ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, January 15, 2018

ኢትዮጵያ፣ግብፅ፣ሱዳን እና ኤርትራ ጦርነት ሊለኩሱ ነው? (የጉዳያችን ልዩ ዘገባ)

በእዚህ የጉዳያችን ዘገባ ስር የሚከተሉት ርዕሶች ተካተዋል -
  • የዛሬ የሰኞ ጥር 7/2010 ዓም ክስተቶች
  •  የአቶ ኢሳያስ የረጅም ጊዜ ወዳጅ -ግብፅ እውን ኤርትራ የለችም?
  • አቶ ኢሳያስ ህወሓትን የእዚህን ያህል ተናግረዋት አያውቁም ህወሓትም እንዲህ ስድብ ውጣ አታውቅም 
  • ኢትዮጵያ፣ግብፅ፣ሱዳን እና ኤርትራ ጦርነት ሊለኩሱ ነው?
  • ጦርነቱ ቢከፈት ማን ይጠቀማል? ማን ይከስራል?

President Sisi during the inauguration of developments projects in Egypt on Monday, 15 January 2017 (Photo: Ahram)

የዛሬ የሰኞ ጥር 7/2010 ዓም ክስተቶች 

"እኛ ወደ ጦርነት መሄድ አንፈልግም።ይህንን ለሱዳን እና ኢትዮጵያ ወንድሞቻችን ነግረናቸዋል" አሉ የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ዛሬ ሰኞ ጥር 7፣2010 ዓም ግብፅ ውስጥ አንድ የልማት ፕሮጀክት ከሚንስትሮቻቸው ጋር ሲመርቁ።አልሲስ ይህንን ይበሉ እንጂ ሱዳን አምባሳደሯን ከግብፅ ከጠራች ሁለተኛ ሳምንቷ ሆኗል።ሱዳን አምባሳደሯን ከግብፅ የጠራችው ከግብፅ ጋር ለዘመናት ካጨቃጨቃት በደቡብ ግብፅ የሚገኘው የሶስት ማዕዘን መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ እንዳለው የሚነገረው በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሚገኘው ሃላይብ የተሰኘው ቦታ ጉዳይ ነው።የሱዳን ፀብ ከግብፅ ጋር ይህ ብቻ አይደለም።ግብፅ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላት ግንኙነት ከአንድ ዓመት በፊት ተጠናክሯል።ሱዳን በአንፃሩ ከኢትዮጵያው የአባይ ግድብ ጋር በተያያዘ ከግብፅ የተለየ መንገድ ይዛለች።ይህም ሆኖ ግን አሁንም ግብፅ እና ሱዳን ከሚገባው በላይ ፀብ ውስጥ ይገባሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ውስጥ የምንገዋለል ነው። በእርግጥ ሱዳን አምባሳደሯን በእዚህ ወር መጀመርያ ሳምንት ከካይሮ ከማስጠራቷ በፊት ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ግብፅን ካሳጣች በኃላ መሆኑ ጉዳዩ በቀላል የሚታይ አለመሆኑን ያመላክታል።

