Monday, December 14, 2015

ኢትዮጵያውያን በሙሉ ኢትዮጵያውያንን አትግደሉ ብለው መቃወም አለባቸው! በኢትዮጵያውያን የተነሳው አመፅ መነሻ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው? መፍትሄውንስ ከምን አንፃር መመልከት ይገባል? (የጉዳያችን ማስታወሻ)


በአገራችን ኢትዮጵያ ሰሞኑ በኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የተነሳው አመፅ ችግሩ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።የችግሩን ምንጭ አንዳንዶች በእራሳቸው የግንዛቤ ልኬት እንደፈለጋቸው ሊመሩት ይፈልጋሉ።የግለሰብ  እና የአንድ ቡድን የግንዛቤ ልኬት እና የሕዝብ ልኬት የተለያዩ ናቸው።ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘው አመፅ በአሁኑ ሰዓት ችግርን በውይይት እና በተጠያቂነት የመፍታት ባህል የሌለው ስርዓት ሰራዊቱን በሙሉ በኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን መንደር አሰማርቶ በመግደል ችግሩን ለመፍታት ይሞክራል።በዛሬው እለት ብቻ 25 ኢትዮጵያውያን በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል።ይህ ቁጥር ከሰሞኑ በእጅጉ ሊጨምር ይችላል።ከእዚህ የከፋ ችግር ሳይፈፀም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ኢትዮጵያውያንን አትግደሉ ብለው መቃወም አለባቸው።ይህ በእንዲህ እያለ ግን በኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የተነሳው አመፅ መነሻ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?  መፍትሄውንስ ከምን አንፃር መመልከት ይገባል

አሁን የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የተነሳው አመፅ የችግሩ ዋና መነሻ:-

1/ የስርዓቱ ዘራፊ ባለስልጣናት ስግብግብነት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ የመሬት ዝርፍያው ቅጥ በማጣቱ እና በእያንዳንዱ ገበሬ ህልውና ላይ በመምጣቱ፣
2/ ስርዓቱ 24 ዓመታት ሲያራግብ የነበረው የጎሳ ፖለቲካ መልሶ እራሱንም የሚያገለው እና የሚገፋውን የባሰ የጎሳ የፖለቲካ ጥያቄ ከሀብት (resource) ጥያቄ ጋር አብሮ ጠንክሮ በመምጣቱ ስርዓቱ እና ስርዓቱ ደግሞ በእርጋት የመፍታት ባህሪ ስለሌለው  በኃይል ለመፍታት መሞከሩ፣
3/ የነፃ ሚድያ መረጃ ስለታፈነ ቀድመው የችግሩን መኖር ደረጃ በደረጃ የሚገልጡ እና ህዝቡ ውስጥ የሚንተከተከውን ስሜት ለሁሉም አካል የሚገልጡ ጋዜጠኞች እንዳይናገሩ እና እንዳይፅፉ መታሰራቸው እና መሰደዳቸው እና
4/  የክልሉ አስተዳዳሪ የነበረው ኦህዴድ በእራሱ የዝርፊያው ተዋናይ ስለነበር ከስርዓቱ መሪዎች ጋር የጥቅም ግጭት መግባቱ የሚሉት ናቸው።

