቲካ ማኔፌስቶ የሚጀምረውም የሚያልቀውም ሆነ ሙሉ መገለጫው ከእዚህ በፊት '' የሜጫ ንግግሩ'' ተብሎ በሚታወቀው የአሜሪካን ሀገር ንግግሩ የተቋጨ ነው። ኦሮምያን የፈለጋት በእዚሁ ንግግሩ ላይ እንደገለጸው የጽንፍ አክራሪ እስልምና ለማራመድ ከሌላው ክልል በተሻለ የእምነቱ ተከታዮች ይገኛሉ በሚል እና ክልሉ የተሻለ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ነው በሚል የሚማልሉ አንዳንድ የመካከለኛ ምስራቅ ሀገሮችን የቆየ አጀንዳ ማስፈጸም ብቻ እና ብቻ ዓላም ያደረገ ነው። 

ጀዋር የኦሮምያ ክልል መተራመስ፣የአማራ ክልል ሰላም ማጣት እና የኢትዮጳ ማዕከላዊ መንግስት አለመረጋጋትን እና የኦሮምያ ክልል የመገንጠል ዓላማን ማራገብ እንደ ስልታዊ ማስፈጸምያ እንጂ አንድም የኦሮምያ ብሔርተኝነት መቆርቆር ፍላጎት የለውም። ጀዋር የሌሊት ወፍ ፖለቲካ በለውጡ መሃል ላይ አራምዷል። የሌሊት ወፍ አንድ የቆየ ታሪክ ይነገርላታል። ይሄውም በአንድ ወቅት የሰማይ አዕዋፋት እና የምድር አራዊት ተጣሉ ይባላል።የምድር አራዊት የሰማይ አዕዋፋት መሬት ላይ አያርፏትም፣ውሃም አይጠጡም ምግብም አይበሉም ብለው አመጹ።የሰማይ አዕዋፋት ደግሞ የምድር አራዊት ዝናብ እንዳያገኙ፣ፀሐይ እንዳይሞቁ እንደደመና አጥልተን እንጎዳቸዋለን ብለው ተነሱ።በእዚህ መሃል ታድያ ከምድር አጥቢ እንስሳትም ሆነ ከሰማይ አዕዋፋት የምትመደበው የሌሊት ወፍ የምድር አራዊት እና የሰማይ አዕዋፋት ላስታርቅ ብላ ተነሳች። ሆኖም ግን ለማስታረቅ ተነስታ ሁለቱን ለማጣላት ላይና ታች ሮጠች። ሆኖም ሁለቱም የሰማይ አዕዋፋት እና የምድር አራዊት አንዳቸው ካለአንዳቸው እንደማይኖሩ አውቀው ታረቁ።ሲታረቁ የሌሊት ወፍ ለሁለቱም ታቀብል የነበረው የማጣያ ነገሯ ተገለጠ። ጀዋር በአንድ ወቅት የኦሮምያ አንድነት ምክርቤት ይህንን ሰነድ ፈርሙ፣ ያንን ቅደዱ እያለ መኖርያው ቤት ድረስ እየጠራ ሲያፈራርም ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ ኦነግ ሸኔን ከኦሮምያ ክልል ጋር ለማስታረቅ ወለጋ ወረድኩ ሲልም ተደምጧል። ሆኖም ግን በሂደት ኦነግ ሸኔም ሆነ የኦሮምያ ክልል ብልጽግና አላመኑትም።የእርሱ አጀንዳ የኦሮምያ ክልል ጉዳይ አይደለም። አጀንዳው ሌላ ነው። ይህ ማለት ግን ከብልጽግናም ሆነ ከኦነግ ሸኔ ከግለሰቡ እና ተከታዮቹ ጋር አይሞዳሞዱም ማለት አይደለም። የሁሉም ጠላት ኢትዮጵያዊነት እና የኢትዮጵያ ያለፈ ታሪክ ጠልነት አገናኛቸው እንጂ አሁንም የጀዋር ግብና መድረሻ አክራሪ መንግስት በኢትዮጵያ ማቆም ነው።ይህንን ደግሞ በግልጽ ወደፊት የበለጠ ፍንትው እያለ የሚመጣ ሃቅ ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ የኦነግ ሸኔ እና የጀዋር መንገድ አንድ ሌላ የጋራ ነጥብ ላይም ይገናኛል።ይሄውም የኦሮምያ ክልልን በረጅም ጊዜ መገንጠል እና የራሷ መንግስት ማድረግ ለእዚህም ከወዲሁ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ አደረጃጀት ማጎልበት በሚለው ጉዳይ ላይ ነው። የጀዋር እና የቡድኑ ፍላጎት በኦሮምያ መገንጠል የአክራሪ መንግስት በኦሮምያ ይመሰረታል በሂደት የምስራቅ አፍሪካን በአክራሪ መንግስት ተጽዕኖ ውስጥ ማስገባት እና መስፋፋት ነው። ይህንን ስልት ደግሞ አንዳንድ የመካከለኛ ምስራቅ ሀገሮች ለረጅም ጊዚ ሲያልሙት የነበረው እና የአፈጻጸሙ ሂደት ሲያጠኑት የነበረ ነው። ኦሮምያን የመገንጠል ፍላጎት የለም የሚለው የአንድ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የፓርላማ ንግግርን እዚህ ላይ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረግ ቀዳሚ ጉዳይ ነው። 

