ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, July 27, 2015

ፕሬዝዳንት ኦባማ በኢትዮጵያ የሰፈነው ስርዓት ከጠበቁት በላይ አስደንግጧቸዋል።አቶ ሃይለማርያም የኢትዮ-አሜሪካንን የእረጅም ጊዜ ግንኙነት ለገዢው ፓርቲያቸው ፖለቲካ ሲሉ ለማደብዘዝ ሞከሩ።(የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ)

ፕሬዝዳንት ኦባማ አዲስ አበባ ሲገቡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለማየት ሲጋፉ 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየመራት ያለው ስርዓት ዲፕሎማሲ፣ፕሮቶኮል፣አቀራረብ፣አቅም እና የውጭ ተሞክሮ ያነሰው፣ ብቻ ሳይሆን ''አያውቁብኝም'' ባይ እና አይን ያወጣ ውሸት በመዋሸት አለምን ያታለለ የሚመስለው መንግስት መሆኑን በእያንዳንዱ የኦባማ ጉብኝት ሂደት መረዳት ትችላላችሁ።

ፕሬዝዳንቱ (አቶ ኦባማ ማለቴ ነው) የእውቀት እና በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ላይ የመረጃ ክፍተት አለባቸው ብዬ አላምንም።ጉዳዩ የጥቅም ጉዳይ ስለሆነባቸው ደግሞም ለሀገራቸው መስራት የሚገባቸውሥራ ስላለ እንጂ።በኢትዮጵያ ያለው የአምባገነንነት እና ሕዝቡን ያገለለ ስርዓት ከጠበቁት በላይ የከፋ መሆኑን ማወቃቸው እና መደንገጣቸውን ለማወቅ ከፈለጋችሁ ዛሬ ከአቶ ሃይለማርያም ጋር የሰጡትን መግለጫ መመልከት ብቻ በቂ ነው።ፕሬዝዳንቱ ከእዚህ በፊት በቀልድ እና በልበ ሙሉነት የሚያሳዩት የመግለጫ አሰጣጥ መንገድ ሁሉ አቶ ኃይለ ማርያም ጎን ቆመው ማምጣት አለመቻላቸው ቀድመው ከነበራቸው ግንዛቤ በላይ ኢትዮጵያ በጣም አደገኛ በሆነ አምባገነን ስርዓት ስር መሆኗ እና መጪው ጊዜም አሳሳቢ መሆኑን እንደገባቸው በግልፅ ይነበብባቸዋል።

በሁኔታው አስከፊነት ተበሳጭተዋል።ይህንን ብስጭታቸውን ለአቶ ሃይለማርያም አጥብቀው መንገራቸውን ለመግለፅ ደግሞ ''ከአቶ ሃይለማርያም ጋር በጥብቅ ተነጋግረናል'' የሚለውን ቃላት በመጠቀም ብቻ ሊያልፉት ሲሞክሩ ተስተውሏል።ኦባማን እያስተናገደ ያለው የኢህአዴግ/ህወሓት ቡድን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋለጠበት ወቅት ላይ ነው።እንዴት? ከነገ የኦባማ የአፍሪካ ህብረት ንግግር በኃላ እንመለሳለን።በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የፕሬዝዳንቱን እና የአቶ ኃይለማርያምን መግለጫ ምሽት ላይ ለሕዝቡ ሳይተረጉም እንዳለ እንግሊዝኛውን ብቻ አቅርቦታል።ይህም ፕሬዝዳንቱ ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚዎችን በዲሞክራሲ ሂደቱ ላይ አሳታፊ ማድረግ የገዢ ፓርቲውን ነው የሚጠቅመው  የሚለው ንግግር እና ሌሎች የኢትዮያ ሕዝብ እንዲሰማቸው የማይፈለጉትን እንደለመዱት ለመቆራረጥ ጊዜ አላገኙም።ንግግሩን ለነገ እንዳያስተላልፉት እና ነገ ቆራርጠው እና ቀጥለው እንዳያቀርቡት ደግሞ ትዝብት ፈሩ።ስለሆነም የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አስር ሚልዮን የሚሆን ጥሩ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ለሌላት ሀገር እንዳለ አቀረበው።

እዚህ ላይ ኦባማ ''ኢህአዴግን በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግስት'' የምትል ቃል መጠቀማቸው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን የሚያስደነግጥ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ከስድብ ያነሰ ንግግር አይደለም።ጉዳዩ ግን የአፍ ወለምታ መሆኑን መረዳት እና ጉዳዩ የቆሸሸ እና የሞራል ልዕልና የራቀው አቀራረብ ለመሆኑ ምንም ማስረጃ መደርደር አይገባውም።ፕሬዝዳንቱ እራሳቸው ጉዳዩን የሚያስተባብሉት ዋሽግተን ሲደርሱ ለመሆኑ ከሰሞኑ የምናየው ነው።የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል የፕሬዝዳንቱን ይህንን ቅጥፈት የትሞላበት ንግግር በመቃወም ለፕሬዝዳንቱ ክብር በቤተ መንግስት በሚደረገው የእራት ግብዣ ላይ እንደማይገኙ አስታውቀዋል።የሰማያዊ ፓርቲ እርምጃ ሚልዮን ኢትዮጵያውያንን ያስደሰተ እና ታሪካዊም ነው።

ኢህአዴግ/ወያኔ በኩል አሁን ለሚድያ ግልፅ ሆነው እየታዩ ያሉት ሁኔታዎች ግን የኢትዮጵያና የአሜሪካንን ዲፕሎማሲ ማጠናከር ላይ ያተኮረ የአንድ ጤነኛ መንግስት ሥራ አይደለም።በእዚህ አይነቱ ተግባር ላይ ኢህአዴግ/ህወሓት እንዳልጠተመደ ለማወቅ የዛሬውን የአቶ ሃይለማርያም ቃል ብቻ መጥቀሱ ይበቃል።

አቶ ኃይለማርያም ዛሬ ከፕሬዝዳንት ኦባማ ጋር በሰጡት መግለጫ 'ከአሜሪካን  ጋር የኢኮኖሚ ትብብር የተጀመረው በቅርቡ ነው''ሲሉ ተደምጠዋል።አንድ ጤነኛ መንግስት ያለው ሀገር መሪ የዲፕሎማሲ ግንኙነቱን ለማጠናከር ትንሹን ግንኙነት አጉልቶ እና አጠንክሮ ማቅረብ አንዱ ተልኮውና ያልታመመ አቀራረብ ነው።አቶ ሃይለማርያም ግን በአለቆቻቸው ልክ በተሰፋ የተሳሳተ ''የዲፕሎማሲ ጥብቆ'' ውስጥ ስለሆኑ እና ሁሉን ነገር ኢህአዴግ/ህወሓት ጀመረው ለማለት ከመፈለጋቸው የተነሳ ''ከአሜሪካን  ጋር የኢኮኖሚ ትብብር የተጀመረው በቅርቡ ነው'' ሲሉ ተደመጡ ያውም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፊት።

ይሁን  እንጂ አሜሪካኖች በኢትዮጵያ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ ከጀመሩ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ያስቆጠረ ለመሆኑ ጥቂት መረጃዎችን ማገላበጥ ብቻ  በቂ ነው።በዘመነ ደርግ ሂደቱ ቢቆምም።ሌላው አቶ ሃይለማርያም ለዲፕሎማሲ ማጉያ ከ115 ዓመታት በላይ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ የግንኙነታችንን ረጅም ታሪክ ማንሳት ሲገባቸው ጉዳዩን በጨረፍታ አልፈውት መድረኩን የጃጀ ኢህአዴጋዊ አስተሳሰብ ሊያንፀባረቁበት ፈለጉ።ግንኙነቱ የተጀመረው አሁን ይመስል 'ከአሜሪካን  ጋር የኢኮኖሚ ትብብር የተጀመረው በቅርቡ ነው'' ብለው ሊያሞኙን ሞከሩ።

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩበትን 100ኛ ዓመት ያከበሩት በ2003 ዓም እንደፈረንጆች አቆጣጠር ሲሆን አሁን 112 ዓመታትን አስቆጥረዋል።በእንዲህ አይነቱ መድረክ ላይ አንድ ሀገር እመራለሁ የሚል መንግስት ንግግሩን የሚጀምረው ከመቶ ዓመት በላይ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት እንዳለን በመግለፅ እና ይህንን በማጉላት መሆን ሲገባው ይህንን ማንሳት ለኢህአዴጋውያን አፄ ምንሊክን፣ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን ያስታውስባቸዋል እና የእረጅም ጊዜ ግንኙነታችንን በማውሳት ዲፕሎማሲውን ከማጠናከር ይልቅ አቶ ሃይለማርያም ባላዋቂ አቀራረብ ግንኙነቱን ''አጋድመው አረዱት'' እና ''ከመጣችሁ አጭር ጊዜ ነው'' አሏቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ፣የአለማያ ዩንቨርሲቲ ምስረታ ሂደት ላይ አሜሪካኖችበንጉሡ ዘመን የእራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።አሁንም እነኝህን አንስቶ መናገር ኢህአዴግ/ወያኔ ''ኢትዮጵያን ዛሬ ፈጠርኩ'' የሚለውን የበሰበሰ አስተሳሰብ ስለሚነካበት ሲያስበው ይደናገጣል።በመሆኑም አቶ ሃይለማርያም ሳያነሱት ቀሩ ወይንም እንዳያነሱ ማስጠንቀቅያ ተሰጣቸው።ይህ ባይሆን ኖሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያለ ማንም ባለሙያ አፅኖት ተሰጥቶት እንዲነሳ ሃሳብ የሚሰጠው ከእነኝህ ነጥቦች እንደሚሆን ማሰብ ከባድ አይደለም።እርግጥ ነው ይህ በካድሬ እና በጎጥ የምትመራ ሃገርን አይመለከትም።

በፕሬዝዳንት ኦባማ የአንድ ቀን ቆይታ፣የፕሮቶኮሉን መዘባረቅ እና ከአየር መንገድ ጀምሮ የባለስልጣናቱ በአግባቡ ተሰልፎ ፕሬዝዳንቱን ከመጠበቅ ይልቅ አሰላፊ እንደሚፈልጉ ሕፃናት አቶ ኦባማን ለማየት ሲንጠራሩ ስመለከት  የኢህአዴግ/ህወሓት ባለስልጣናት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ማነስ፣በራስ የመተማመን የሞራል ልዕልናቸው ሁሉ  መውረዱ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።ስነ-ስርዓት የሚባል ነገር የለም እንዴ?

የኬንያው ፕሬዝዳንት ''እኛ ኬንያውያን ከአሜሪካ የማንጋራቸው ባህላዊ እሴቶች አሉ ለምሳሌ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ'' ያሉበትን ንግግር በተመለከትንበት ማግስት፣ በእራሱ የአፍሪካ ድምፅ መሆን የሚገባት ኢትዮጵያ አሁን ባሉት መሪዎቿ ከደረጃ በታች በሆነ አቀራረብ ተወክላ ማየት ሌላው አሳዛኝ ክስተት ነው።በኬንያ እና በኢህአዴግ/ህወሓት መካከል የተስተዋለው የልዩነት መጠን ለመግለፅ ቀላል ምሳሌ ሆኖ የታየኝ  የእግር ኳስ ቡድን ነው።በሰሞኑ የአቶ ኦባማ መስተንግዶ ኢህአዴግ/ወያኔ አንድ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የሌለው የእግር ኳስ ቡድንን ያህል ሲርበተበት፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት አቀራረብ እና በእራስ መተማመንን ስመለከት የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያለው  የእግር ኳስ ቡድንን ልዩነት ያህል ተለያይተውብኛል።

ኢትዮጵያ አዋቂዎቿን በሙሉ የገፋባት፣ያሰደደባት እና ያሰረባት ኢህአዴግ/ወያኔ እንደማይወክላት በተግባር የምታሳይበት ቀን እሩቅ አይሆንም።ኦባማ ግን ኢትዮጵያን ትተው ሲሄዱ ጥሩ ነገር እየሸተታቸው እንደማይሆን መረዳት ይቻላል።ፕሬዝዳንቱ ቀድሞ ከነበራቸው መረጃ በላይ በጉብኝታቸው ወቅት ካሰቡት በላይ ሀገራችን አስከፊ ደረጃ ላይ መሆኗን  ይረዳሉ።ለነገሩ የእርሳቸው መረዳትም ሆነ አለመረዳት ፋይዳው ለሀገራቸው ነው።ለኢትዮጵያ ወሳኙ እና እጣዋን የሚወስነው የእራሷ አንጡራ ህዝቧ ነው።ኢትዮጵያ ከዘረኝነት፣ፍትህ ማጣት እና ከፋፋይ ስርዓትን በሕዝብ ፍቃድ በተመሰረተ መንግስት ከመቀየር መለስ  ስለምንም ነገር መነጋገር የሚቻልበት ደረጃ ላይ አይደለችም።ነፃነት ከሁሉ በፊት ሊቀድም ይገባል።


ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ሐምሌ 21/2007 ዓም ( ጁላይ  28/2015)

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...