ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, January 5, 2018

የመካከለኛው ምስራቅ አጠቃላይ ጦርነት ሳይቀሰቀስ በኢትዮጵያ ለውጥ በቶሎ መምጣት እንዳለበት የለውጥ እድሉ እጁ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቀው ይገባል።

Photo: - Financial Times © FT montage; AP/Gettyፎቶ : - ፋይናንሻል ታይምስ 

በእዚህ ማስታወሻ ስር የተካተቱ ርዕሶች: -
  • የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ መግጠም
  • አፄ ዮሐንስ በ20ኛው ክ/ዘመን፣ህወሓት በ21ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያን ለባዕዳን አጋልጠው ሰጥተዋል 
  • አንድ መቶ ሚልዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ የመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ መንግሥታት ስጋት 
  • "ጣልያኖች ኢትዮጵያ የሚመጡት እኔ የሮም ገዢ ሆኘ ስሄድ ነው። ፈረሴ የቀይ ባህር ውሃ ሳይጠጣ አይመለስም፣የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር ነው" ራስ አሉላ።

የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ መግጠም


የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት የአፍሪካ ቀንድን ጨምሮ አዳዲስ ''አካባቢያዊ ኃያላንን'' እያሳተፈ ግለቱ እየጨመረ ነው።በኢራን የሚደገፈው የየመኑ የሆውቲ (Houthi)  ሽምቅ ተዋጊዎች የሳውዲ አረብያ ስጋቶች መሆናቸውን ቀጥለዋል።ሳውዲ አረብያ በአካባቢው የነበራት የጦር ኃይል እና የገንዘብ ጡንቻ ከእስራኤል በቀር የሚያሰጋት እንደሌለ ታስብ ነበር።የሳውዲ የጦር ኃይል ከጥራት ይልቅ ውድ እና ውስብስብ ቴክኖሎጂ የታጠቁ የምዕራቡ ስሪት ጀቶች እና ሚሳአሎች አሏት። ሆኖም ግን አጠቃቀም ላይ በቂ የሰው ኃይል ያላፈራች ነች በማለት ባላንጣዎቿ ኢራን እና  ኳታር ያሟታል። የሳውዲ አረብያን የበላይነት በሚገባ እየተገዳደሯት ያሉት ኢራን እና ኳታር ናቸው።


ሳውዲአረብያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት በየመን ላይ በፈፀሙት የአየር ጥቃት በሺህ የሚቆጠሩ የየመን ሕፃናት፣ወጣቶች እና አረጋውያን እረግፈዋል።ከተሞች ወደ ትብያነት ተቀይረዋል።ሆኖም ግን ሳውዲአረብያን የተናገረ የምዕራብ ሀገር የለም።በተባበሩት መንግሥታት በኩልም ይህ ነው የሚባል የረባ  ወቀሳ አልተሰማም።የገንዘብ ኃይል የመንግስታቱን ስሜትም፣ ሰብአዊነትን ሁሉ አጣሞ እና አንሸዋሮ አስቀምጦታል። 


ሳውዲ አረብያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ወታደሮቻቸውን ከኤርትራ እስከ ሱማልያ ድረስ አስፍረዋል። በአፍሪካ ቀንድ የሰፈረው ጦር ይህ ብቻ አይደለም።መሽቶ በነጋ ቁጥር ኢትዮጵያን ዙርያ የሚሰፍሩት የመካከለኛው ምስራቅ ጦር ኃይል እየጨመረ መጥቷል።ቱርክ ከአውሮፓ ድረስ ዘላ ሱማሌ ሞቃዲሾ አጠገብ ያሰፈረችው የጦር ኃይል ሀገሪቱ ከቱርክ ውጭ ያለው ጦሯ ከፍተኛውን ቁጥር ይዟል።ግብፅ በሌላ በኩል በኤርትራ ዘመናዊ መሳርያ የታጠቀ ጦሯን ማስገባቷ ተሰምቷል።የመካከለኛው ምስራቅ ጥልፍልፍ እንዲህ ቀጥሏል።ይህ ሁሉ ቦታ የመያዝ ሩጫ አንድ አይነት አካባቢያዊ ጦርነት እንደማይቀር አመላካች ነው። በተለይ በሳውዲ በኩል በተሰለፈው ኃይል እና በኢራን ጎን በተሰለፈው ኃይል መሃከል የአካባቢ ኃያልነት ሩጫ ወደ ማይቀረው ግጭት እንደሚያመሩ ግልጥ ነው። 


ሃገራቱ ግጭታቸው ባሉበት መልከአ ምድር ውስጥ ብቻ እንደማይሆን አንዱ አመላካች ነጥብ ደግሞ በተናጥል እየፈፀሙ ያሉት የወታደራዊ ስምምነት ጉዳይ ነው። ኤርትራ ከግብፅ፣ሳውዲ እና የተባበሩት መንግሥታት ጋር ስምምነት ያላት ሲሆን በህወሓት የምትመራው ኢትዮጵያ በቅርቡ ከታር ጋር በከፍተኛ ልዑክ ደረጃ ወታደራዊ ንግግር እንዳደረገች ተሰምቷል።በአጭሩ የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ከጀርባ ሃያላኑ እያቀጣጠሉት ወደ ጦርነት አፋፍ ላይ መድረሱ አይቀርም።ምናልባትም እስራኤል በእዚህ ጦርነት የመካከለኛ ምስራቅ ባላንጣዎቿን የምታደክምምበት መልካም ቀን ይመጣ ይሆናል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።


አፄ ዮሐንስ በ20ኛው ክ/ዘመን፣ህወሓት በ21ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያን ለባዕዳን አጋልጠው ሰጥተዋል


ኢትዮጵያ ባለፉት ሃምሳ አመታት ውስጥ ያልገጠማት ደካማ የውስጥ አስተዳደር እና ሃገራዊ አንድነት አደጋ ላይ ነች።ይህ ደግሞ ህወሓት ለስልጣኑ ብቻ ያለመ እጅግ አደገኛ እና የኢትዮጵያን ጥቅሞች አሳልፎ ከመስጠት ባለፈ የኢትዮጵያን የአንድ እናት ልጆች ሆን ብሎ በመከፋፈል ሃገራዊ አንድነታችንን አደጋ ላይ ጥሎታል። እዚህ ላይ በተቃዋሚ ጎራ ያሉ ከሀገራዊ አንድነት ያልቅ የጎሳ ፖለቲካን እንደ የመጨረሻ አልፋና ኦሜጋ ግብ በማስቀመጥ ሕዝብ ግራ በተጋባ ስሜት ውስጥ እንዲገባ ያደረጉ የስልጣን ጥማት ብቻ ያናወዛቸው ለሀገራዊ አንድነት መላላት አስተዋፅኦ አላደረጉም ማለት አይቻልም።


ኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ንዝህላልነት፣የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ለባዕዳን የመስጠት ሸፍጥ፣ ለባዕዳን   በኢንቨስትመንት ስም የተጋለጠው የሀገሪቱ ደህንነት እና የህዝቡ ሃገሩን የመከላከል አቅሙን በምጣኔ ሀብት ድቀት የማዛሉ ደረጃ ሁሉ ኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ በሚባል ደረጃ ያለችበት ወቅት መሆኑን መካድ አይቻልም። ህወሓት አሁን እየሰራ ያለው አፄ ዮሐንስ ደጃች በዝብዝ በሚል ስያሜ በሚታወቁበት ደረጃ በቀጥታ ሀገሪቱን ለባእዳን ያጋለጡበት ወቅትን ይመስላል። የቀደሙት ደጃች በዝብዝ በኃላ አፄ ዮሐንስ ኢትዮጵያን በ20ኛው ክፍለ ዘመን በሁለት መንገድ ለባእዳን እንዳጋለጡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ከሶስት አመታት በፊት በ2007 ዓም በታተመው   'አዳፍኔ' በተሰኘው   መፅሐፋቸው ላይ ገልጠውታል።ይሄውም የመጀመርያው  የአፄ ቴዎድሮስን ጦር ሊያጠቃ የመጣውን የእንግሊዝ ሰራዊት ሙሉ የስንቅ እና የመንገድ መምራት ሥራ ሰርተው አፄ ቴዎድሮስ እንዲሞቱ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው እና ራስ አሉላ አባነጋ የኢትዮጵያን ጦር በያኔዋ ባህረ ነጋሽ በአሁኗ ኤርትራ ላይ የነበራቸውን የበላይነት እና የኢትዮጵያን ድንበር የማስከበር አኩሪ ተግባር ራስ አሉላን ከስልጣናቸው ዝቅ በማድረግ እና ወደ ጣልያን ጦር እንዳይገሰግሱ ምክንያት በመስጠት መሆኑን ያብራራሉ።


 አፄ ዮሐንስ የእንግሊዝን ሰራዊት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ አድርገው አፄ ቴዎድሮስ እራሳቸውን ከሰዉ በኃላ ለእንግሊዝ ንግስት የፃፉት ደብዳቤ የተወሰደ እንዲህ ይነበባል : - "ጥንቱንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለመንግስት የበቃሁ እርስዎ በሰጡኝ መድፍ፣ነፍት፣ባሩድ ነው" (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አዳፍኔ፣ገፅ 11)

"ጣልያኖች ኢትዮጵያ የሚመጡት እኔ የሮም ገዢ ሆኘ ስሄድ ነው። ፈረሴ የቀይ ባህር ውሃ ሳይጠጣ አይመለስም፣የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር ነው" በሚሉ ታሪካዊ ንግግር የሚታወቁትን ራስ አሉላን የውግያ ሞራል የገደሉ አፄ ዮሐንስ መሆናቸውን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ከጠቀሱት ጥቅስ ውስጥ እንዲህ የሚለው ይገኝበታል።
   ''ከዶጋሊው ጦርነት ወዲህ የጦር ጠቅላይ አዛዥነቱን ንጉሰ ነገስቱ ከራስ አሉላ አንስተው ለታላቅ ወንድማቸው ልጅ ለራስ ኃይለ ማርያም ሰጥተው አሉላን በሃማሴን ግዛት ስለወሰኗቸው (ራስ አሉላ) ቅሬታ ነበራቸው ይባላል።" (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም አዳፍኔ፣ገፅ 13)

ከላይ እንደተጠቀሰው የአፄ ዮሐንስን ለስልጣን ሲሉ የባዕድ ወታደር ማስገባት በመቀጠልም የኢትዮጵያ አሉ የተባሉ የታሪክ ድርሳናት እና የብራና መፃህፍት ከመቅደላ (የመፃህፍቱን ብዛት 11 ግመል ሙሉ የተጫኑ የሚሉ አሉ) ተጭነው ወደ እንግሊዝ ሲሄዱ የኃላው አፄ ዮሐንስ የቀድሞው ደጃች በዝብዝ አጋፋሪ መሆናቸው የታሪካችን ጠባሳ ነው። ይህ ብቻ አይደለም የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ከቤተሰቡ ጋር ስጋዝ  አሁንም ደጃች በዝብዝ ለብረት ልዋጭ እና ለንጉሰ ነገስት ስልጣን የሀገር ክብር ሲያልፍ ቆመው ተመልክተዋል። በእርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግና አድናቂ ነው እና የአፄ ዮሐንስ ታሪክ ሲነሳ ሁለ የሚወሳው ለኢትዮጵያ ሲሉ መተማ ላይ መሰዋታቸው ነው።የዛሬው የህወሓት መንግስት ግን የአፄ ዮሐንስን አንገት ቆርጠው ካርቱም ገበያ ለገበያ እያዞሩ የተሳለቁትን የያኔዎች ደርቡሾች የዛሬ ሱዳኖች ጋር እየተሞዳሞደ የኢትዮጵያን ድንበር ቆርሶ እየሰጠ ነው። 


ኢትዮጵያ በ20ኛው ክ/ዘመን የገጠማት የባዕዳን ከበባ አሁንም ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ልክ አፄ ዮሐንስ እንዳደረጉት ለባእዳን ሀገሪቱን አስረክቦ ስልጣኑን ለማቆየት ብቻ የሚያልም ነው።ህወሓት ኢትዮጵያዊ ጥቅም የሚል አጀንዳ እንደሌለው ከስሙ ጀምሮ ባለመቀየር ግልጥ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።ለጎሳው ከጎሳውም ለአድዋ ቅድምያ የሚሰጠው ህውሓት በስልጣን ላይ መቆየቱ ብሔራዊ አደጋ ነው።በ20ኛው ክ/ዘመን የነበረው የአውሮፓውያን ኃይል በመካከለኛው ምስራቅ ኃይል ከመተካቱ ውጭ ጊዜው ለኢትዮጵያ ያለው አደገኛ ገፅታ ቀላል አይደለም።ይህ ማለት ኢትዮጵያ ህወሓት በስልጣን ላይ እያለ አደጋዋን ትከላከላለች ብሎ የሚያስብ ካለ በአሁኑ ነባራዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ውስጥ የሌለ መሆን አለበት። ህወሓት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ነው።አቶ ለማ መገርሳ የኦሮምያ ፕሬዝዳንት ደጋግመው የእኛ ስልጣን ከሀገር ደህንነት አይበልጥም የሚሉት የሚያውቁት በርካታ የህወሓት ምስጢሮች ስላሉ እንደሆነ መጠርጠሩ አይከፋም።አቶ ለማ በደህንነት መስርያቤቱ ውስጥ እንደመስራታቸው መጠን በርካታ መረጃዎች በተለይ ህወሓት የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ በሚጥል መንገድ የሄደበትን ሂደት መረዳታቸው ውስጣቸውን እየፈነቀለ እንዲናገሩ እንዳደረጋቸው መረዳቱ አይከፋም።ብዙ ስታውቅ ብዙ የውስጣዊ ስሜት መፈንቀል ያጋጥማል።ለእዚህ ነው አቶ ለማ  ኢትዮጵያ ሃገራዊ አንድነቷ መጠበቁ አስፈላጊ መሆኑን ደጋግመው ሲናገሩ የምንሰማቸው።

Picture source: Financial Times

አንድ መቶ ሚልዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ የመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ መንግሥታት ስጋት 

በ20ኛው ክ/ዘመን  ሁለተኛ አጋማሽ ላይ አውሮፓውያን በአራቱም ማዕዘናት ከበዋት እና በኃላ ጣልያንን ሲልኩባት  ለድል የበቃችው በዳግማዊ ምንሊክ በተፈጠረው ውስጣዊ አንድነት ጭምር ነው።ዛሬም የመካከለኛው ምስራቅ አጠቃላይ ጦርነት ከመነሳቱ እና ኢትዮጵያ የጥቃቱ ኢላማ ከመሆኗ በፊት የውስጥ የቤት ሥራ መስራት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ኃይሎች የተሰጠ የቤት ሥራ ነው።ህወሓት በስልጣን ላይ እያለ ሀገር የመከላከል ሥራ ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም።ስለሆነም ኢትዮጵያዊ የሆነ መንግስት ለማቆም ህወሓት ለሃያ ስድስት አመታት ከኖረበት ስልጣን ገለል ማድረግ ምንም አማራጭ የለውም።ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጣዊ አንድነቱን እያጠናከረ እና በጎሳ የሚከፋፍሉትን ማናቸውም  ውጫዊ ኃይሎች  ወደ ኢትዮጵያ የጋራ መድረክ እንዲመጡ ማስገደድ ይጠበቅበታል።


ለማጠቃለል  የመካከለኛው ምስራቅ አጠቃላይ ጦርነት ሳይቀሰቀስ በኢትዮጵያ ለውጥ በቶሎ መምጣት እንዳለበት የለውጥ እድሉ እጁ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቀው ይገባል።ጦርነቱ አካባቢያዊ አድማሱን ማስፋት እና በአጋጣሚው የውሃ ማማዎችን መቆጣጠርን ያለመ እንደሆነ ግልጥ እየሆነ መጥቷል።ኢትዮጵያ የጦር ሰራዊቷ ህዝቧ ነው። አንድ መቶ ሚልዮን የሚቆጠረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ ሀገሮች እንደ ስጋት ይመለከቱታል።ስለሆነም መከፋፈሉ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። የመከፋፈሉን ሥራ የሰራው እና ለሰራበት እየተከፈለው የሚገኘው ህወሓት ደግሞ የበለጠ ለመሰነጣጠቅ በፖሊሲ ደረጃ ሲንቀሳቀስ 27 ዓመታት እያስቆጠረ ነው። ስለሆነም ህወሓት ከስልጣን መወገዱ የሀገሪቱ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚጠነክርበት ሃገራዊ አጀንዳዎች ለሕዝቡ የሚደርሱበት ጊዜ መሆኑን የታመነ ነው።

=============////============

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...