ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, January 18, 2018

ሰበር ዜና - የአዲስ አበባ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዛሬው የጥምቀት ከተራ በዓል ጥይት ሲተኮስ አምሽቷል።የታሰሩ ምዕመናን አሉ።ምዕመኑ ቤተ ክርስቲያናችንን እናስከብራለን ብሎ ተነስቷል።




  • የሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን በእዚህ ደረጃ ለማስከበር መነሳት በሌሎች አጥብያዎች ያለውን ተመሳሳይ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ዘረፋ እና ብክነት ጉዳይ ይቀሰቅሳል የሚል ሽብር በአባካኞቹ መንደር ሁሉ  ፈጥሯል።
  • ካለ አንዳች ጥፋት ታቦት አጅበው  ይዘምሩ የነበሩ  መዘምራን  በፖሊስ ታፍሰው ነበር።
  • ውጥረቱ ተባብሷል።ምእመን አብዛኞቹ የታሰሩትን አስፈትቷል።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከተማ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የዛሬ አስራ አምስት ቀን ምእመኑ በሙስና እና በቤተ ክርስቲያን ንብረት ዘረፋ የከሰሳቸውን የቤተ ክርስቲያኑን አለቃ የሂሳብ ሹም እና የሰበካ ጉባኤ  ታህሳስ 10/2010 ዓም በድንገት በቤተ ክርስቲያን በመድረስ የሂሳብ ሹሙ እና የሰበካ አባላት እንዳይወጡ ካደረገ በኃላ ለፓትርያሪኩ ፅህፈት ቤት፣ለአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት እና ለቅዱስ ሲኖዶስ ባለ 26 ነጥብ የያዘ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።በወቅቱ የቀረበው ጥያቄ ዋና ጭብጥ ሐራ ዘተዋህዶ በድረ ገፁ እንደዘገበው የሚከተሉትን ነጥቦች የያዘ ነበር። እነርሱም : -

  • ዋና አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣ ዋና ጸሐፊው ዕፁብ የማነ ብርሃን፣ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር ካሳሁን ገብረ ሕይወት እና ሒሳብ ሹሙ ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፤
  • በሕገ ወጥ መንገድ ያለምእመን ተሳትፎ በዝግ አዳራሽ የተመረጠውና በቀሲስ ካሳሁን ገብረ ሕይወት የሚመራው ሰበካ ጉባኤ ፈርሶ በቃለ ዐዋዲው መሠረት ምእመኑንና የካቴድራሉን አገልጋዮች የሚወክል ሰበካ ጉባኤ እንዲመረጥ፤
  • በቀጣይም በካቴድራሉ አስተዳደር ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርቶ ለሕግ የሚያቀርብ ኮሚቴ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከሀገረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነትና ከአጥቢያው ምእመናን እንዲዋቀር፤
  • የውጭ ኦዲተር ተመድቦ የካቴድራሉ ገቢና ወጪ ኦዲት እንዲደረግ የሚሉ ነበሩ፡፡

በእዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ ኀሙስ፣ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ችግሩ በግልጽ ተጣርቶ የመጨረሻ እልባት እስኪሰጠው ድረስ፡-የሚከተሉት አገልጋዮች እንዲታገዱ ወሰነ።
  1. አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣
  2. ዋና ጸሐፊው ሊቀ አእላፍ ዕፁብ የማነ ብርሃን፣
  3. ሒሳብ ሹሙ ሊቀ ትጉሃን ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ፣
  4. ተቆጣጣሪው ቀሲስ ሳሙኤል ደሳለኝ፣ 

ሆኖም እግዱ ከተፈፀመ በኃላ ቀን ከሌሊት ምዕመናን ቢሮው ውስጥ ያለው ሰነድ እንዳይሰረቅ እየጠበቁ ከአንድ ሳምንት በላይ ቀን ፀሐይ ሌሊት ብርድ እየተፈራረቀባቸው ዘልቀዋል።ቢሮው በክፍለ ከተማ፣በፖሊስ፣ከምዕመናን የተውጣጣ ኮሚቴ  እና በሀገረ ስብከት እማኝነት ብቻ እንዲከፈት አፅንኦ ምዕመኑ ሰጥቶ ቀንና ሌሊት እየተፈራረቀ መጠበቅ ጀመረ።ሆኖም በተደጋጋሚ ጉዳዩን ለመሸፋፈን የሞከሩ  የሀገረ ስብከት ሰዎች ለብቻቸው በመምጣት ለመክፈት እንደሞከሩ እና ምዕመኑ በተቃውሞ እንዳገዳቸው ተሰምቷል። ከአስተዳዳሪው ጋር የጠበቀ የጥቅም ግንኙነት እንዳላቸው የተወሳው ፓትርያርኩ ለአቤቱታ የሄዱ ምዕመናንን በአግባቡ ከማስተናገድ ይልቅ አግባብነት የሌለው ንግግር ብዙዎችን አሳዝኗል።

ምእመኑ በድንገት የአለቃውንም ሆነ የስራ ባልደረቦቻቸውን ቢሮ ማሸጉ  በፖሊስ ኃይል ለአባካኝ ክፍሉ አለቃውን ጨምሮ  ሽፋን ለመስጠት እየሞከረ ያለው የመንግስት ኃይልም ሆነ በጥቅም ትስስር የሚታሙት የቤተ ክህነት ሰዎች ትልቅ ዱብ ዕዳ ሆኖባቸዋል።በተለይ የተቃውሞው እለት ምእመኑን ሽጉጥ ቤተ ክርስቲያን ቅፅር ግቢ አውጥቶ ሊያስፈራራ የሞከረው የሂሳብ ሹም ''ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች '' የሚለውን ተረት ተደጋግሞ በብዙ ምእመናን በዕለቱ ከመሰማቱም በላይ  ምዕመኑ በከፍተኛ ቁጣ ከአሁን በኃላ ማንንም ኃይል አንፈራም በሚል እንደቆረጠ ተስተውሏል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ የጥምቀት ከተራ በዓል ምሽት ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ፖሊስ መዘምራንን ማፈስ ጀምሮ ነበር።በመቀጠል ህዝቡ ሲቃወም ፖሊስ በተኩስ አካባቢውን አውኮ አምሽቷል።ሁኔታውን መምህር ዘመድኩን በቀለ  እንደሚከተለው የነበረውን ሁኔታ ገልጦታል።
      "ዘሬ ታቦቷን ወደ ባህረ ጥምቀቱ ላለማውረድ ወስነው በቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ ድንኳን መጣል ተጀምሮ ነበር ። በኋላ የመንግሥት አካላት መጡና " ለገፅታ ግንባታችን " ጥሩ ስላልሆነ ታቦቱ በተለመደው ስፍራ ይውጣ ፣ ጥበቃውን በጋራ ከእናንተ ጋር በመናበብ እንሠራለን ይላቸዋል ። ህዝቡም ተስማማ ። ነገር ግን የቤተክርስቲያን ጥበቃውን በተመለከተ የህወሓት ፖሊስም ባለስልጣንም እውነት በመናገር ያማይታወቁና የማይታመኑ በመሆኑ አብዛኛው ህዝብ በጥበቃው ላይ ሆኖ ሌላው ደግሞ ወደ ከተራው እንዲሄድ ይስማማሉ ።
ጉዞ ወደ ባህረ ጥምቀቱ ተጀመረ ። መሃል ላይ የፌደራል ፖሊስ ላይ ከች አለ ። እናም ታቦቷን አጅቦ የሚዘምሩትን ወጣቶች አያስገደደ ወዳዘጋጀው መኪና መጫን ጀመረ ። 'አረ ምንድነው በህግ አምላክ!' ቢባል ወይ ህግ " መስሚያዬ ጥጥ ነው " ብሎ ፖሊስ  ምእመናኑን እየደበደበ መጫኑን ቀጠለ ። እንዲህማ አይደረግም ብለው የቀረቡት አረጋውያንና አባቶች ላይም ጥይት ወደላይ መተኮስ ጀመረ ።  ፖሊስ  ሕዝብ እንደድሮው ጥይት ሲተኮስ የሚፈረጥጥ መስሎታል ። " የራበው ህዝብ መሪዎቹን ይበላል " እንዲል ዶር መረራ ጉዲና ህዝቤ እንዳንገሸገሸው አላወቀ ዝም ብሎ ይተኩሳል ።
ህዝቡም ተኩሱን እንደ ሙዚቃ በመቁጠር ያፈሳችኋቸውን ልጆቻችን ፍቱ! ያለበለዚያ ዛሬ ነገር ይበላሻል !ብለው ድርቅ አሉ ። ፖሊስ   ጨነቃት ፣ ድንጋይ በእጁ የጨበጠው በዛ ፣ ሊተናነቅና ጥሎ ሊሞት ያሰፈሰፈውም እንዲሁ በረከተ ። አዲስአበባ ወደ ጦር አውድማ ልትቀየር ደረሰች ። ይህን የህዝቡን ጽናት ያየውና የተመለከተው ፖሊስ ሆዬ ነገር አብርድ አለ ። እናም ከነቃችሁ አትገደዱም ፣ እኛ እናንተን አስቦክተን ግዳጃችንን ልንወጣ ነበር ፣ አልተሳክቶም ብሎ ያሠራቸውን ፈትቶ ሹልክ ብሎ ሔዷል ።"

በመጨረሻም  የሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን በእዚህ ደረጃ ለማስከበር መነሳት በሌሎች አጥብያዎች ያለውን ተመሳሳይ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ዘረፋ እና ብክነት ጉዳይ ይቀሰቅሳል የሚል ሽብር በአባካኞቹ መንደር ሁሉ  ፈጥሯል።


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

No comments: