Wednesday, February 7, 2018

የዘመነ አክሱም ስልጣኔ ቅርሶች የማን ናቸው?


በቀሲስ መንግሥቱ ጐበዜ
ሉንድ ዩንቨርሲቲ ፣ ስዊድን
(ቀሲስ መንግስቱ ጎበዜ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አርኪኦሎጂ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና በሉንድ ዩንቨርስቲ የዶክትሬት የመጨረሻ ዓመት ትምህርታቸውን በታሪክ ዘመን አርክዮሎጂ በማጥናት ላይ ይገኛሉ)
የአክሱም ሐውልት
አክሱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ስልጣኔ እምብርት፣ የጠንካራ መንግሥታዊ አስተዳደር ማዕከል እና የድንቅ ባህል መድረክ እንደነበረች ይታወቃል። የታቦተ ጽዮን መገኛ፣ የቅዱስ ያሬድ መፍለቂያ፣ የመጀመሪያው ጳጳስ አባ ሰላማ (ፍሬምናጦስ) መንበር፣ የዘጠኙ ቅዱሳን በዓት የነበረችው አክሱም በኢትዮጵያ የክርስትና ሐይማኖት ታሪክ ልዩ ክብርና ስፍራ አላት። አክሱም የመጀመሪያዎቹ የሙሃመድ ተከታዮች ከሃገራቸው በተሰደዱ ጊዜ በእንግድነት ተቀብላ መጠጊያ ስለሆነች በሙስሊሙ ዓለምም ውለታዋ የሚዘነጋ አይደለም።

የአክሱም መንግሥት በትንሹ ከመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ መኖሩ ሲታወቅ፤ ጠንካራ መሪዎችና የራሱ የሆነ የመገባበያ ገንዘብ እንደነበረውም ይታወሳል። በዚሁ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ዞስካለስ በመባል የሚታወቀው ንጉሥ የግሪክኛ ቋንቋን በደንብ የሚያውቅና የአዶሊስ ወደብን በዋና የንግድ ማዕከልነት ይጠቀም እንደነበር ተመዝግቧል። የአክሱም መንግሥት ኃያልነት ከ2ኛው እስከ 3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረው የአዶሊስ ሐውልት ጽሑፍ (Adulis Inscription) ላይ ተጠቅሷል። በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ማኒ የተባለ ፐርሺያዊ ጸሐፊ አክሱምን ከሮም፣ ከፐርሺያና ከቻይና ጋር በመደመር በዘመኑ ከነበሩት የዓለም ሃያላን መንግሥታት ተርታ አስቀምጧታል። ከ4ኛው እስከ 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለነበረው ከፍተኛ የሆነ የአክሱም መንግሥት እድገትና ብልጽግና ከበቂ በላይ የታሪክ ምስክሮች ይገኛሉ። የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ንጉሥ ኢዛና እና የ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ንጉሥ ካሌብ በቤተመንግሥትም ሆነ በቤተክህነቱ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ናቸው።

የአክሱም ስልጣኔ አንድአንዶች እንደሚመስላቸው አንድን ህብረተሰብ ብቻ የሚወክል ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የድምር እንቅስቃሲያቸው ውጤት ነው። ለምሳሌ ያህል አክሱም የሚለውን መሰረተ ሥርወ ቃል (etymology) መመልከት ተገቢ ይሆናል። አክሱም የሚለው ቃል ‘አኽ’ ከሚለው የአገውኛ ቃል (ትርጉሙ ውሃ ማለት ነው) እና ‘ስዩም’ ከሚለው የግዕዝ ቃል (የተሾመ፣ ሹም እንደ ማለት ነው) የተገኘ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት አለ። በአንድ ላይ ተጠቃሎ ሲነበብም ‘የውሃ ሹም’ የሚለውን ትርጉም ይሰጣል። እስከ ዛሬ ድረስ በአክሱም ‘ማይ ሹም’ (የውሃ ሹም) ተብሎ የሚታወቅ ቦታ መኖሩ የስያሜውን እውነትነት ያጠናክረዋል። ለረጅም ዘመን የዋግ (ሰቆጣ) መሪዎች ‘ዋግ ሹም’ በሚል የማዕረግ ስም ይጠሩ እንደነበርም ይታወቃል። ከላስታ ነገሥታት መካከልም ሁለቱ ‘ግርማ ስዩም’ (የንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ አባት) እና ‘ዛን ስዩም’ (የንጉስ ላሊበላ አባት) ተብለው ይጠሩ እንደነበር ልብ ይሏል። አክሱም የሚለው ቃል ስያሜ መሰረቱ የኩሽ (አገውኛ) እና የሴም (ግዕዝ) ቋንቋዎች ጥምረት ከሆነ የአክሱም መንግሥት፣ ሥልጣኔ እና ቅርሶቹ የኩሽና የሴም ሕዝቦች መስተጋብር ውጤት መሆናቸውን ከዚህ በላይ ማሳያ የለም።

