ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, June 30, 2023

የዘመኑ ምሑር ችግር፣ትልቁን ሀገራዊ ስዕል ትቶ በጥቃቅን የመንደር ጉዳዮች የመዋጥ ችግር ነው።


=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች።በእኛ ዘመን እንደገባችን መጠንም ብቻ አይደለችም።ከ20ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የተነሳው ትውልድ የገጠመው የዕውቀትም ሆነ መጪውን የሚያመላክተው የኮከብ ምሑራን እጦት በእጅጉ ጎድቶታል። ከ1960 ዎቹ የተነሳው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የመሩት ሐያዎቹን ያልዘለሉ፣በስሜት እና ከውጭ የግራ ክንፍ ጽሑፎች ባነበቡት የኢትዮጵያን ታሪክ ለመገልበጥ የሞከሩ መሆናቸው በቀጣይ ሀገሪቱን ወዴት እንደመራት እና ዛሬ ድረስ የእዚህ ሁሉ ውጤት ለጎሰኛ እና ስርዓት አልበኛ የፖለቲካ ድርጅቶች መፈልፈል አሳልፎ ሰጥቶትን ብዙ ነገሮች እንዲበላሹ አድርጎ ኢትዮጵያን ጎድቷል።

አሁን ያለው ምሑር ችግር ትልቁን ሀገራዊ ስዕል ትቶው በጥቃቅን ጉዳዮች መዋጥ። ትውልድ የሚያሻግረውን አጀንዳ ጥሎ ከከንፈር እስከ አፍንጫ የሚደርስ አጀንዳ አንጠልጥሎ መብረር እንደ አዋቂ እያስቆጠረ ነው።ይህ የሀሳብ ልዕልና የመውረድ ችግር በጊዜ ካልተገታ አጠቃላይ ውድቀት ያስክትላል። የሚድያ ውይይቶቹ፣ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚቀርቡት የወቅታዊ ጉዳይ ተብለው የሚነሱት ርዕሶች ትውልዱ ትልቅ እና ተሻጋሪ ሃሳቦችን ላይ እንዲያሰላስል የሚያደርጉ ሳይሆኑ፣እገሌ የተባለው ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የወጣው መረጃ ተብሎ ምሑራን ሃሳብ ይስጡበት ተብሎ የሚጠየቅበት፣ከተጨባጭ መረጃዎችና የጥናት ውጤቶች ይልቅ ''እየተወራ ያለው '' ተብሎ የሀገር ፖለቲካ የሚተነተንበት ሂደት ይህንን ትውልድ ከማስደንበር እና መጪውን ጊዜ አጨልሞ እያየ እንዲባንን ከማድረግ በላይ የነገዋን ኢትዮጵያ ፈጽሞ አይገነባም።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ስናነሳ የምናነሳበት ጥግ በጣም ደካማና የመንደር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ከመሆኑ የተነሳ ኢትዮጵያን አስፈንጥረው የሚያነሱ አንኳር ጉዳዮችን ለትውልዱ ለማሳየት እና አጀንዳ ለመፍጠር ምሑራንም ሆኑ ጋዜጠኞች ሲጥሩ አይታይም። ለእዚህ ደግሞ ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው። አንዱ ከፍተኛ የአቅም ማነስ እና ልዩነት ይታያል።ወቅታዊውን ጉዳይ አብስሎ የመከታተል፣የማንበብ፣ለማወቅ የመጣርና፣ያወቁትን እውነት ለማንጠር ያለመቻል ችግር በግልጽ ይታያል።ይህ አቅም ደግሞ በድንገት በአንድ ምሽት የሚመጣ አይደለም።ልምድ፣ዕውቀትና አንጥሮ የመለየት አቅም ማዳበር ላይ ብዙ ይቀረናል። ሁለተኛው ምክንያት ለተከታታይ ዓመታት በጠባብ የጎሳ አስተሳሰብ ስርዓት ውስጥ ተነክሮ የመውጣት ችግር ነው። ይህ ሁለተኛው ችግር በተለይ አጥብቦ የማየት ችግር በመሆኑ የተሻለ ነገር ለማማተር ስንኩል የሆነ አካሄድ አስከትሏል።

ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች።መጪው ትውልድ ደግሞ የዛሬ ጋዜጠኞች እና ምሁራን በሚያነሱት የአስተሳሰብ ልክ በየቀኑ እየተቀረጸ ይሄዳል። የዛሬ ምሁራን እና ጋዜጠኞች የሚያነሱት ትልቁን የኢትዮጵያ ጉዳይ ሳይሆን ጥቃቅን እና የመንደር ወሬዎች ላይ ባተኮሩ ቁጥር ለትልቋ ኢትዮጵያ የሚቆም ትውልድ እና የቱ የሀገሪቱ ትልቅ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የማያውቅ ትውልድ ማፍራት ይጀመርና ኢትዮጵያን ወደ የባሳ አደጋ ይዟት ይሄዳል። የሀሳብ ልዕልና የመውረድ ችግር በጊዜ ካልተገታ አጠቃላይ ውድቀት ያስክትላል።ስለሆነም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የምትወያዩ፣ የምትጽፉ እና ወቅታዊ ጉዳዮች በሚል የሀገር ጉዳይ ላይ የምትናገሩ ሁሉ ከትናንሽ አጀንዳዎች ወጥታችሁ፣ ትልቁ፣ሀገራዊና ትውልድ ተሻጋሪ በሆኑ ሀሳቦች ላይ አትኩሩ።ትልቅ ሀገርን የሚመጥን አጀንዳ ከወሬ እና ከይመስለኛል ሀሳቦች የራቀ ጠንካራ እና ውስጥን የሚሰረስር ትውልድ የሚያነቃ ነው። 
==========///==========

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...