የኦሮምያ ክልልል ህዝብም ከወዲሁ ሊያውቀው የሚገባው ይህ ሁሉ በክልሉ ያለው ግርግር መድረሻ ክልሉን መገንጠል ነው። በክልሉ የሚገኙ የሌላ ክልል ተወላጆች ማባረር፣የንግድ ተቋሞቻቸውን ለምሳሌ በሻሸመኔ የተፈጸመው ዓይነት የማውደም ስራ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን እና መስጊዶችን ማውደም፣የትርክት ታሪክ መፍጠር እና ለማሳመን መሞከር፣የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ከብሔራዊ መዝሙር አልቆ ለማሳየት የሚደረገው መጋጋጥ ሁሉ ግቡ ኦሮምያን ለመገንጠል ነው። መገንጠሉን ብሔርተኞቹ ከብሔር አንጻር ሲያዩት ጀዋር እና ቡድኑ ግን ሁሉንም በመጨረሻ አስወግዶ የአክራሪ ጽንፈኛ መንግስት ከተቻለ በኢትዮጵያ ደረጃ ካልተቻለ በኦሮምያ ክልል ደረጃ መመስረት ነው። በእዚህ ፍላጎት ውስጥ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የኦሮምያ ክልል የአሁኑ ግፈኛ እና ሙሰኛ ቡድን ጨምሮ የብልጽግና መንግስትም እንዲዳከም እነኝሁ ቡድኖች አብረው ይሰራሉ። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት መዳከም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ያቀነቅናሉ የሚባሉ የአማራ፣አፋር፣ሱማሌና ጌድዮ ጭምር ሰላም እንዳይኖራቸው እና እንዲታወኩ የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ እንዲታወክ ሁሉም ቡድኖች አብረው ይሰራሉ።

መፍትሔዎቹ 

ኢትዮጵያውያን ዋና ግባችን ሊሆን የሚገባው ዛሬም ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ብቻ መሆን አለበት። የጀዋር የሌሊት ወፍ ፖለቲካም ሆነ የኦነግ ሸኔ ዓላማዎች ኢትዮጵያዊነትን ማደብዘዝ ነው።ይህንን መሰሪ አካሄድ አለማወቅ ትልቅ ጥፋት ነው። ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ ለማስኬድ ደግሞ አንዳንዶች እነርሱ ስልጣን ላይ ሲመጡ ብቻ የሚሳካ አድርገው ይህንኑ ስልጣን ለመያዝ በሚደረግ ፍትጊያ ውስጥ ብቻ ይጠመዳሉ። የፖለቲካ ስልጣን ማለት ቤተመንግስት መግባት ብቻ አይደለም። በየትኛውም መንገድ ተጽኖ ፈጥሮ ዓላማን ማስፈጸም ነው።ኢትዮጵያዊነትን የማይቀበል እና የማያጎላ መንግስት እንዳይኖረን የግድ ቤተመንግስት መግባት እና ፖሊሲ አውጪ መሆን ብቻ አሁን ባለንበት የ21ኛው ክ/ዘመን ብቸኛው መንገድ አይደለም። የማስፈጸም አቅምን መገንባት እና አሁን ያለውን መንግስት ፖሊሲ አስገድዶም ሆነ አስረድቶ ኢትዮጵያዊነትን ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ ዓይነተኛው መንገድ ነው። የሚወጣውን ጸረ ኢትዮጵያዊ ፖሊሲ መቃወም እና ኢትዮጵያዊ አጀንዳዎች በትክክል እንዲተገበሩ የጎሳ ፖለቲካ እንዲሽቀነጠር ተጽዕኖ የመፍጠር መንገድ በራሱ የፖለቲካ ስልጣን ነው። ይህንንም ከሰላማዊ ትግል እስከ የምሁራን ተከታታይ ሞጋች ጽሑፎች እና ንግግሮች፣ከትምሕርት ፖሊሲው አስጣጥ እስከ የመገናኛ ብዙኃን የእየዕለቱ መልዕክቶች ሁሉ መዳሰስ እና በኢትዮጵያዊነት ቅኝት እንዲቃኙና ትውልድ እንዲያፈሩ ማድረግ ሁሉ የተጽዕኖ መፍጠርያ እና መተግበርያ መንገዶች ናቸው። ኢትዮጵያዊነት አገንግኖ እንዲወጣ እና የጎሳ ፖለቲካን አሽቀንጥሮ ሁሉም በህብረ ብሔራዊ ስሜት ከጎሳ አደረጃጀት የጸዳ እውነተኛ የፌድራሊዝም ስርዓት በኢትዮጵያ ለማምጣት የሞት ሽረት ትግል ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ አክራሪ የሌሊት ወፍ ፖለቲከኛን ሴል ከማምከን እስከ የጎሳ ፖለቲካ ሙሰኞች ድረስ ያለውን ትብተባ መበጣጠስ ይጠይቃል።ዛሬም ለአፍታ መዘናጋት አይገባም። ኢትዮጵያዊነትን ቀና ለማድረግ የተኛህ ንቃ! ይህ ግዙፍ ኃይል የተዳፈነ እረመጥ ነው።ሲነሳ ማንም አይስቆመውም።ጀዋርም ሆነ ኦነግ ሸኔ፣የጎሳ ፖለቲካ የተከለው ህወሓትም ሆነ የጽንፍ ኃይሎች ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ ጉድጓድ ምሰዋል።ነገር ግን በማሱት ጉድጓድ ገቡ።ነገሩ እንደ የጅማው ምስኪን ''ያንን ጉድጓድ ማን ማሰው? ያ! ሰው። ማን ገባበት? የማሰው።'' እንዳለው ነው። አሁን ኢትዮጵያዊነትን ቀና እናድርገው።የጎጥ ፖለቲካን እንቅበረው። በህብረት ከተነሳን እንችላለን።ነገር ግን በየጎጡ እየተቧደንን ለኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገራችንን የማስረከብ አደጋ ላይ ነን።
================//////=============
ቀና በል!
በድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሣሁን




No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...