ሆኖም ግን የታሪክና የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች እንደሚመሰክሩት የአገው ሕዝቦች በአክሱም ዘመነ መንግሥት አስተዳደርና እና የስልጣኔ ፈርጦቹ የነበራቸውን ከሁሉም የላቀ አስተዋጽኦ መካድ አይቻልም። ከጅምሩ አገዎች በቁጥር ብዙና በመልካዓ ምድራዊ አሰፋፈራቸውም ቀላል የማይባለውን የአክሱም መንግሥት ወሰነ ግዛት ያካተተ ነበር። አገዎች የመካከለኛውና የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ቀደምት ነዋሪዎችና አገር አቅኝዎች መሆናቸውም ይታወቃል። እነዚህ ሕዝቦች የአባይ ወንዝ መነሻ ከሆነው ከጣና ጀምሮ የጎጃም፣የጎንደር፣ የላስታ፣የዋግ (ሰአቆጣ) እና የትግራይ በርካታ አካባቢዎችን በማካተት የመረብን ወንዝ ተሻግረው እስከ ኤርትራ ግዛት ከረን ድረስ ሰፍረው ይኖሩ ነበር። ይህ ትልቅ የሕዝብ ቁጥርና ሰፊ የቦታ ይዞታ በራሱ አገዎች በዘመነ አክሱም ተጽእኖ የመፍጠር አቅም እንደነበራቸው አመላካች ነው።

አገዎች ዓይነተኛ በሆኑ ጥንታዊ የታሪክ መዛግብት (primary sources) ከተጠቀሱት ጥቂት ሕዝቦች መካከል አንዱ ናቸው። ከላይ በተጠቀሰው የአዶሊስ የሃውልት ላይ ጽሑፍ (Adulis Inscription)፣ የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የንጉሥ ኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ (Ezana Inscription)፣ እንዲሁም በ6ኛውመቶ ክፍለ ዘመን የኮስሞስ ጽሑፍ (Christian Topography of Cosmas Indicopleustes) የአገዎችን እንጅ በዘመናችን የሚታወቁ የሌሎች ሕዝቦችን ስም አናገኝም። ከአገው ሌላ አጋዚ የሚለው ስም በጥንቱ መዛግብት የተገለጸ ሲሆን ይኸውም የግዕዝ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን (አጋዝያን) የሚመለከት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። በአዶሊስ ሐውልት ጽሑፍ (Adulis Inscription) ላይ የአክሱም ንጉስ ከአጋዚ ነገድ ጋር እንደተዋጋ ተጥቅሷል። በሌላ በኩል ከአክሱም መንግሥት ሥልጣኔ ጋር የቅርብ ዝምድና ሊኖራቸው ይችላል ተብለው የሚታሰቡት ሕዝቦች ስማቸው በጥንቱ የአክሱም ዘመን የታሪክ ሰነዶች አልተካተተም። ለምሳሌ የትግራይ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ ተጠቅሶ የሚገኘው በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአክሱም መንግሥት ማክተም በኋላ ነው።

አገዎች በአክሱም መንግሥት የባህል፣ የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው የሚጠቁሙ አያሌ ማሳያዎች አሉ። ከነዚህም አንዱ አገዎች በአክሱም መንግሥት በከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያገለግሉ እንደነበር የሚያስረዳው የኮስሞስ ጽሑፍ ነው ። በዚህ የታሪክ ሰነድ ላይ እንደተገለጸው በንጉሥ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነትና እምነት የሚጠይቀውን ረጅም የወርቅ ንግድ መተላለፊያ መስመር የሚቆጣጠረው የአገው ሰው ነበር። በተለይ ደግሞ ለአክሱም ስልጣኔ መዳበር አገዎች የነበራቸውን ጉልህ ሚና የምንረዳው የራሳቸውን መንግሥት ላስታ ላይ ከመሰረቱ በኋላ የአክሱምን ሥልጣኔ አሻሽለው መድገማቸው ነው። የመንግሥት ማዕከሉ ከአክሱም ወደ ላስታ ከመሸጋገሩ ውጭ በሁለቱ ዘመናት የነበረው የአስተዳደር ዘይቤ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የውጭ ግንኙነት ወዘተ የጎላ ልዩነት ነበረው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። በአክሱምም በዛጉዬም ዘመናት ግዕዝን በዋና ቋንቋነት ይጠቀሙ ነበር። በአክሱምም በዛጉዬም ዘመናት ቤተ መንግሥትና ቤተክህነት እጅግ የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው። በርግጥ በዛግዬ ዘመን ነገሥታት ካህናትም ተፈጥረዋል። የአክሱም ነገሥታት በተለይ ከግብፅና ከኢየሩሳሌም ጋር የነበራቸው ግንኙነት በዛጉዬ ዘመንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። የአክሱም ዘመን የህንፃ አሰራር ጥበብ በዳበረ መልኩ በዛጉዬ ዘመን ተንፀባርቋል።

አገዎች የአክሱም መንግሥት አካል ስለነበሩ ድሮም የሚያውቁትን የኪነ ህንፃን ሥራ በረቀቀ መንገድ በላስታ ላይ አሳይተዋል። በተለይ ደግሞ የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ስንመለከት ከአክሱም ዘምን የህንፃ ጥበብ ጋር ያላቸው የቅርብ ዝምድና ሁለቱም ከአንድ ምንጭ የተቀዱ መሆናቸውን ለመረዳት አያዳግትም። ወጥ ዓለትን በመፈልፈል ለሚፈልጉት ዓላማ ማዋልን መሰረት ያደረገው ኢትዮጵያዊ ሥልጣኔ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከአገው ሕዝቦች ጋር የተዛመደ ስለመሆኑ ዋነኛ አመላካች ነው። መርዶክ የተባለው ጸሐፊ “ሁሉም ማስረጃዎች የሚጠቁሙት የአገው ሕዝብ በአፍሪካ በባህላዊ የፈጠራ ክህሎቶች የተካኑ መሆኑን ነው።” በማለት የገለጸው ከዚህ ተነስቶ ሳይሆን አይቀርም።

ሲጠቃለል የአክሱም ዘመን ስልጣኔ ውጤት የሆኑ መንፈሳዊና ባህላዊ ቅርሶችን የራሱ ብቻ እንደሆኑ አድርጎ የሚያስብ የህብረተሰብ ክፍል ቢኖር ታሪካዊ እውነታው አይፈቅድለትም። ያም ከሆነ ከአገው ሕዝብ በላይ የቀረበ ማንም እንደሌለ የሚመሰክሩ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ። አገዎችም ቢሆኑ በጊዜ ብዛት በተለይ በአማርኛ፣ በትግርኛ እና በኋላም ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተዋጡ (assimilated) ወይም ከነዚህ ሕዝቦች ጋር የተቀየጡ (mixed) በመሆናቸው ብዙውን የጥንቱን የአገው ማኅበረሰብ የምናገኘው በነዚህ ሕዝቦች ውስጥ ጭምር መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ደግሞስ አክሱም የሚለው ስያሜ ራሱ ከላይ እንደተመለከትነው በኩሽና በሴም ቋንቋዎች ጥምረት የተፈጠረ ቃል አይደል! ስለሆነም የጥንቱ የአክሱም ዘመን ስልጣኔ ቅርሶች የሁላችንም ቅድመ አያቶች ድንቅ የእምነት፣ የስራና የፈጠራ ውጤቶች መሆናቸውን ማስተባበል አይቻልም። አክሱማዊ ቅርሶቻችን የሁሉም ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሰርተውና ጠብቀው ያቆዩልን የጋራ ሀብቶቻችን ናቸው። ከዚህም በላይ የአክሱም መካነ ቅርስ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ የሚገኝ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ሀብት መሆኑም ማወቁ ተገቢ ነው።

ማጣቀሻዎች
McCrindle, John Watson (ed.,tr), 1897. The Christian Topography of Cosmas, an Egyptian monk, London.

Merid Wolde Aregay, 1971. ‘Southern Ethiopia and the Christian Kingdom 1508-1708’. Unpublished PhD thesis, School of Oriental and African Studies, University of London.

Munro-Hay, S. 1991. Aksum. An African Civilisation of Late Antiquity. Edinburgh University Press, Edinburgh.

Munro-Hay, Stuart. 2003. ‘Aksum’, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden

Murdock, George P., 1959. Africa: Its people and their culture history, New York

Phillipson, D.W. 2009. Ancient Churches of Ethiopia, Fourth–Fourteenth Centuries. Yale University Press: New Haven/London.

Phillipson, D.W. 2004. The Aksumite roots of medieval Ethiopia. Azania 29: 77-89.

Quirin, James. 2003. ‘Agäw’, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden

Sergew Hable Selassie. 1972. Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270. United Printers: Addis Ababa.

Sima, Alexander. 2003. ‘Agazi’, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden

Smidt, Wolbert. 2010. ‘Tigray’, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden

Taddesse Tamrat, 1972, Church and state in Ethiopia, 1270-1527, Oxford.

Taddesse Tamrat, 1988. Process of Ethnic Interaction and Integration in Ethiopian History: the Case of the Agaw (Special Issue in Honour of Roland Oliver), the Journal of African History, 29, 1, 5-18.

Tuesday, January 30, 2018

የትግራይ ሕዝብ ይህ አጋጣሚ ባያልፈው ይመረጣል።የአድዋዎችን የመገንጠል እና ትግራይን ከቀረው ሕዝብ የማጋጨት ሥራ በመቃወም የሚነሳበት ጊዜ አሁን ነው (የጉዳያችን ማስታወሻ)