አልሲስ በዲፕሎማሲ ንግግር "ከወንድሞቻችን ጋር ፀብ ውስጥ አንገባም" እያሉ አቶ ኃይለማርያም ከአዲስ አበባ ተነስተው ግብፅ ይገባሉ እየተባለ እየተጠበቀ ነበር። ዘግይቶ በተሰማ ዜና መሰረት የአቶ ሃይለማርያም የሰኞ ጉዞ መሰረዙ ተሰምቷል።"ኢጂፕት ቱዴይ" የአቶ ሃይለማርያም ጉዞ ወደ ሮብ መዞሩን ዘግይቶ ገልጧል።ለጉዞው መሰረዝ የተሰጠ ምክንያት የለም።የአቶ ኃይለማርያም ጉዞ በእራሱ  "ሀገር አሰዳቢ ጉዞ" ቢባል ይቀላል።ከወር በፊት ከአስራ አምስት በላይ የሚሆኑ የግብፅ ምክር ቤት አባላት ፊርማ አሰባስበው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይመጡ ሲሉ ማመልከቻ ለአፈ ጉባኤው አስገብተው ነበር።ይህ በሆነ በሁለት ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ "ጥቂቶች ናቸው" የሚለው የህወሓት አነጋገር ተጠቅመው የግብፅ ምክር ቤት አባላት ጉዞውን የተቃወሙ የግል ተወዳዳሪዎች እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ የሚወክሉ አይደሉም አሉ። ቃል አቀባዩ ይህንን ለሀገር ውስጥ ዜና ማሰራጫዎች ይናገሩ እንጂ አንድ የምክር ቤት አባል ማለት ስንት ሚልዮን ሕዝብ ወክሎ ምክር ቤት መግባቱን ቢያሰሉት ጉዳዩ ምን ማለት እንደሆነ በተረዱት ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው ግብፅ ሰኞ ይገባሉ የተባሉት  አቶ ኃይለ ማርያም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አቶ ወርቅነህን ማስከተላቸው እየታወቀ አንዳንድ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን "የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለ ማርያም" ግብፅ ይገባሉ እያሉ መፃፋቸው የተሰማው።  አቶ ኃይለማርያም ሀገር አሰዳቢ በሆነ የልምምጥ ፈገግታቸው ግብፅ ገብተው ምን ሊናገሩ እንደሚችሉ አምላክ ይወቅ።ኢትዮጵያ ከሃያ አምስት ዓመት በፊት የነበራትን የአካባቢ ተሰሚነት ሁሉ አፈር ድሜ ያበላው ህወሓት ድርድሩ ሁሉ ከስልጣኑ ጉዳይ ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ዘለቄታ ጥቅም ጋር የተቆራኘ እንዳልሆነ ያለፉት ዓመታት አስተምረውናል።

የአቶ ኢሳያስ የረጅም ጊዜ ወዳጅ -ግብፅ እውን ኤርትራ የለችም?

ግብፅ የአቶ ኢሳያስ የረጅም ጊዜ ወዳጅ ነች።ሻብያን አቶ ኢሳያስ እንዲያጠናክሩ የግብፅ እርዳታ ቀላል እንዳልነበር ብዙ የተባለለት ነው።በካይሮ ከሚገኝ የነዳጅ ማደያ ስጦታ አንስቶ ግብፅ ለሻብያ ያልሆነችው የለም።አቶ ኢሳያስም ወደ ካይሮ መመላለስ ያበዛሉ።የአሁኑ የግብፅ ፕሬዝዳንት አልሲስ ስልጣን ከያዙ ብቻ ባለፈው ሳምንት ካደረጉት ጉዞ ጨምሮ ካይሮን ከከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው ጋር ሲረግጡ አራተኛ ጊዜያቸው ነው።ግብፅ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የጦር አማካሪ ልካ እንደነበር እና ይህንንም አዲስ አበባ በሚገኙ ዲፕሎማቷ ሳይቀር "ጡረታ የወጡ ጀነራሎች የት ሀገር እየሰሩ እንዳሉ የመከታተል ግዴታ የለብንም" በሚል ማመኗ ይታወሳል።ይህ በእንዲህ እያለ ግብፅ በኤርትራ መሬት ላይ ወታደር ማስፈሯን አልጀዚራ ሳይቀር የዘገበው በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ነው።ይህንኑ ጉዳይ ኤርትራ ፈጥና ያላስተባበለች ሲሆን አቶ ኢሳያስ ካይሮ ደርሰው ከተመለሱ በኃላ ባለፈው እሁድ ምሽት ለኤርትራ ራድዮ እና ቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ ላይ የአልጀዚራን ዘገባ አስተባብለዋል።ይህ ማስተባበል ግን ከካይሮ ምክር በኃላ እንደመጣ የሚያስታውቀው አልጀዚራ ዘገባውን እንዳወጣ የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፈጥኖ አለማስተባበሉ ነው።

