ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, January 30, 2023

የብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የማስተዳደር አቅሙ የወደቀ ለመሆኑ ህዝብ ድምዳሜ ላይ እየደረሰ ነው።የአቡነ እስጢፋኖስ በጅማ ፖሊስ ጣብያ ታስረው መዋል ፓርቲው ክቡር ለሆነ የኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ እሴት (''ሶሻል ቫልዩስ") ያለው የንቀት ደረጃ ህዝብ በሚገባ ለክቶበታል።

ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ፣የም፣ ኮንታ፣ዳውሮ እና ሰሜን ጎንደር ሊቀጳጳስ

  • ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል የሆነው ከ70 ሚልዮን በላይ የሆነ ቀረጥ ከፍሎ የሚያድረው ህዝብ በከፈልኩት ቀረጥ መንግስት ቤተክርስቲያኔን የመጠበቅ ግዴታህን ተወጣ የሚል እጅግ የከበደ ጥሪ ነው፣
  • ጅማን ህይወት የዘሩባት አቡነ እስጢፋኖስ ላይ የተፈጸመው ግፍ ብልጽግና በህዝብ ላይ ያለው የንቀት ጥግ ያሳያል።
  • የኢትዮጵያ ኦ/ ተ/ቤተክርስቲያን በተሞከረባት የመበተን ሙከራ አንጻር ቤተክርቲያኒቱ  እንደ ተቋም ምዕመናኖቿ ደግሞ እንደ የቤተክርስቲያን ልጅነት ሊወስዷቸው የሚገቡ ሁለት ስልታዊ እርምጃዎች ምን እና ምን ናቸው?
 
=========
ጉዳያችን
=========

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመክፈል ያለመ ያልተሳካ ሙከራ ከተደረገ በኋላ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የሚደረጉት የሽብር ተግባራት ቀጥለዋል። የሽብር አፈጻጸሙ ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱን አባቶች እና አገልጋይ ካህናት ለማሸማቀቅ እየተደረገ ያለው ሙከራ ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ እየቀሰቀሰ ከመሆኑም በላይ በብልጽግና የሚመራው መንግስት ቤተክርስቲያኒቱን ህዝብ በከፈለው ቀረጥ የመጠበቅ ግዴታው ላይ ያሳየው ንዝህላልነት እና ንቀት የፓርቲው ሃገር የማስተዳደር አቅም ከአማካይ በታች እንደሆነ አስመስክሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሲኖዶሱን ለመክፈል የሞከሩትን ስልጣነ ክህነት ከመሻሩ በላይ አሁንም ለንስሃ ተመልሰው ይቅርታ ከጠየቁ ጉዳዩ እንደሚታይ ጠቅሶ ጉባዔውን አጠናቋል። ይህ ውሳኔ ድንገት ደራሽ የሆነ እና ለአበበ ወይንም ለከበደ ተብሎ የሚለይ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ጥያቄ ሲሆን በጉባዔ ቀርበው የሚያስረዱበት በቀጥታ ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል የምዕመናንንን አንድነት ለመበተን የሚደረግ አደገኛ ሙከራን ደግሞ በፍጥነት ስልጣነ ክህነትን መሻር ነው። ይህ ቤተክርስቲያኒቱ ዛሬ የጀመረችው ሳይሆን ከሓዋርያት ጉባዔ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እና ዛሬም የምስራቃውያን አብያተክርስቲያናት የሚጠቀሙበት ነው።

ቤተክርስቲያኒቱ በቀኖናዋ መሰረት ይህንን ብትወስንም የህገወጦቹ ደጋፊ መሆኑን በሚያሳብቅ ደረጃ የተወገዙትን ልዩ የጥበቃ አገልግሎት ለመስጠት ሽር ጉድ ሲል የታየው የኦሮምያ ብልጽግና ልዩ ኃይል ነው። ይሄው ልዩ ኃይል ህገወጡ ሹመት በተደረገበት ቦታ ተገኝቶ የጥበቃ አገልግሎት ከመስጠት ጀምሮ ህገወጦቹን አንቀበልም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በግድ ለመላክ ያደረገው የከሸፈ ሙከራ ሁሉ የብልጽግና ፓርቲ በቤተክርስቲያኒቱ አንጻር እያሳየ ያለው አደገኛ መንገድ ግልጽ ያደርገዋል።

