ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, September 21, 2015

የመስቀል ደመራ በአል በኢትዮጵያ፣በኦስሎ፣ኖርዌይ እና በመላው ዓለም በመጪው እሁድ ይከበራል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም በብቸኛ ቅርስነት ከጠበቀቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል የመስቀል ደመራ በአል አንዱ ነው።የመስቀል ደመራ በአል ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም ተሰደው በሚኖሩ በሚልዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አማካኝነት አለም የበአሉ ታዳሚ እየሆነ ነው።የውጭ ሃገራት የከተማ አስተዳደር የባህል ክፍል ኃላፊዎች በከተማቸው ከሚከበሩት በአላት ዝርዝር ውስጥ እያስገቡ አስፈላጊውን የማስተናበር አገልግሎት መስጠት የተለመደ ነው።የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ከዘመን ዘመን በተለያየ ጊዜ ቢሆንም ሽፋን ይሰጡታል።ሆኖም ግን በአለም አቀፍ ደረጃ በአሉ በአግባቡ እንዲታወቅ እና በበቂ ሁኔታ አለም አቀፍ ሽፋን እንዲያገኝ ብዙ የሚሰሩ ስራዎች ይቀራሉ።በእርግጥ በአሉ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣የትምህርት እና የባህል ኮሚሽን ''በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት'' መመዝገቡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአለም ጠብቃ ቅርስ የማቆየቷ አንዱ ማስረጃ ነው።

በዘንድሮ የመስቀል ደመራ በአል ላይ ለመገኘት በሀገር ቤት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ አቡነ ቴዎድሮስ ካልዕ ወደ ሀገር ቤት እንደሚያመሩ ከአዲስ አበባ ተሰምቷል።የግብፅ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ነው።የእዚህ አይነቱ ጉብኝት ከፕሮቶኮል  እና በቀለማት ካሸበረቀ የአደባባይ በአል አከባበር ባለፈ በከፍተኛ የአስተዳደር ችግር ላይ የምትገኘውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀና አባቶች እና ምእመናን  በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር እና የገንዘብ አያያዝ እና ቁጥጥር ዘዴዎች መንፈሳዊ ቅናት እንደሚያድርባቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እስከ ባለስልጣናት እና ዋልጌ ነጋዴዎች ድረስ በተዘረጋ የሙስና መዋቅር ውስጥ ተዘፍቃ በከፍተኛ ችግር ላይ እንደምትገኝ የአደባባይ ምስጢር ነው።በቅርቡ ሀገር አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ህብረት ግልፅ፣ሰላማዊ እና ቁርጥ አላማ የያዘ ጥያቄ በማንሳት  በሙሰኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ እና የቤተ ክርስቲያኒቱ  የማይገሰስ መንፈሳዊም ሆነ ሞራላዊ ልዕልና እንዲጠበቅ መጠየቁ ይታወቃል።ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴው ከቤተ ክርስቲያን አባቶች አልፎ የመንግስት አካላትን በየደረጃው በጉዳዩ ላይ ተነጋግሯል።ይህ ጉዳይ ያስጨነቃቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አባቶችም የችግሩን ቅርንጫፎች በየንግግራቸው መሃል ለማንሳት ተገደዋል።ሆኖም ግን ችግሩን ለመፍታት የቆረጠ እርምጃ ሲወስዱ አልተስተዋሉም።

የመስቀል ደመራ በአል ከሀገር ውስጥ አልፎ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በአንድ አደባባይ የሚያገናኝ፣ሕፃናትን እና ወጣቶችን ትንሿን ኢትዮጵያ የሚያሳያቸው እና እንዲናፍቁ የሚያደርጋቸው አንዱ አጋጣሚ ነው እና ልንንከባከበው ይገባል።ሀገር በወታደር፣በፖለቲካ እና በገንዘብ ብዛት ብቻ አንድ ሆኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ አይሸጋገርም።እንደዛ ቢሆን ኖሮ በሀብት እና በጦር ኃይል የተነከሩ ሀገሮች በየዘመኑ እየተሰባበሩ ታሪካቸው አመድ አይሆንም ነበር።ሀገር በማኅበራዊ እሴቶቿ፣ሕዝብ ዋጋ በሚሰጣቸው የሃይማኖት ስርዓት ሁሉ አንድነቷ ሳይናጋ ትውልድ ተሻጋሪ ትሆናለች።በመሆኑም የመስቀል ደመራ የመሰሉ ብሔራዊ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ  
መገለጫቸው ጉልህ የሆኑ በአላት ፋይዳቸው ብዙ ነው።

ከእዚህ በታች የመስቀል ደመራ በአል ለምን ይከበራል? እውነተኛው የክርስቶስ መስቀል ወደሀገራችን እንዴት፣መቼ እና በማን መጣ? የሚሉትን እና በአሉ በዩኔስኮ  ( UNESCO) የተመዘገበበት ዘገባ የያዙ ማስፈንጠርያዎች (link) ከእዚህ በታች ማግኘት ይችላሉ።

ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
መስከረም 10/2008 ዓም (ሴፕቴምበር 21/2015)

No comments:

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)