የችግሩ መፍትሄ:-

1/ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች መኖራቸውን ማመን፣

2/ ችግሩን በጊዚያዊነት አለባብሶ ለማለፍ አለመሞከር፣

3/ ይህ የተነሳው ችግር ለጊዜው ይዞት የተነሳው የአዲስ አበባ ፕላን ጉዳይ ይሁን እንጂ በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎች በእየዘመኑ ከአገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች ጋር የሚያያዙ ጉዳዮች ከመኖራቸው በላይ ይብሱን ባለፉት 24 ዓመታት  ውስጥ በተለየ መልኩ የክልሉ ተወላጆች በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከአገሪቱ የስልጣን እርከኖች መራቃቸውን መገንዘብ።
ለምሳሌ ላለፉት 100 ዓመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ ብንመለከት የጦር ኃይሉን ከአፄ ምንሊክ ዘመን ጀምሮ በፍፁም ኢትዮጵያዊነት  በበላይነት ይመራ የነበረው የክልሉ ሕዝብ ምን ያክል ባለፉት 24 ዓመታት እንደተገለለ እና በስርዓቱ ከፍተኛ ንቀት ይፈፀም እንደነበር መገንዘብ።ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅስብራት’ ነው።በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ዘመንም ሆነ በደርግ ዘመን በጦር ኃይሉ እና ፖሊስ ሰራዊት ከከፍተኛ መኮንኖች እስከ ታች ባሉ ባለማእረጎች የክልሉ ተወላጆች አገራቸውን አገልግለዋል። ይህ ስርዓት በመንገድ ላይ ለማኝ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የቀድሞ ሰራዊት አባላት ውስጥ በርካቶች የኦሮምኛ ተናጋሪ እንደነበሩ ብዙዎቻችን እንረሳለን።

4/ በየትኛውም አቅጣጫ በስርዓቱ የውስጥ ሴራ የሚነሱ የክልሉን ሕዝብ ከሌላው ጋር ለማጋጨት የሚሞከሩ ማናቸውንም ሙከራዎች ማክሸፍ። ለምሳሌ የሱማሌ ክልልን በኦሮሞ ላይ እንዲዘምት፣የአማርኛ ተናጋሪዎችን ከኦሮምኛ ተናጋሪዎች ጋር ለማጋጨት የሚደረገው ሙከራ ነቅቶ መጠበቅ እና እንዲሁም የትግርኛ ተናጋሪውን በሙሉ በጠላትነት የሚመለከቱ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ ዘመቻዎች አሁንም የስርዓቱ አቀንቃኞች ሥራ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት፣እንዲሁም  በአንዳንድ ቦታዎች ላይ በግንፍልተኞች አንዱን በተለየ መልክ ለማጥቃት የሚደረጉ ሙከራዎች ወይንም ድርጊቶችን  የአጠቃላይ ሕዝብ ሥራ አድርጎ ከማቅረብ መጠንቀቅ እና


5/ ይህንን ከፍተኛ የሕዝብ መነሳሳትን ከመላው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጥያቄዎች ጋር ማስተሳሰር እና ከፅንፈኛ የእስልምና አደጋዎች መታደግ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
ታኅሳስ 4/2008 ዓም (December 14/2015)

Friday, December 11, 2015

የኦሮሞን ሕዝብ ከፅንፈኛ የእስልምና አቀንቃኞች እንታደግ! በኢትዮጵያዊነታቸው የፀኑ የክልሉ ተወላጅ ምሁራን ሕዝቡን ለመምራት መነሳት አለባቸው።


  •  የኦሮሞን ብሔር ከኢትዮጵያዊነቱ የማይለያይ ከፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ የፀዳ መሪ ያስፈልገዋል።

እናትና አባቱ ጥረው ግረው አስተምረውት ደሙ በመንገድ ላይ እንደዋዛ የሚፈሰው ኢትዮጵያዊ የኦሮሞ ብሔር እንዴት ያሳዝናል? መብቱን በሰላማዊ መንገድ የጠየቀን ሕዝብ እንዴት የጥይት አረር ይሰጠዋል? ይህንን የፈፀሙ በሙሉ ይዋል ይደር እንጂ ሕዝብ ለፍርድ ማቅረቡ አይቀርም።

