ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, July 28, 2015

የፕሬዝዳንት ኦባማ የሰሞኑ ጉብኝት ምን አስተምሮን አለፈ? (የጉዳያችን ማስታወሻ)

 ''እኛ ለራሳችን እንበቃለን፣እናንተን አንፈራችሁም፣በፈቀድነው ጊዜ ከኛ ቦታ (ጋራዎች) እንደ ድንጋይ እንንዳችለን'' እቴጌ ጣይቱ ከአድዋ ጦርነት አስቀድመው ለጣልያን መልክተኛ የተናገሩት  

''ጣይቱ ብጡል'' ከተሰኘው መፅሐፍ የተወሰደ 

 አሁን በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ሁኔታዎች በፍጥነት ከመለዋወታቸው አንፃር ትኩረት፣የቅድምያ ትንበያ እና ስልታዊ አሰራሮች በእጅጉ የሰፈኑበት ነው።የቀደሙት ትውልዶቻችን በዘመናቸው የገጠማቸውን ፈታኝ ሁኔታ ሁሉ በፅናት፣በቆራጥነት እና በብልሃት ተወጥተው አሁን ላለነው ትውልድ አስረክበውናል።ባለፉት ዘመናት የነበሩ የውስጥ የስልጣን ሹክቻዎች እና የባዕዳን ጣልቃ ገብነት በዘመኑ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ እና የእራሱን መልክ ይዞ ኢትዮጵያን ፈትኗታል።ሆኖም ግን በዘመኑ የነበረው ትውልድ እና የኢትዮጵያ መሪዎች ቅድምያ ለሀገራቸው፣ለእምነታቸው እና ለሞራላዊ ልዕልና የሚሰጡ ስለነበሩ የገጠሟቸውን ፈተናዎች በሙሉ ለማለፍ ችለዋል።

ሐምሌ 19/2007 ዓም እሁድ ምሽት የአሜሪካው  ፕሬዝዳንት ኦባማ ከኬንያ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት እና በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ንግግር ለማድረግ አዲስ አበባ ገቡ።የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ዋና ዋና አላማዎች ሶስት ናቸው።እነርሱም የመጀመርያው ኢትዮጵያ በሱማልያ ሰራዊቷን ለተጨማሪ አመታት እንድታዘምት እና በአንፃሩ አሜሪካ የገንዘብ፣ቁሳቁስ እና የጦር መሳርያ እርዳታ እንደምታደርግ ለማግባባት፣ሁለተኛው እየገፋ የመጣውን የቻይና የአፍሪካን መቆጣጠር ለመግታት እና ሶስተኛው የአሜሪካ ''አሻንጉሊት'' መንግስት ናቸው ተብለው የሚታሙትን የህወሓት፣የኡጋንዳው እና የኬንያ መንግስታትን በተቻለ መጠን የማሻሻያ የጥገና ለውጥ በማድረግ በውስጣቸው ያለውን ውጥረት እንዲያረግቡ ለማግባባት የሚሉ ናቸው።

እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚኖርብን ቁም ነገር አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ከማንኛውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የምትገኝበት ወቅት ነው።የመጀመርያ የውጥረቷ ምንጭ በሀገር ውስጥ ያለው የማኅበራዊ እና የምጣኔ ሀብት አለመረጋጋት፣የሩስያ ምስጢራዊ አካሄድ በማናቸውም ጊዜ ግጭት በሚያስነሳ መልክ ተንጠልጥሎ መቆየቱ፣የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ (ግብፅን ጨምሮ) ያለው አለመረጋጋት እና ወዴት እንደሚያመራ በቀላሉ መተንበይ አለመቻሉ የሚሉት ይጠቀሳሉ።በእነኝህ ሁሉ ሁኔታዎች ነው እንግዲህ አቶ ኦባማ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የመጡት።''የተራበ ልጅ ምግብ አይመርጥም'' እንደሚባለው በእዚህ ጊዜ ለአሜሪካ ጥቅም የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ አጋር መፈለግን በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኃይል የአምባገነንነት ቀንበር የተጫነባቸው የአፍሪካ ህዝብን በደፈናው አግልሎ ከአምባገነኞቹ ጋር ብቻ ተነጋግሮ መምጣት የሚያስከፍለውን ዋጋ ያውቃሉ እና በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ስለ መልካም አስተዳደር፣ሙስና እና ዲሞክራሲ ንግግር ማድረግ አስፈላጊነት ተወሰነ።የእዚህ አይነቱ ''ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ ላይ የመውጣት''ሙከራ አሜሪካንን ዋጋ የሚያስከፍላት ጉዳይ እንደሆነ ማንም አይስተውም።ጥቅምን ፈልጎ በምሽት ከአምባገነኖች ጋር መደነስ፣ሲነጋ ደግሞ የዲሞክራሲ እጦት የሚያመጣውን ጉዳት ላይ ንግግር ማድረግ ለአሜሪካ የሚፈይደው ጉዳይ እንዳለ በጊዜ የምናየው ነው። 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት በፕሬዝዳንት ኦባማ ወይንም በሌላ የባዕድ ኃይል አይገኝም 

አሁን ያለንበትን ጊዜ ኢትዮጵያን የሚመሯትን መሪዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ የማናምንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።ሕዝብ ብዙ አይኖች አሉት።ይህ ክፉ እድልም ሆነ እጣ ነው።ስለአንዲት እና የተባበረች አሜሪካ የሚሰብኩን ኦባማ ኢትዮጵያ ላይ ስላለው የጎሳ ፖለቲካ አደጋ ለመንገር አልደፈሩም።ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያን በመከፋፈል አሜሪካ ሁል ጊዜ ተጠቃሚ ነች ብሎ ማሰብ በተለይ በእዚህ ጊዜ ትክክል ላይሆን ይችላል።የሱማልያ፣የደቡብ ሱዳን የኤርትራ ጉዳዮችን ለመዘወር ኢትዮጵያ አይነተኛ መሳርያ ሆና እንድታገለግል ይፈለጋል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እራሷን አጠናክራ በአካባቢያዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ አለምን የምትሞግት  ሆና እንድትወጣ አይፈለግም።የእዚህ አይነቱ የኢትዮጵያ ጥንካሬ ምናልባትም ኢትዮጵያ በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት እንዲወጡ የረዳችውን ያህል አሁን አፍሪካ ዙርያዋን ከከበባት የተፈጥሮ ሃብቷን ለመበዝበዝ ከቆሙ ከሩቅ ምስራቅ እስከ አሜሪካ ድረስ ካሰፈሰፉ ኃይሎች የማዳን ሚና እንዳትጫወት ይፈራል።ይህ የሚሆነው ደግሞ በቅድምያ እራሷን ማቆም ከቻለች ስለሆነ በተቻለ መጠን መንጥቃ እንዳትወጣ እንደ ወያኔ ያለ ከፋፋይ ኃይል ጋር መወዳጀቱ እንደ አንድ ስልት በባእዳን ዘንድ ተይዟል።

ይህ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነፃነት የሚደረገው ትግልን የሚገዳደሩት የሀገር ውስጥ ''ሆድ አደር'' እና ጎጠኞች ብቻ ሳይሆኑ ከስልታዊ ጥቅም አንፃር ኢትዮጵያ የተዳከመች ሆና እንድትኖር ማድረግ ቢያንስ ባለፉት 100 አመታት ውስጥ የታየ ጉዳይ ነው።በአስራ ዘጠነኛው ክ/ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ ያሉትን ሁኔታዎች ብናጤን ከጥቅማቸው አንፃር ባእዳን ኢትዮጵያን ማዳከም   እንደ አንድ ስልት ሲጠቀሙበት እንመለከታለን።ለእዚህም አብነት የሚሆኑን የአድዋ ጦርነት፣የ1928 ዓም ዳግመኛ የኢጣልያ ወረራ ላይ የዓለም መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ ማደም፣በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የተሰሩ የተለያዩ ደባዎች፣በ1967 ዓም የሱማልያ ወረራ ወቅት አሜሪካ ኢትዮጵያን ላለማስታጠቅ የወሰደችው እርምጃ፣አመታት የፈጁት የሰሜን ጦርነቶች በከፍተኛ ደረጃ በባእዳን ወጪ መካሄዱ እና አሁን በዘመናችን ደግሞ በጎሳ የተደራጀ መንግስትን በመደገፍ እና ኢትዮጵያን የመከፋፈል ተግባር ላይ በተዘዋዋሪ እጃቸውን የከተቱ መንግስታትን መጥቀስ ይቻላል። 

'አሜሪካናይዜሽን'' እና ''አይሮፓናይዜሽን'' ሆኖ የወጣ ትውልድ አፍርተናል

ከላይ የተጠቀሱት ታሪኮችን እና አሁን ያለውን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት ''በሰጥቶ መቀበል'' ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ካልሆነ በቀር ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጠንክራ እንዳትወጣ የሚኮረኩማት በብዛትም ሆነ በአይነት ለእድገቷ በጎነት ካላቸው በእጅጉ ይበልጣሉ።እዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ከጊዜ ጋር በተናበበ መልኩ ኢትዮጵያ በጥቅሟ ላይ የማይደራደር መንግስት በፍጥነት ካልኖራት በቀር እጅግ አደገኛ ሁኔታዎች መከሰታቸው አይቀርም።ለእዚህም አይነተኛው እና አንዱ ምክንያት በእዚህ ዘመን የሚኖር ትውልድ የቀደሙት አባቶቹ የአለምን ፖለቲካ ከሚረዱበት አቅም በእጅጉ ያነሰ እና የጀርባ ድርጊቶችን የመተንተንም ሆነ የማወቅ ችሎታው ያነሰ መሆኑ ነው።ለእዚህም ዋነኛ መክንያቶቹ ባዕዳውያን ለእረጅም ጊዜ በአዲሱ ትውልድ ላይ የሰሩት ተከታታይ ግን ደግሞ  የጠለቀ የስነ-ልቦና ዘመቻ  ነው።በእዚህ የስነ-ልቦና ዘመቻ ሳበያ በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኝ ምህር እስከ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል ድረስ የተጠቃ ስለሆነ በሀገሩ የአምባ ገነኖችን ታግሎ ነፃነቱን ከመቀዳጀት ይልቅ ምዕራባውያንን እያሞገሰ በትምህርት ክህሎቱ ''አሜሪካናይዜሽን'' እና ''አይሮፓናይዜሽን'' ሆኖ የወጣ ትውልድ አፍርተናል።የእዚህ አይነቱ ትውልድ መገለጫዎች እና የሚያመጣው ጉዳት እንዲሁም የችግሩ መፍትሄ በተመለከተ በእዚህ አጭር ፅሁፍ ለመዘርዘር አይቻልም።ውጤቱን ግን ስንመዝነው ግለኝነት፣እራስን ብቻ የማየት ሃገርን እና ህዝብን የመመልከት እንዲሁም ኃላፊነትን የመረዳት ችግር አንዱ እና አይነተኛው የውጤቱ መገለጫ ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል እና ለመጪው ትውልድ ጎሰኘነት እና ድህነትን ላለማውረስ ኢትዮጵያዊነትን አስቀድሞ ለነፃነት ከመነሳት ባነሰ አንድም አማራጭ የለም።ኢትዮጵያ እንድትሆን የምንፈልገውን ለማግኘት በመፃፍ፣ጋዜጣ በማተም፣ለፍትሃዊ ምርጫ በመታገል የሚፈለገው ውጤትን ማግኘት አልተቻለም።ለእዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ  ፍፁም የሆነ የጎጥ ስርዓት መሰረታዊ ባህሪ ምክንያት እና የባዕዳን በገንዘብ፣በምክር እና በሎጀስቲክ ሁሉ ከፍተኛ ድጋፍ ስለሚያገኝ ነው።በእዚህ ሁሉ ውስብስብ ዓለም ውስጥ ከእኛ በላይ ለእኛ ማን ሊቆም ይችላል? 

