=========
ጉዳያችን ምጥን
=========
አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ በአፍሪካ ውስጥ በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ ከተነሱት የዓለማችን አምባገነኖች የሚመደቡ ብቻ ሳይሆኑ በእነኝህ ዓመታት የተነሱ አምባገነኖች የቀዝቃዛው ጦርነት ውጤቶች ስለሆኑ የተካኑበት ጉዳይ አንድ እና አንድ ነው።ይሄውም በ20ኛው ክ/ዘመን ያረጀው እና ያፈጀው ግጭት፣ሴራ፣እና ጦርነትን ብቻ አራግቦ ስልጣን ማቆየት ነው። አቶ ኢሳያስ የሊብያውን ሙሐመድ ጋዳፊ ከሚያደንቁ መሪ አንዱ ነበሩ። ጋዳፊ ከስልጣን ሲወገዱ ቀኝ እጃቸው የተቆረጠ ያህል በሃዘን መጎዳታቸውን የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
አቶ ኢሳያስ የ20ኛውን ክ/ዘመን የሴራ ፖለቲካ በ21ኛው ክ/ዘመን የዲጂታል እና የአርቴፍሻል ኢንተለጀንስ ዘመን ላይ ዓለም የፖለቲካውን፣የምጣኔ ሃብቱንም ሆነ የወታደራዊውን ዓለም በምን ያህል ፍጥነት እንደቀየረው እና ዓለም የሚሰራበት አሰራር እንዳልገባቸው ብቻ ሳይሆን በጣም እንደከበዳቸው ለማወቅ ብዙ ሊቅ መሆን አይፈልግም።
በአቶ ኢሳያስ እና በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መሃከል ያለው የዕውቀት፣ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት እና የመጪውን ዘመን በሚገባ የመተንበይ አቅም የሰማይና የምድር ያህል ብቻ እርቀት ያለው አይደለም። ዶ/ር ዐቢይ የብዙ ክህሎቶች ባለቤት መሆናቸው ብቻ አይደለም፣አንባቢነታቸው እና ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት እና ችግርን ወደ መልካም የመቀየር ክህሎትም ብቻ አይደለም። ዶ/ር ዐቢይ ብቁ አማካሪዎች ከማቅረብ እና ከእነርሱም የመማር ክህሎታቸው ሁል ጊዜ እጥፍ እርምጃ እንዲቀድሙ ያደርጋቸዋል።
የአፍሪካ መሪዎች አንዱ ችግር ብቁ አማካሪ አለማቅረብ እና አዋቂ አለመስማት ነው። ዶ/ር ዐቢይ በእዚህ በኩል ችግር የለባቸውም።ከአርበኞች ግንቦት 7 ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋን፣ከአብን የአይቲ ባለሙያ፣ከቀድሞ የኦነግ ሰዎች በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሌላው ቀርቶ ህወሐትን ሲያገለግሉ የነበሩትን የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ አማካሪ አድርገው የኢትዮጵያን ሥራ ለመስራት ዶ/ር ዐቢይ ልቀታቸውን አሳይተዋል። አቶ ኢሳያስ ዶ/ር ዐቢይ ያሉበት የልቀት ደረጃ ለመድረስ ከአሁን በኋላ ሌላ የ34 ዓመታት ቢጨመርላቸውም ሊደርሱበት ፈጽሞ አይችሉም። ይህ ተራ ትንበያ አይደለም። ይልቁንም አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የባሕር በር ከሦስት አስር ዓመታት በላይ ይዘው ለኤርትራ ሕዝብ ብልፅግና ሳይሆን አንድ የረባ ህንጻ አስመራ ላይ አልቀየሩም። በንጉሱና በወታደራዊ ዘመን የተሰሩና የታደሱ ስታድዮም ላይ ዘንድሮም የኤርትራ 34ኛ ዓመት በዓል ብሎ የማክበር ያህል የሚያሳፍር ጉዳይ ምን አለ?
አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ በዘመናቸው ሁለት ትውልድ ከኤርትራ ተሰዶ በደርዘን የሜዴትራንያን ባሕር የዓሳ ነባሪ ''ሲሳይ '' ሲሆን እና በሊብያ በረሃዎች ሲንከራተት ማየት እንዴት ህሊና ይሰብራል?