በኢትዮጵያ አርሲ፣ወለጋ ምዕራብ ሸዋ እና ሐረር ለሞቱት ኢትዮጵያውያን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከዋሽንግተን እስከ ጀርመን ተቃውመው እየወጡ ነው።አሁን በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ችግሩን የመፍታት ስነ-ልቦናዊ፣ርዕዮተ አለማዊና ተቋማዊ ብቃት አንሶታል።በእዚህ ሁሉ መካከል ተቃውሞው የሚመራው በፌስ ቡክ እና ትዊተር ፎቶ ግራፍ እና ቁርጥራጭ ፊልሞችን በሚለጥፉ መሆኑ በእራሱ አደገኛ ነው።እንደ ጅማ ዞን ወጣ ባሉ፣አርሲ እና ባሌ አካባቢዎች በፅንፈኛ የእስልምና አመለካከት  የኦሮምኛ ተናጋሪውን ኢትዮጵያዊ የቁጣ ስሜት ተጠቅመው አካባቢውን ወዳልተፈለገ የፅንፍ ጫፍ ለመውሰድ የሚፈልጉ እንዳሉ ማንም የሚያውቀው ነው።ይህንን ጉዳይ እንዳላዩ ማለፍ ወይንም አሁን ትግሉን ለማደብዘዝ የሚነሳ ሃሳብ ነው ማለት በእራሱ አደገኛ ነው።ይህንን ሁኔታ እንዲያውም በውጭ የሚገኙ ነፃ ሚድያዎች ለሕዝብ መረጃውን በትክክል ማድረስ አለባቸው።እውነታው ሶስት ነው።
አንድ፣ኢህአዴግ ወያኔ ሕዝቡን በዘር ፖለትካ ከፍሎታል።
ሁለት፣ፅንፈኛ የእስልምና አቀንቃኞች በኦሮሞ ሕዝብ ተንጠላጥለው ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር ለማጥፋት ይፈልጋሉ።
ሶስት፣አብዛኛው የኦሮሞ ተወላጅ ይህንን ፈፅሞ አይቀበልም።እነኝህን እውነታዎች ፈፅሞ ለስልት ሲባል መካድ አይቻልም።

ከአምስት እና ስድስት አመታት በፊት በእነኝህ አካባቢዎች በእምነታችን ለማይመስል ሰው ግብር መክፈል የለብንም የሚል እና በእምነታቸው መለየት ብቻ ለእረጅም ጊዜ እና ለትውልዶች በቡና ይዞታ ይኖሩ የነበሩ ከእድር እየተለዩ ሲባረሩ የነበሩ መሆኑን ለስራ ጅማን ባየሁበት ጊዜ ከአካባቢው የመጡ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በሃዘን ሲናገሩ አስታውሳለሁ።ግብር መክፈልን ከእምነት ጋር ማያያዝ እንደ ኢትዮጵያ ባለች አገር ላይ ማንሳት የነማን ሃሳብ እንደሆነ ማሰብ ይችላል።

የኦሮሞን ሕዝብ ከፅንፈኛ የእስልምና አቀንቃኞች እንታደግ! የክልሉ ተወላጆች የማስተማር እና የመምራት ኃላፊነቱን የመውሰድ  ግዴታ አለባችሁ።

የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕብረተስባችን በደረሰበት በደል ምክንያት እያሳየ ያለው የእንቅስቃሴ አቅጣጫ በፅንፈኞች እንዳይመራ መጠበቅ ያስፈልጋል። ፅንፈኞች ሁል ጊዜ ግባቸውን ለመምታት የሚያደርጉት አንድ  ነገር ነው።ይሄውም ሕዝቡን ከኢትዮጵያዊነት ስሜት መለየት ነው።ይህንን ተግባር ኢህአዴግ/ወያኔ በብዙ መንገድ ሲፈፅመው ላለፉት 24 አመታት ኖሯል።ይሄውም  የኢትዮጵያዊ ስሜቱን ቋንቋን መሰረት ባደረገ ፌድራል ስርዓት ይብሱን ቤንዚን ስያርከፈክፍበት እንደነበረ ይታወቃል።ትናንት ህዳር 30/2008 ዓም ለኢሳት ራድዮ ከወለጋ ሆሮ ጉድሩ ቃላቸውን የሰጡ የአካባቢው አዛንትም ይህንኑ እንዲህ በማለት አረጋግጠዋል:
 ''ስርዓቱ አንተ አማራ፣አንተ ኦሮሞ አንተ ትግሬ እያለ እየከፋፈለ እርሱ እንደዳኛ ሆኖ መቀመጥ እና መምራት ነው የሚፈልገው'' ነበር ያሉት።

የኦሮሞን ሕዝብ ለመምራት የምዳዱት ፅንፈኞቹ ግን በአንድ ደረጃ ኢህአዴግ/ህወሃትን ይበልጡታል።እነርሱ ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ከሕዝቡ ስነ-ልቦና ለማውጣት የሚከተሉት መመርያ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥተኛ ስልታዊ እና ታሪካዊ ጠላትነት ካላቸው ኃይሎች ጋር በገንዘብ፣በማቴርያል እና በሰው ኃይል በመታገዝም  ጭምር ስለሚንቀሳቀሱ ነው።ይህ ''የኢትይጵያ ታሪካዊ ጠላቶች'' የሚለው አባባል የደርግ አባባል የሚመስላቸው ከጅኦ-ፖለቲካ ሳይንስ እራሳቸውን ያገለሉ የዋሆች ይኖሩ ይሆናል።ነገር ግን እውነታ ነው።ምናልባት ኢህአዴግ/ህወሃት ከእነኝህ ኃይሎች ጋር የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ እየሰጠ ስለተመሳሰለ ቃሉ በኢትዮጵያ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ስለማይሰማ የሉም ካላልን በቀር።ስለዚህ ይህ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲይዝ እና ከፅንፈኛ የእስልምና ኃይሎች እጅ እንዲወጣ  የክልሉ ተወላጆች ባላችሁ መንገድ ሁሉ ወጥታችሁ የማስተማር እና የመምራት ኃላፊነቱን የመውሰድ  ግዴታ አለባችሁ።


የኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ከማንም በላይ ለኢትዮጵያ ቀድሞ መስዋዕትነት የከፈለ ሕዝብ ነው።አገራችን በአድዋ ጣልያንን ድል ስታደርግ ከወንድሞቹ ጋር የተዋጋ፣ኢትዮጵያ በሱማሌ ስትወረር በሚልሻነት አገር ያዳነ፣ በቀድሞ ሰራዊትም ሆነ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን በበርካታ የጦር አለቆቹ በከፍተኛ የአገር መሪነት የፕረዝዳንትነትን ቦታ ሁሉ ጨምሮ (/ መንግስቱን እና አፄ ምንሊክን መጥቀስ ይቻላል) ኢትዮጵያን ስመ ጥር ያደረገ ኢትዮጵያዊ ነው። ይህንን ሕዝብ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እንዲመራው ያዘጋጁለት ፅንፈኛ የእስልምና እንቅስቃሴ እንዲሆን ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል።አሁንም ሕዝቡን የመምራት ሚና የሚወስድ ከፅንፈኛ እስልምና የፀዳ እና አብሮ በመኖር የሚያምን መሪ በፍጥነት መታየት አለበት።ይህንን አመራር ደግሞ የመደገፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው።አንዳንዶች በውጭ አገራት ጥገኝነት የመጡ ኢትዮጵያውያን ወጣት የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አልይዝም ሲሉ ይገረማሉ።ነገር ግን ያላስተዋሉት ነገር ይህ ኢትዮጵያዊነትን የማስጠላት ሥራ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በእጅ አዙር የተደገፈ እና ለእረጅም ጊዜ ሲሰራበት የነበረ መሆኑን ነው።ፍቅር ያሸንፋል! እና ሚልዮኖች የኦሮምኛ ተናጋሪ ወንድሞቻችንን ልብ ከኢትዮጵያዊነት የሚያሸፍት ምንም አይነት ኃይል የለም።ነገር ግን ዛሬ ላይ የክልሉ ተወላጆች በኢትዮጵያዊነታቸው የፀኑቱ የመምራት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ካልተነሱ አደጋ አለው።ዝምታ ይብቃ! በስህተት ህዝብን ከኢትዮጵያዊነት ለመለየት የሚሞክረውን ለመቸውም ጊዜ ቢሆን ወደ እራሱ ካልተመለሰ የጥፋት እና የባዕዳን ፈረስ ከመሆን ስለማይድን ''አካፋን አካፋ'' የማለት ባህል መዳበር አለበት።


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
ታህሳስ 1/2008 ዓም (December 11/2015)

The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church is in turmoil in Athens, Greece.

His Holiness Abune Mathias I, Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church, met with Greece's Ambassador to Ethiopia, Antonios Sg...