አቶ ኢሳያስ ህወሓትን የእዚህን ያህል ተናግረዋት አያውቁም ህወሓትም እንዲህ ስድብ ውጣ አታውቅም 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን በከሰላ በኩል የሚያዋስናት ድንበር ከመዝጋቷ በላይ ብዛት ያለው ሰራዊት እያሰፈረች መሆኑን የዜና ዘገባዎች በተከታታይ እየዘገቡ ነው።ዛሬ ሰኞ ጥር 7/2010 ዓም ብቻ ተጨማሪ ጦር ሱዳን መስደዷ ተሰምቷል።አቶ ኢሳያስ በእሁዱ ምሽት ቃለ መጠየቃቸው ላይ በከሰላ በኩል እየተከማቸ ያለው የሱዳን ወታደር ሳይሆን የህወሓት ሰራዊት ነው ካሉ በኃላ " እንደ ሕፃን አዝለን በታንክ እያገዝን አዲስ አበባ ስናስገባው የተሻለ ነገር ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ያመጣል ብለን ነበር።ሆኖም ለአካባቢው ጠንቅ ሆኗል።የአንቀልባውን ገመድ በጥሰን እናወርደዋለን" ብለዋል።
አቶ ኢሳያስ ጥር 6/2010 ዓም ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ 
Photo : Asmara, 15 January 2018 - Eri-Tv and Radio Dimtsi Hafash

 አቶ ኢሳያስ በህወሓት አንፃር በርካታ መግለጫዎች ሲሰጡ ተሰምተዋል እንደ አለፈው እሁድ ያለ ንግግር ግን ተናግረው አያውቁም።" The game is over" "ጫወታው (ድብብቆሹ) አብቅቷል" በሚል ንግግር የታጀበው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ህወሓት በምንም አይነት ጥገናዊ ለውጥ ሊያንሰራራ እንደማይችል አስረግጠው ተናግረዋል።እዚህ ላይ የህወሓት አድናቂዎች ልክዱት የማይችሉት አንድ አብይ ነጥብ አለ። ይሄውም ህወሓት በትክክል ድክሞ የሚያለከልክ ማረፍያ ጥግ የምያማትር ምስኪን ፍጥረት እንደሆነ ነው።ይህ ባይሆን ኖሮ አቶ ኢሳያስ ገና ስያነጥሱ ዶክመንተሪ ፊልም የሚያዝጎደጉድ ድርጅት ዛሬ አንቀልባውን እንበጥሰዋለን ሲባል  አንድም ምላሽ ለአቶ ኢሳያስ ሳይሰጥ ጀንበር መጥለቁ በእውነትም ህወሓት ከምንገምተው በላይ ደክሟል።የስርዓቱ ደጋፊ የሆነው የአዲስ አበባው የሚሚ ስብሃቱ ራድዮ ጣብያ ዛሚ  ይብሱን አቶ ኢሳያስን ከመውቀስ ይልቅ አቶ ኢሳያስ አንድም የግብፅ ወታደር ኤርትራ የለም አሉ የሚል ዜና ብቻ መዘገቡ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው።

አቶ ኢሳያስ 90 ደቂቃ በፈጀው የእሁዱ ቃለ መጠይቅ ላይ የግብፅ እና የኢምሬት ወታደሮች በኤርትራ አሉ የሚለው ዜና "ጆክ" ነው ይህ ዜና ሆን ተብሎ የተፈበረከ ነው ብለዋል። ሆኖም ግን የአቶ ኢሳያስ ምላሽ ብዙም ተአማኒነት የለውም።ምክንያቱም አቶ ኢሳያስ እንዳሉት ቢሆን ኖሮ እራሳቸው የግብፅ እና የኢምረት መንግሥታት ማስተባበል ነበረባቸው እንጂ አቶ ኢሳያስ እስኪያስተባብሉ ባልተጠበቀ ነበር።የአልጀዚራ ዘገባ ውሸት ቢሆን ኖሮ ግብፅ እና ኢምረት በአልጀዚራ ላይ ለመውረድ ሰዓታት አያጠፉም ነበር።ስለሆነም የአቶ ኢሳያስ ምላሽ ማለት ያለባቸውን ይበሉ እንጂ ብዙም ሚዛን የሚሰጠው አይደለም።አቶ ኢሳያስ በአንፃሩ ይልቁንም የቱርክ ጦር በቀይ ባሕር ዳርቻ በሚገኘው ምዕራባዊ ሱዳን መሬት ላይ መስፈራቸውን ወቅሰዋል።

ኢትዮጵያ፣ግብፅ፣ሱዳን እና ኤርትራ ጦርነት ሊለኩሱ ነው?

በኢትዮጵያ፣ግብፅ፣ሱዳን እና ኤርትራ በተለያየ ሁኔታዎች ውስጥ ይገኛሉ።ሁሉም የጋር የሚያደርጋቸው ጉዳይ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ሰንጎ ይዟቸዋል።ይህ በአንዱ ሀገር ያለው ከሌላው የተለየ ሊሆን ይችላል።ግብፅ የአባይ ግድብ ጉዳይ እንደ አጀንዳ የምታነሳው ከእረጅም ጊዜ ስልት አንፃር እንጂ በአጭር ጊዜ ግድቡ ስጋት ይሆናል የሚል አይደለም።የግብፅ ህልውና ውሃው ነው አበቃ።ይህ ብዙ ምርምር አይፈልግም።ደጋግሞ እንደሚነገረው አባይ ከሌለ ግብፅ ዕቃዋን ጠቅልላ ሌላ ሀገር መሄድ አለባት።መጠጥ ውሃው፣እርሻው፣መብራት ኃይል ኢንዱስትሪው ሁሉም አባይን የተቆራኙ ናቸው።ይህ አዲስ ክስተት አይደለም።

ሱዳንን በተመለከተ ከፍተኛ የመዋለ ንዋይ ቁርኝት ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከህወሓት ድርጅቶች ጋር ገብታለች። በአንድ ወቅት የሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ ሱዳን በኢትዮጵያ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ ቀዳሚ ሀገር እንደሆነች መዘገቡ (ስታስቲክሱን በሚገባ ባያሳይም)  የቁርኝቱን መጠን የሚያሳይ ነው።የሱዳን ፕሬዝዳንት የህወሓት ልደት የካቲት 11 ሲከበር በረው መቀሌ የሚገቡት ወደው አይደለም።በሌላ በኩል ለም የሆነውን የእርሻ መሬት የደቡብ ሱዳንን ካጣች ወዲህ ሱዳን እያደገ ለመጣው የህዝብ ብዛት በቂ የእርሻ መሬት የማግኘት ሕልም አላት።ሱዳን በሳህል ቀጠና እንደመገኘቷ እየተስፋፋ የመጣው የበረሃማ የአየር ጠባይ በመጪዎቹ ዓመታት ከፍተኛ ችግር ሊገጥማት እንደሚችል ይታወቃል።ስለሆነም ከህወሓት ጋር እየተሞዳሞደች ለማግኘት የምትጥረው የጎንደር ለም መሬቶችን ወደ ግዛቷ መጠቅለል ነው።ይህ ተስፋ በህወሓት በኩል ከመሰጠት አልፎ የአየር ላይ ፎቶ የማንሳት ሥራ እንደተከናወነ ተሰምቷል።ይህ ማለት ሱዳን አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከህወሓት ጋር እድሉን አቆራኝቷል።ከእዚህ በመነሳት ነው ተሰምቶ የማያውቀው የአንድ ሀገር ከፍተኛ የኒሻን ሽልማት ለሌላ ሀገር የጦር ኢታማዥር ሽልማት ሰጡ የሚል የሰማነው።የሱዳን መንግስት ለሳሞራ የኑስ የተሰጠው የሱዳን መንግስት ከፍተኛ ሜዳልያ የቁርኚቱ ልክ ማጣት የሚያሳይ ነው።