  • ህወሓት አሁን ለእርድ ያቀረበው የትግራይን ሕዝብ ነው
  • ህወሓት በእጁ የቀረው የትግራይ ሕዝብ ስለሆነ ከእጁ እንዳያፈተልክበት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብቷል።
ህወሓት ሙሉ የስልጣን ዘመኑን ያሳለፈው ሕዝብ ከህዝብ ሲያጋጭ ነው።የምናውቀውን ኦሮምኛ ተናጋሪውን ኦነግ፣አማርኛ ተናጋሪውን ግንቦት 7፣ሱማልኛ ተናጋሪውን የኦጋዴን ገንጣይ እና የአልሸባብ ተላላኪ እያለ በጅምላ ሕዝብ እየፈረጀ እርስ በርስ ስንፈራራ እንድንኖር አድርጎናል።ለስልጣኑ ሲል ለእርድ የማያቀርበው ሕዝብ በህወሓት ዘንድ የለም።ህወሓት አሁን ለእርድ ያቀረበው የትግራይን ሕዝብ ነው።
አንዳንዶች ህወሓት ከትግራይ ስለተነሳ ለትግራይ ሕዝብ የሚጨነቅ አድርገው የሚያስቡ አሉ።ህወሓት የትግራይን ሕዝብ የምፈልገው ለስልጣን መንጠላጠያ ብቻ ነው።

የተቀሩትን የኢትዮጵያ ክፍሎች ለማናከስ በተለይ በኦሮሞ እና አማራ መካከል ያለው ግጭት አልፈጠር ሲል ህወሓት በእጁ የቀረው የትግራይ ሕዝብ ስለሆነ እርሱ እንዳያፈተልክበት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብቷል። ይህንንም ስላወቀ ሕዝቡን በስጋት ውስጥ ከትቶ የፋሺሽታዊ ስራው ሙሉ በሙሉ ተባባሪ እንዲሆን እና እንዳያፈነግጥ ወጥሮ ይዞታል። ለእዚህ ማስረጃው ህወሓት በመጀመርያ የትግራይን ሕዝብ ከጎንደር ሕዝብ ጋር አጣላው በመቀጠል ከወሎ ሕዝብ ጋር ግጭት እንዲፈጠር አደረገ። አንዳንዶች ይህ ተግባር ለትግራይ ታስቦ የተደረገ ቢመስላቸው መጃጃላቸውን ከመግለፅ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም። ሕዝቡን የሚወድ ድርጅት በተቻለ መጠን የሚወደው ሕዝብ ከሌሎች ጋር እንዳይጣላ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል እንጂ እንዴት ለወልቃይት ችግር ክላሽ እናቶች አሮጊቶችን እያስያዘ ያስዝታል? ሕዝቡን የሚወድ ድርጅት እንዴት በወልዲያ ጫወታ ላይ ቀድሞ ካረዎቹን ልኮ በአደባባይ እየተፉ የሚዝቱ ጠብ ጫሪዎች  እንደ መንገድ ጠራጊ ነቢይ ቀድሞ ልኮ እሳት ይለኩሳል? ሕዝቡን የሚወድ ድርጅት እንዴት ሕዝቡን እንደ ግል እቃው ቆጥሮ ስለመገንጠል ያዜምለታል።
ሎሚ ፅባ በሶፍያ አፅብሃ (በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምነው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊትን ግንባር ድረስ ሄደው በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ላይ ያነቃቃ የነበረው የሙዚቃ ሉዑክ )
አሁን የትግራይ ሕዝብ በአድዋ ስብስብ አማካይነት የደረሰበትን ፍጥጫ እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የገባውን መቃቃር የሚያደበዝዝ መልካም አጋጣሚ ህወሃቶችን የመገንጠል አጀንዳ በማንሳታቸው ምክንያት አትወክሉንም ብሎ መነሳት ካለበት ወቅቱ አሁን ነው።ሕዝብ ለዘላለም ይኖራል ድርጅቶች ግን በእየዘመኑ ተለዋዋጭ ናቸው።የትግራይ ህዝብም መመልከት ያለበት ይህንን የው።አሁን ምንም አይነት ቅሌን ጨርቄን የሚያስብለው ጉዳይ የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ላይ መነሳት እና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መስመሩን ማስተካከል የቀረበለት መልካም ዕድል ነው። እድሉን መጠቀም ብልህነት ነው።ህወሓት እኛን አይወክልም።መገንጠል የሚል አጀንዳ የትግራይ ሕዝብ አይደለም! የጥቂት ህወሃቶች እብደት ነው! ብሎ ድምፅን ማሰማት የብዙ በሽታ መፈወሻ ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Friday, January 26, 2018

ሳተናው

ጉዳያችን / Gudayachn
ጥር 19/2010 ዓም (ጃንዋሪ 27/2018)


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Tuesday, January 23, 2018

ለቤተ መንግሥቱም ሆነ ለቤተ ክህነቱ አልቅሱለት! ጥቁሩ ሰማይ እየመጣ ነው (የጉዳያችን ማስታወሻ)

በጽሁፉ መጨረሻ ላይ የቴዲ አፍሮ የባህር ዳር ኮንሰርት ቪድዮ ይገኛል።
ጉዳያችን /Gudayachn
ጥር 17፣2010 (ጃንዋሪ 24/ 2018 ዓም )

የኢትዮጵያ ፖለቲካ መዳረሻ ብዙዎቻችን እንደምንመኘው አለመሆኑ ግልጥ እየሆነ ነው።ብዙዎች የስርዓቱ አቀያየር የሰውም ሆነ የንብረት ጥፋት ከሁሉም በላይ ደግሞ የነበረውን ማኅበራዊ አንድነት በማይነካ መልክ ወይንም ጉዳቱ በቀነሰ መልክ ቢሆን የሚል ምኞት ነበራቸው።ህወሓት ግን በጥላቻ በተመረዘ ልቡ አስከሬን ከወለጋ እስከ ወልዲያ እያነጠፉ በመምጣት ብቻ ስልጣን ለማስጠበቅ ወስኗል።ሕዝብም የህልውና ጉዳይ ነው እና እራሱን ከመከላከል ከተሞቹን እና ገጠሩን ከህወሓት በዘር ጥላቻ ከተወጋ ሰራዊት ማፅዳት ብቸኛ መንገድ መሆኑን እያመነ የመጣበት ወቅት ነው።

በኢትዮጵያ የትኛውም መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የህወሓት የመንደር ልጅ መሆን እንደ መስፈርት እየተወሰደ ድርጅቶቹን መቆጣጠር ከተጀመረ ሁለት አስር ዓመቶች አልፈውታል።ይህም በመሆኑ ከአሁን በኃላ የሥርዓት አካሄዶች እና ስለ ኢትዮጵያ ሲባል የነበሩ ጨዋነቶች ሁሉ የመጨረሻ እንጥፍጣፊ ደረጃ ላይ ደርሷል።

"ህወሓት እና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው" የሚለው አባባል ቀድመው የነገሩን ደጋግመው በየመድረኩ ላይ የሚዘፍኑልን የህወሓት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች ናቸው።እነርሱ ያሉትን ሌላው ሕዝብ ካነሳው ደግሞ "ዘረኛ" ይባላል።እሺ! ህወሓት እና የትግራይ ሕዝብ አንድ አይደለም ሲባል ደግሞ ሕዝቡን ከድርጅቱ ለመለየት ነው የሚል ነጠላ ዜማ ይለቀቃል።እውነታው ግን በኢትዮጵያ የሰፈነው የህወሓት የአፓርታይድ (የዘረኘንት) ስርዓት ከመቼውም በላይ የፋሽሽት ባህሪውን እየተፋ ነው።በቅርቡ በመቀሌ የተደረጉ የህውሓት ስብሰባዎች በስልጣን ለመቆየት በጅምላ መፍጀት የሚል እንደሆነ ያፈተለኩ መረጃዎች እንደደረሷቸው የሚናገሩ የመብዛታቸውን ያህል ከእሬቻ እስከ ነቀምት፣ከአምቦ እስከ ወልዲያ በህወሓት የተፈፀሙት የጅምላ ፍጅቶች ቤተ መንግሥቱም ቤተ ክህነቱም እንደማይተርፉ እና ጥቁሩ ደመና እየመጣ መሆኑን አመላካች ነው።

 ለቤተ መንግሥቱም ሆነ ለቤተ ክህነቱም አልቅሱለት! 

ላለፉት ዓመታት ለተፈፀሙት ግድያዎች ሀዘኑን በቅጡ መግለጥ ያቃታቸው ቤተ መንግስት እና ቤተ ክህነት ጥቁሩ ሰማይ እየመጣ መሆኑን መረዳት አለባቸው።የቤተ መንግሥቱም ሆነ የቤተ ክህነቱ ችግር እንደ ሸረሪት ድር ያደራባቸው የህወሓት ጎሳዊ መዋቅር እንጂ በእራሳቸው ያመነጩት እኩይ ባህሪ እንደሌለ ግልጥ ነው። ቤተ መንግስቱ ውስጥ ከምዕራብ አፍሪካ የፕሮቴስታንት ነቢይ ነን የሚሉ ግለሰቦች እያስመጡ ያስባረቁበት አቶ ሃይለማርያም እና አባ ዱላ ስለ እውነት ሊናገሩ ቀርቶ እበላ ባይ አንደበታቸውን ስርዓቱን ለማቆየት የውሸት ክምር ሲከምሩ በሃይማኖት ስም የቆሙ የአጋንንት ልጆች መሆናቸውን ነው በአደባባይ ያስመሰከሩት።