ጅማን ህይወት የዘሩባት አቡነ እስጢፋኖስ ላይ የተፈጸመው እስር ብልጽግና በህዝብ ላይ ያለው የንቀት ጥግ የሚያሳይ ነው።

ብጹዕ አቡነ እስጢፋኖስ፤ የጅማ፣የም፣ ኮንታ፣ዳውሮ እና ሰሜን ጎንደር ሊቀጳጳስ ባለፈው ቅዳሜ ለጅማ ደብረ ኤፍራታ ቅድስት ማርያም ካቴድራል የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ለመገኘት ጅማ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በኦሮምያ ክልል ፖሊስ ለጥያቄ እንፈልጋችኋለን ተብለው ፖትሮል በያዙ አካላት ወደ ጅማ ፖሊስ መምሪያ ተወስደው በበዓሉም ላይ ሳይገኙ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጓል። ጅማን በልማት ለማሳደግ የአቡነ እስጢፋኖስን ያህል የለፋ ላለመኖሩ ክርስቲያኑ አይደለም የሙስሊም ማኅበረሰብ የሚመሰክረው ነው።አቡነ እስጢፋኖስ በጅማ ሃገረስብከት ባገለገሉባቸው ዓመታት ውስጥ ጅማ ከተማ ብቻ ተቀምጠው ያገለገሉ አባት ብቻ አይደሉም። ከጅማ ውጭ የሚገኙ ቦታዎችን በሞተር ሳይክል ሳይቀር እየተመላለሱ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ሳይቀር ድጋፍ ያደረጉ አባት ናቸው። ዛሬ ላይ ግን የብልጽግና መንግስት ህይወት በዘሩባት ከተማ ያሰሩትን ቤተክርስቲያን እንዳያስመርቁ ከአየርማረፍያ ተወስደው ፖሊስ ጣብያ እንዲታሰሩ ተደረገ። ለእዚህ ለተፈጸመ ግፍ አሳሪው ዋጋውን መከፈሉ አይቀርም።

የኢትዮጵያ ኦ/ ተ/ቤተክርስቲያን በተሞከረባት የመበተን ሙከራ አንጻር ቤተክርቲያኒቱ  እንደ ተቋም ምዕመናኖቿ ደግሞ እንደ የቤ/ክርስቲያን ልጅነት ሊወስዷቸው የሚገቡ ሁለት ስልታዊ እርምጃዎች 

የኦሮምያ ብልጽግና ከጽንፈኛ የክልሉ ኃይሎች ጋር ሆኖ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ለመክፈል ያደረገው የከሸፈ ሙከራ በአባቶች ላይ የሽብር እና የማሰር ግፍ ብቻ ሳይሆን የፈጸመው ቤተክርስቲያኒቱ በግልጽ (በኦፊሻል) ለመንግስት የቤተክርስቲያኒቱን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ በቅዱስ ፓትሪያሪኩ ብጹዕ አቡነ ማትያስ ባለፈው እሁድ ጥር 21፣2015 ዓም ላደረጉት ጥሪ አንዳችም ምላሽ አልሰጠም። ይህ ጥያቄ እና ጥሪ የአቡነ ማትያስ ወይንም የሌላ አባት ድምጽ አይደለም። ''ኦፊሻል" ጥያቄው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ድምጽ ነው። ይህ ከ70 ሚልዮን በላይ የሚሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ እና ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል የሆነው ከ70 ሚልዮን በላይ የሆነ ቀረጥ ከፍሎ የሚያድረው ህዝብ በከፈልኩት ቀረጥ መንግስት ቤተክርስቲያኔን የመጠበቅ ግዴታህን ተወጣ የሚል እጅግ የከበደ ጥሪ ነው። ይህንን ጥሪ አለመስማት ጅልነትም ነው።ይህንን ጥሪ ችላ ብሎ ህገወጦቹን በልዩ ኃይል ለማስጠበቅ መንደፋደፍ ህዝብን የመናቅ አደገኛ ደረጃ ነው። 

አሁን የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ የሙስሊሙም ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል የሚደረገው ሙከራ ከመስመር ያለፈ ብቻ ሳይሆን በትዕቢት የተወጠረ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው። ለእዚህ ምላሽ እንዲሆን ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፎች በመጪው ረቡዕ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ከሚደረገው ሰልፍ በተጨማሪ በመጪው ዕሁድም ግዙፍ ሰልፎች በመላው ዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ ይደረጋሉ።ይህ የብልጽግና ፓርቲ በመላው ዓለም በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ እየሰራ ያለውን የንቀት እና የጥላቻ ተግባር የሚያጋልጥ ነው።

ከእዚህ በተጨማሪ ግን ቤተክርስቲያኒቱ እንደ ተቋም፣ምዕመናን እንደልጅነት የሚሰሯቸው ሁለት ቁልፍ እና ስልታዊ ስራዎች ሊኖሩ ይገባል።

ቤተክርስቲያኒቱ እንደተቋም አሁን ለገጠማት ችግር መስራት የሚገባት ሁለት ጉዳዮች ናቸው። አንዱ እራሷን በፍጥነት ንብረቷን እና የሰው ኃይሏን በፈጠነ ዘመናዊ መንገድ መያዝ እና ማስተዳደር።ይህንን ደግሞ ለምሳሌ በአጭር ጊዜ የቤተክርስቲያኒቱን አጥብያዎች እና አድባራት እንዲሁም ገዳማት አስተዳደር በአይቲ ማገናኘት ይህንንም ሥራ ለቤተክርስቲያኒቱ ልጆች መስጠትና ውጤት ማምጣት ይገባል። ይህም የገንዘብ አስተዳደሩን ብቻ ሳይሆን የሪፖርት ፍሰት እና መረጃዎች በማዕከል ቤተክህነት በቶሎ ለማቀላጠፍ ይረዳዋል።

ሁለተኛው ቤተክርስቲያኒቱ በፍጥነት መከወን ያለባት ከእህት አብያተክርስቲያናት ጋር እና ከምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ተከታታይ ግንኙነቶች ማድረግ እና ያሉባትን ተግዳሮቶች ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በብልጽግና ላይ እንዲደረግ ማድረግ እና የአቅም ግንባታዋ እንዲታገዝ ማድረግ ነው። 

ምዕመናን እንደልጅነት ሊያከናውኑት የሚገባው አንዱ እና ዋና ተግባር ሃገራዊ በሆኑ ቤተክርስቲያኒቱንም ልጆቿንም ሰላም እየነሳ ያለው እና የጽንፍ ኃይሎችን ጉልበት እየሰጠ ያለው የጎሳ ፖለቲካን በሃገር አቀፍ ደረጃ በመቃወም ዘመቻ ማድረግ ነው። ይህንን የጎሳ ፖለቲካ የኢህአዴግ አባል የነበሩት የብልጽግና አባላት ሲሳሱለት እየታየ ነው። ከአሁን በኋላ ግን የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ኢትዮጵያ ተነክራ ከቆየች የእያንዳንዱ ሰው ህልውና ብቻ ሳይሆን የመጪው ትውልድ አደጋ በመሆኑ የጎሳ ፖለቲካን በመቃወም በመላ ሃገሪቱ ምዕመናን እንደልጅነት ቤተክርስቲያን ደግሞ በአስተምሮቷ እንደተቋም በግልጽ እና በአደባባይ በመቃወም መላው የኢትዮጵያ ህዝብን ከጎኗ የምታቆምበት ጊዜ አሁን ነው። የጎሳ ፖለቲካን እንዴት እንደሚነቅል የሱማሌ፣የደቡብ፣የአፋር፣የቤኒሻንጉል፣የአማራ፣ኦሮሞና ትግራይ ክልል ህዝብ ሁሉ የሚያስነሳው እየጠበቀ ነው። አሁን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስተምሮቷም ክርስትናም የጎሳ ፖለቲካ ተቃራኒ በመሆኑ ይህንን መልካም ሥራ ምዕመናኖቿ በግልጽ ወጥተው ግዙፍ ንቅናቄ የሚፈጥሩበት ጊዜ አሁን ነው።

ባጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን መልካም እሴቶች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ኢትዮጵያን በሁሉ መልክ ሰጥታ ለዘመናት ያሻገረች የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን አንጻር ያሳየው የመበተን ሙከራ እጅግ አስጸያፊ ብቻ ሳይሆን በስጋም በነፍስም ትልቅ ድፍረት ነው።ድፍረቱ የተሰጠውን መንግስታዊ ኃላፊነት ህዝብን እና ከህዝብ በሰበሰበው ቀረጥ የህዝብ የሆነ ሃይማኖትን የመጠበቅ ግዴታ ከመወጣት ይልቅ ህገወጦችን እያደራጀ ቤተክርስቲያኒቱን ለመግፋት ሲሞክር ማየት አሳዛኝ ነው።ምናልባት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በወታደራዊው መንግስትም ሆነ የህወሃት መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጡ ቤትክህነቱን ለመቆጣጠር የሄዱበትን እርቀት ብልጽግና እንደ የልማድ ትምህርት ወስዶ ያንኑ ሊሞክር ያስብ ይሆናል። ይህ  ግን ዘመኑን ያለመዋጀት ችግር ነው።በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ ያለችው የዛሬዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በ1966 ዓም ሆነ በ1983 ዓም እንዳለችው ያለች አይደለችም። ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆቿ ተደራጅተዋል ብቻ ሳይሆን ለመስዋዕትነት የተዘጋጁ ሚልዮኖች በሙሉ ልብ ከቤተክርስቲያን ጎን የቆሙበት ጊዜ ነው። ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆቿ በመላው ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ብቻ ሳይሆኑ የአንዳንዶቹ ሃገሮች የደም ስርም ጭምር ናቸው። በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ለሚሞከር ምንም ዓይነት የመበተን እና የመከፋፈል ሙከራ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል አይደለም።ባጭሩ የ1966 እና 1983 ዓም ስሌት ዛሬ ላይ እንደማይሰራ ብልጽግና ግልጽ ካልሆነለት ግልጽ ሊሆንለት ይገባል።የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አንድነቷን ማክበር የኢትዮጵያን አንድነት ማክበር ማለት ነው። በእዚህ መንገድ ብቻ ነው ቤተክርስቲያኒቱ የልማት አጋር አድርጎ ሃገር በጋራ ማሳደግ የሚቻለው። ከእዚህ ውጭ የሚያስኬድ አንዳችም መንገድ የለም።
====================///////=====================

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።