======
ከጉዳያችን
=====
=====
መነሻ
ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ታሪክ፣የረጅም ዓመታት የመንግስት ሥሪት እና የትውልዶቿ ያልተቋረጠ ተጋድሎ ውጤት ነች። ኢትዮጵያ እንዳትኖር፣እንድትበታተን እና የማያባራ የእርስበርስ ግጭት ውስጥ እንድትገባ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ እየተያዘ በጠላቶቿ ብዙ ጥረት ተደርጓል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማዳከም ሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ። እነርሱም ሀገሩን የሚሸጥ ባንዳ ማሰስ እና የሃይማኖት ተቋማቷ ለብጥብጥ መነሻ እንዲሆኑ በማስከፋት መቀስቀስ
በእዚህ ፅሑፌ ላይ ከላይ የተጠቀሱትን ሑለት ጉዳዮች ላይ ያሉትን የሕግ ክፍተቶች የሚሞላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማውጣት የሚገባው ሕጎች ላይ ያተኩራል።
ሕግ 1
ኢትዮጵያ ወረራ በገጠማት ወቅት አብራ ያስተናገደችው ፈተና ከራሷ ውስጥ የወጡ ባንዳዎች ናቸው። ባዕዳንን እየመሩ ሀገር ማስወረር በኢትዮጵያ ታሪክ ጎልቶ ባይታይም፣ፈፅሞ ደግሞ አልነበረም ማለት አይቻልም። ለምሣሌ የአፄ ቴዎድሮስ የመጨረሻ ዓመታት ላይ በመቅደላ ተራራ በከተሙበት ጊዜ የእንግሊዝን ሰራዊት እየመራ መቅደላ ድረስ ያመጣ የደጃች በዝብዝ ካሣ ምርጫ በኋላ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ተብለው የነገሱት ይጠቀሳሉ። ደጃች በዝብዝ ለኢትዮጵያ በመተማ መሰዋታቸው ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ዋጋ ተሰጠው እንጂ ባዕድን እየመሩ አምጥቶ የራስን ሀገር ንጉስ አሳልፎ መስጠት የንጉሱ ልጅና ሚስት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረግ፣በ17 ግመል ሙሉ የኢትዮጵያ ጥንታውያን መፃሕፍት እና ቅርስ ተጭኖ ሲወሰድ አጅቦ መሸኘት እና በልዋጩ አሮጌ መሳርያ መቀበል አሳፋሪው የታሪካችን ገፅታ ነው።
በዘመናችንም የባንዳነት ታሪክ ''ዓይን አፍጥጦ፣ ጥርስ አግጥጦ'' የሚታየው በተለየ መልኩ ነው። ትናንት ስለ ኢትዮጵያ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል የነበረ፣ ዛሬ ላይ ባለመሾሙ ወይንም በመሰረታዊ የኢትዮጵያ ጥላቻ ታውሮ ኢትዮጵያን ለባዕዳን አሳልፎ ለመስጠት ከዩቱበር እስከ ምሑር ነኝ ባይ ሲባዝኑ መመልከት ተለምዷል። ቀስ በቀስም ለባንዳነት የሚሰጠው የመጠየፍ ደረጃ ማነሱ በራሱ ሌላው አሳሳቢው ጉዳይ ነው። ባንዳነት በተገቢው መልክ ዛሬ አለመጠየፍ እና ለባንዳም ተገቢውን ሥነ ልቦናዊ፣ማኅበራዊ እና አካላዊ ቅጣት ጭምር አለመስጠት መጪው ትውልድ እንዲለማመድ የሚያደርግ አደገኛ ሁኔታ ይፈጥራል።
በመሆኑም የተወካዮች ምክር ቤት ባንዳ የሚለውን ትርጉም ከዘመኑ ሁኔታ ጋር አሻሽሎ ከመተርጎም ጀምሮ (ባንዳነት በማኅበራዊ ሚድያም እየተገለጠ ስለሆነ) እስከ በባንዳነት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆኖ በኢትዮጵያ ላይ የሚቀስጥ ግለሰብም ሆነ ቡድን ላይ በሀገር ቤት የሚገኝ ሀብት ከመውረስ አንስቶ እስከ ባንዳነት ስም መሰየም፣ በሕግም ቅጣቱን/ቅጣቷን የምታገኝበት መንገድ ላይ በፍጥነት መሰራት አለበጥ
ሕግ 2
በኢትዮጵያውያን የኖረ ባሕል እና የማኅበረሰብ ጥብቅ ሕግ ውስጥ የእምነት ተቋማትን መዳፈር ነው። ይህ በኢትዮጵያውያን አዕምሮ ተፅፎ የኖረ እና የተከበረ ነው።በታሪካችን ከታዩት ኃይማኖታዊ መልክ ካላቸው እንደ የ16ኛው ክ/ዘመን ጦርነት ውጪ ኢትዮጵያውያን በእርስ በርስ ጦርነት ክርስቲያኑ የሙስሊሙን መስጊድ ሲያቃጥል፣ሙስሊሙም የክርስቲያኖችን አብያተክርስቲያናት ሲያፈርስ አልታየም። የእዚህ ዓይነት ተግባራት በጎሳ ጥ=ፀብ ሳቢያ ቢፈጸምም ድርጊቱን በቶሎ የሚያርመው በጋራ ተባብሮ መልሶ በመስራት እና ይቅርታ በመጠያየቅ ነው።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ በተለይ በአብያተክርስቲያናት ላይ የሚደረጉት የማጥፋት፣ክርስቲያኖችን የመግደል እና የማሳደድ ድርጊቶች በተለይ እንደ አርሲ ዞን ባሉ ቦታዎች ጉዳዩ እየተዘወተረ፣በማኅበራዊ ሚድያ የሚመለከተው ትውልድም ለዓይኑ እየለመደው የመጣ ይመስላል። ይህ አደገኛ ሁኔታ ነው። ''ከሃጢአት ልማድን ፍራ'' እንዲል ልማድ በትውልዱ አዕምሮ ላይ የሚፈጥረው የነገዋን ኢትዮጵያ ገፅታ ነው።
ይህ አደገኛ አካሄድ የሚታረመው እጅግ ጠንካራ በሆነ ሕግ እና አፈጻጸም ነው። በቅርቡ በዮርዳኖስ በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ በአራት ግለሰቦች የተፈጸመው ጥቃት እና የዮርዳኖስ መግስት የወሰደው እርምጃ አስተማሪ ነው። ጥቃቱ የተፈፀመው እ.ኤ.አ. ጥቅምት 23 ቀን 2026 በደቡባዊ ዮርዳኖስ ካራክ ግዛት ሃሙድ (Hmoud) መንደር በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ ከ30 በላይ ሰዎች ቆስለዋል። ሦስት የታጠቁ ግለሰቦች (ሁለት ዮርዳኖሳውያን ወንድማማቾች እና የእህታቸው ባል) በቤተክርስቲያኑ ውስጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ባለበት ወቅት በመግባት በተሰበሰቡ ሐዘንተኞች ላይ ነበር ጥቃቱ የተፈፀመው። ከጥቃቱ በኋላ የዮርዳኖስ መንግስት የወሰደው እርምጃ ፈጣን እና አስተማሪ ነበር። ይሄውም በድርጊቱ የተሳተፉ በስቅላት እንዲቀጡ ነው የወሰነው። ዮርዳኖስ የሙስሊም ሀገር ብትሆንም በእምነት ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ላይ እንዲህ ያለ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ የዕምነት ተቋማት አይደፈሬ መሆናቸውን አስመስክራለች።
ኢትዮጵያ ከእዚህ ባለፈ መሔድ ያለባት እርቀት ያስፈልጋል። ይህች ሀገር የሦስቱ ጥንታውያን ዕምነቶች ማለትም የክርስትና፣እስልምና እና ይሑዲ ዕምነቶች ያስተናገደች አብዛኛው ሕዝቧ በሃይማኖት ውስጥ ያለ መሆኑ የሚነገርለት ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ ከሁሉም በፊት የዕመንት ቦታውን የሚያስከብርለት መንግስት እና ሕግ ይፈልጋል። ሰዎች እንደፈለጉ አብያተክርስቲያናት እና መስጊድ አፍርሰው የሚኖሩባት ሀገር መሆን የለባትም። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፋጣኝ ሕግ ማውጣት አለበት። ይሄውም ማንም ግለሰብ ሆነ ቡድን በዕምነት ተቋማት ላይ ከማጥላላት እስከ ማናቸውም ድርጊት ቢፈፅም ሕጉ በአስቸኳይ ፍርድ ለመስጠት የሚያመች አዲስ ሕግ ያስፈልጋል። ይህ ሲባል እስካሁን ያለው ሕግ አይሰራም ማለት አይደለም። ሕጉ አሁን መጥበቅ እና አስደንጋጭ መሆን አለበት። በተለይ የዕመንት ተቋማት ላይ እና ሰዎችን በዕመነታቸው ሳብያ ጥቃት የፈጸመ እንደ ድርጊቱ ክብደት እስከ ሞት በፍጥነት የሚያስፈፅም ሕግ መደንገግ እና ለያንዳንዱ ድርጊት የተፈረዱት ፍርዶች ለሕዝብ መገለጥ አለባቸው።
ለማጠቃለል የኢትዮጵያ የሕልውናዋ ምሰሶዎች ላይ የኢትዮጵያ ታሪካው ጠላቶች አነጣጥረዋል። ትናንት የፈፀሙትን ነገም ይደግሙታል። የተወካዮች ምክር ቤት ግን ሊፈጥን ይገባል። ይሄውም አዲስ እና የጠበቀ ሕግ ለባንዳነት እና የሃይማኖት ተቋማትን ለሚያጠቁ ሊያወጣባቸው እና አፈጻጸሙን ሊከታተል ይገባል።
====================/////===================

No comments:
Post a Comment