ከ34 ዓመታት በኋላም አቶ ኢሳያስ በዘንድሮ ''የነፃነት በዓል '' ብለው ቀድሞ በኢትዮጵያ የተገነባው ስታድዮም ውስጥ ባደረጉት ንግግር አዲስ የኢትዮጵያን ህዝብ በጎሳ ለማጋጨት ያለመ ንግግር አድርገዋል።|
አቶ ኢሳያስ በእዚሁ በግንቦት 16፣2017 ዓም ባደረጉት ንግግር ላይ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ዓለም አቀፋዊ የቀይ ባሕርን በሙሉ መብትነት የመጠቀም ጥያቄ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን የአንድ ክልል ጥያቄ አድርገው ለማቅረብ የሞከሩበት መንገድ በራስ ላይ የመተኮስ አደገኛ አካሄድ አሳይተዋል።ይህ ንግግራቸው የተስፋ መቁረጥ ንግግር መሆኑን አስረግጦ መንገር ግን ስህተት አይሆንም። ሰው ተስፋ ሲቆርጥ የሚያደርገው የማይቧጠጥ ነገር ይቧጥጣል።
አቶ ኢሳያስ በእዚሁ ንግግራቸው ላይ እንዲህ ማለታቸው ተስምቷል፡ ፟
"ሊያቀርቡ የሚፈልጓቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው። የውሃ ጉዳይ፣ አባይ እና ቀይ ባሕር፣ የባሕር በር ማግኘት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል የኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኩሽ እና የሴም ግጭት፣ የአፋር ሕዝብ እና መሬትን ለዚህ አጀንዳ መጠቀም እንዲሁም ጦርነት በሰፊው መቀስቀስ"
በእዚህ ንግግራቸው አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ስለ ዓባይ ግድብ እና የቀይባሕር ጉዳይ የሚያነሳው አንድ ክልል ነው የሚል ፌዝ አዘል ንግግር ነው። ስለ ኩሽና የሴም ጉዳይ ሲያነሱም የተስፋ መቁረጥ ልኩ የመጨረሻ የጎሳ ካርድ በኢትዮጵያ ላይ ለመምዘዝ የመውተርተር ጉዳይ ነው። አቶ ኢሳያስ ግን ይህ መንገድ እንደማያዋጣቸው በትክክል ያውቁታል። በብዙ ዕውቀት ቢጎዱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠንቅቆ በማወቅ ግን ጉድለት ያለባቸው አይመስልም። የኢትዮጵያ ህዝብ በዓባይ እና በቀይባሕር ጉዳይ እንደማይደራደር ብቻ ሳይሆን ማንም መንግስት ጋር በእነኝህ ቁልፍ የህልውናው ጉዳይ ላይ አብሮ ይቆማል። እንዴት በቅጽበት አንድነቱን እንደሚፈጥር እና እንደግስላ ተቆጥቶ እንደሚቆም በሚገባ ያውቁታል።
ለማጠቃለል አቶ ኢሳያስ የቀይባሕር ጉዳይ የአንድ ክልል ጥያቄ እንዳልሆነ እርስዎም ጠንቅቀው ያውቁታል።የኢትዮጵያ ህዝብ ሲወድ ይንከባከባል፣ ከዚያም አልፎ ''ኢሱ! ኢሱ!'' ይላል።ሁሉን እረስቶ ማለት ነው። ሊከፋፍሉት ሲሞክሩ ግን ቢያንስ በምፅዋ በቀይባሕር ውስጥ ለኢትዮጵያ (ኤርትራን ጨምሮ) የተሰዉትን ልጆቹን ያስታውሳል።ይቆጣል። አሁን አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያን ሕዝብ አስቆጥተዋል። በዘር ለመከፋፈል የተጠቀሙበት ንግግር አቶ ኢሳያስ ኢትዮጵያን በዘር የመከፋፈል ሴራ ውስጥ የለሁበትም በማለት ከእዚህ በፊት እየማሉ የተናገሩትን ሁሉ ሃሰት መሆኑን ያረጋገጠ ነው። ''የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም '' እንዲሉ።ባጭሩ አቶ ኢሳያስ አፈወርቅ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያሰሙት ከፋፋይ እና ጎሰኛ ንግግር መልሶ ወደራሳቸው ላይ እንደሚባርቅ እረስተውታል።
====================////=============
No comments:
Post a Comment