አሁን ጥያቄው ሱዳን በኤርትራ ላይ ጦርነት ታውጃለች ወይ? የሚለው ነው። አቶ ኢሳያስ ባለፈው እሁድ እንደገለጡት በከሰላ በኩል ያለው የኢትዮጵያ ጦር ነው የሚለው አባባል ትንሽ እውነትነት ይሸታል።ምክንያቱም ሱዳን ከኤርትራ ይልቅ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ድረስ የሄደችበት ጉዳይ ከግብፅ ጋር ያላት እንኪያ ሰላምታ ነው።አምባሳደሯን የጠራቸውም ከካይሮ ነው።አሁን ወታደሮቿን ለምን ወደ ከሰላ ታስጠጋለች? ለእዚህ ሁለት ምክንያቶች ሊቀርቡ ይችላሉ።አንድ ህወሓት ሱዳን መተላለፍያ መሬት እንድትሰጠው እና ኤርትራን ከምዕራብ በኩል ለመውጋት ፈቃድ አግኝቶ በምትኩ የጎንደር መሬትን ጨምሮ ለሱዳን ለመስጠት ተዋውሎ አለበለዝያም አልጀዝራ እንደዘገበው ግብፅ በኤርትራ በኩል በመስፈሯ ስጋት ተፈጥሮበት።

ጦርነቱ ቢከፈት ማን ይጠቀማል? ማን ይከስራል?

ሱዳን እና ህወሓት በአንድ በኩል ኤርትራ እና ግብፅ በሌላ አንፃር ሆነው ጦርነት ቢከፈት ወይንም የውክልና ጦርነት ቢያደርጉ የመጀመርያ ተጠቂዎች ሱዳን እና ህወሓት ይሆናሉ። ምክንያቱም የሱዳን ወታደራዊ አቅም ለእረጅም ጊዜ ሲገነባ የኖረ ቢሆንም በመረጃ በኩል ግብፅ እና ኤርትራ ብዙውን ጉዳይ ያውቁታል።አቶ ኢሳያስ ደግሞ እንደ ሱዳን የሚንቁት ጎረቤት የላቸውም።ገና ወደ ስልጣን እርከን ሳይደርሱ በደርግ ዘመን የቢቢሲ "ፎከስ ኦን አፍሪካ" ጋዜጠኛ ለአቶ ኢሳያስ አንድ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። ጥያቄው " ለምንድነው ለሶስት አስርተ አመታት ስትዋጉ አስመራ መግባት ያልቻላችሁት?" የሚል ነበር። አቶ ኢሳያስ ሲመልሱ " የምንዋጋው ከሱዳን ወታደር ጋር አይደለም።ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር ነው" ነበር ያሉት። አቶ ኢስያስ ይህንን ያሉት የሱዳንን አቅም ለማሳነስ ብቻ ሳይሆን የቢቢሲው ጋዜጠኛ የሱዳን ተወላጅ መሆኑን ስላወቁ ነበር። ሱዳን በእዚህ ሁሉ ሂደት የሚያሰጋት የተለመደው የመፈንቅለ መንግስት ስለሆነ ኤርትራ እና ግብፅ አንድ ቀን ካርቱም ውስጥ አንዱን ኮለኔል የመፈንቅለ መንግስት ማድረጉን ሊያሳውጁባት ይችላሉ።በሱዳን በኢኮኖሚ ቀውስ ሳብያ የዳቦ ዋጋ በመጨመሩ ከፍተኛ የተማሪዎች አመፅ ተነስቶ ከካርቱም እስከ ዳርፉር ባሉ ግዛቶች የሰው ሕይወት መጥፋቱ ከተነገረ ገና አንድ ሳምንቱ ነው።ስለሆነም ግጭቱ ከተፈጠረ ሱዳን እና ህወሓት ከውስጥ ከተነሳባቸው የህዝብ ማዕበል አንፃር ባጭር ጊዜ እጅ የሚሰጡ ሲሆኑ ኤርትራ እና ግብፅ የውስጥ ቀውሳቸውን ማስታገሻ ፓናዶል ሊያደርጉት ይችላሉ።

ባጠቃላይ በግብፅ፣ሱዳን፣ኤርትራ እና ኢትዮጵያ መካከል ግጭቱ መነሳቱን ሁሉም መንግሥታት  ከሀገራቸው ካለው ቀውስ አንፃር የሚፈልጉት ይመስላል።ግብፅ አልሲስ ለህዝባቸው የውሃ ጉዳይ በጦር ኃይል ያስከበሩ መሪ ተብለው መሞገጽ ይፈልጋሉ።በእዚህም በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት ከፍ ያደርጉበታል።የግብፅ ሕዝብ ለስሙ እና ለዝኛው ትልቅ ቦታ ይሰጣል።በሱዳን አንፃር ሕልውናው ከህወሓት ጋር ተያይዞበት ተቸግሯል።ግብፅ ለዘብተኛ መንግስት ካርቱም ላይ እንዲኖር እየሰራች እንደሆነ ገብቶታል ስለሆነም የውጭ ፖሊሲው ከህወሓት ጋር ካልተናበበ ብዙ እርቀት መሄድ የማይችል አድርጎ ያሰበ ይመስላል።ይህንን መንገድ ግን የሱዳን ሕዝብ ይደግፈዋል ተብሎ አይታሰብም።በአቶ ኢሳያስ ኤርትራ በኩል ህወሓት እያለ እንቅልፍ የሚባል ነገር የለም።ህወሓት እንደከዳቻቸው አቶ ኢሳያስ ደግግመው ተናግረዋል።ህወሓት ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ፀር ነው።ለእዚህም ኃላፊነት የሚወስዱት ሲደግፉት የኖሩ ሁሉ ናቸው ነበር ያሉት አቶ ኢሳያስ ባለፈው እሁድ መግለጫቸው።በእዚሁ መግለጫቸው ላይ (በሀገር ውስጥ የሚመለከት ክፍል ሁለት ቃለ መጠይቅ በመጪው ቅዳሜ እንደሚኖር ተነግሯል) ህወሓት አብቅቶለታል የሚለው ንግግራቸው በህወሓት መንደር ትልቅ ሽብር ፈጥሯል።ህወሓት አሁን የጦር ኃይል ከመላ ሀገሪቱ አንቀሳቅሶ ወደ ጦርነት ለመሄድ የሚችልበት ቁመና ላይ አይደለም።እራሱ የፈጠራቸው ክልሎች በተለይ የኦሮምያ እና የዐማራ ክልሎች ከህወሓት ውጭ ሲንቀሳቀሱ እየታዩ ነው። ሌላው ቀርቶ ህወሓት የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ ማስቆም የሚችለው አዲስ አበባ ያውም መስቀል አደባባይ ብቻ መሆኑ ተመስክሯል። ቴዲ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ባህር ዳር ላይ የተከለከለ ኮንሰርቱን እንዲያቀርብ የዐማራ ክልል ፈቅዷል።ዘመን ተገልብጧል።ከእዚህ በላይም ይገለበጣል።ህወሐቶች ከእዚህ በላይ ስልጣናቸው በአይናቸው እያዩ ያጣሉ።የኢትዮጵያ በሔራዊ ጥቅም ከአካባቢ ሀገሮች ስልታዊ እና መልከዓ ምድራዊ ጥቅም አንፃር እንዳይጎዳ ግን የኢትዮጵያ ጦር ኃይል ውስጥ የነቃው ክፍል አንድ አይነት እርምጃ መውሰድ ይገባዋል።ሕዝብ ኃይል ነው።ማንኛውም የጦር ኃይል በትክክል የህወሓትን እጅ መጠርነፍ እስከቻለ ድረስ ሕዝብ አብሮት ይቆማል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምም በትክክል ይከበራል።ጦርነቱ ካልቀረ ህወሓትም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችም ማፈር አለባቸው።ከህወሓት የበለጠ ጠላት ከኢትዮጵያ ፊት አሁን የለም።ህወሓት ሲገለጥ ግን ሌሎች እንደቆሙ በትክክል ማየት ይቻላል።ለእዚህ ነው የጦር ኃይሉ ውስጥ የነቁ ክፍሎች ፈጥነው እርምጃ መውሰዳቸው አንገብጋቢ የሚያደርገው።በህወሓት ጥገናዊ ለውጥ ኢትዮጵያ ትሰምጣለች እንጂ ትለማለች ብለን እንዳንጠብቅ።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...