ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, January 31, 2023

ጠ/ ሚ/ር ዐቢይ ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመክፈል የሞከሩ ሕገወጦችን አስመልከተው የተናገሩት ንግግራቸው በታሪክም በሕግም ያስጠይቃቸዋል።




በእዚህ አጭር ጽሑፍ ስር፣
  • የሞሰቡን ባለቤት ከራሱ ሞሰብ ላይ ቆንጥረው ያጎረሱትን እየቆጠሩ ከውለታ ቁጠርልኝ፣
  • ቤንዚን ማርከፍከፍ
  • ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተፈጸመው ወንጀል የሚያስከትለው መዘዝ ገብቷቸዋል።
  • ሚኒስትሮች! የሃይማኖታችሁ ጉዳይ አይመለከታችሁም! ዝም በሉ!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ጥር 23፣2015 ዓም ሰላም እና ሃይማኖት በተመለከተ የተናገሩት በሚል በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተናገሩት ንግግር በዋናነት ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ለመክፈል በኦሮምያ ክልል የተነሳውን ቡድን አስመልክተው የተናገሩት በታሪክም በሕግም ያስጠይቃቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእዚሁ ንግግራቸው ፈጽሞ ፍትሃዊነት የጎደለው፣የህገወጦቹ ቃል አቀባይ እስኪመስሉ ድረስ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተሞከረው የመክፈል ሙከራ የመንግስት ሚናው እና ቦታውን ያላሳየ ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ ወገናዊነት የታየበት ከቃላቶቻቸው ድምጸት እስከ የህገወጦቹ ካሉት በላይ አስተዛዝነው ለማስረዳት የሄዱበት እርቀት ሁሉ በቤተክርስቲያኒቱ መከፍል ያላቸውን አቋም ማንም በግልጽ ሊረዳው የሚችለው ነው። እስኪ ከንግግሮቻቸው ውስጥ የሚከተሉትን እንመልከት።

የሞሰቡን ባለቤት ከራሱ ሞሰብ ላይ ቆንጥረው ያጎረሱትን እየቆጠሩ ከውለታ ቁጠርልኝ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በእዚህ ንግግራቸው መግብያ ላይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንግስት ሰጠ ያሉትን መሬት እየሰፈሩ ከሌላው የእምነት ተቋማት ጋር ለማነጻጸር በእዚህም የመንግስታቸው ''ቸርነትን'' ለማሳየት ሞክረዋል። በመጀመርያ ይህ ተሰጠ ያሉት መሬት ማስረጃ የትነው ያለው? ሲቀጥል ይህ ንጽጽር በራሱ ሁለት መሰረታዊ ስህተቶች አሉት። አንድ፣ ኦርቶዶክሳዊው በራሱ ሃገር እንደምጽዋተኛ የሚታይ አይደለም።የራሱን ሞሰብ ላይ ያጎረሱትን እየቆጠሩ ከውለታ ቁጠሩልኝ መሰል ንግግር ትዝብት ላይ ይጥላል።አንድ መንግስት ለሺህ ዓመታት ለኖረች ቤተክርስቲያን መሬት ሰጠሁ ብሎ እንደ ታላቅ ውለታ የሚነገርባት ሃገር ኢትዮጵያ መሆኑ ያስገርማል። በሁለተኛ ደረጃ ክርስቶስ ባረገ በዓመቱ ክርስትናን የተቀበለች፣በአራተኛው ክ/ዘመን ክርስትና ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ የታወጀባት ሃገር ኢትዮጵያን የሰራች ቤተክርስቲያን የተሰጣትን መሬት ከሌሎች ጋር የማወዳደሩ አካሄድ ያውም በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሆነ ለመፍጠር የተፈለገውን ስዕል ያሳያል።የስሌቱ አካሄድ በራሱ የትንሽነት አስተሳሰብ ሰለባነትን ያሳያል።

ቤንዚን ማርከፍከፍ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ያደረጉት ንግግር እንደ መንግስት መሪ ነገሮችን በሁለት ዐይን የተመለከተ ሳይሆን ፍጹም አድሏዊ፣ሃላፊነት የጎደለው እና የህገወጥ ቡድኖችን ተግባር ለማንሞካሸት ሩብ ጉዳይ የቀረው ያህል ነው። እነርሱ ያሉት በቋንቋቸው የመማር ጥያቄ እንዳነሱ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቤተክርስቲያኒቱ በቋንቋ በኩል ምን እየሰራች እንዳለች ለመናገር አልፈለጉም።በነገሩ ላይ ቤንዚን ይጨምርልኛል ያሉትን ብቻ እነርሱ ያሉት እያሉ አስተዛዝነው ሀገር በደም ለመንከር በህገወጥነት እና ፍጹም በሆነ ውንብድና ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል የሞከሩትን ቡድኖች በመንግስት ሚድያ ለማስተላለፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ይህንን ያህል በሃሰት ሲጋጋጡ ማየት ለትውልዱ አሳፋሪ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ህገወጥ ቡድኑ በመንግስታቸው የክልል ወታደር እንደሚታጀቡ፣ቤተክህነትን ሲጠብቅ የነበረ ፖሊስ እንዲነሳ የተደረገበትን ምክንያት፣አቡነ እስጢፋኖስ በጅማ ለንግስ እንደሄዱ ለምን ከአየር ማረፍያ ተይዘው ፖሊስ ጣብያ ታስረው እንደዋሉ፣ዛሬ በያቤሎ የመንግስታቸው ወታደሮች ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል ሞክረው የተወገዙትን ግለሰቦች ህዝብ እንዲቀበል ሊያስገድዱ ሲሞክሩ ህዝብ እምቢ ማለቱን አልነገሩንም። በአጭሩ በዛሬው ንግግራቸው በቤተክርስቲያኒቱ ላይ በታሪኳ ደርሶባት የማያውቅ መንግስት የሚባል አካል ባለበት በሃገር ውስጥ ሆኖ ሲኖዶስ እከፍላለሁ ያለ ቡድን ድርጊትን '' እንደ እኔ ቀላል ጉዳይ ነው '' በማለት ሊያጣጥሉት የሞከሩበት እርቀት በራሱ ስለ ቤተክርስቲያኒቱ ያላቸውን ያልበሰለ ወይንም ሆን ተብሎ የማጣጣል አቀራረብ ያሳያል።ባጭሩ ንግግራቸው በችግሩ ላይ ቤንዚን ያርከፈከፈ እና ህገ ወጦችን አይዟችሁ ቀረሽ ንግግር በጣም የሚያሳፍር ነው።

ሌላው በዛሬው ቤንዚን አርከፍካፊ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ያነሱት ''ባለፈው የትግራይ ጳጳሳት ያን ያህል ሲሉ ምንም ያልተባሉትን ዛሬ ሁሉም እየተነሳ'' በህገወጦቹ ላይ እጅ አበዛችሁ ለማለት ሞክረዋል። በመጀመርያ ደረጃ የትግራይ ጳጳሳት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተለየን ሲሉ ሁሉም ዝም ብሎ ነበር? እርግጠኛ ነዎት? ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳይን አስመልክቶ የተነጋገረበትን ጉዳይ ያውቃሉ? ከእዚህ ገጽ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በየደረጃው ዝም ነው ያሉት? በሌላ በኩል በሁለቱ መሃል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? የትግራይ ጳጳሳት ፓትርያሪክ በሌለበት ኢጲስ ቆጶስ እንሹም ብለው ተነስተዋል? ለመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ያለ ሰው ባልተረጋገጠ እና መረጃ በሌለው የፌስ ቡክ ወሬ ተመስርቶ እንዲህ ባለ ትልቅ የሃይማኖትም ሆነ የሃገር ጸጥታ ጉዳይ ላይ ''እገሌ ሲሆን ዝም ብላችሁ እገሌ ላይ ትወርዱበታላችሁ'' በማለት ቤንዚን ያርከፈክፋል?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተፈጸመው ወንጀል የሚያስከትለው መዘዝ ገብቷቸዋል።

በዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ሌላው ያነሱት መንግስታቸውን የሚቃወም ህዝባዊ ኃይል እንደሚነሳ በግልጽ ጠቁመው በአመጽ የምትመጡበትን መንገድ እንዳይሞከር የሚል በጣም የወረደ የማስፈራርያ አይሉት ሌላ ቃላት ተጠቅመዋል። ወታደራዊ መንግስት በ''ኩዴታ'' ጉዳይ የመጣ ስለነበር ማንም በእዚህ መንገድ ሊጥለው አልቻለም። ህወሃትም በሽምቅ ስለመጣ እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑም አልቻሉትም በሚል ንግግር የተናገሩት ዐቢይ እኛም በምንም ብትመጡ እናቃለን በሚል የሚያሞኝ ንግግር አክለውበታል። ከእዚህ በተጨማሪ ጦርነት አስከፊ መሆኑን ለሚነሱባቸው ተቃዋሚዎች ለመምከር ከሞከሩ በኋላ አሁንም ለመግደል ወደ ከተማ እየመጡ ነው የተወሰኑ ይዘናቸዋል ብለዋል።

ስለሃይማኖት እና ሰላም የነበረው የርዕሳቸው ንግግር አመጽ እንደሚነሳ እና ቀጣዩ አመጽም በየት እንደሚመጣ እንደሚያውቁ እና እንደሚያከሽፉ ተናግረዋል። በመጀመርያ ደረጃ መንግስት የሰራውን ክፉ ሥራ ገብቶታል ማለት ነው? አመጽን ምን አመጣው? አመጽ እንደሚነሳ በምን አወቀ? አመጽ የከፋው እና የተከፋ ሕዝብ ይፈልጋል።መንግስት የገፋው እና የተገፋ ህዝብ መኖሩን በማወቁ ነው መንግስቴን ሊገለብጡ የሚነሱ አሉ ያሉት? የሰራውን የሚያውቅ ሁሌ መደንበሩ የተለመደ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ አመራራቸው የሰራውን ስለሚያውቁ እና ይህም ሥራ ትክክል አለመሆኑ ግልጽ በመሆኑ ከህዝብ የሚነሳ ተቃውሞ እንደሚኖር ለማመላከት ተገደዋል።ባጭሩ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የተፈጸመው ወንጀል ገብቷቸዋል። በአደባባይ ቢክዱትም።

ሚኒስትሮች! የሃይማኖታችሁ ጉዳይ አይመለከታችሁም! ዝም በሉ!

ሌላው አስቂኝም ሆነ አስገራሚው የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የተፈጸመውን መንግስታዊ ድጋፍ የተቸረው ቅዱስ ሲኖዶስን የመክፈል ሙከራ አስመልክቶ ለሚነሱ ማናቸውም ጉዳዮች ሚኒስትሮች አንዳች እንዳይናገሩ አስጠንቅቀዋል። ይህንን ንግግር የሙስሊም ወንድሞቻችን ላይ ቢናገሩት ብላችሁ አስቡት።በሌላ አነጋገር አንተ ሚኒስትር ሆነህ የኦርቶዶክስ ተከታይ ብትሆንም ሃይማኖትህ ሲከፈል፣ህገወጦች በጎጥ ተነስተው ቤተክርስቲያንህን ለመክፈል ቢሞክሩ ዝም በሉ! የሚል አስገራሚ መልዕክት አስተላልፈዋል። ሚኒስትር ኢትዮጵያዊነትን ቢያስቀድም ኢትዮጵያን የሚያውቃት በእምነቱ ውስጥም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንግተውታል።ኢትዮጵያ የሚኒስትር ቦታ አይደለም የንግስና ዘውዳቸውን አስቀምጠው ክርስቶስን ሊከተሉ ገዳም የገቡ መሪዎች ባለቤት ሃገር መሆኗን አሁንም እረስተውታል። ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ምንም ሃሳብ መስጠት እንደማይችሉ የተናገሩበት ድምጸት በራሱ ያስገርማል። ይህ የነገሩን የትኩሳት ልክ፣በቤተክርስቲያኒቱ ላይ መንግስታቸው የሰራውን የመከፋፈል ወንጀል ዲግሪ እና ከምንም በላይ በሃይማኖቱ ያውም በግፍ ሊከፍሉት የመጡበትን እንዴት ባለ መግነጢሳዊ የኃይል ስሜት ህዝብ እንደቋያ እንደሚያስነሳ ማንም ተራ ሰው ያውቀዋል። ግፍ ተሰርቷል።የእግዚአብሔርን ቤት ከሓዋርያት መሰረት ጀምሮ የኖረ ከክርስቶስ የተገኘች ሲኖዶሳዊ አሰራር ላይ ከባድ ድፍረት ተፈጽሟል።ይህንን ደግሞ የፈጸሙት በመንግስት ቀጥተኛ ድጋፍ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕገወጦቹ ሽፋን ለመስጠት በተፍጨረጨሩበት ንግግር ግልጽ ሆኗል።

ባጠቃላይ 

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ለደረሰው ሲኖዶስን የመክፈል ሙከራ በኢትዮጵያ ላይ የእርስ በርስ ጦርነት ከመጫር በላይ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እንደሚያመጣ ለመተንተን አልሞከሩም።ለምን? ለጸጥታ ጉዳይ አማካሪዎቻቸው እተወዋለሁ። ይህ የሃገር የጸጥታ ጉዳይ አይደለም? ይህ በኢትዮጵያ ጦርነት አያስነሳም? የሃገሪቱ መሪ ቀላል ጉዳይ ነው ብለው የሚነግሩን እንዴት ነው?  በመንግስታቸው የጸጥታ ኃይል ድጋፍ ጭምር ህገወጦቹ ጥበቃ እየተደረገላቸው ሳለ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ፓትሪያሪኩ ግልጽ ጥሪ ለመንግስት አቅርባ  መንግስታቸው አንድም ዓይነት ''ኦፊሻል '' ምላሽ ሳይሰጥ የቤተክርስቲያኒቱ አባላትን የጸጥታ ሃይሎች እያሰሩ እና እየፈቱ እንደጅማ ሃገረ ስብከት ደግሞ ሃገረ ስብከቱ ለስብከተ ወንጌል የሚጠቀምባቸውን መኪናዎች ጭምር እንዳያንቀሳቅስ የመንግስታቸው መዋቅር ትዕዛዝ እንደሰጠ እያወቁ ጉዳዩን ለማጣጣል እና የኢትዮጵያን ህዝብ ለማሞኘት የሄዱበት የጅል መንገድ ዋጋ ያስከፍላል።ባጭሩ ጠ/ ሚ/ር ዐቢይ ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመክፈል የሞከሩ ሕገወጦችን አስመልከተው የተናገሩት ንግግራቸው በታሪክም በሕግም ያስጠይቃቸዋል።የእግዚአብሔር ፍርድም ከበር ይጠብቃቸዋል።ኃይሉን ንቀውታል።አዛውንት ሊቃነ ጳጳሳትን እንደ ምናምንቴ ቆጥረው ጉዳዩን ሊያቃልሉት ሞክረዋል።የሚታዘባቸውን የኢትዮጵያን ህዝብ ቀላል ነው እያሉ ለመሸንገል ሞክረዋል። በድርጊቱ ግን አዛውንት መነኮሳት እንባቸው ፈሷል፣ወጣቶች ልባቸው ተቃጥሏል፣ታዳጊዎች ጳጳስ በሃገሩ ካለምንም ጥፋት መታሰሩን ሰምተዋል።ዛሬ ደግሞ የሃገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳዩ እንደ እኔ ቀላል ነው ብለው ሲዘብቱ ተመልክተዋል።

===============///////========



No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...