ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, January 24, 2023

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለመክፈል የተሞከረው ሙከራ በሁሉም ክልል በሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱን ልጆችና አባቶች ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ የጠነከረ ህብረት እና አንድነትን ፈጥሯል።



  •  በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን በሙስሊሙም ማኅበርሰብ ዘንድ ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል የሚደረገው ሙከራ ከፍተኛ ቁጣን ፈጥሯል።
  • ንዝረት የተኛ ነርቭ ያነቃቃል።
  • ቤተክርስቲያን ተሸንፋ አታውቅም ሊከፋፍሏት የሞከሩትን ሁሉ ግን አለት ሆና ስታደቅ በታሪክ ታይቷል።
  • ቅዱስ ሲኖዶስ የነገውን አስቸኳይ ስብሰባ ህገወጦቹን ከማውገዝ ባለፈ የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ሁኔታ ለማዘመን ከምር ከምዕመናን ጋር መክሮ ወደ ሥራ የሚገባበት መሆን አለበት። ይህንን የአንድነት ስሜት መጠቀም ይገባል።

==========
ጉዳያችን ምጥን
=========
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የተለያየ ምክንያት ለራሳቸው እየሸጎጡ በከንቱ ጥላቻ ውስጥ የሚንገዋለሉ መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።ኢትዮጵያን ከነፊደልዋ፣ከነታሪኳ፣ባሕሏ እና ነጻነቷ እንድትቆይ ሃላፊነት ወስዳ በሰራች እና ለትውልድ ሃገር የማሸጋገር ሥራ ላይ ቀዳሚ ሚና በመጫወቷ በሚያምኑት እምነት መለየት ወይንም ኢትዮጵያን በማስቀደሟ የባንዳነት ዛራቸው የሚያጓራባቸው እንዲሁም ቀርበው ሳያውቋት በርቀት በስማ በለው በቡና ላይ ወሬ ሊተርኳት የሚሞክሩ ሁሉ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ።

በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ያለው የጥላቻ ደረጃ በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ እንደ የሊባኖሱ ሂዝቦላ ተሸሽጎ የፋሺዝም ተግባር የሚይራምደው ከኦነግ ሸኔ ጀምሮ በባዕዳን ድርጎ የሚንቀሳቀሱ የሃይማኖት ያልሆኑ ግን ሃይማኖት መሰል ስብስቦች ሁሉ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የሸረቡት ተንኮል ሁሉ ምዕመኑ ሳያውቀው ቀርቶ አይደለም። ሁሉን እየሰማ እንዳልሰማ፣ እየተመለከተ እንዳልተመለከተ የሃገር ጉዳይ ይቅደም እያለ አልፎታል። ሆኖም ግን ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል በከፍተኛ ወጪ ባለ ኮከብ ሆቴል የሚያርፉ መነኮሳትን ሰብስቦ እና በዘር እና በመንደር ተደራጅቶ የቤተክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አካል የሆነውን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመክፈል የድፍረት ድፍረት ይፈጸማል ብሎ የገመተ የለም። የሆነው ግን ይሄው ነው።ዐይን አውጣነት፣ሸፍጥ እና ክህደት በተሞላበት መንገድ ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚያውቀው ውጪ ኢጲስ ቆጶሳት ሾመናል የሚሉ አካላት ሲነሱ መንግስታዊ አካል ጉዳዩ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እንደሚያመጣ እያወቀ እና የሃገሪቱ ትልቁንና ጥንታዊውን ተቋም በህገወጦች በእዚህ ደረጃ ለመግፋት ሲሞከር አንድም የህጋዊውን ሲኖዶስ ደህንነት ለማስጠበቅ የተንቀሳቀሰ እና ህገወጦቹን ለመውቀስ የተሰማ እንቅስቃሴ አሁንም ከመንግስት በኩል አልተሰማም።
ይልቁንም በዛሬው ዕለት የተሰማው መንግስት ጥበቃ ያደርግ የነበረበትን የቤተክርስቲያኒቱን ከፍተኛ አካላት ቦታዎች ሁሉ ፖሊሶቹ እንዲነሱ ማድረጉ ነው የተሰማው።

ይህ ሁኔታ የፈጠረው ሁኔታ ግን ከእዚህ በፊት ባልታየ እና ባልተሰማ ደረጃ በሁሉም ክልል የሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮች እና አባቶች መሃል እጅግ ከፍተኛ ህብረት እና አንድነት ተፈጥሯል።''ክርስቲያን እና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል '' እንዲሉ በአሁኑ ጊዜ ከሁሉም በላቀ መልኩ እየተሰራ ያለው ደባ በኦሮምያ ክልል የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተረድተውታል። ድርጊቱ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን በሙስሊሙም ማኅበርሰብ ዘንድ ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል የሚደረገው ሙከራ ከፍተኛ ቁጣን ፈጥሯል።ንዝረት የተኛ ነርቭ ያነቃቃል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለመክፈል የተሞከረው ሙከራ በሁሉም ክልል ላሉ የቤተክርስቲያኒቱን ልጆችና አባቶች የጠነከረ ህብረት እና አንድነትን ፈጥሯል።በቤተክርስቲያኒቱ እና በምዕመናኖቿ ላይ እየተፈጸሙ ያሉት በደሎች ምን ዓይነት ቁጣ አስከትለው እንደሚያልፉ እና የት እርቀት ድረስ ሊከፋፍሏት የሞከሩትን እንደሚያሽቀነጥራቸው አሁን ግምቱን ማስቀመጥ ቢከብድም ከታሪክ የምንማረው ግን አንድም ቀን ቤተክርስቲያን ተሸንፋ እንደማታውቅ ብቻ ሳይሆን ሊያጠፏት እና ሊከፋፍሏት የሞከሩትን ሁሉ አለት ሆና ስታደቃቸው መኖሯን ነው።

በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ ነገ አስቸኳይ ምልዐተ ጉባዔው ቤተክርስቲያኒቱን ለመክፈል የሞከሩትን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ይወያያል።ከውይይቱ በኋላ የሚሰጠው ውሳኔ የምዕመናንም ውሳኔ ሆኖ ይቀጥላል።ከእዚሁ ጋር በማስከተል ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን አስቸኳይ ስብሰባ በህገወጦቹ ላይ ሲኖዶሳዊ ውሳኔ ከማሳለፍ በላይ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ለማዘመን የሚሰሩ ሥራዎች እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ውሳኔ እና ቁርጥ የሥራ ሂደት ማስኬድንም አብሮ ሊያስብበት ይገባል።አጋጣሚው መልካም ነው።የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ሁኔታ ማዘመን የምዕመናንም የአባቶችም ጥያቄ ነው።ይህንን የአሁኑን በምዕመናንና አባቶች መሃል የተፈጠረርውን እጅግ የጠነከረ ህብረት እና አንድነት እና በቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው የጥቃት ቁጭት መልካም አጋጣሚ ነው።ይህንን ስሜት እና ሁኔታ መጠቀም ብልህነት ነው። 

ቤተክርስቲያንን አንተውም ከቶ! መዝሙር



No comments: