ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Wednesday, September 2, 2015

የአሸንዳ እና ቡሄ ወግ (የጉዳያችን ጡመራ ማስታወሻ)



አሸንዳ =     ''ቡሄ እንዴት ሰነበትክ?''

ቡሄ =        ''አለሁ የዋህ ምን ይሆናል።ለሺህ አመታት ሰው አክባሪዎቹ ታዳጊ ሕፃናት
                  ነሐሴ በገባ በአስራ ሶስት 'ሆያ ሆዬ ሆ!' እያሉ ያከብሩኛል።እንዳንተ በኢቲቪ
                 ባይነገርልኝም። እንዴው አሸንዳ አንድ ጥይቄ ልጠይቅህ?''

አሸንዳ =   ''ምንድነው ጠይቀኝ ጠይቀኝ''

ቡሄ =       ''እኔ ለስንት እና ስንት አመታት ከገጠር እስከ ከተማ የታወቅሁኝ ሆኘ ሳለ፣ከደቡብ እስከ ሰሜን
                ያለ ሕዝብ የምዝፍንልኝ በየበሩ ላይ ችቦ እያበሩልኝ ሳለ አንድ ቀን በቴሌቭዥን በዜናነት ቀርቤ ሳላውቅ፣
                ቤተ መንግስት ከገባሁማ ከ40 ዓመት በላይ ሆነኝ።አንተ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉ አንተን ለማክበር
               ቀድመው ነው አሉ የሚገኙት።ዛሬ ኢቲቪ ላይ ደግሞ ከመጀመርያ ዜናዎች ውስጥ ሆነህ ይብሱን አንዷ
               ለኢቲቪ ዛሬ ነሐሴ 27/2007 ዓም ቀርባ 'አሸንዳ ማክበር የዲሞክራሲያዊ ሂደቱ አካል ነው' ስትል ሰማሁ።
               እስኪ ምስጢሩን ንገረኝ።ስለ እኔ አንድ ቀን ያላወራው ኢቲቪን እና ቤተ መንግስቱን እንዴት እንዲህ          ዋኘህበት? በሞቴ ንገረኝ? እ?''

አሸንዳ = ጉሮሮውን ጠራረገ እና '' አንድ የተረሳ አለ ማለቴ አንተ ቤተ መንግስት እና ኢቲቪ ትላለህ በመጪው   እሁድ በሚሊንየም አዳራሽ እንደሚከበር ኢቲቪ በዛሬው ነሐሴ 27/2007 ዓም  ዜና እንዲህ ማለቱን አልሰማህም?  ''በመጪው እሁድ የአሸንዳ ባህል በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች እና የባህሉ አድናቂዎች  በከፍተኛ ሁኔታ ያከብሩታል።በዓሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የትግራይ ቱሪዝም ቢሮ ጥረት እያደረገ ነው'' ምን ነበር የጠየከኝ? እ እ እ? ያንተን ጥያቄ ተወው እና ለምን ወዳጄ ቡሄ እሁድ አሸንዳ ላይ አትገኝም?''

ቡሄ   =   ፈገግ አለ እና ''ምን ችግር አለው እገኛለሁ።በእኔ እና በአንተ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? እኔ     ለዘመናት የኖርኩ ነኝ፣ኢትዮጵያ ምድር ላይ ባብዛኛው እታወቃለሁ፣ጎሳ እና ቋንቋ አልለይም፣ሆያ ሆዬ በትግርኛ፣በኦሮምኛ፣በሃድያኛ፣በጉራጊኛ በሁሉም እዘፈናለሁ ሀገር  አስተሳስራለሁ።ነገር ግን አንተ በኢቲቪ ትታያለህ፣ጠቅላይ ሚንስትሩ ላንተ በአል ሀገር አቋርጠው ተሰባብረውም ቢሆን ይገኛሉ።

አሸንዳ = ''ምናልባት አንተ ሁሉንም ስለምታቅፍ ይሆን ያራቁህ? ማለቴ ወደ ሆነ ክልል ጠጋ ብትል ማለቴ እ እ ''

ቡሄ   = ''ገባኝ ገባኝ ተወው ባንተ አልፈርድም።አንተማ እኔንም ታከብራለህ እኔም ያንተን አከብራለሁ ችግሩ እኔን ዝቅ አድርገው እንዲያ በኢቲቪ በር ላይ ሆያ ሆዬ ሲል እየሰሙ እንዳልሰሙ ዝም ሲሉኝ ማየቴ ነው የሚያሳዝነኝ ፣ደግሞስ ጋዜጠኞቹ ቴሌቭዥን ጣብያው ህንፃ ማዶ ያለው አምባሳደር ኬክ ቤት በር ላይ ጫማ ሲያስጠርጉ ስንት ቀን በሚያማምሩ ልጆች አንደበት የዘፈንኩላቸው? ሆያ ሆዬ እያልኩ ጉሮሮዬ እስኪነቃ እንዳልጮኩ፣ቤተ መንግስትስ ቢሆን ከግንቡ አናት ላይ ሆኖ ከሚጠብቀው ጠባቂ እስከ  በገብርኤል በር በኩል ለቆመው ወታደር ሁሉ ስንቴ ዘፍኘለት በደስታ ሳንቲም እንዳልወረወሩልኝ እ እ! እኔን ካንተ ማሳነስ ነበረባቸው ምናለበት አንዲት ቀን ኢቲቪ የቡሄ በዓል በመላዋ ኢትዮጵያ ተከበረ'ብሎ ቢናገር?'' ቡሄ በደረሰበት አድልዎ ማዘኑ እንዳይታይ ወደ መሬት አቀረቀረ እና ''ለማንኛውም አንድ ስጋት አለኝ'' አለ።

አሸንዳ  = ደነገጠ ''ምን? ምንድነው ስጋትህ?''

ቡሄ መለሰ = ''አይ የትግራይ ቱሪዝም ቢሮ በዩኔስኮ  አንተን ሊያስመዘግብ ጥረት እያደረገ መሆኑን ዛሬ በኢቲቪ ተናግሯል።እንደምታውቀው ዩኔስኮ በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የሚመዘግበው የእራሱን መስፈርት አለው።ቅርሱ ለሰው ልጅ ቅርስ መሆን አለበት።እኔ ባቅሜ ቡሄ ዝም ብሎ ማንም 'ግንድ እግር ' እንዲጨፍር አልፈቅድም በፍፁም! ከልጆችም ቀጠን ቀጠን ያሉ፣ ተናካሽ ውሻ ቢመጣ ሮጠው የሚያመልጡ፣ድምፁ  መረዋ የሆነውን በሆያ ሆዬ አውራጅነት፣ጎርነን ያለው ሆ! ብቻ እንዲል እያደረኩ ነው የማስጨፍረው።እናም አይደለም ዩኔስኮ እኔም ባቅሜ ስርዓት አለኝ ለማለት ፈልጌ ነው።በነገርህ ላይ ዩኔስኮ ቢመዘግብህ እኔ ደስታውን አልችለውም።ግን የዓለም ቅርስነት ቀርቶ እንደ ቡሄ በሀገር ውስጥም ታውቀሃል ወይ? ብሎ ምርመራ ውስጥ ከገባ እና ነገሩን በጣም ከመረመረው እኔን ዘመን ጠገቡን  ልመዝግብ ብሎ እንዳይመጣ  ብዬ ከፍተኛ ስጋት ላይ ነኝ''

አሸንዳ  = ''ዋይ! ለእሱስ አታስብ ቱሪዝም ውስጥ ቁልፍ ቁልፍ ሰው አለን'' አለና አሸንዳ ፈገግ አለ።ግን ነገሩን ሳስበው  ይገርመኛል።ሰው ከሰው ሀገር ከሀገር የሚለያየው ስርዓት በዓል ከበአል እየለየ ለዘመናት አብረን የኖርነውን እኔና አንተን? እ? በእኔ እና በአንተ ይምጡ? አሸንዳ እና ቡሄ ተቃቅፈው ተላቀሱ።
''ኢቲቪ ቀጠለ የአሸንዳ በዓል ለዲሞክራሲ አስተዋፆ ያደርጋል'' አሸንዳ ኢቲቪን ቀና ብሎ አየና ''እኔና ዲሞክራሲ የሚያገናኘንን መንገድ የሚነግረኝ ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ በሞቴ'' አለ።

/////////======//////////=======/////////===========//////////=========



ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ነሐሴ 27/2007 ዓም  (ሴፕቴምበር 2/2015)

No comments:

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።