በሌላ በኩል በቤተ ክህነቱ በኩል ከፓትርያሪክ እስከ አጥብያ አስተዳዳሪ ከህወሓት መወለድ ብቻ እንደመስፈርት ተቆጥሮ ለሺህ ዓመታት ሕዝብ ከመንግስት እየዳኘች፣የፍትህ ምንጭ ሆና መሪዎችን በስነ ምግባር ብቻ ሳይሆን በአስተዳደር ጥበብ ሁሉ ስታንፅ የኖረች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ልጆቿ ታቦተ ሕጉን በጥምቀት በዓል አጅበው ሲወጡ በመትረጌስ ሲፈጁ ድርጊቱን መቃወም አይደለም የፍትሐት ጸሎት የማያደርጉ ፓትርያሪክ እየመሯት መሆናቸው የታሪክ ቁስል ነው።ቤተ ክህነቱ እንደ አየር መንገዱ ተርሚናል ፈታሾች የስራ ቋንቋ ትግርኛ እስኪመስል ድረስ ከአጥብያ አጥብያ እየዞሩ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ መተዳደሪያቸው የሆኑ ህወሐታውያን ተግባር አሁን ላይ የመረረ ምላሽ ከህዝብ ሊያገኝ ጫፍ ላይ ደርሷል። የሚነሳውን ማዕበል የታንክ እና የመትረጌስ ጋጋታ አያድነውም።ቁስሉ የተዘጠዘው ሕዝብ ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል አይመልሰውም።ህወሓትም ሕዝብ የሚያታልልበት ቃላትም ሆነ ሃሳብ አልቀውበት ባዶ አዳራሽ የሚንገላወድ ሰካራም ሆኖ ከወዲያ ወዲህ መንቆራጠጥ ብቻ ስራው ሆኗል።

ጥቁሩ ዳመና እየመጣ ነው

አሁን ለቤተ መንግሥቱም ለቤተ ክህነቱም አልቅሱለት።ሁኔታው ያስፈራል።ማስፈራት ብቻ ሳይሆን በስሜት የሚወሰደው የህዝብ እርምጃ ታሪካችንንም እንዳያጠለሽ ማሰብ ያስፈልጋል።በማሰብ ብቻ ግን የሚያስቀረው አንዳችም ነገር ያለ አይመስልም።አንድ ቀን ጧት ወይንም ቀትር ላይ አልያም ምሽት ላይ ፍልጥ የያዙ እናቶች፣አባቶች፣ወጣቶች እና ሕፃናት ሳይቀሩ በድንገት ቤተ ክህነቱም ሆነ ቤተ መንግስቱ በር ላይ ይደርሳሉ። ያን ጊዜ የሚፈልጉትን ሰው ያውቃሉ።በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ መተዳደሪያቸው አድርገው  ቅምጥል ኑሮ እየኖሩ በነፃ ደፋ ቀና የሚሉትን የቤተ ክርስቲያኗን አገልጋዮች የምያስለቅሱት የት ናቸው ብሎ ግቢውን ይወረዋል።ያን ቀን የጥቁሩ ደመና ቀን ተብሎ ይጠራል።በእዚህ ቀን ፈድራል ፖሊስ ሆነ ህወሃታዊነት አይድንም። ያን ጊዜ የአቶ መለስን ፎቶ ከአቡነ ሺኖዳ እና አቡነ ጳውሎስ ጋር  የሰቀልኩ  ባለ ውለታ እኔ ነኝ ብሎ ማሽቃበጥ የለም።ያን ጊዜ በጠቆረ ሰማይ ስር አመልጣለሁ ማለት የለም። ይህ ቀን ያስፈራል።ፍትህ ሳያገኙ ሕዝብ እጅ የሚወድቁ ሊኖሩ ይችላሉ።

በተመሳሳይ ቤተ መንግሥቱም እንዲህ እንዳስፈራ አይኖርም።ሴቷ ማማሰያ ወንዱ ፍልጡን ይዞ ከመርካቶ ከኮተቤ ከእንጦጦ  እና ከተቀረው ክፍል ሕዝብ ይተማል። ያን ጊዜ የምዕራብ አፍሪካ የፕሮቴስታንት ነቢይ ተብዬዎች አያስጥሉም ። ፍትህ በሕዝብ እጅ በመውደቅ ምቾት እንደተሰማት በግልፅ ታውጃለች። በእርግጥ አሁንም ያስፈራል።ሆኖም ግን ስላላወራነው ይቀራል ማለት አይቻልም።ህወሓት በወልዲያ፣በአምቦ፣በሐረር ፣በሕር ዳር እና በጎንደር  ያደረገው ግድያ እና የጅምላ ጭፍጨፋ ይዘው የሚመጡት ይህንኑ ነው።ያን ጊዜ ለቤተ መንግሥቱም ሆነ ለቤተ ክህነቱ ግፈኞች አልቅሱላቸው። እውነታውን ከአሁኑ አውቆ መስመሩን የሚያስተካክል ቢኖር በአለቀ ሰዓትም ቢሆን እራሱን ያወጣል።ፍልጥ ግን ለቤተ መንግሥቱም ቤተ ክህነቱም ያሰጋዋል።ከእዚህ በፊት በጉዳያችን ላይ የተባሉት ነገሮች የማይደርሱ ሕልም የሜመስሏቸው ብዙዎች ነበሩ።ዛሬ ላይ ሆነው ሲመለከቱት ግን አይወቅሱም።የቤተ መንግሥቱም ሆነ የቤተ ክህነቱ ፍልጥ በያዘ ሕዝብ መከበቡ እና መመንጠሩ የማይቀር የቅርብ ጊዜ ክስተት አይሆንም ለማለት አያስደፍርም።

አዲስ ላይ ተከልክሎ ባህር ዳር ላይ የተፈቀደው የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የባህር ዳር ኮንሰርት  
ማስታወሻ : -ከላይ የቀረበው ፅሁፍ ከቴዲ አፍሮ ኮንሰርት  ጋር የተገናኘ አይደለም።


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Thursday, January 18, 2018

ሰበር ዜና - የአዲስ አበባ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዛሬው የጥምቀት ከተራ በዓል ጥይት ሲተኮስ አምሽቷል።የታሰሩ ምዕመናን አሉ።ምዕመኑ ቤተ ክርስቲያናችንን እናስከብራለን ብሎ ተነስቷል።




  • የሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን በእዚህ ደረጃ ለማስከበር መነሳት በሌሎች አጥብያዎች ያለውን ተመሳሳይ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ዘረፋ እና ብክነት ጉዳይ ይቀሰቅሳል የሚል ሽብር በአባካኞቹ መንደር ሁሉ  ፈጥሯል።
  • ካለ አንዳች ጥፋት ታቦት አጅበው  ይዘምሩ የነበሩ  መዘምራን  በፖሊስ ታፍሰው ነበር።
  • ውጥረቱ ተባብሷል።ምእመን አብዛኞቹ የታሰሩትን አስፈትቷል።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የዛሬ አስራ አምስት ቀን ምእመኑ በሙስና እና በቤተ ክርስቲያን ንብረት ዘረፋ የከሰሳቸውን የቤተ ክርስቲያኑን አለቃ የሂሳብ ሹም እና የሰበካ ጉባኤ  ታህሳስ 10/2010 ዓም በድንገት በቤተ ክርስቲያን በመድረስ የሂሳብ ሹሙ እና የሰበካ አባላት እንዳይወጡ ካደረገ በኃላ ለፓትርያሪኩ ፅህፈት ቤት፣ለአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ባለ 26 ነጥብ የያዘ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።በወቅቱ የቀረበው ጥያቄ ዋና ጭብጥ ሐራ ዘተዋህዶ በድረ ገፁ እንደዘገበው የሚከተሉትን ነጥቦች የያዘ ነበር። እነርሱም : -

  • ዋና አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣ ዋና ጸሐፊው ዕፁብ የማነ ብርሃን፣ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር ካሳሁን ገብረ ሕይወት እና ሒሳብ ሹሙ ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፤
  • በሕገ ወጥ መንገድ ያለምእመን ተሳትፎ በዝግ አዳራሽ የተመረጠውና በቀሲስ ካሳሁን ገብረ ሕይወት የሚመራው ሰበካ ጉባኤ ፈርሶ በቃለ ዐዋዲው መሠረት ምእመኑንና የካቴድራሉን አገልጋዮች የሚወክል ሰበካ ጉባኤ እንዲመረጥ፤
  • በቀጣይም በካቴድራሉ አስተዳደር ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርቶ ለሕግ የሚያቀርብ ኮሚቴ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከሀገረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነትና ከአጥቢያው ምእመናን እንዲዋቀር፤
  • የውጭ ኦዲተር ተመድቦ የካቴድራሉ ገቢና ወጪ ኦዲት እንዲደረግ የሚሉ ነበሩ፡፡

በእዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ ኀሙስ፣ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ችግሩ በግልጽ ተጣርቶ የመጨረሻ እልባት እስኪሰጠው ድረስ፡-የሚከተሉት አገልጋዮች እንዲታገዱ ወሰነ።
  1. አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣
  2. ዋና ጸሐፊው ሊቀ አእላፍ ዕፁብ የማነ ብርሃን፣
  3. ሒሳብ ሹሙ ሊቀ ትጉሃን ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ፣
  4. ተቆጣጣሪው ቀሲስ ሳሙኤል ደሳለኝ፣ 

ሆኖም እግዱ ከተፈፀመ በኃላ ቀን ከሌሊት ምዕመናን ቢሮው ውስጥ ያለው ሰነድ እንዳይሰረቅ እየጠበቁ ከአንድ ሳምንት በላይ ቀን ፀሐይ ሌሊት ብርድ እየተፈራረቀባቸው ዘልቀዋል።ቢሮው በክፍለ ከተማ፣በፖሊስ፣ከምዕመናን የተውጣጣ ኮሚቴ  እና በሀገረ ስብከት እማኝነት ብቻ እንዲከፈት አፅንኦ ምዕመኑ ሰጥቶ ቀንና ሌሊት እየተፈራረቀ መጠበቅ ጀመረ።ሆኖም በተደጋጋሚ ጉዳዩን ለመሸፋፈን የሞከሩ  የሀገረ ስብከት ሰዎች ለብቻቸው በመምጣት ለመክፈት እንደሞከሩ እና ምዕመኑ በተቃውሞ እንዳገዳቸው ተሰምቷል። ከአስተዳዳሪው ጋር የጠበቀ የጥቅም ግንኙነት እንዳላቸው የተወሳው ፓትርያርኩ ለአቤቱታ የሄዱ ምዕመናንን በአግባቡ ከማስተናገድ ይልቅ አግባብነት የሌለው ንግግር ብዙዎችን አሳዝኗል።

ምእመኑ በድንገት የአለቃውንም ሆነ የስራ ባልደረቦቻቸውን ቢሮ ማሸጉ  በፖሊስ ኃይል ለአባካኝ ክፍሉ አለቃውን ጨምሮ  ሽፋን ለመስጠት እየሞከረ ያለው የመንግስት ኃይልም ሆነ በጥቅም ትስስር የሚታሙት የቤተ ክህነት ሰዎች ትልቅ ዱብ ዕዳ ሆኖባቸዋል።በተለይ የተቃውሞው እለት ምእመኑን ሽጉጥ ቤተ ክርስቲያን ቅፅር ግቢ አውጥቶ ሊያስፈራራ የሞከረው የሂሳብ ሹም ''ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች '' የሚለውን ተረት ተደጋግሞ በብዙ ምእመናን በዕለቱ ከመሰማቱም በላይ  ምዕመኑ በከፍተኛ ቁጣ ከአሁን በኃላ ማንንም ኃይል አንፈራም በሚል እንደቆረጠ ተስተውሏል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ የጥምቀት ከተራ በዓል ምሽት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ፖሊስ መዘምራንን ማፈስ ጀምሮ ነበር።በመቀጠል ህዝቡ ሲቃወም ፖሊስ በተኩስ አካባቢውን አውኮ አምሽቷል።ሁኔታውን መምህር ዘመድኩን በቀለ  እንደሚከተለው የነበረውን ሁኔታ ገልጦታል።
      "ዘሬ ታቦቷን ወደ ባህረ ጥምቀቱ ላለማውረድ ወስነው በቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ ድንኳን መጣል ተጀምሮ ነበር ። በኋላ የመንግሥት አካላት መጡና " ለገፅታ ግንባታችን " ጥሩ ስላልሆነ ታቦቱ በተለመደው ስፍራ ይውጣ ፣ ጥበቃውን በጋራ ከእናንተ ጋር በመናበብ እንሠራለን ይላቸዋል ። ህዝቡም ተስማማ ። ነገር ግን የቤተክርስቲያን ጥበቃውን በተመለከተ የህወሓት ፖሊስም ባለስልጣንም እውነት በመናገር ያማይታወቁና የማይታመኑ በመሆኑ አብዛኛው ህዝብ በጥበቃው ላይ ሆኖ ሌላው ደግሞ ወደ ከተራው እንዲሄድ ይስማማሉ ።
ጉዞ ወደ ባህረ ጥምቀቱ ተጀመረ ። መሃል ላይ የፌደራል ፖሊስ ላይ ከች አለ ። እናም ታቦቷን አጅቦ የሚዘምሩትን ወጣቶች አያስገደደ ወዳዘጋጀው መኪና መጫን ጀመረ ። 'አረ ምንድነው በህግ አምላክ!' ቢባል ወይ ህግ " መስሚያዬ ጥጥ ነው " ብሎ ፖሊስ  ምእመናኑን እየደበደበ መጫኑን ቀጠለ ። እንዲህማ አይደረግም ብለው የቀረቡት አረጋውያንና አባቶች ላይም ጥይት ወደላይ መተኮስ ጀመረ ።  ፖሊስ  ሕዝብ እንደድሮው ጥይት ሲተኮስ የሚፈረጥጥ መስሎታል ። " የራበው ህዝብ መሪዎቹን ይበላል " እንዲል ዶር መረራ ጉዲና ህዝቤ እንዳንገሸገሸው አላወቀ ዝም ብሎ ይተኩሳል ።
ህዝቡም ተኩሱን እንደ ሙዚቃ በመቁጠር ያፈሳችኋቸውን ልጆቻችን ፍቱ! ያለበለዚያ ዛሬ ነገር ይበላሻል !ብለው ድርቅ አሉ ። ፖሊስ   ጨነቃት ፣ ድንጋይ በእጁ የጨበጠው በዛ ፣ ሊተናነቅና ጥሎ ሊሞት ያሰፈሰፈውም እንዲሁ በረከተ ። አዲስአበባ ወደ ጦር አውድማ ልትቀየር ደረሰች ። ይህን የህዝቡን ጽናት ያየውና የተመለከተው ፖሊስ ሆዬ ነገር አብርድ አለ ። እናም ከነቃችሁ አትገደዱም ፣ እኛ እናንተን አስቦክተን ግዳጃችንን ልንወጣ ነበር ፣ አልተሳክቶም ብሎ ያሠራቸውን ፈትቶ ሹልክ ብሎ ሔዷል ።"

በመጨረሻም  የሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን በእዚህ ደረጃ ለማስከበር መነሳት በሌሎች አጥብያዎች ያለውን ተመሳሳይ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ዘረፋ እና ብክነት ጉዳይ ይቀሰቅሳል የሚል ሽብር በአባካኞቹ መንደር ሁሉ  ፈጥሯል።


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com