ለኢትዮጵያ ከኢትዮጵያውያን በላይ ማንም ሊቆም አይችልም 

የኢትዮጵያ ጉዳይን ባዕዳን አደባባይ፣ዋይት ሃውስ በር ላይ፣ወዘተ የተጮሁት የነፃነት ድምፆች እና አምባገነኑን የኢህአዴግ/ወያኔ መንግስት አትደግፉ የሚሉት አቤቱታዎች ሁሉ ባእዳኑ ለኢትዮጵያ እና ለህሊናቸው ተገዝተው እንዲመለሱ ሳይሆን ያደረጋቸው  ለጥቅማቸው የበለጠ የሀገራችንን አንድነት እና ህልውና ሊያናጋ በሚችል መልክ የበለጠ ከፋፋይ የጎሳ የፖለቲካ መርዝ ከሚረጨው ስርዓት ጋር ሲተባበሩ ተስተውለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የነፃነት ትግል በአዲስ አቅጣጫ እና አካሄድ መሄድ ያለበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።በአሁኑ ወቅት ለነፃነት ትግል ህዝብን በመምራት ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ኃይሎችን በአቅም፣በገንዘብ እና በእውቀት መርዳት ብሎም  በቀጥታ እገዛ ማድረግ አንገብጋቢው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ጥሪ ነው።ይንንም ለመከወን የሚከተሉት ነጥቦች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። እነርሱም - 
  1. እኛነታችንን በኢትዮጵያዊነት ቅኝት በአግባቡ መቃኘት።ይህ ማለት ያለፈ ማንነታችንን እና ክብራችንን እንዲሁም  የመከባበር እና የመተሳሰብ ባህላችንን ማስፈን፣
  2. ኢትዮጵያን መልሶ ከማቆም እና ያለፉ የታሪክ ስህተቶችን በማይደግም መልኩ የነፃነት ትግሉን መቀየስ፣
  3. ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጣ የባእዳንን ፍላጎት ማጋለጥ እና መታገል።ይህ ማለት ከየትኛውም የባዕዳን ኃይሎች የነፃነት ትግሉን በሚደግፍ መልኩ የሚሰጡ ድጋፎችን መግፋት ይገባል ማለት አይደለም።
  4. የማንንም የባዕድ ኃይል ተፅኖ የሚገዳደር አቅም በእራስ መፍጠር፣
  5. ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን አደገኛ ሁኔታ ላልተረዳው ወገን በሙሉ በሚገባ ማስገንዘብ፣ማስረዳት እና ወደ ሥራ እንዲገባ ማገዝ፣
  6. አንድ ሰው አሁን ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ብዙ የመስራት አቅም እንዳለው ማስገንዘብ እና በውጭ ሃገራት ሁሉ  ተፅኖ ፈጣሪ ማህበረሰብ እንዲኖር መስራት እና 
  7. በሀገር ጉዳይ ማንም ዝም እንዳይል ማድረግ፣ማብቃት እና ቸልተኘንትን በህብረተሰቡ ውስጥ ለመዝራት የሚፈልጉትን ማረም፣መምከር እና ወደ እውነታው ኢትዮጵያን መልሶ ለማቆም ለሚደረገው የነፃነት ትግል እንዲቆሙ ማብቃት  የሚሉት ናቸው።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያን በሚስጥር የሚሸጥ መንግስት ስልጣን ላይ እስከቆየ ድረስ የእኛነታችን አሻራ መጥፋቱ የማይቀር ብቻ ሳይሆን ለከፋ ባርነት የአሁኑን ብቻ ሳይሆን መጪውንም መዳረግ የእረጅም ጊዜ ክስተት አይሆንም።ዛሬ በዓይናችን የምናየውን የቅጥፈት ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ነው ያሉን ባእዳን፣እየራበን አደጋችሁ እያሉ የተሳለቁብን ''መሪዎቻችን''፣እያሰሩን አንድም ያሰርነው የለም እያሉ ያላገጡብን እና በባእዳን ያስላገጡብን፣እህቶቻንን  በእየአረብ ሃገራቱ ሲሸጡ ያሻሻጡ የአራት ኪሎ ቅምጥሎች ኢትዮጵያን ደብዛዋን ለማጥፋት ከባእዳን ጋር ሌት ተቀን እየደከሙ ለመሆናቸው ከባሕርያቸው፣እየሰሩ ካሉት ሀገር የማፍረስ ሥራ እና የባእዳኑ በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ገብተው የመፈትፈት ተግባር ሁሉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።ከኢትዮጵያውያን በላይ ለኢትዮጵያ የሚመጣ ወትሮም አልነበረም ወደፊትም አይኖርም።ከነፃነት መለስ ምንም የመነጋገርያ ቦታ ሊኖረን አይገባም።የሰሞኑ የፕሬዝዳንት ኦባማ ጉብኝትም ያመላከተን አንድ እና አንድ ነገር ብቻ ነው።ይሄውም የነፃነት ትግሉን ከመደገፍ በላይ ምንም አማራጭ የለም።


                ሐምሌ 22/2007 ዓም (ጁላይ 29/2015)

No comments:

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...