ኢትዮጵያ የገባችበት ብድር ከፍተኛ ቢሆንም የመሰረታዊ ፍላጎቶችን በዋና ከተማ ደረጃም ማዳረስ አልቻለችም በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር የት ገባ?
==================================================================
የብድር ጉዳይ አዲሱ የዓለማችን ሃገራትን የማንበርከክያ መሳርያ እየሆነ ነው።በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሀገራት ብድር በሁለት ጎራ በተከፈሉ ኃይሎች መካከል በነበረ ፍትግያ ሳብያ የማምለጫውም ሆነ ፋታ ለማግኘት የመደራደር አቅም ነበረ።አሁን ባለንበት ዓለም ግን የእዚህ አይነቱ ዕድል አይታይም።ለእዚህም አይነተኛ ምሳሌ የምትሆነው ግሪክ ነች።የግሪክ የብድር ቀውስ የምጣኔ ሀብቷን ከማድቀቁም በላይ የሀገሪቱን የውስጥ ፀጥታ ያናጋ እና በቅርቡ በሕዝብ በተመረጠውን መንግስቷ እና በሕዝቡ መካከል መተማመንን ያጠፋ አሁንም ይሄው የብድር ቀውስ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በኢህአዴግ/ወያኔ የ24 ዓመታት የስልጣን ዘመን ሀገሪቱ በታሪክ አይታ የማታውቀው ዕዳ ውስጥ ተዘፍቃለች።ብድሩ ለልማ ሥራ ውሎ ቢሆን ጥሩ ነበር።ሆኖም ግን የዓለም የገንዘብ ድርጅቶችም ሆኑ የእራሱ የመንግስት ኦዲተር ሪፖርት የሚያሳየን አንድ ነገር ነው።ይሄውም አብዛግኛው በአሁኑ ትውልድ እና በመጪው ትውልድ ስም የሚፈፀመው ብድር በጥቂት ባለስልጣናት እና ሙሰኛ አጋሮቻቸው ወደውጭ ሃገራት መወሰዱ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑ ነው።''ግሎባል ፋይናንስ ኢንተግሪቲ'' ባለፈው ዓመት ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ በአስር ዓመታት ውስጥ ብቻ በሕገ ወጥ መንገድ 16.5 ቢልዮን ዶላር በተለያየ መንገድ መውጣቱን በምሬት ገልጧል።ሀገር በእድገት መንገድ ላይ ነው የሚባለው አብዛኛውን የልማት ሀብት በሀገር ውስጥ አፍርቶ ቀሪውን በብድር ወስዶ የልማት ፕሮጀክት ሲሰራ ነው እንጂ እስከ 65 በመቶ የሚሆን የሀገሪቱን ሀብት በብድር ላይ ጥሎ በብድር የተገኘውንም ገንዘብ ለጥቂት ቅምጥል ባለስልጣኖች እና አጋሮቻቸውም ኪስ ማድለብያ እያደርጉ ሀገሪቱን ወደ ባሰ ድህነት መክተት ከወንጀል ተጠያቂነት አያድንም።ባለፉት 5 ዓመታት የትራንስፎርሜሽን እቅዱን እየሰራን ነው ያለው ስርዓቱ ሚያዝያ 2/2006 ዓም የ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ባቀረበው የአምስት ዓመት ትራንስፎርሜሽን ክንውን ላይ ከተባለው ግብ ኢትዮጵያ መድረስ አለመቻሏን አምኗል። የምክር ቤቱ ብቸኛ ተቃዋሚ አቶ ግርማ ''ቀድሞውንም ዕቅዱ በአግባቡ ያልታሰበበት ለመሆኑ አሁን ላለበት ውጤት መብቃቱ በራሱ ምስክር ነው'' ብለዋል።
ይህ ሁሉ ሆኖ ነው እንግዲህ ሀገራችን በብድር ላይ ብድር እየተወሰደ ዛሬ ከ14ቱ በብድር ብዛታቸው አደጋ ላይ ከወደቁ የዓለም ሃገራት ተርታ አሰለፋት።በነገራችን ላይ ''ደፋሮቹ'' የስርዓቱ አውራዎች አሁንም ለሌላ 5 ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ እያቀድን ነው ብለው መሰብሰባቸው ይታወቃል።ምናልባትም ነሐሴ መጨረሻ ላይ ለሕዝቡ ማባበያ ያቀርቡት ይሆናል።እውነታው ግን በአሁኑ ትውልድ እና በመጪው ትውልድ ስም ብድር ተበደሩ፣ግልፅነት እና ተጠያቂነት የሌላቸው የልማት ፕሮግራምቀረፅን አሉ፣መሰረታዊ መርሆዎችን ያልተከተሉ ፕሮጀክቶች አስተዋወቁ በፕሮጀክቶቹ ስም ገንዘብ ወደ ውጭ ሸሸ።በመጨረሻ ብድር የመመልስ አቅም የሌላት ብቻ ሳይሆን አሁን ላለው አስመጪ ነጋዴ የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ የማይችል ብሔራዊ ባንክ አስታቅፈው ቁጭ አሉ።
ፅሁፌን ከመደምደሜ በፊት ለእዚህ ፅሁፍ መንደርደርያ የሆነውን የ''ዘጋርድያን'' ዘገባ መሰረት አድርጎ የ''አዲስ አድማስ'' ጋዜጣ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 11/2007 ዓም ለንባብ ያቀረበው ዘገባ ከእዚህ በታች ይመልከቱት ዘንድ እጠይቃለሁ።
የውጭ ብድር እዳ ኢትዮጵያን ያሰጋታል ተባለ
አዲስ አድማስ
Saturday, 18 July 2015 10:55
• ስጋት ከተጋረጠባቸው 14 ሀገራት ውስጥ ተካታለች• ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ሞዛምቢክ በዕዳ ተዘፍቀዋል
የውጪ ብድር እዳ ኢኮኖሚያቸውን ሊፈታተን ይችላል የሚል ስጋት ከተጋረጠባቸው 14 የአለም አገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ዘ ጋርዲያን የአለም ባንክን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር እዳ እንዳለባት የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 45 በመቶ የሚሆነው ከብድር የተገኘ ገንዘብ እንደሆነ ጠቁሞ፤ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ይህ አኃዝ ወደ 65 በመቶ ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ ከለጋሽ ተቋማትና ሃገራት የሚገኝ ብድር ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለው አስተዋጽኦ ከ30 በመቶ በላይ ከሆነ ሀገራት ወደ ከፍተኛ የእዳ ቀውስ እያመሩ መሆኑን እንደሚያመለክት የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያም በዚህ የአደጋ ቀጠና በከፍተኛ ደረጃ ከገቡ 14 የአለም ሀገሮች መካከል ተጠቅሣለች። ከፍተኛ የውጭ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉት 14 ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡታን፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ዶሚኒካ፣ ጋና፣ ላኦስ፣ ሞሪታኒያ፣ ሞንጐሊያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሣሞኣ፣ ሣኦቶሜ ፕሪንቼቤ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል 24 የአለም ሀገሮች የውጭ እዳቸው በሚያሰጋ ደረጃ እየጨመረና ወደ አደጋው ቀጠናም እየተንደረደሩ ነው በሚል ተጠቅሰዋል፡፡
አንዳንድ በአስጊ ደረጃ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉ ሀገራት፣ የተበደሩትን ገንዘብ ለተገቢው አላማ መጠቀም አለመቻላቸው ለቀውስ እንደዳረጋቸው በሪፖርቱ የተጠቆመ ሲሆን በዚህ ረገድ ጋና ምሣሌነት ተጠቅሳለች፡፡ ሌሎችም አዋጭ የሆነ የብድር አመላለስ ስርአት ባለመከተላቸው የችግሩ ሠለባ እየሆኑ እንደመጡ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ እነዚህ ሀገራት ከዚህ እዳ የሚወጡበትን መንገድ ካላጤኑ ከፍተኛ ቀውስ ሊገጥማቸው ይችላል ብሏል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የግል ኩባንያዎችና መንግስታት አለም ባንክን ከመሳሰሉ አበዳሪ ተቋማት ከ2009 እ.ኤ.አ ጀምሮ በየአመቱ የሚበደሩት ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡ በ2013 እ.ኤ.አ የአለም ሀገራት አጠቃላይ የብድር መጠን 11.3 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን በ2014 13.8 እንዲሁም በዘንድሮው አመት 14.7 ትሪሊዮን ዶላር መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ዘገባ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ።ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG
ሐምሌ 11/2007 ዓም (ጁላይ 18/2015)
No comments:
Post a Comment